ተማሪም ሆነ መምህር ሆኜ ባሳለፍኳቸው ዘመናት ኩረጃ ነውር መሆኑን አስረግጬ ተምሬያለሁ፤ አስተምሬያለሁም። ዛሬ ግን ለበጎ ይሁን እንጂ ኩረጃም አሪፍ ነው የሚል አቋም እንዲኖረኝ የሚያስገድድ ነገር አጋጠመኝና ያንን ላወጋችሁ ወደድኩ። ያለውን የወረወረ ንፉግ አይባልም አይደል ብሂሉ! ግን ግን እዚህ ላይ እንዲሰመርበት የምፈልገው ጉዳይ አሁንም ቢሆን በትምህርት ላይ ኩረጃ አስፈላጊ አለመሆኑንና ስርቆት ነውር መሆኑን ፈጽሞ እንዳልካድኩ ነው። ሌላው የለፋበትን ዕውቀት ያለምንም ድካም በኩረጃ ማግኘት ክብርን ከማጉደሉም በላይ ስርቆት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነውና።
ሀገራት በቴክኖሎጂ የሚበልጽጉት ሁሌም አዲስ ነገርን በራሳቸው ፈጥረው አይደለም አንዳንዴ ኮርጀውም እንጂ። እንዴት አትሉኝም? እግር ጥሏችሁ ወደ ኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ብታቀኑ የቴክኖሎጂ ክምችት የሚል አንድ ክፍል ታገኛላችሁ። በዚህ ክፍልም ማንም ሰው ወስዶ ሊጠቀምባቸው የሚችል በ100 ሺዎች የሚቆጠሩ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች አሉ። ቴክኖሎጂዎቹ ቻይናን ጨምሮ ከተለያዩ ምዕራባውያን ሀገሮች የተፈበረኩና የተቀመጣላቸው የባለቤትነት መብት ቆይታ በመጠናቀቁ ማንም ሰው ወስዶና አሻሽሎ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ናቸው።
ይህ ማለት እንግዲህ በአጭር አማርኛ የተፈቀደ ኩረጃ ማለት ነው። ከላይ እንደጠቀስኩት በስልጣኔ ማማ ከፊት ቀድመዋል የተባሉ ሀገራት ጭምር ህጋዊ በሆነ መንገድ ቴክኖሎጂን ይኮርጃሉ። በኩረጃው ላይም የራሳቸውን ፈጠራ ያክሉበትና በጥቅም ላይ ያውሉታል። ይህን ፈጠራ መነሻ በማድረግም አዳዲስ ፈጠራዎችን ያከናውናሉም። ስለሆነም ስርቆት አይሁን እንጂ በጎ በጎውንና የተፈቀደውን መኮረጅ ሃጥያት አይሆንም ማለት ነው። ሃጥያት የሚሆነው ክፉና አጥፊ ነገርን ለእኩይ ዓላማ መኮረጅ ይመስለኛል።
ላወጋችሁ ወደተነሳሁበት ጉዳይ ስመለስ እኛ በሀገር ውስጥ ያለን ኢትዮጵያውያን ከዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን ብንኮርጀው ብዬ ያሰብኩት ነገር “ከአንድ ማኪያቶ አንድ ዶላር ለወገን” በሚል እያከናወኑት ያለውን በጎ ተግባር ነው። እውነት ለዚህ ቅዱስ ዓላማ መኮረጅ ጽድቅ እንጂ ፈጽሞ ሃጢያት አይሆንም። እነሱ ከአንድ ማኪያቶዋቸው አንድ ዶላር ለወገን ብለው እንደተነሱ እኛም የአንድ ጃምቦን፣ ሻይን ወይም ለስላሳን ገንዘብ ለወገን ብለን ለመጀመር ምን የሚያግደን ነገር አለ? ቅንነትን እንላበስ አንጂ ምንም!
