የኢትዮጵያ ትምህርት ከሰላና ተባ ሂስ ያመለጠበትን ጊዜ ፈልጎ ማግኘት ይከብዳል። ዘላለም አለሙን እንዳነጋገረ፣ እንዳከራከረ፣ መንግስትና ምሁራንን፣ መንግስትና ህዝብን፣ ፖለቲከኞችንና ፖለቲከኞችን ያለ እረፍት እሰጥ አገባ ውስጥ እንደከተተ፤ ከዚያም አልፎ ለአመራሮቹ ሁሉ “ዮዲት ጉዲት” ተቀፅላን እንዳተረፈ ጉደኛ አጀንዳ ብቻ ሳይሆን፤ እግረ መንገዱንም “’ያልተመረቁ ምሩቃን’ን ከማፍራት አልፎ ማንበብና መፃፍ የማይችል፤ እውቀትና ክሂሎት የሌለው ትውልድን እያፈራ” ነው። ሁለት ጥፋት ይሏልም ይህ ነው። ይህ ያሁኑ ነው። የፈለግነውን ያህል ርቀት ወደ ኋላ ብንጓዝም የምናገኘው ውዝግብ እንጂ ሌላ አይደለም። ምንልባትም ልዩነቱ የአሁኑ በከረረ ፖለቲካ መወጠሩና አንዳንዴም አገርን ሳይሆን የግል ማንነትን፣ ስሜትና ማን አለብኝነትን የተደገፈ፤ ወቅታዊውን የዓለም ሁኔታ ሳይሆን የፓርቲ ርእዮትን የተመረኮዘ ሆኖ መገኘቱ ነው።
መግቢያችንን ገታ እናድርግና በቀጥታ ወደ ርእሰ ጉዳይ ትንተና እንግባ። ትንተናውንም ከርእሰ ጉዳዩ ተተኳሪነትና አነጋጋሪነት አኳያ በመስኩ ባለሙያዎች ምርምርና ግኝት ላይ እናድርግ። በሂደቱም ከተጠቃሽ ምሁራንና መፃህፍታቸው፣ ለውይይት ከቀረቡ የተቋማትና ምሁራን ጥናትና ምርምር ስራዎች እንዲሁም ሌሎችን እያጣቀስን ከነበረበት “ድሮ” እስካለበት “አሁን” ድረስ ያለውን እናሳይ።
ለግልፅ ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ አቅጣጫችንን ከኋላ ወደ ፊት እናድርግና ከሩቁ ወደ ቅርቡ እንምጣ። ለዚህ ደግሞ ጉዳዩ ከአትዮጵያ ዘመናዊነት (Modernism) አጀማመር ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለውና ከአፄ ቴዎድሮስ እንጀምር። ከዛ በፊትስ? ለሚለው የአገራችን ትምህርት ባብዛኛው ከሃይማኖት ጋር የተሳሰረ፤ በዘርዓያቆብና የእሱ ተማሪ በሆነው ወልደ ሕይወት ስራዎችና ፍልስፍናዎች በሚገባ የተንፀባረቀ፤ የነበረው አጠቃላይ ማእቀፍም በእነዚሁ ሁለት ጎምቱ የዚያ ዘመን ኢትዮጵያውያን ፈላስፎች አስተሳሰብና ፍልስፍና ውስጥ የነበረ በመሆኑ የእነዚህን ፈላስፎች ስራና ህይወት መፈተሽ ጠቃሚ መሆኑን ለአንባቢ በመጠቆም ማለፍ አወራረዳችንን ያቀለዋልና ከተስማማን እንለፈው። (በነገራችን ላይ ዘርዓያቆብና ፈረንሳዊው ሳይንቲስት፣ ሂሳብ ተመራማሪ እና ፈላስፋ ሬኔ ደካርት (1596–1650) ዘመንኛዎች ናቸው።) “ዘመንኛዎች ናቸው” እንጂ “አቻ ናቸው” አልተባለም። ምክንያቱም ሁለቱ በፍልስፍና አቅምና ስራዎቻቸው ሲመዘኑ ታላቁ ዘርዓያቆብ ሆኖ ስለመገኘቱ በተደጋጋሚ የጥናትና ምርምር ስራዎች ተረጋግጧልና ነው። ወልደ ሕይወትንም ብንወስድ ቀላል ፈላስፋ ሆኖ የምናገኘው ሰው አይደለም። የተለያዩ ስራዎቹ እንደሚያመለክቱት፤ በተመራማሪዎችም ተደጋግሞ እንደተብራራው ምንም እንኳን የዘርዓያቆብ ደቀ መዝሙር ይሁን እንጂ ከመምህሩ ደቀ-መዝሙሩ እንዲሉ የመምህሩን ስራና ፍልስፍናዎች በመመርመር አጥብቆ ያሄስ የነበረ ታላቅ ፈላስፋ ነበር። ምንም ይሁን ምን ግን የሁለቱም ዓላማቸው አንድ፤ መንገድና ዘዴያቸው ግን የተለያየ ነበር። የአገራችን የወደፊት ሁኔታ እንዴትና በምን አይነት መንገድና አቅጣጫ ይጓዝ፤ የትምህርት ፍልስፍናውስ ምን መሆን አለበት? እና የመሳሰሉት የሁለቱ እኩል ጉዳዮች፤ እኩል አሳሳቢያቸው፤ እኩል ስራዎቻቸው አብዝተው እንዲጨነቁላቸው ያደረጋቸው ፈላስፎች ነበሩ።
ሁለቱን በተመለከተም ብሩክ “የዘርዓያቆብና ወልደ ሕይወት ትምህርቶችን መመልከት ያለብን ከአንድ ወሳኝ ከሆነ ነጥብ አንፃር [፤ …] ለወደፊቱ የኢትዮጵያ ዘመናዊነት ፕሮጀክት አስቀድሞ የባህል መደላድል ለመፍጠር የተደረገ የመጀመሪያ ሙከራ [አድርገን] ነው” ያለውን እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባልና አተያያችን በዚሁ መንገድ እንዲሆን ያሻል። (እጥር ምጥን ላለ ማብራሪ የዶ/ር እጓለን “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”ን፤ የብሩክ አለምነህን “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ን፣ በተለይ “ክፍል ፫”ን፣ የፕ/ር ጌታቸው ኃይሌን “ደቂቀ እስጠፋኖስ”ን ይመለከቷል።)
ለጊዜው ከእነዚህ ሁለት ፈላስፎች ወዲህ መጥተን የመሪዎችን ኢትዮጵያን የማዘመን ፍላጎትና እርምጃ ስንመለከት መነሻችን አፄ ቴዎድሮስ ላይ አርፎ መድረሻችን አሁን ሆኖ እናገኘዋለን።
በ”የኢትዮጵያ ፍልስፍና” ላይ እንደተመለከተው
አገሪቱንና አጠቃላይ ህብረተሰቡን ከነበረበት ነባር አሰራር፣ አኗኗር ወዘተ ለማውጣትና ወደ ዘመናዊነት ደረጃ ለማሸጋገር በየዘመናቱ በመጡ መሪዎች ፕሮጀክቶች እየተቀረፁ ስራ ላይ ለማዋል ይሞከር ነበር። የመጀመሪያው “የአፄ ቴዎድሮስ የዘመናዊነት ፕሮጀክት” ሲሆን ዓላማውም ምእራባዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ሀገር ውስጥ በማምረትና የእውቀት ሽግግርን ሳቢ ማድረግ ነበር። ሁለተኛው ወደ ዘመናዊነት የማሸጋገሩ ሙከራ በአፄ ሚኒሊክ የተደረገው ሲሆን እሱም “የአፄ ምኒልክ የዘመናዊነት ፕሮጀክት” ነበር። ፕሮጀክቱ ምእራባዊ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባትን ታሳቢ ያደረገ ነበር። ሶስተኛ ሙከራ “የአፄ ኃይለ ሥላሴ የዘመናዊነት ፕሮጀክት” ነው። ይህ ፕሮጀክት አቢይ ትኩረቱ የፈረንጅ ትምህርትን ማስፋፋት ሲሆን፤ አራተኛውና በስሩ ሁለት ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን ያካተተው ደግሞ ፀሀፊው “የአብዮቱ ፕሮጀክት” ሲል የገለፀው ነው።
