የሥነ-ትምህርት ሳይንስም ሆነ ፍልስፍና እንደሚለው፤ የሁሉም ነገር መሰረት ትምህርትና የሱው ውጤት የሆነው እውቅት እንዲሁም «ፖሊሲውን» ነው። በመሆኑም የሁሉም ነገር (“ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር …” እያልን አይደለም) የስበት ማእከል ትምህርት ሆኖ ትኩረቶች ሁሉ እሱው ላይ አርፈው ይታያሉ። ለውድቀትም ሆነ ለእድገት ተጠያቂው ትምህርትና ይሄው ከላይ “ፖሊሲ” ያልነው ፖለቲካ መራሹ ሰነድ ነው። ወደ ጨረቃ መውጣት አለመውጣት ምክንያቱ ትምህርትና የሚመራበት ፖሊሲው ነው በሚል ስርአተ-ትምህርታቸውን የፈተሹ፤ የመረመሩና ሊያመጥቃቸው በሚችል መልኩ እንደገና የቀረፁ ወገኖች ተጠቃሚ ሆነውበትም ታይቷል። ባጭሩ ዶ/ር እጓለ ለሁሉም ነገር ስኬት “አንደኛ ትምህርት፣ ሁለተኛም ትምህርት፣ ሶስተኛም ትምህርት” እንዳሉት ነው።
የትምህርት ስርአትም ሆነ “ፖሊሲ” የሚቀየረው ለተሻለ የሰብእና እድገት፤ ለኣንዳች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ከሁሉም በላይ ሰብአዊ ፋይዳ እንጂ ለዜሮ ድምር ተብሎ ወይም በአጉራህ ጠናኝ ስሜት እንደ አሮጌ ጫማ አሽቀንጥሮ በመጣል በሌላ በባሰበት ለመተካት አይደለም። ትውልድም የሚመዘነው በዚሁ ትምህርትና ፖሊሲ ተብዬው መስፈርት ነውና የተጣመመ ፖሊሲ የፈጠረው የተጣመመ ትውልድ ወደ ህዋ ሊወጣ ቀርቶ ራሱ ህዋ ስለመኖሩም ላያውቅ ይችላል። በዚህ ደግሞ ከቶም ሊፈረድበት፤ ሊኮነን አይገባውም። ወደ መነቀል-መነጠላችን እንምጣ።
አንዳንድ ሰዎች ንግግራቸውን ሲጀምሩ ኮስተር ብለው–”በመሰረቱ”–በማለት ነው። እኛም ይህንኑ እንዋስ።
በመሰረቱ በእኛ አገር መማር-ማስተማር ሂደት መነቀል ወመነጠል ሲስተዋል አዲስ አይደለም። ነበር፤ ይኖራልም – ፈጣሪ በመገላገያው ካልገላገለን በስተቀር። ይህን ስንል ዝም ብለን አይደለም፤ ለዚህ የትምህርት ኮሌጅ ሰው መሆንም አይጠበቅብንም። መንግስት በተቀየረ ቁጥር የሆነውን ሁሉ
ማየት፤ የፀደቁና የተሻሩ ፖሊሲዎችን መፈተሽ ብቻ በቂ ነው።
ወደ ኋላ ሄድ ብለን ጥቂት ብንመለከት እንኳን የንባብ ቤት፣ የቅኔ ቤት፣ የዜማ ቤት፣ የትርጓሜ ቤት ወዘተ ሀይማኖታዊ ናቸው ተብለው ተነቅለው ተጥለዋል፤ ተማሪዎችም ከእነዚህ የትምህርት አይነቶች ተነጥለዋል። የዛሬው ትውልድ እነ “አቡጊዳን” የሚያውቀው በዘፈን ነው። በአሁኑ ሰአት “መልእክተ ዮሀንስ”ን ያነሳ ሰው ካልተሳቀበት ይገርማል። ቀጥታ ወዳለንበት እንምጣ።
