ወቅቱ የተማሪዎች ምርት መሰብሰቢያ ተደርጎ ይታያል።በተለይም ደግሞ የክልል አቀፍ (ሚንስትሪ) ፈተና ተፈታኞች እና የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ (ማትሪክ) ተፈታኞች ፈተናዎቻቸውን ወስደው (ተፈትነው) የሚያጠናቅቁበት ነበር።ከመፈተን ባሻገርም ተማሪዎች ሌሎች ተስፋዎችን ይሰንቃሉ።ፈተና የወሰዱባቸውን ወረቀቶች (ሽት) ደግሞ በመስራት ምን ያህሉን መልሻለሁ? ሲሉም ምርታቸውን ለማረጋገጥ ጥረት ሲያደርጉ የሚስተዋልበት ጊዜ ነበር ሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት፡፡
አሁን ላይ ይህ እድል የለም።የገጽ ለገጽ ትምህርት መማር ማስተማር ተዘግቷል። በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች በኢትዮጵያም ፣በዓለም ላይም እንደተከረቸሙ ዘልቀዋል።ቻይናውያን ወረርሽኙን ተቆጣጥረነዋል ‹‹ልጆቻችን ወደ ትምህርት ገበታቸው ይመለሱ›› በሚል ቫይረሱ በጀመረባት የውኃን ግዛት ጭምር ከፍተው ነበር።ነገር ግን በቻይና በሽታው መልሶ በማገርሸቱ የተነሳ ትምህርት ቤቶቿን መልሳ ለመዝጋት ተገድዳለች።አልፎ አልፎ አንዳንድ አገራት ፈራ ተባ እያሉም ቢሆን ትምህርት ቤቶቻቸውን ሊከፍቱ ሞክረዋል።መቀጠል ግን አልቻሉም።
እነዚህን ሁኔታዎች ተከትሎ በዓለም ላይ የትምህርት ሥርዓቱ መልኩን ቀይሯል።ከገጽ ለገጽ ትምህርት ወደ ርቀት ትምህርት መረሃ ግብር እና ወደ በይነ መረብ ትምህርት አቅጣጫውን አዙሯል የሚሉ አገራት ብዙ ናቸው።የመማር ማስተማር ስራቸውን በተገቢው በኢ-የመማማሪያ ሥርዓት በመቀየር የተጠናከረ ክትትል አድርገው ትምህርቱን በማስቀጠል በዚሁ መንገድ የምዘና ሥርዓታቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።በዚህ ረገድ ተማሪዎች ያገኙትንና ያተረፉትን ሲገልጹ በቤት ውስጥ በመዋላቸው የተነሳ ከሚፈጠርባቸው የድብርትና የድባቴ ስሜት እንደገላገላቸውና በቴክኖሎጂ የአጠቃቀም ክህሎታቸው ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተላቸው ይናገራሉ።ከዚህ በተጨማሪም ትምህርት ቤት ሄደው በሚማሩባቸው ጊዜያት ይፈጠርባቸው
የነበሩ ስሜቶችን ለመፍጠር ከተማሪ አቻዎቻቸው እና ከአስተማሪዎቻቸው ጋር በቴክኖሎጂ አማካኝነት ያንን አውድ በመፍጠር ‹‹ትምህርት ተዘግቷል›› የሚል ስሜት እንዳይሰማቸው እስከማድረግ መድረሳቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ተማሪ አብዱ መሐመድ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው።የዓለምም የኢትዮጵያም ስጋት በሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ በአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆዩ አድርጎ አስቦ እንደነበር ይናገራል።ይሁን እንጂ ትምህርት ቤቶች ወደ ቀድሞው መማር ማስተማር በአጭር ጊዜ መመለስ እንደማይችሉ እየተገነዘቡ እንደመጡ በመግለጽ፤ ለተማሪዎች በተለያዩ መንገዶች ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ እንደሞከሩ ይገልጻል።