አገራችን ሁለት ዓይነት ገጽታ የሚስተዋልባት አገር እንደሆነች ብዙዎች ሲገልጹ ይስተዋላል። ጥቂቶች ቢሆኑም ገንዘቤን የት ላጥፋ ብለው የሚጨነቁና እጅግ የተጋነነ ህይወት የሚመሩ እንዲሁም የሚላስ የሚቀመስ አጥተው ችግር ጢባጢቤ የምትጫወትባቸው የሚሊዮን ምስኪን ዜጎች መኖሪያ። በምሽቱና በሳምንት መጨረሻዎች አዲስ አበባንና አንዳንድ የሀገሪቱን ከተሞች ለተመለከተ ኢትዮጵያ ውስጥ ኑሮው ፍስሃን የተሞላና ፈጽሞ ችግር የሌለ የሚያስመስል ነው። ከትልልቅ መናፈሻዎች እስከ ሆቴሎችና ግሮሰሪዎች ቤት ሞልቶ ውጪው እስኪጣበብ ድረስ ይበላል፤ ይጠጣል፤ ይጨፈራል…ወዘተ
ላብን ጠብ አድርገው ያፈሩት ሀብት እስከሆነ እጅግም መረን አይልቀቅ እንጂ መብላት መጠጣቱና መዝናናቱ በምንም መመዘኛ ስህተት ነው ሊባል አይችልም። ይሁንና እኔና ቤተሰቤ እንዲህ ተመችቶን ብስል ከጥሬውን ስንበላና ስንጠጣ እንዲሁም ስንዝናና ሚሊዮኖች ግን የእለት ጉርስ አጥተው መማር እንደተሳናቸው፣ እንኳን ሰው እንስሳት እንኳ ሊጠጡት የማይገባውን ውሃ እየጠጡ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖች እንዳሉን ልናስታውስ ግድ ይለናል። ያለዚያ መዝናናቱ ግንጥል ጌጥ ይሆንና የአዕምሮ ወቀሳን ማስከተሉ አይቀሬ ነው።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በተጀመረበት ወቅት አንድ የአዕምሮ ህመምተኛ የተናገረው ንግግር ዛሬም ድረስ ከአዕምሮዬ አልወጣም። ወቅቱ 2004 ዓ.ም አካባቢ ሲሆን በዚያን ወቅት ለግድቡ ግንባታ ህዝባችን የቦንድና ሌሎችም ድጋፎች ያጧጧፈበት ጊዜ ነበር። ይህ ሰው ሰዎች በመጠጥ በሚዝናኑበት አካባቢ ቆሞ የአባይን ግድብ መሙላት እኮ ቀላል ነው። እያንዳንዱ ድራፍት ጠጪ አንድ አንድ ጃምቦ ወደ ዓባይ ቢደፋ ግድቡ በአንዴ ነበር ከአፍ እስከ ገደፉ የሚሞላው ይል ነበር ንግግሩ። ንግግሩ በመዝናናት ላይ የነበሩትን ሰዎች በከፍተኛ መጠን ቢያስቃቸውም ለኔ ግን መልዕክቱ እጅግ ጥልቅ ነበር።
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በመላ ኢትዮጵያ በዓመት የሚጠጣው የቢራ መጠን በሚሊዮን ሄክቶ ሊትር የሚለካ ነው። እስኪ አስቡት በዚህ መጠን ከሚጠቀመው ህዝብ በቀንም፣ በሳምንትም ሆነ በወር ከሚጣጠጣው ሶስትም ሆነ አራት ቢራ አንዱን ትቶ ገንዘቡን ለተቸገሩ ሰዎች ቢለግስ ምን ያህል ሚሊዮን ብር ተዋጥቶ ስንት ወገኖችን ከችግር አያላቅቅምን? ለዚህም ነው ዳያሰፖራዎቹ ከአንድ ማኪያቶ አንድ ዶላር እየለገሱ እንዳለው እኛም የአንድ ጃምቦአችንን አስር ወይም አስራ ሁለት ብር እንለግስና ታሪክ አንስራ ማለቴ።