በዚህ “የአብዮቱ (የተማሪዎች) የዘመናዊነት ፕሮጀክት” ስር በመጀመሪያ ደረጃ የሰፈረው “የደርግ የዘመናዊነት ፕሮጀክት” ሲሆን እሱም ሶሻሊዝምን መሰረት፤ ሁለተኛው “የኢህአዴግ የዘመናዊነት ፕሮጀክት” በበኩሉ የባህል ብዝሃነትንና የማንነት ልዩነትን ማእከል ያደረገ እና በዚሁ መሰረትም እየሰራ የሚገኝ መሆኑ ከቀድሞዎቹ ሶስቱ ይለየዋል።
ብሩክ እንደሚለው ከሆነ ፕሮጀክቶቹ ሁሉም አልተሳኩም። ምክንያቱንም “እጣ ፈንታችን ንጉሱ በተቀያየረ ቁጥር እኛም ከአንደኛው የዘመናዊነት ፕሮጀክት ወደ ሌላኛው መገላበጥ” መሆኑን በማለት ያስቀምጣል።
ባጭሩ ከላይ ያየናቸው ፕሮጀክቶች ይህንን የሚመስሉ ሲሆን ለመንደርደሪያነት ተጠቅመንባቸዋል። መንደርደራችንም የአሁኑ ወቅት የትምህርት ሥርዓታችን ያለበትን አጠቃላይ ሁኔታ ለመዳሰስ ታሪካዊ ዳራን ለመፍጠር ነው።
በመግቢያችን እንደጠቆምነው ባለንበት የፖለቲካ ሥርዓትና የመንግስት አስተዳደር አጥብቆ የተተቸ ፖሊሲ ቢኖር አዲሱ “የኢፌዴሪ ትምህርት ፖሊሲ” ነው። እስኪበቃው ተብጠልጥሏል። ችግሩ ማብጠልጠል ብቻውን የትም አለማድረሱ፤ ጩኸቱ ሰሚ ማጣቱና ፖሊሲው ከነችግሮቹ እዚህ ድረስ መዝለቁ ነው። “ችግሩ” ስንል ከምን መነሻ? የሚል ጥያቄን ሊያስነሳ ይችላል። ካስነሳ ምላሻችን “መነሻችን የባለሙያዎች ጥናቶች ናቸው” በመሆኑ ወደ እነሱው እንለፍ። (ሃሳባችንን እጅግ ወቅታዊ ለማድረግ የቅርብ ጥናቶችን ብቻ መጠቀሙን መርጠናል።)
አንድ ዓመት ወደ ኋላ ሄደን በትምህርት ካሪኩለሙ ላይ የተደረጉ ጥናቶችን ስንዳስስ በጥናቶቹ ጎላ ብሎ የምናገኘው ካሪኩለሙ አስኳል ሃሳብ “ኢትዮጵያዊ ማንነትንና ሀገራዊ እውቀቶችን አላካተተም። ሀገሪቱን ጥገኛና ያሏትን ሀብት በአግባቡ እንዳትጠቀም አድርጓታል።” የሚል ነው። ባለፈው ዓመት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ በዘንድሮው ደግሞ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተካሄዱ ኮንፈረንሶች ላይ የቀረቡ በርካታ ጥናቶች የሚስማሙበት አቢይ ጉዳይ ቢኖር ቀደም ሲሉ ከነበሩት “ተደራሽነት”፣ “የልህቀት ማእከል”፣ “ሽፋን”፣ “ፍትሀዊነት” ወዘተ ከሚሉት በተለየ ሁኔታ ጥራትና ይዘት ላይ ማተኮራቸው ነው።
‹‹ትምህርትና ሁለንተናዊ ለውጥ በኢትዮጵያ፣ ተግዳሮቶችና የወደፊት እይታዎች›› በሚል አጠቃላይ ርዕስ በጎንደር በተካሄደው 3ኛው አገር አቀፍ የትምህርት ጉባኤ ላይ በተሳታፊዎች ዘንድ “ካሪኩለሙ ሀገሪቷ ከምዕራባውያን የመጣውን የትምህርት ስልት በቀጥታ ገልብጣ ተግባራዊ በማድረጓ ሀገራዊ እውቀቶችን በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉና እንዳያድጉ” ማድረጉ የጋራ ተቀባይነት ሲያገኝ፤ የደብረ ብርሃኑም ከዚህ የተለየ ሆኖ አልተገኘም።
