
ዓለማችን በአይን በማይታይ ድንበር ተሻጋሪ ተዋህሲያን ጤናዋ ተቃውሷል። መላውን ዓለም በስጋት ያራደው የኮሮና ቫይረስም ሕይወት ከመቅጠፍ ባለፈ የሰዎችን ማህበራዊ የሕይወት ዘይቤና መስተጋብር በመለወጥ ሞቶችን በወግ ሥርዓት አልቅሶ መሸኘትም ሆነ መቀበርም እንዲሁም ደግሶ ልጅን መዳርን የመሳሰሉ ማህበራዊ ትውፊቶችን ሳይቀር ከልክሏል።
አገራትም ቫይረሱን ድል ለማድረግ ይረዳቸው ዘንድ ድንበራቸውን ጠርቅመዋል። ወደቦችን ዘግተዋል። ሰዎች በተቻለ መጠን ቤታቸው እንዲቆዩ ትእዛዝ አስተላልፈዋል። ትምህርት ቤቶች፣ ዩኒቨርሲቲዎች፣ ጂምናዚየሞች፣ ሙዚየሞች፣ ጭፈራ ቤቶች፣ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶችና ሌሎችም ተመሳሳይ የመዝናኛ ማዘውተሪያዎችን እንዲሁም ከታላላቅ የንግድ ማዕከላት እስከ ተራ ሱቅ ድረስ ዝግ አድርገዋል።
በቫይረሱ የተነሳ በርካታ የዓለማችን ከተሞች ዝም ያለ እንቅስቃሴ ውስጥ ሰንብተዋል። በየአገራቱ ለወትሮ የሰው ግርግር የሚያደምቃቸው ከተሞችና ቦታዎች የኮሮናን መምጣትን ተከትሎ ፀጥ ረጭ ብለዋል። የንግድ ትስስር ተበጥሶ ከትንሽ እስከ ግዙፍ ኩባንያዎች ስራቸው በመስተጓጎሉ ሚሊየኖች ስራ አልባ ሆነዋል።
ኮቪድ 19 ቫይረስ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ሚሊየኖችን ከማጥቃት ባለፈ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ሕይወት እየቀጠፈ በፍጥነት በመስፋፋት ላይ ይገኛል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜም ከአራት መቶ አርባ ስድስት ሺ በላይ ሰዎች ህይወት ነጥቋል። በቫይረሱ የተያዙ ዜጎች ቁጥር ደግሞ ከስምንት ሚሊዮን ሁለት መቶ ሺ በላይ መድረሱን የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ አረጋግጧል።
ቫይረሱ ከእስያና ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸር በአህጉራችን አፍሪካ ቀሰስተኛ ስርጭት ቢያስመለክትም፣ እስካሁን ባለው ሂደት ከ251 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲታወቅ፣ ስድስት ሺህ ሰባት መቶ በላይ ህይወት መንጠቁን በአፍሪካ የበሽታ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማእከል (አፍሪካ ሲዲሲ)መረጃ አመላክቷል።
ወረርሽኙን በተመለከተ እያደር አስደንጋጭ፣ አሳዛኝና ተስፋ አስቆራጭ እንጂ ይህ ነው የሚባል በጎ ነገር ሳይሰማ ቀናትና ሳምንታት ብሎም ወራት መፈራረቃቸው በቀጠሉበት በዚህ ወቅትም የተለያዩ መገናኛ ብዙሃንና ምሁራን በጉዳይ ላይ ሰፋፊ ትንታኔዎችን በመስራት አስተያየቶችን በመስጠት ላይ ተጠምደዋል።
በተለያዩ አበይት ጉዳዮች ላይ ከሚቀርቡ ዘገባና አስተያየቶቻቸው መካከልም ኮቪድ 19ኝ ለመከላከል ተግባራዊ የተደረጉ የእንቅስቃሴ ገደቦች የዜጎችን ሕይወት በመታደግ ረገድ ተጨባጭ ለውጥና አስተዋፆኦ ማበርከታቸውንና ገደቦች ባይተገበሩ የተጠቂዎችም ሆነ የማቾች ቁጥር ከዚህም ይልቅ እንደነበር ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት ሰጥተው ዘግበዋል።
በዚህ ረገድ ለንደን የሚገኘው ኢምፔሪያል ኮሌጅ ያጠናው ጥናት ለአብነትም የዜጎችን እንቅስቃሴን የገደቡ 11 የአውሮፓ ሀገራት ማለትም ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን፣ ብሪታኒያ፣ ስፔን፣ ቤልጂየም፣ ኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ኖርዌይ እና ስዊድንና ስዊዘርላንድ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ገደማ ሞት መከላከል መቻላቸውን አሳውቋል።