በየከተሞች ያሉ ካፍቴሪያዎችን ብንመለከት የሻይ፣ ቡናና ማኪያቶ ተጠቃሚው ቁጥር የትየሌለ መሆኑን እንረዳለን። እንዲያውም ብዙውን ጊዜ ሻይ ቡና ወይም ማኪያቶ የምንለው አስፈልጎን ሳሆን ከጓደኛ፣ ከወዳጅ ወይም ከእንግዳ ጋር አረፍ የምንልበትን መቀመጫ ፈልገን ይመስለኛል። ሳያስፈልገን ልማድ ሆኖብንም በቀን ሶስት አራት ጊዜ ቡና ወይ ሻይ የምንጠጣም ብዙዎች ነን። እናም ከእነአካቴው መተውን ተትን በቀን ከምንጠጣው ሁለት፣ ሶስት፣ አራት ቡና፣ ሻይ ወይ ማኪያቶ የአንዱን ዋጋ ለበጎ ተግባር ብናውለው ምንያህል ዜጎቻችንን ከችግራቸው በፈወስን።
ያነሳሁትን ነጥብ ለማጠናከር የደቡብ ኮሪያውያንን ታሪክ እዚህ ጋር ማንሳቱ ተገቢ መስሎ ይሰማኛል። ዕድል ገጥሞኝ ደቡብ ኮሪያን ስለጎበኘሁ ምድራዊ ገነት ብሎ ከማለፍ ውጪ እድገቷን በቃላት ገልጾ ለማለፍ ያዳግተኛል።
ይህቺ ሀገር ከ50 እና 60 ዓመት በፊት የነበረችበት ድህነት ግን አንጀት በጥስ የሚሉትና ለመናገርም የሚከብድ እንደነበር ዜጎቿ ያወጋሉ። ይሁንና በወቅቱ የነበረው መንግስት ሲያደርገው የነበረው የጸረ ድህነት ትግል ከጫፍ የደረሰው ግን ደቡብ ኮሪያውያን ሴቶች ያላቸው ወርቃቸውን የሌላቸው ደግሞ ጸጉራቸውን እየቆረጡ እየሸጡና የሴተኛ አዳሪነትን ስራ ሳይቀር እየሰሩ ያገኙትን ንዋይ ለሀገራቸው ልማት እንዲውል በመለገሳቸው ነበር። ደቡብ ኮሪያውያን እነዚህን እንስት ጀግኖቻቸውን በብሄራዊ ጀግናነት በየዓመቱ የሚያስቡበትና ክብር የሚሰጡበት ቀን አላቸው። ለአገር ዕድገት ሲባል የሚከፈለውን ይህን መሰሉን አኩሪ ገድል ስንመለከት እኛስ ምን አደርገናል ከማስባሉም በላይ የቡናና የሻይ ሂሳብን ለወገን መለገስ ምን አላት የሚል ጥያቄ ወደ አዕምሯችን መምጣቱ አይቀሬ ይሆናል።
እኛ ኢትዮጵያውያን የሀገራችን ሉዓላዊነት በተደፈረ ጊዜ ህይወትን ያህል መተኪያ የሌለው ነገር ያለ ምንም ፍርሃት ለመስዋዕትነት በማቅረብ አቻ እንደሌለን አምናለሁ። ይሁንና እርስ በእርስ መፈቃቀሩና አንዱ የአንዱን ሸክም በማቃለልና በመረዳዳቱ ላይ ግን ገና ብዙ እንደሚቀረን ይሰማኛል። ይህ ሁኔታ ግን ዛሬ መቀየር እንዳለበት አምናለሁ። ለራሳችንም ችግር ከራሳችን በላይ ማን ሊቆረቆርልንና ሊደግፈን እንደማይችልም ሳይታለም የተፈታ ነው። ለዚህም ነው በጎ የሆነውን የዳያስፖራዎች የድጋፍ እንቅስቃሴ እንኮርጅ ማለቴ!
