ሙስናን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ቢሆንም ትግሉ በቂ ውጤት አላስገኘም፡፡ በአሁኑ ወቅትም ሙስናን ለመዋጋት ተቋማት የየራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ነው፤ ለዚህ ደግሞ የፌዴራል የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፀረ ሙስና ትግል እንዲጠናከር የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክተሮችን እያቋቋመ ነው።
ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ አቶ ከበደ ኩማ፤ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በርካታ ፕሮጀክቶች ስላሉ በሚሰራው ስራ ላይ ግልጸኝነትና ተጠያቂነት መኖር እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡ በዚህ አካባቢ የሚወጣው ገንዘብ ብዛት ያለው ከመሆኑም በተጨማሪ ከአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ምሁራን የሚሳተፉበት ብሎም ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈስበት መሆኑ ሊጤን ይገባል፡፡ በዚህ ላይ የሚሰሩ ተግባራትም ጥቅማቸው እንዳለ ሆኖ ከሙስና ጋር የተንሰላሰለ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡
የድሃ አርሶ አደርን ንብረት መስረቅ ‹‹ከነውሮች ሁሉ ነውር›› ነው የሚሉት አቶ ከበደ፤ በትምህርት ተቋማት በርካታ ፀያፍ ተግባራት እንደሚከናወኑ ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም እነዚህን ተቋማት በበላይነት የሚቆጣጠረው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በዚህ ላይ በአንክሮ መስራትና ከኮሚሽኑ ጋር መናበብ አለበት፡፡ ሚኒስቴሩ በጀት ከመመደብ በዘለለ ገንዘቡ ምን ያክል ሥራ ላይ ውሏል የሚለው በጥልቀት ሊመረምርና በቦታው ሙስናን ሊዋጉ የሚችሉ ቅንና ጠንካራ ሰዎችን መመደብ አለበት፡፡ የፌዴራል ኦዲት ምርመራ ውጤትም በዩኒቨርሲቲዎች ላይ ትኩረት ሊያደርጉና ሪፖርትም በሚገባ ሊያሳውቁ እንደሚገባ ነው የሚያሳስቡት፡፡
እንደ አቶ ከበደ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት 45 የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በአገሪቱ ይገኛሉ፡፡ አገሪቱም 25 ከመቶ በጀት ለትምህርት እየበጀተች ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ግዙፍ በጀት ሲመደብ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ያስገነዝባሉ፡፡ ይህ በመሆኑም የአመራሩ አመለካከት የተስተካከለ እንዲሆን በትኩረት ሊሠራ ይገባል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ኮሚሽኑ በዚህ ላይ ከፍተኛ መስዋዕትነት ሊከፍል ይገባል የሚል አቋም አላቸው፡፡
ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ወይዘሮ መብራት ሽፈራው፤ ሙስናን ለመዋጋት የሥነ ምግባር መመሪያ ዝግጅቱ ባለፈው ዓመት ሰፊ ውይይት ተደርጎ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በዚያን ወቅትም አስፈላጊ ምክክር ተደርጎ ለሁሉም ተቋማት ይደርሳል በሚል ድምዳሜ ውይይቱ ተጠናቋል፡፡ ይሁንና መመሪያው የውሃ ሽታ ሆኖ እስካሁን ለተቋማቱ አልደረሰም፡፡ ይህ በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው ሙስናን እንደምን ይዋጋል ሲሉ ይጠይቃሉ። መመሪያው ያለመሰራጨቱ በስራው ላይ የፈጠረው ጫና እንዳለም ይገልጻሉ፡፡የተቀናጀ ሙስና ከመከላከልና ስትራቴጂን ከመዘርጋት አኳያም በርካታ ችግሮች አሉ፡፡በመሆኑም ሙስና የአገርን ትልቅ ሀብት ለብክነት እየዳረገ በመሆኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ይላሉ፡፡
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ የተለያዩ አካላትን ሀብት እንደሚመዘግብ መንግስት ይፋ ካደረገ መቆየቱን በመጠቆም፤ ሙስናን ለመዋጋት ያስችል ዘንድም ሀብት ማስመዝገብ ያለባቸውና ክትትል የሚያስፈልገው አካል ላይ ትኩረት ቢደረግ መልካም መሆኑን ይመክራሉ፡፡ሙስናን ለመዋጋት የተጀመረው ጥረት በመላ አገሪቱ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ያሳስባሉ፡፡በፌዴራል ደረጃ የወጣው ደንብ ቁጥር 144/ 2000 ለትግበራ አስቸጋሪ መሆኑንም ነው የጠቆሙት፡፡ ይህ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተካቶ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ በተለይም በዚህ ደንብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ዳይሬክተር ተጠሪነቱ ለተቋሙ ፕሬዚዳንቱ ከሆነ እንዴት ሙስናን መከላከል ይቻላል ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ከዚህ በዘለለም ሙስና ለመዋጋት አስፈላጊ በጀት ሳይኖር ከወረቀት የዘለለ እቅድ አይኖርም የሚል እምነት አላቸው፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መከላከል ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሙሉጌታ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ሙስናና