በደብረ ብርሃኑ አገር አቀፍ ኮንፈረንስ ላይ ከቀረቡት 14 የተለያዩ የምርምር ስራዎች (የሁሉም ትኩረት የአገራችንን ትምህርት ታሪካዊ አመጣጡንና ወቅታዊ ይዞታውን መፈተሽና የወደፊት አቅጣጫውን ማመላከት) መካከል የአርሲ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ትምህርት መምህርና ተመራማሪው ዶ/ር ሮብሰን መርጎ “A Critical Review and Analysis Ethiopian Modern Secular Educa¬tion from Multiculturalism Perspectives: The Quest for Balancing Indigenous Knowledge and Western Knowledge” የሚለው ይገኝበታል።
እንደ ዶ/ር ሮብሰን መርጎ ጥናትና ማብራሪያ አገራችን
በአገር በቀል እውቀት የበለፀገች፣ የበርካታና ለዓለም የተረፉ የማይዳሰሱና የሚዳሰሱ ቅርሶች ባለቤት ሆና እያለ ይህ በአገራችን ትምህርት ውስጥ ተካትቶ ሲሰጥና ትውልድን ሲቀርፅ እስከ ዛሬ አልታየም። ይህ ደግሞ የአንድ መንግስት ወይም ሥርዓት ችግር ብቻ ሳይሆን በአራቱም ሥርዓተ መንግስታት (ከአፄ ሚኒሊክ እስከ ኢህአዴግ) የተስተዋለና ተከታታይ ትውልድን ለባእዳን ፍልስፍና አምላኪነት አሳልፎ የሰጠ፤ በማንነት ጉዳይ ላይ የከፋ ውዥንብርን የፈጠረና የትውልድን ከገዛ ባህል መነጠልን ያስከተለ ሂደት ሆኖ ያለፈ፤ አሁንም እየሆነ ያለ የመማር-ማስተማር ሂደት ነው።
“አገራችን፣ ገዳ፣ ደመራ፣ በኦርቶዶክስ ሃይማኖት “ንባብ ቤት”፣ “ቅኔ ቤት” እያለ የሚሄደውና ለማጠናቀቅ 16 ዓመታትን የሚወስደው (ይህ ከምእራባውያን የዲግሪ ፕሮግራም ጋር እኩል ነው)፤ በእስልምናውም “መድረሳ”ን የመሳሰሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ቅርሶች፤ እድሜ ጠገብ ትውፊቶች፣ ባህላዊ ህክምናዎች፣ እደጥበባት፣ የፅሁፍና የቃል ቅርሶች፤ የኮንሶ እርከን ስራ፣ ግጭት አፈታት ሥርዓታችን፣ ጨምበላላ … ወዘተ የመሳሰሉ ሀብቶችና ማህበረ-ባህላዊ እሴቶች እያሏት እነዚህ በሥርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ተካትተው ትውልድ እንዲያውቃቸውና ትውልድን እንዲቀርፁ፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን እንዲገነቡ፣ የተለያየ ባህል ያላቸው ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው እንዲተዋወቁ፣ ትውልድ ከባህሉ እንዳይነጠል ማድረግ ሲገባ አልተደረገም።” የሚሉት አጥኚው ይህ አገራዊ ችግር ከአሁን በኋላ ሊቀረፍና የአገራችን ሥርዓተ ትምህርት ቀረፃ ከውጭው እውቀትና ፍልስፍና ጋር ሚዛን ጠብቆ ሊካተት ይገባል ሲሉም በአፅንኦት ይመክራሉ።