ከአሁኑ አስቀድመው ይሰጡ የነበሩ የትምህርት አይነቶች ከ”እርሻ” (ዛሬ ስለ ችግኝ ማፍላት፣ ዛፍ መትከል፣ አካባቢ ጥበቃ፣ የጓሮ አትክል ልማት ከፍተኛ ወጪ እየወጣ በየቀበሌው ትምህርት ሲሰጥ ይታያል፤ ቀደም ሲል ግን እነዚህ ሁሉ የሚያልቁት በትምህርት ቤት፤ በ”እርሻ ክፍለ ጊዜ” ነበር።) ጀምረው፣ “ሙዚቃ”ን አስከትለው፤ “እጅ ስራ” (እደ-ጥበብ)ንና “ባልትና ሳይንስ”ን አካተው፣ የ”እንጨት ስራ”ና “ኤሌክትሪሲቲ”ን በጎንና ጎን፣ “ሥነ-ሥእል”ን በግራ ሸጉጠው ለተማሪዎች ይቀርቡ የነበሩ ሲሆን፤ ከዋና ዋና የትምህርት አይነቶቹ ጋር መሳ ለመሳ (ከክፍለ-ጊዜ ብዛት በስተቀር) በሙያው በሰለጠኑ መምህራን ይሰጡን ነበር – ሳይነቀሉ። እነዚህ የትምህርት አይነቶች ለተማሪዎች ሁለንተናዊ/ሁለገብ ሰብእና ያደረጉትን አስተዋፅኦ ለባለሙያዎቹ ትተን በግርድፉ እንያቸው።
ትምህርቶቹ ተፈጥሯቸው በራሱ “ንድፍ-ተኮር”፣ “ፕሮጄክት-ተኮር” ከሚሏቸው የትምህርት አይነቶች የሚመደቡ ሲሆን ይህም በክፍል ውስጥ ከሚሰጠው የንድፍ ሀሳብ ትምህርት ጎን ለጎን ንድፈ ሀሳቡን ወደ ተግባር ለመተርጎም በሚያስችል መልኩ የተቀረፁ፤ ተማሪው ገና ከጅምሩ በወደፊት የግል ህይወቱ የሚጠብቁትን ተግባራት የሚያውቅበትና በመጪው ህይወቱ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ ናቸው። ምን ያደርጋል፤ እነዚህ የትምህርት አይነቶች ከትምህርት ገበታው ላይ ተነቀሉ፤ ተማሪውም ከእነዚህ ትምህርቶች ተነጠለ።
ቀደም ባለው ጊዜ ስለ ሙዚቃ ፅንሰ-ሀሳቦች፣ መሳሪያዎች፣ ምንነትና ፋይዳቸው፣ ስለአምስቱ የኢትዮጵያ ቅኝቶች ወዘተ
እውቀት የሚገበየው ገና 7ኛ ክፍል እንደተገባ ነበር። ሙዚቃውም ተነቀለ፤ ተማሪውም ተነጠለ። ስለ እደ ጥበብ እውቀት የሚገኘው እንዲህ እንደዛሬው በመደራጀት ሳይሆን በመደበኛው ትምህርት በ”እንጨት ስራ” አማካኝነት ከጠቀስነው ክፍል ጀምሮ ነው። እያንዳንዱ ተማሪ ይለካል፣ ይቆርጣል፣ ከመጋዝ ጀምሮ የሁሉንም መሳሪያዎች አጠቃቀም አሳምሮ ያውቃል፣ ዳስተርና የመሳሰሉትን ይሰራል፣ ዲዛይን ያደርጋል፣ ተገቢውን የህይወት ትጥቅ ይዞ ይወጣል። የሚያሳዝነው ዛሬ ሁሉም ከስርአተ-ትምህርቱ ተነቅለዋል፤ ትውልድም ከእነሱ ተነጥሏል። ሀሳባችን ግልፅ ነውና ሌሎች ተነቅለው የተጣሉትን በዚሁ አይነት ሳንዘረዝራቸው ብናልፍ መልእክቱን ጎዶሎ አያደርገውምና ላንባቢ ትተን እንሂድ። (አይ የሚል ካለም የ”ሥነ-ምግባር” ትምህርትን ጉዳይ አንስተን መነጋገር እንችላለን።)
ሁሌም እየተነገረ የምንሰማው፣ እየተፃፈ የምናነበው ትምህርት ነክ ጉዳይ ቢኖር “ቀድሞ የነበሩ አሁን ግን የሌሉ” በሚል ቁጭት ላይ የቆመ ስለ “አገር፣ ባንዲራ፣ የጋራ ባህል፣ እሴትና ትውፊት፣ ታሪክ” ወዘተ የሚያውቅ ትውልድ ቁጥሩ እየተመናመነ፣ ወደ መጥፋት ደረጃ እየደረሰ መገኘቱን የሚወተውት ተረክ ሲሆን፤ ለዚህም የጠቀስናቸውና ሌሎች ነባር የትምህርት አይነቶች ከስርአተ-ትምህርቱ መነቀላቸውና ተማሪዎችም ከእነዚህ አገራዊ ፍልስፍናን፣ ባህልን፣ የአኗኗር ዘዴ/ዘይቤን፣ ማህበራዊነትን፣ ባህላዊ አሰራርንና አመራረትን፤ ከሁሉም በላይ ሰብአዊነትን ከሚያሰርፁ ትምህርቶች መነጠሉ እንደሆነ ብዙም ሳንርቅ የመስፍንን “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ”ን፣ የእጓለን “የከፍትኛ ትምህርት ዘይቤ”ንና መሰል ስራዎችን ቀስ ብሎ መመልከት ይበቃል። “ሁሉም ዜሮ ዜሮ” ከመሆኑ በፊት ማለት ነው።