ብልሹ አሰራርን ለመዋጋት ላለፉት 17 ዓመታት በርካታ ጥረቶች ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ከነዚህ ጥረቶች መካከል በፌዴራልና በክልል ትግሉን የሚመሩና የሚያስተባብሩ አካላትን ማቋቋምና ማደራጀት አንዱ ነው ይሁንና ወንጀሉ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚፈጸምና የራሱ ልዩ ባህሪ ያለው እንደመሆኑ ችግሩ በአንድ አሊያም በተወሰኑ ተቋማት ሩጫና ጥረት ብቻ የሚቃለል ሳይሆን በየደረጃው ያሉ ተቋማትና ማህበረሰቡም በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ የሚያደርጉትን በባለቤትነት ስሜት ላይ የተመሰረተ ተሳትፎ በእጅጉ እንደሚጠይቅ ይጠቁማሉ፡፡
ኮሚሽኑ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት ከሚያደርገው በተጨማሪ ባለበጀት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶችን፣ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች እንዲያደራጁ በማድረግ አቋማቸውን በማጠናከር የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ተግባሩን ተቋማዊ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ እስካሁን ባለው እንቅስቃሴም ኮሚሽኑ ወቅቱ በፈቀደው ልክ ከሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ጋር በመቀናጀት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ያብራራሉ፡፡ ከውጤት አኳያ ሲታይ ግን ጉልህ ክፍተት የሚታይበት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህም በመነሳት ትግሉ የደረሰበትን ደረጃ በመገምገም ወቅቱ የሚፈልገውን አቅጣጫና የግንኙነት ደረጃ አስቀምጦ መሄድ ጠቃሚ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ያለፈውን አካሄድ ማጤን፣ የቀጣይ አቅጣጫ የጋራ ግንዛቤ መያዝና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችን ማመላከትም አስፈላጊ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
እንደ አቶ አክሊሉ ገለፃ፤ የሙስና ወንጀል ጥቆማዎች መቀበያ ሥርዓት ማመቻቸትና ማስተዋወቅ፣ የሃሳብ መስጪያ ሳጥን ማዘጋጀት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታዎችንና የሙስና ወንጀል ጥቆማዎችን መቀበል፣ ማጣራትና ለአመራሩ የመፍትሄ ሃሳብ ማቅረብ፣ ማማከር ጉዳዩ በህግ መታየት የሚገባው ከሆነም ለፖሊስ ኮሚሽን ማሳወቅ፣ የአቤቱታዎች ወይንም የቅሬታ ዓይነቶችንና ብዛት የተሰጠ መፍትሄ ወይም እርምጃ በየወሩና በየሩብ ዓመቱ እየተጠቃለለ ለኮሚሽኑ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡
አዳዲስ መረጃዎችን፣ቅሬታዎችን፣ጥቆማዎችንና ግብረመልሱን በማስታወቂያ ሰሌዳ በመለጠፍ ሠራተኛው እንዲያውቀው፣የኦዲት ክፍል ግኝቶች፣ በንብረት አወጋገድ፣ በግዥና ጨረታ አፈፃፀም ላይ አዘውትሮ ክትትል ማድረግ፣ በመስሪያ ቤት የበላይ ኃላፊዎች ትኩረት ያለመስጠት ችግሮች መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ በኮሚሽኑ በኩል የሚጠበቅበትን ድጋፍ አለመስጠት፣ የሚሰሩና የማይሰሩ በቦታው ተቀምጠው ውጤት የሌላቸውን በመለየት የሚበረታቱትን ማበረታታት፣ ከቦታው መነሳት የሚገባቸው እንዲነሱ ለተቋሙ ኃላፊ አስተያየት መስጠት፣ የተቋማቱን ችግርና ድክመት ከሥነ ምግባር መኮንኑ ጋር በልዩ ልዩ መንገድ ማጋለጥ እንዲሁም የሥራ ተነሳሽነትና ዝግጁነት፣ የቁርጠኝነት ችግር መኖር፣ቦታውን መቆያ ማድረግ፣ለሠራተኛውና ለተገልጋዩ ውግንና ከመቆም ይልቅ ለግል ጥቅምና ፍላጎት ሲባል ከኃላፊዎች ጋር አለአግባብ መወገን፣ ጥፋቱን ከመጋፈጥ ይልቅ በቸልተኝነት ማለፍም ዋንኞቹ ችግሮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባር እና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቶ አየልኝ ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ የፀረ ሙስና ትግሉ የብዙ አካላትን ተሳትፎ፣ጥረትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ ሥራ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ተቋም ምንም ከፍተኛ በጀት ቢኖረውም በተናጠል የሚያደረገው ትግል ውጤታማ አያደርገውም፡፡ በመሆኑም የመንግስት ተቋማት፣ የልማት ድርጅቶች፣ ሕዝባዊ ድርጅቶች እንዲሁም መላው ሕብረተሰብ ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን ለመከላከል የባለቤትነት ስሜት፣ በተደራጀና በተቀናጀ መልክ የሚያደርጉት ጥረት መኖር እንዳለበት ያስገነዝባሉ፡፡ ኮሚሽኑም የፀረ ሙስና ትግሉ ውስጥ የሁሉም ርብርብ እንዲኖር ለማስቻል በየተቋማቱ የሥነ ምግባር ክፍሎች እንዲቋቋሙና በሰው ኃይል እንዲሟሉ በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ ብክነትን ማስወገድ ዋነኛ ሥራ ነው፡፡ በዚህም ሙስናን የመከላከል ጥረቱ ከመቼውም በበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋግጣሉ፡፡
ክፍለዮሐንስ አንበርብር