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ መሪነት የተጀመረውን ለውጥ እንደሚደግፍና የተጠየቀውን ድጋፍ ሁሉ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በሀገሪቱ ሁሉም ጫፍ በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ አደባባይ ወጥቶ ድጋፉን እንደቸረ ብዙም ያልራቀ ትውስታችን ነው። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከበዓለ ሲመታቸው አንስቶ ባደረጉት ንግግርም ድጋፍ በተግባር ይገለጽ የሚል መልዕክት ደጋግመው አስተላልፈዋል። ስለሆነም ትውልደ ኢትጵያውያኑ የጀመሩትን ወገንን የመታደግ በጎ ተግባር ቁጭት ቀስቅሶብን ለለውጡ ያለንን ድጋፍ የምንገልጽበት ምቹ ዕድል እንደተፈጠረልን ይሰማኛል። ያኔ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል አንተስ ለአገር ለወገንህ ምን አድርገሃል? ብለን የመጠየቅ የሞራል ብቃትን የምንጎናጸፍ ይሆናል።
ምንም እንኳን ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር በሀገራችን ያለው ሲቪል ሰርቪስ ቁጥር አናሳ ቢሆንም እስከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርስ ሲቪል ሰርቫንት በሀገራችን እንዳለ ይታመናል። ይህ ሃይል በአነስተኛ ክፍያ አገሩን እያገለገለ ያለ መሆኑና ኑሮውም ከእጅ ወደአፍ መሆኑ ከማንም የተሸሸገ አይደለም። በዚህ ዓይነት ሁኔታም ውስጥ እየኖረ እንኳን ይህ የኅብረተሰብ ክፍል ለታላቁ የህዳሴ ግድብ እውን መሆን ግንባር ቀደም ድጋፍ በማድረግ የወርቅ ታሪክን የጻፈ ነው። የአገርና የወገን ጉዳይም ሁሌም ግድ እንደሚለውም ሀገርና ህዝብ ችግር ውስጥ በገቡበት ሰአት ሁሉ ጉልበቱንና ገንዘቡን በመለገስ በተደጋጋሚ አረጋግጧል። አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አንድ ብር የሚገዛልን ትርጉም ያለው ነገር የለም። ይሁንና ሚሊዮኖች ግን አንድ አንድ ብር ቢያዋጡ ሚሊዮኖች ሆኖ ትርጉም ያለው ለውጥ እንደሚያመጣ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለሆነም ሁላችን የሲቪል ሰርቪስ ሰራተኞች በወር አንድ ብር ብቻ በመለገስ ለወገን አለኝታ ብንሆን ምን ይለናል? እውነት እውነት ይታሰብበት!
በሙስናና ሁነኛ መፍትሄ በማጣት የሀገራችን ኢኮኖሚ አጅግ ዝቅተኛ በሚባል ደረጃ ላይ ይገኛል። የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ብዙ ሲለፈፍለት ቢኖርም የአብዛኛውን ሰው ህይወት በመቀየር ረገድ የተገኘው ለውጥ ግን እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ስለሆነም እንደሀገር ለልመና እጆቻችንን መዘርጋቱ ቀጥሏል። መሪዎቻችን በተለያዩ ሀገራት በሚደርጉት ጉብኝትም ቀዳሚ ተግባራቸው የሚያደርጉት ይህ ጎድሎናልና እባካችሁ እርዱን የሚል ነው። በቅርቡ እንኳን ዶክተር ዓብይ አህመድ በአደረጓቸው ጉብኝቶች ለዜጎች የዊልቸርና የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ድጋፍ ሲጠይቁ እንደነበር አስተውለናል። ይህ ደግሞ የነጻነትና የኩሩ ህዝቦች አገር ለሆነችው ኢትዮጵያ ፈጽሞ የማይመጥንና የማይገባ ነው ብዬ አምናለሁ።
ከዚህ ዓይነቱ ክብራችንን ከሚያዋርድ ሁኔታ ለመውጣት ቀዳሚውን ኃላፊነት መወጣት የእኛ የኢትዮጵያውያን ድርሻ ይሆናል። ለዚህም ነው ከማንም በፊት ለወገናችን ችግር ቀዳሚ ደራሾች ራሳችን እንሁን፤ በትንሹ የሻይና ቡና ሂሳባችንን በመለገስ ዜግነታዊ ግዴታችንን እንወጣ ማለቴ። ስለሆነም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ለትውልደ ኢትዮጵያውያን ያቀረቡትን ጥሪ ለእኛም በሀገር ውስጥ ላለን ዜጎች እንዳቀረቡት እንቁጠርና ያለንን እንወርውር እኛም እንጀምረው እላለሁ!
አዲስ ዘመን ጥር 15/2011
ፍቃዱ ከተማ