በቴሌቭዥን ፣በሬዲዮና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች ትምህርት ለመስጠት ተሞክሯል።በዚህም በስልካቸው ‹‹ፌስ ቡክ›› እንኳን እንዲጠቀሙ ለልጆቻቸው የማይፈቅዱ ወላጆች ጭምር በሚሰጠው ትምህርት በማመናቸው መፍቀድ ችለዋል።በዚህ የተነሳም ተማሪዎች በተለያዩ የማህበረራዊ ሚዲያ አማራጮች በሚመጡላቸው የትምህርት ይዘቶች ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉና ትምህርታቸውን እንዲጠኑ እገዛ አድርጓል።
በተጨማሪም የማህበራዊ ሚዲያዎችን የአጠቃቀም ችሎታ እንዳሳደገላቸው ተማሪ አብዱ ተናግሯል።በዚህ ሁኔታ ፈተናዎች ጭምር ይሰጣሉ ብሎ እንደጠበቀ የሚናገረው ተማሪ አብዱ አሁን ላይ ግን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ መመሪያዎች ሲያወርድልን ነው የፈተና ጊዜ የማናሳውቃችሁ የሚሉ መልዕክቶችን ትምህርት በሚላላኩባቸው የማህበራዊ ሚዲያ ትስስሮች ስለገለጹላቸው በመጠበቅ ላይ እንደሆኑ ተናግሯል።ይህ ጊዜ ከትምህርት ቤት እና ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር በመሆን በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ በመሰማራት እያከናወኑ በመሆናቸው ጊዜውን ደስተኛ ሆኖ እንዲያሳልፍ እንዳገዘውም ተማሪ አብዱ ተናግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የመሰናዶ ትምህርት ቤት የኬምስትሪ አስተማሪው መምህር ጌታቸው ክፍሌ በበኩሉ መንግስት ትምህርት ቤቶችን መዘረጋቱ የወረርሽኙ
መስፋፋት ለመቆጣጠር የሚያስችል ተገቢ ርምጃ እንደሆነ ያምናል።ትምህርት ቤቶችን መዝጋት ብቻም ሳይሆን የዓለም አገራት የሚሄዱበትን ርቀት ለመከተል ይሞክራል።ለምሳሌ ለተማሪዎች ትምህርት ለማድረስ ይጥራል።ተማሪዎች በቤታቸው በሚቀመጡባቸው በዚህ ወቅት የተለያዩ የፈጠራ ስራዎችን እንዲሰሩና እንዲወዳደሩ ጭምር እድሎችን እያመቻቸ እንደሆነ ያስረዳል።ነገር ግን ካለው የኢንተርኔት የተጠቃሚነት፣ የተደራሽነት አቅምና ልምድ የተነሳ በቂና ከፍተኛ ሚና ያለው ስራ መስራት ባይችልም ሙከራዎቹ የሚበረታቱ እንደሆነ ተናግሯል።እነዚህ በማህበራዊ ሚዲያዎች በተፈጠሩ ትስስሮች የተሰጡ ትምህርቶች ለፈተና ያበቃሉ የሚል እምነት እንደሌለው የተናገረው መምህሩ፤ የሚኒስትሪ ፈተናዎች የሚዘጋጁት በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም ተማሪዎች በመሆኑ በርካታ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ደግሞ የቴክኖሎጂ ተደራሽነቱ ውስን ስለሚሆን በዚህ መንገድ በተሰጠ ትምህርት መፈተን አይችሉም ባይ ነው።ነገር ግን ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ እንዳያጠፉ እና ትምህርት እየተማርኩ ነው የሚል ስሜት በማሳደር በኩል የማይተካ ሚና እንደተጫወተ አስረድተዋል።
መደበኛው የመማር ማስተማር ሂደት የተቋረጠው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ነው።ስለዚህ ተማሪዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከወረርሽኙ እንዴት መጠበቅ እንዳባቸው እንጂ የፈተናውን ጉዳይ መንግስት የሚያስብበት በመሆኑ እነሱን ሊያሳስባቸው እንደማይገባም መክረዋል።