ብሩክ አለምነህ በ”የኢትዮጵያ ፍልስፍና”ው እንደሚነግረን “በሳይንስ፣ ኢንጂነሪንግ፣ ሂሳብና ቢዝነስ ትምህርቶች የሰውን ልጅ ባህል/አስተሳሰብ አኗኗር መቀየር አይቻልም። […] መቀየር የሚቻለው የራሱንና የህብረተሰቡን ኑሮ እንደ መስተዋት ሆነው
በሚያሳዩ ትምህርቶች ነው።” (ገፅ 163) እኛም የምንለው ይሄንኑ ነውና ብሩክን እናመሰግናለን። (በእርግጥ የአዲስ አበባ መስተዳድር በከተማዋ በሚገኙ 90 ት/ቤቶች የግብርና ተግባራትን ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ነግሮናልና ይበል እንላለን።)
በአሁኑ ዘመን ትምህርቶቹ እንዲነቀሉ፣ ተማሪዎችም እንዲነጠሉና ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ በእነዚህ የትምህርት ዘርፎች ከዜሮ ለመጀመር፤ የተነቀሉትን ፍለጋ በጥቃቅንና አነስተኛ ሲደራጁ እያየን ነው። የተነቀሉቱ የተማሪዎችን የፈጠራ ስራ፣ የስራ ባህልንና የጋራ እሴት፣ ኢኮኖሚያዊ ብልፅግና፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚ (ባሁኑ ቋንቋ) ወዘተ ሁሉ እውቀትና ክሂል ከማዳበር አኳያ የሚተካቸው የለም። ኬሚስትሪም ይሁን ፊዚክስ፤ እንግሊዝኛም ይሁን ሂሳብ … አንዳቸውም ሊተኳቸው የሚችሉ አይደሉም (ኣያስፈልጉም አላልንም)። እዚህ ጋር አንድ አስገራሚ ጉዳይ አለና በእሱ እንለያይ።
አስገራሚው ጉዳይ ከንቅለ-ንጠላው በኋላ እላይ ለማገናኘት የምናደርገው ጥረት ነው። ትምህርቶቹ ከትምህርት ሰሌዳው ይነቀሉ፤ ተማሪዎችም ይነጠሉ እንጂ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ እራሳቸውን ችለው የሚሰጡና እስከ መጨረሻ ዲግሪ ድረስም የሚያስመርቁ መሆናቸው ነው። ጥያቄው የት በያዙት መሰረት ነው ምርጫቸው ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት፣ ሀሮማያ ግብርና ዩኒቨርሲቲ፣ አዲስ አበባ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ … የሚሆነው? ከገቡስ በኋላ ተቋማቱ ከየቱ ጋር ጀምረው ነው ትምህርቱን ለተማሪዎቹ እሚሰጡት?
ከመነቀልና መነጠል ጋር በተያያዘ ከላይ ያየነውና በታችኛው ላይ የተፈፀመ ሳይሆን በላይኛው፤ በከፍተኛ ትምህርትም ተከናውኗል። የታሪክ፣ ፎክሎር … ትምህርቶች ተነቅለው፣ መምህራንና ተማሪዎች ከመስኩ ተነጥለው እነሆ የ”ተመልሶ ይተከል” ክርክሩ ብቻ ቀርቶ ይገኛል። ሌላም ብዙ አለ። “ከመነቀል እና መነጠል ይሰውረን” ብለን እንተወው እንጂ።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
ግርማ መንግሥቴ