ውቤ ከልደታ
ዓለም የተለያዩ የአስተዳደር መርሆዎች አሏት። ዴሞክራሲን አስፍነናል ከሚሉት የአሜሪካና አውሮፓ አገራት ጀምሮ ፍፁም አምባገነናዊ ናቸው በሚል እስከሚተቹት የአፍሪካና የኤሽያ አገራት ድረስ ሁሉም የየራሳቸው መርህ አላቸው። አንዳንዶቹ ለህዝባቸው የተሻለ ነገር ለመስራት ፍፁም አምባገነናዊ ስርዓት ያስፈልጋል በሚል ወታደራዊ አገዛዝን ተግባራዊ ሲያደርጉ ከፊሎቹ ደግሞ ዴሞክራሲ ለሰው ልጆች ወሳኝ ነው በሚል ሌሎችም ይህን እንዲከተሉ ከመምከር እስከማስገደድ ይሄዳሉ። ያም ሆኖ ግን ልዩነቶቹ እንደተጠበቁ እንደየአገሩ አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ሁሉም የየራሱን ስርዓት ተግባራዊ ያደርጋል።
የአህጉራችን አብዛኞቹ አገራትም በአምባገነናዊ ስርዓቶቻቸው ይተቻሉ። በተለይ በአብዛኛው መሪዎች ወደስልጣን የሚመጡበት መንገድ በጦርነትና በኃይል መሆኑ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል። ወደስልጣን ከመጡ በኋላም በተለያዩ መንገዶች በማጭበርበር የስልጣን እድሜን የሚያራዝሙ መሪዎች ቁጥር ቀላል አይደለም።
በእንዲህ አይነት መንገድ ስልጣን ላይ የወጡና የቆዩ መሪዎች ስልጣን የሚጠቀሙት ለግል ፍላጎት ማሟያ ነው። በአፍሪካ አንዴ ስልጣን ላይ የወጡ መሪዎች ከስልጣን መውረድ ጣዕረሞት ስለሚሆንባቸው ስልጣንን ሙጭጭ ብለው መያዝ የተለመደ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ስልጣን ላይ በሚቆዩበት ወቅት በተለያዩ ወንጀሎችና ሙስናዎች ስለሚነከሩ ከስልጣን መልቀቅ ተጠያቂነት ያስከትላል በሚል ፍራቻ ነው።
በአፍሪካ ባለስልጣን መሆን ህዝብን ለማገልገል ከሚውልበት አግባብ ይልቅ ለራስ ለመጠቀም የሚውልበት መንገድ ከፍተኛ ነው። በዚህ የተነሳ ስነቃሎቻችን ጭምር ይህንን የስልጣን ምንነት የሚያሳዩ ናቸው። “ሲሾም ያልበላ፤ ሲሻር ይቆጨዋል” የሚለው የአበው አባባል ለዚህ ማሳያ ነው። በቅርቡ በኢህአዴግ ዘመን ደግሞ “የኢህአዴግ ስልጣን የዛፍ ላይ እቅልፍ ነው” በሚል ከስልጣን ላይ የምትወርድበት ጊዜ አይታወቅምና ስልጣን ላይ እስካለህ ድረስ ቶሎ ብለህ ለራስህ የሚጠቅሙ መንገዶችን ሥራ የሚል መልዕክት ይተላለፋል።
በአፍሪካ ባለስልጣን መሆን የተሻለ መኪና ለመንዳት፣ የተሻለ ቤት ባለቤት ለመሆን፣ ሌሎች የቅርብ ዘመዶችን ለመጥቀም፣ ወዘተ ያስችላል። በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችንም የስልጣን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። ሥራ ለመቀጠር፣ የተሻለ የንግድ ሥራ ለማካሄድ፣
የገበያ ትስስር ለመፍጠር፣ ወዘተ ባለስልጣን ዘመድ የግድ ያለበት ነባራዊ ሁኔታን እናስታውሳለን። እነዚህና መሰል ነባራዊ ሁኔታዎች የስልጣንን ዋጋ በእጅጉ አስፈላጊ ያደረጉ ሁነቶች ናቸው።
በሌላ በኩል በዚህ ዘመን ራሳቸውን የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ቁንጮና ጠበቃ አድርገው የሚመለከቱትን የአሜሪካና የአውሮፓ አገራትን ስንመለከት ዴሞክራሲን ለመለማመድ ምን ያህል ረጅም ጊዜን የሚፈልግ እንደሆነ እንረዳለን። ለምሳሌ አሜሪካ ዴሞክራሲዊ ስርዓትን ገንብተናል ካሉ ከ200 ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። ነገር ግን ከነዚህ ረጅም ዓመታት በኋላ እንኳን አሁንም በዴሞክራሲ ትግበራ ላይ የሚታዩ በርካታ ህጸፆች አሉ። በተለይ የጥቁር ህዝቦቿን ነፃነት ከማክበር አንጻር ገና ብዙ የቤት ሥራ እንዳለባት የሰሞኑ የጆርጅ ፍሎይድ አሟሟትና ያስነሳው ቀውስ ማሳያ ነው። በየጊዜው በሚታዩ ክፍተቶችም መነሻነት ህገመንግስቱ እየተሻሻለ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
230 ዓመታትን ባስቆጠረው የአሜሪካ ህገመንግስት ውስጥ የህግ ማሻሻያዎች እንዲካሄዱ 11ሺህ 770 ጥናቶች ተደርገዋል። ከነዚህ ውስጥ የአሜሪካ ኮንግረስ የህገመንግስት ማሻሻያዎች እንዲደረጉ 33 ጊዜ የውሳኔ ሃሳብ ያቀረበ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 27ቱ ፀድቀው ወደተግባር ተቀይረዋል። በሌሎች አውሮፓ አገራትም የህገመንግስት ማሻሻያዎችን ማካሄድ የተለመደና የዴሞክራሲ እድገት ማሳያዎች ተደርገው ይወሰዳሉ።