የተለያዩ የዓለም አገራት የትምህርት ዘርፍ ባለሙያዎችም ወረርሽኙ በፈጠረው ችግር የተነሳ መፍትሄዎች ለማበጀት በርብርብ ላይ እንደሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።በዚህ የተነሳም በትምህርት ፖሊሲው ላይ አንዳች ለውጥ ይዞ የሚመጣው እንደሆነ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።በቴክኖሎጂ ታግዞ የማስተማር ስነዘዴው የትምህርት ሥርዓት ሆኖ ሊቀጥል የሚችልባቸው እድሎች እንዲፈጠሩም የአሰራር ሥርዓትን የሚያበለጹጉ ‹‹አፕልኬሽኖች›› እና ‹‹ሶፍት ዌሮች›› ለማበርከት በሰፊው እየተሰራ ነው።ወደዚህ አይነት ገበያው ጓዛቸውን ጠቅልለው በመግባት ላይ የሚገኙም ድርጅቶች ቁጥር እያሻቀበ
መጥቷል፡፡
በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎችም ቢሆኑ በቀጣይ የመማር ማስተማሩን ስራ ሊያግዙና ሊያሳልጡ በሚችሉ ስራዎች ላይ ተጠምደው እንደሚያሳልፉ ይገልጻሉ።ከመግለጽ ባለፈ አገራት፣ ተቋማት እና በትምህርቱ ዘርፍ የሚሰሩ ድርጅቶች በአሰራሮቻቸው ዙሪያ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶችን፣ የትብብር ስራዎችን እና የቅንጅት አሰራሮችን የበለጠ ለማሳለጥ እድሎች የሰጠ በመሆኑ የወረርሽኙን መከሰት በበጎ ጎኑ የሚያነሱም አልጠፉም፡፡
እነዚህን ተሞክሮዎች ኢትዮጵያም ማስፋት ይገባታል።ምክንያቱም በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ላይ መቋጫ ያላገኙ በርካታ ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ብዙ ናቸው።ለአብነት ያህልም ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ማጥራት፣ በዘላቂነት ፋይዳ የሚያስገኙ የቴክኖሎጂ አሰራሮች መዘርጋት ፣የመረጃ ሥርዓቱን ማደራጀት፣ በዘርፉ የተሰሩ ተቋማት በአሰራር ወጥ ሆኖ መናበብ መቻል እና ሌሎች በርካታ ሊሰሩ የሚገባቸው ተግባራት አሉ።ስለሆነም እነዚህን መልክ ማስያዝ የሚችሉባቸው አሰራሮችን ለመዘርጋት ጊዜውን ቢጠቀሙበት አገራዊ ፋይዳው የላቀ ነው።
በአጠቃላይ በመላው ዓለም 290 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው በየቤታቸው እንደሚገኙ የዩኒሴፍ መረጃ ያሳያል።ቅድሚያ ለጤና እንጂ ቅድሚያ ለትምህርት የሚሰጥ ባለመሆኑ ተማሪዎች በየቤታቸው መሆናቸው ተገቢ ነው።ነገር ግን የትምህርት በቤትዎን መርህ በማስታወስ ሥራ ፈት ሆነው ከሚቀመጡ በቴክኖሎጂዎች እየታገዙ ሊማሩ ይገባል በማለት ይመክራል። አያይዞም ተማሪዎች ከፍተኛ የሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ልምድ እንደሚያስገኝላቸው ተገንዝበው በቴክኖሎጂ ማቀድ፣ በቴክኖሎጂ መወያየት፣ በቴክኖሎጂ መረጃ መሰብሰብ፣ እና በጥቅሉ በቴክኖሎጂ የማይሰራና የማይከናወን ተግባር አለመኖሩን ተገንዝበው ብቃታቸውን ለማሳደግ መማር እንዳለባቸው እና በየአገራቱ የተጀመሩ ጥረቶች መጠናከር ይገባቸዋልም ነው ያለው፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
ሙሐመድ ሁሴን