‹‹ሀገራቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመቀነስ እነዚህን እርምጃዎች ባይወስዱና ጥብቅ ክልከላዎችን ባያስቀምጡ እስከ ባለፈው ግንቦት ወር ብቻ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከ12 ሚሊዮን እስከ 15 ሚሊዮን ሊደርስ ይችል ነበር›› ብሏል።
ጥናቶች ስለ እንቅስቃሴ ገደብ ትሩፋት መሰል መረጃዎችን እያመላከቱና ቫይረሱም በከፍተኛ መጠን ጨካኝ መሆኑን እያስመሰከረ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ታዲያ አንዳንድ አገራት ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ይረዱ የነበሩ ክልከላዎችን ማላላት ብሎም ማንሳት ጀምረዋል። በተለይ በአውሮፓ በቫይረሱ ሳቢያ አዲስ የሚያዙ እንዲሁም ህይወታቸው የሚያልፍ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ተከትሎ አገራት ክልከላዎችን በማንሳት ላይ ተጠምደዋል።
በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ከ29 ሺህ በላይ ዜጎቿን የተነጠቀችው ጣሊያን፣ መሪዋ ቦሪስ ጆንሰን በቫይረሱ ተይዘው ከቀናት በኋላ ያገገሙላት ብሪታኒያ፣ ጀርመንና ፈረንሳይን ጨምሮ በርካታ አገራትም ቀደም ሲል ያስተላለፉትን የክልከላ ውሳኔዎች ማላላት ብሎም ማንሳት ጀምረዋል።
እነዚህን ጨምሮ በርካታ አውሮፓውያን አገራት መሰል ውሳኔዎችን ማስተላለፋቸውን ተከትሎም ለወራት ያህል ፀጥ ረጭ ብለው የሰነበቱ ጎዳናዎች የናፈቁትን ሰው አግኝተዋል። ትምህርት ቤቶች፣ ካፌና ሬስቶራንቶችን ጨምሮ ሱቆች፣ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎቶች ለተጠቃሚዎች ክፍት ሆነዋል።
በከተሞች አካባቢም ዜጎች፣ አፍና አፍንጫቸውን ሸፍነው ሲንቀሳቀሱና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ግድ በመሆኑም ሰላምታ የመለዋወጡ ሂደትን ጨምሮ ማኅበራዊ መስተጋብሮች እንደወትሮው ለማከናወን ሲቸገሩም ተስተውለዋል።
ኒውዝላንድ ደግሞ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ይረዳል በሚል ተግባራዊ አድርጋ የቆየቻቸውን ሁሉንም ክልከላዎች በማንሳት ቀዳሚ አገር ሆናለች። አገሪቱ በርካታ ሆኖ በአንድ ቦታ መሰብሰብን ጨምሮ ማህበራዊ ርቀት መጠበቅ ግዴታ አለመሆኑን አሳውቃለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ጃኪንዳ አርደን፣ በደስታ ከታጀበ ገፅታና በመጠነኛ ዳንስ ታጅበው ይህኑ በማረጋገጥ ቀጣይ ትኩረታቸውም ኢኮኖሚውን ዳግም ማንሳት እንደሚሆን አስገንዝበዋል። አገሪቱ ክልከላዎችን ማንሳቷን ብታሳውቅም ከሌሎች አገራት ጋር የሚያስተሳስራትን ድንበሮች ግን ክፍት ማድረግ አልመረጠችም። ከውጭ የሚመጣ ማንኛውም ዜጋም ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ መሰንበት ግዴታው መሆኑን አሳውቃለች።
አገራት ክልከላዎችን ማላላትና ማንሳት መጀመራቸውን ተከትሎ ኢኮኖሚያቸው ከወደቀበት ለመነሳት መዳህ ቢጀምሩም በጉዳዩ ላይ ሰፊ ትንታኔን በማቅረብ ላይ የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃንና ምሁራን በአንፃሩ፣ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጨካኝ ቅጣቱን እያሳረፈ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ለመከላከል የሚያግዙ ክልከላዎችም ማንሳት ግዙፍ ስህተትና ጊዜውም አለመሆኑን በመወትወት ላይ ተጠምደዋል።
ይህ ስጋት አግባብ ስለመሆኑም ሩቅ ምስራቃዊታ አገር ቻይና ምስክር ሆና ቀርባለች።በአገሪቱ ዋና ከተማ ቤጂንግ በሚገኝ የጅምላ ማከፋፈያ የገበያ ስፍራ ላይ የኮሮና ቫይረስ መገኘቱን ተከትሎ ወረርሽኙ በሁለተኛው ዙር ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ነግሷል።