ሌላውና በዚሁ መድረክ “Ethiopian Education and Their Contribution to Developing Peace” በሚል ርእስ ጥናት ያቀረቡት የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲው እጩ ዶ/ር አክሊሉ አበራም በአብዛኞቹ ትምህርት ቤቶቻችንም ሆነ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ባህላዊ እሴቶቻችን ምንም አይነት ትኩረትን አላገኙም። በመሆኑም ምንም አይነት ጠቀሜታን አልሰጡንም፤ ሰጥተዋል ከተባለም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ባይ ናቸው። “ስለዚህ” ይላሉ አጥኚው “ባህላዊ እሴቶቻችን ለሀገራዊ ጠቀሜታ፣ ለትውልዱ መልካም ሰብእናና ሌሎችም መሰረታዊ ፋይዳዎች ሲባል ከዘመናዊው ትምህርት ጋር በጥምረት መሰጠት አለባቸው።”
ወደ ጎንደሩ ኮንፈረንስ ስንመለስ ሌላው የምናገኘው የአቶ ፋንታሁን ዋቄን “የመንግስት መር መደበኛ ሥርዓተ ትምህርትና የኢትዮጵያዊነት እሴቶች›› ጥናት ሲሆን “ካሪኩለሙ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናና የእውቀት መንገድ ያልተከተለ ነው፡፡” በሚለው ማእከላዊ ነጥብ ላይ ያጠነጠነ ሆኖ እናገኘዋለን። ‹‹ሰጥተን መቀበል የምንችል እውቀት እያለን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍናዎችንና እውቀቶችን ኋላ ቀር በሚል አባዜ በሥርዓተ ትምህርቱ ባለማካተታችን ተጎጂ ሆነናል፤ የነበሩንን እውቀቶችና ሀብቶች በምዕራብያውያን” ተዘርፈናል። በመሆኑም “የማህበረሰቡ ማህበራዊ መስተጋብር የወለዳቸው እውቀቶችና የጋራ ፍልስፍና በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ መካተት” አለባቸው፤ በካሪኩለሙም ልዩ ኢትዮጵያዊ ማንነትን ያካተተ ፍልስፍና፣ የትምህርት ይዘት፣ የትምህርት አቀራረብና አወቃቀር ያለው የትምህርት ሥርዓት ሊኖር” ይገባል በማለት ቀደም ሲል የጠቀስናቸውን ጥናቶች ያጠናክራል።
በሌሎች ጥናቶች ላይ የተመለከቱት ይዘቶችም ከዚህ የተለዩ አልነበሩም። ‹‹ሰውን ማዕከል ያደረገ የትምህርት ሥርዓት ሊኖር ይገባል››፤ “በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የሀገሪቱን መልካም ባህልና እውቀት ከማካተት ይልቅ የሌላ ማንነት በመምጣቱ ዓላማው ግቡን እንዳይመታ አድርጓል”፤ ‹‹የጎደለብንንና ያልደረስንበትን በተጨማሪ አድርገን መውሰድ ሲገባን እንዳለ ከሌላ ዓለም ማምጣታችን አዲስ እውቀት እንዳንፈጥር ወይም ያለንን እንዳናሳድግ አድርጓል››፤ “እያንዳንዱ የትምህርት አይነትም የተማሪዎችን የማገናዘብና ዕድሜ ግምት ውስጥ ያስገባና ማህበራዊ መሰረት ያለው መሆን” ይገባዋል፤ “አሁን ያለው የትምህርት ፖሊሲ የቅድመ መደበኛ ትምህርትን ‘አስፈላጊ ነው’ ከማለት ውጭ ውጤት በሚያመጣ መልኩ አልተሰራበትም” እና የመሳሰሉት ተደጋጋፊ ሃሳቦች የሚያመለክቱን አቢይ ጉዳይ ቢኖር እየተመራንበት ያለው የትምህርት ፍልስፍና ከጨለማ ወደ ዘመናዊነት ከማሻገር ይልቅ መልሶ ወደ ጨለማ የሚወስድ መሆኑን ነው።
“ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ነች። በሀብት፣ በሰው ሃይል፣ በተፈጥሮ ፀጋ፣ በህዝብ ስብጥር ትልቅ አገር ነች። በእያንዳንዱ አካባቢና ህብረተሰብ ዘንድ የራሱ የሆነ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እሴቶች አሉ” የሚለው የዶክተር ሮብሰን ጥናት አገር በቀል እውቀትን “የተረሳ፤ ግን ደግሞ ጠቃሚና ከእኛም አልፎ ለአፍሪካም የሚተርፍ እውቀት ተቀብሮ ቀርቷል።” ይለዋል። አክሎም “የአሁኑ ትውልድ ጭንቅላቱ ፈረንጅ ሲሆን አካሉ ኢትዮጵያዊ ነው። ይህን የተዛባ የማንነት ሥነልቦና ውቅርን ለማስታረቅ ብዙ መስራትን ይጠይቃል። ይህን ማድረግ ከቻልን አንድ ቆም ብሎ የሚያስብ ትውልድ ፈጠርን ማለት ነው። ይህም በራሱ አንድ ትልቅ ነገር” መሆኑን ያስነብባል። ረ/ፕ/ር ምህረት ሻንቆም ባጭር አገላለፅ የሚሉት ይህንኑ ነው፤ በአሁኑ የመማር-ማስተማር ሂደት “ያልተመረቁ ምሩቃን”ን እያፈራን ነው።
ዶክተር ሮብሰን “እስከ ዛሬ ድረስ ስናቀነቅን የመጣነው ስለ ምእራባውያን እውቀትና ፍልስፍና ነው። ይህ ሊሆን አይገባውም ነበር። ይህን ስንል የእነሱን ጠራርገን እናስወጣ ማለታችን አይደለም። ይጠቅመናል። መሆን ያለበት ማጣጣምና ሚዛኑን ጠብቆ ማቅረብ” ተገቢ ነው ያሉ ሲሆን መሆን ያለበትንም ከነመፍትሄው አስቀምጠዋል።
ብሩክ ቀደም ሲል በጠቀስነውና አድቅቆ ባየበት “የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ው የፕሮፌሰር መስፍንን “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”ን አስታኮ የህብረተሰቡ “ኑሮው፣ ሃይሉና ታሪኩ የተረሳ ነው። […] በእንደዚህ አይነት ሁኔታ 1700 በቆየው ሥርዓተ ትምህርቶችን ውስጥ የሥነ ሰብእ ትምህርቶች ቦታ አልነበራቸውም። […] የጥንቱን የአክሱማዊት ሥልጣኔ ወደ መናፈቅ አልገባንም።” በማለት ችግሩ የምእተ ዓመታት መሆኑን ይነግረናል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባለው የከፍተኛ ትምህርት አጠቃላይ ይዞታን በተመለከተ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ይገልፃል። ከእነዚህም አንዱ በ”ልየታ/Differentiation” መሰረት ዩኒቨርሲቲዎቹን እንደገና በሶስት ዘርፎች (ትምህርት፣ ምርምር እና ፖሊቴክኒክ) ማደራጀት መሆኑም ተናግሯል። በሂደቱ እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ያደርጋል ተብሎም እየተጠበቀ ነው። አገሪቱ ወደ ዘመናዊነት የመሻገር የቆየ ህልምም በዚህ ይፈታል ብለን እናምናለን።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
ግርማ መንግሥቴ