ኮሮና ቫይረስ በመላው ዓለም እና በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየተሰራጨ እና የሰዎችንም ህይወት እየቀጠፈ የሚገኝ ወረርሽኝ ነው። የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ሃላፊነት በተሞላበት ምላሽ በብዙ መገደብ የሚቻል መሆኑ ይታወቃል። ግን “የማን ሃላፊነት ነው?” የሚለውን ጥያቄ በወጉ መመለስ ያስፈልጋል።
ሰዎች በአመዛኙ ሃላፊነት ለሚወስዱበት ነገር ትኩረት እና ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ሃላፊነት ሲወስዱ እያንዳንዱን ንግግራቸውንና ተግባራቸውን ይመዝናሉ፤ ንግግራቸውና ድርጊታቸው የሚያመጣውንም ውጤት ይመረምራሉ፤ ለስማቸው፣ ለሃላፊነታቸው፤ ለሥራቸው እና ለደህንነታቸው ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄ ያደርጋሉ። ሃላፊነቶች የሚከፋፈሉ እንጂ በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ብቻ የሚወድቁ አይደሉም።
አንዳንድ ሰዎች ሃላፊነት መውሰድ እንደሚከብዳቸው ይታወቃል። ይህ ከመጠን ካለፈ ደግሞ የስነልቦና ችግር ይፈጥራል። አንዳንድ ምሁራኖች እንደሚሉት ሰዎች ለሚያደርጉት ወይም ለማያደርጉት ነገር (action or in¬action) ሃላፊንት መወሰድ ሲሳናቸው ሃላፊነት የጎደለው የአኗኗር ቀውስ (Responsibility Deficit Syndrome) ሰለባ ይሆናሉ።
በሌላ መልኩ ሰው ለሁሉም ነገር ሃላፊነት መውሰድ አይጠበቅበትም። ለሁሉም ነገር ሃላፊነት መውሰድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። በስነልቦና ሳይንስ
ውስጥ “ለሁሉ ነገር ሃላፊነት መውሰድ አለብኝ” የሚሉ ሰዎች በተለያዩ የስነልቦና ጫናዎች እና ቀውሶች ሊሰቃዩ ይችላሉ። ለምሳሌ የሌላውን ሃላፊነት የራሳቸው አድርገው የሚወስዱ ሰዎች በስነልቦና ጫና (stress) ውስጥ ከመውደቃቸውም በላይ በአንዳንዶች ላይም በሃሳብ የመብሰልሰልና- በድርጊት የመገደድ ህመም (OCD) ጋር እንደሚያያዝባቸው አንዳንድ ጥናቶች ይጠቁማሉ። የዚህ ህመም ሰለባዎች አንድ ነገር ጉዳት ያደርሳል ብለው ሲያስቡ ራሳቸው ላይ ወይም ሌላው ሰው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ወይም ራሳቸውን ወይም ሌላውን ሰው ከጉዳት ለመጠበቅ ከመጠን ያለፈ ሃላፊነት ይወስዳሉ። ይህ ደግሞ ለፍርሃት እና ለከፍተኛ ጭንቀት ይዳርጋቸዋል። ለሁሉም ነገር ሚዛናዊ መሆን ይጠይቃል። አርስቶትል “ጥበብ ያለበት ምርጫ መካከለኛው ነው” ይላል።
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን የመገደብ ሃላፊነት ታዲያ የማን ነው? ወላጆች ስለ ልጆቻቸው እጅግ ይጨነቃሉ፤ ያስባሉ፤ ይፈራሉ። በተቻለ መጠን ልጆቻቸው ከዚህ ወረርሽኝ ተጠብቀው መጪውን ዘመን እንዲያዩ ትግል ያደርጋሉ፤ ልጆቻቸውን “ከቤት አትውጡ፣ ከሰው ጋር አትገናኙ፤ እጃችሁን ታጠቡ፤ አፍና አፋችሁን ሸፍኑ” ወዘተ እያሉ ይወተውታሉ። ልጆቻቸው በኮሮና ቫይረስ እንዳይያዙ ሃላፊነቱ የማን ነው? የወላጆች ብቻ ነው? ወይስ ልጆቹም ሃላፊነት አለባቸው? ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል።