በአገራችንም ቢሆን የዴሞክራሲ ስርዓቱን መሰረት እንዲጥል ጥረቶች እየተደረጉ ነው። በ1987 ዓ.ም የፀደቀው የአሁኑ ህገመንግስት በአተገባበሩ ላይ በርካታ ህፀጾች ቢነሱበትም ላለፉት 25 ዓመታት ሥራ ላይ ቆይቷል። በነዚህ ዓመታት ግን አንድም ጊዜ ማሻሻያዎች አልተደረጉለትም። ዘንድሮ ሊካሄድ የታቀደውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ ግን ባጋጠመው ችግር ምክንያት ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉና በዚህ አጋጣሚ የሚፈጠረውን የህገመንግስት ክፍተት ለመሙላት የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤው ጥናት አድርጎ የህገመንግስት ትርጉም መስጠቱ ይታወሳል። በዚህም መሰረት በኮሮና ምክንያት ምርጫ ለማካሄድ የማይቻልበት ሁኔታ በመኖሩ ምርጫውን ማራዘም ማስፈለጉንና በዚህ መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ኮሮና ወረርሽኝ እስከሚገታ ድረስ ስልጣን ላይ እንዲቆይ መወሰኑ ይታወቃል። ይህ የህግ ውሳኔ ደግሞ አንዱ የአገራችን ህገመንግስት ማሻሻያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህ ውሳኔ የአገሪቱን ህገመንግስት ያከበረና
ለህገመንግስቱ መሻሻል እድል የሰጠ ሲሆን በቀጣይም የተሻለ ህገመንግስት ለመፍጠር ለሚደረገው ጥረት አጋዥ እንደሚሆን ይታሰባል። ህገመንግስቱን በየምክንያቱ አፍርሶ አንድ ብሎ ከመጀመር ባለው ላይ እየጨመሩ መሄድ ዴሞክራሲውን ወደፊት የሚያስኬድ በመሆኑ የሚበረታታ ተግባር ነው። እንዲህ አይነት ባህሎችም ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል።
ሌላው የአገራችን የዴሞክራሲ እድገት ማሳዎች ደግሞ በመሪዎቻችን ላይ እየመጡ ያሉ ለውጦች ናቸው። ለምሳሌ በአገራችን የስልጣን ገደብን በማበጀት ስልጣንን ለተተኪው አስረክቦ መውረድ በኢፌዴሪ ህገመንግስት በመስፈሩ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ አንድ ማሳያ ነው። ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ ህገመንግስት ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ አምስት ፕሬዚዳንቶችን ቀያይራለች። ከነዚህም ውስጥ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በስልጣን ላይ እያሉ ስልጣን በቃኝ ብለው የለቀቁ መሪ ናቸው።
ሌላው ደግሞ የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ የጀመሩት የመተካካት መርህ አንዱ የዴሞክራሲ እድገት ማሳያ ጅማሮ እንደነበር ብዙዎች ይመሰክራሉ። በርግጥ ይህ አሰራር በአቶ መለስ ህልፈተ ህይወት ቢጨናገፍም በስልጣን ላይ ያለው ኃይል ለተተኪው ትውልድ ስልጣን ለማስረከብ ትልቅ እድልና አጋጣሚ እንደነበር ይነገራል።
ከዚያ በኋላ በአገሪቱ ታሪክ ትልቅ የዴሞክራሲ እመርታ ተደርጎ የተወሰደው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቅ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምንም እንኳ ከፍተኛ ጫና በዝቶባቸው ስልጣናቸውን እንደለቀቁ ቢገለፅም በገዛ ፈቃዳቸው የወሰዱት እርምጃ ግን በብዙዎች ዘንድ ስልጣን ለህዝብ ማገልገያ እንደሆነ ያሳዩበት እንደነበር ይመሰክራሉ። ለዴሞክራሲ እድገትም ትልቅ እርምጃ ተደርጎ የወሰዳል።
በአጠቃላይ በአገራችን አሁን ዴሞክራሲው መንገድ ገና በእንጭጭ ደረጃ ላይ ያለ ነው። ይህ ዴሞክራሲ አድጎና ጎልብቶ ስርዓት እስከሚሆን ድረስ በርካታ መንገጫገጮች ይገጥሙታል። እስከዚያም ድረስ ፈተናዎች እንደሚበዙ ይታመናል። ያም ሆኖ ግን አልፎ አልፎ የሚታዩት ጅምር የዴሞክራሲ አግባቦች መስመሩን የሚገነቡ በመሆኑ ሊበረታቱ ይገባል። እንዲህ እንዲህ እያለ ከሄደ ዴሞክራሲያችን ልክ እንደሰለጠኑት አገራት መሰረት የማይይዝበትና ምርጫ በመጣ ቁጥርም ሳንሳቀቅ የምንፈልገውን የምንመርጥበት አስተማማኝ ስርዓት እንደሚፈጠር ጥርጥር የለውም።
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
ውቤ ከልደታ