መንግስት ዜጎች በኮሮና ቫይረስ እንዳይያዙና እና ሊፈጠር የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ እንዳይሆን ጠቅላይ
ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናትና ሚዲያዎች ትኩረታቸውን ሁሉ
የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በማስተማርና በመምከር እያሳለፉ ይገኛሉ። መንግስት ከማስተማርና ከመምከር በተጨማሪ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ ዜጎች ሊያደርጉ የሚገቧቸውን ጥንቃቄዎች በህግም ደንግጎ ተፈፃሚ እንዲሆኑ እየታገለ ይገኛል። ዜጎችን ከኮሮና ቫይረስ የመታደግ ሃላፊነት የማን ነው? የመንግስት ብቻ ነው? ከላይ ላሉት ጥያቄዎች ምላሽ ማግኘት ያስፈልጋል።
ሃላፊነት የመውሰድ ጉዳይ መርህ አለው። ለአንድ ሰው ወይም ለአንድ አካል የሚሰጥ ብቻ አይደለም። ወላጆች ሃላፊነት እንዳለባቸው ሁሉ ልጆችም ሃላፊነት አለባቸው፤ መንግስት ሃላፊነት እንዳለበት ሁሉ ዜጎችም በመንግስት የተደነገጉ ህጎችንና መመሪያዎችን በማክበር እና በመተግበር ራሳቸውንና ሌሎችን የመታደግ ሃላፊነት አለባቸው፤ ሚዲያው ሃላፊነት እንዳለበት ሁሉ እያንዳንዱ የሚሰማው ግለሰብ በምክሮቹና በትምህርቶቹ የሚተላለፉ መልእክቶችን የመተግበር ሃላፊነት አለበት፤ አንዱ ሃላፊነቱን እየተወጣ ሌላው ሃላፊነቱን በማይወጣበት ሁኔታ የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት መግታት አይቻልም።
የኮሮና ቫይረስን ሥርጭት ለመግታት የሃላፊነት ክፍፍል ይጠይቃል። በሃላፊነት ክፍፍል (Responsi¬bility Pie) ውስጥ “የኔ ሃላፊነት ምንድ ነው?” ብሎ እያንዳንዱ ሰው እና ተቋም ራሱን ሊጠይቅ ይገባል። ዜጎች ኮሮና ቫይረስን የመከላከል ሃላፊነት የመንግስት ብቻ እንደሆነ ሊያስቡ አይገባም፤ መንግስት ድርሻ አለው፤ ዜጎችም ድርሻ አላቸው፤ ቤተሰብ ድርሻ አለው፤ የሃይማኖት እና ሌሎች ተቋማትም ድርሻ አላቸው፤ እኔና እርሶም ድርሻ አለን። በመሆኑም አንድን ችግር ለመወጣት ለምሳሌ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት የግል እና የጋራ ሃላፊነቶች እንዳሉን ተረድተን ሁላችንም በየፊናችን ሃላፊነቶቻችንን ልንወጣ ይገባል። ሰዎች የራሳቸውን ሃላፊነት ሲወጡ የአሸናፊነትን ስሜት ይጎናፀፋሉ፤ ደስታን ይፈጥርላቸዋል፤ ከህሊና ተጠያቂነትም ይድናሉ፤ ለራሳቸውና ለሌሎች ሰዎች ያላቸውን ዋጋ ተምነዋልና የአዕምሮ እረፍትን ይጎናፀፋሉ!!
ቸር እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ሰኔ 12/2012
ወንድወሰን ተሾመ
(የስነልቦና ባለሙያ)