በህንድ ቢሆን የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑ ተመላክቷል። አገሪቱ ክልከላዎችን ማላላቷና የባቡር ትራንስፖርት፣ የሀገር ውስጥ በረራ፣ ሱቆችና የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች በከፊል አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ወረርሽኙ ዳግም እንዲከሰት ምቹ መደላድል መፍጠሩ ተመላክቷል።
በሽታውን መቋቋም የሚያስችል አቅም አጥሯት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ዜጎች በቫይረሱ የተያዙባትና ከአንድ መቶ ሺ በላይ ዜጎችን የተነጠቀችው፣ በተጠቂዎችም ሆነ በማቾች ቁጥር ዓለምን የምትመራው ዩናይትድ እስቴትስ
መንግስት ሳይቀር ክልከላዎችን ማላላቱ በርካቶችን ከማስገረም ባለፈ እያበሳጨ ይገኛል። ውሳኔውን ተከትሎም በወረርሽኙ ምክንያት ከስራ ገበታቸው ርቀው ከቆዩ ከ44 ሺ በላይ ዜጎች መካከል በአሁኑ ወቅት ግማሽ ያህል ወደ ስራ ተመልሰዋል።
ይህ አይነቱ የነጩ ቤተመንግስት ውሳኔም የኤን ፒ አሩን ፀሃፊ ስኮት ሆርስሊን ጨምሮ በርካቶች እስካሁን ከሆነው ይልቅ ወደፊት የሚሆነው እጅግ የከፋና የአገሪቱ ቁስል በሁለተኛ ሩብ ዓመት ይበልጡን እንደሚያመረቅዝ ግምታቸውን እንዲያስቀምጡም ምክንያት ሆኗል።
ስመጥሩ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ ሪቻርድ ዎልፍም፣ ወረርሽኙ በሁለተኛ ዙር ከተከሰተ በአሁኑ ወቅት ወደ ስራ ለመግባት በመፍጨርጨር ላይ የሚገኙ የንግድ ተቋማት እስከወዲያኛው ሊዘጉ እንደሚችሉና ሰራተኞቻቸውን የከፋውን መጋፈጥ ግድ እንደሚላቸው አስረድተዋል።
ዩ ኤስ ኒውስ ስመጥር የኢኮኖሚ ፀሃፊ የሆነው አንድሪው ሰርጄል፣ ፔን ዋርተን በጀት ሞዴል ጥናትን ዋቢ በማድረግ ኢኮኖሚውን ዳግም መክፈት በአሜሪካ ምድር በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ዜጎች ቁጥር በእጥፍ እንደሚጨምረው አትቷል።
ክልከላዎችን በማንሳት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ዳግም ክፍት ማድረግ ሚሊዮኖችን ወደ ስራ የሚመልስ ቢሆንም በዚህ ወር ብቻ ከ233 ሺ በላይ ዜጎችን ሕይወት ይነጥቃል፣ሲል አስነብቧል። ይህም አገሪቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከሞቱባት ዜጎች እኩል መሆኑን አሳይቷል።
አገራቱ መሰል ውሳኔዎችን ለማስተላለፋቸው ታዲያ በርካታ ምክንያቶች ይዘረዘራሉ። በር ዘግታችሁ ተቀመጡ ሲባል ‹‹ምን ልንበላ?›› ብለው የሚጨነቁ ሚሊዮን ነፍሶችን ጨምሮ የምርመራ አቅም መጎልበትና የኢኮኖሚ ድቀት ከምክንያቶቹ መካከል ቀድመው ይጠቀሳሉ።
ባለሙያዎቹ በአንፃሩ ክልከላዎችን ማንሳት ለኮቪድ 19 ምቹ ከባቢን መፍጠርና የሰዎችን ሞት ማስቀጠል መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል። የምርመራ አቅም መጎልበት ብቻውን ዋስትና እንደማይሆን ጠቁመው፣ ‹‹አዲስ የመያዝ መጠን በእጅጉ መውረዱ ባልተረጋገጠበት ክልከላዎችን ማንሳት የማይታረም ስህተት ነውም›› ብለዋል።
የምርመራ አቅምን በመተማመንና የኢኮኖሚን ድቀት በመፍራት ብቻ ክልከላዎችን በተለይ የጉዞ ገደቦችን ማንሳት መጪውን ታሳቢ አለማድረግ መሆኑን አፅዕኖት ከሚሠጡት ምሁራን መካከልም የጃፓኑ የሆካይዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሩ ሒሮሺ ኒሺውራ አንዱ ናቸው።
ፕሮፌሰሩ ክልከላዎች በማላላት ድንበሮችን ክፍት በማድረግ በኮቪድ 19 ከተቃወሱ አገራት አንድ ሺ የሚሆኑ ዜጎች የጃፓንን ምድር ቢረግጡና ከመካከላቸው 10 የሚሆኑት ቫይረሱ ቢገኝባቸው፣ በቀጣይ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወረርሽኙ በ98 ነጥብ 7 በመቶ ከፍ ይላል››
ብለዋል።
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለሌላ ጥፋት አህጉር መቀየሩ የሚያስታውሱ ምሁራንና መገናኛ ብዙሃን በተለይ አፍሪካ ኮቪድ 19ኝን ለመከላከል ያስተላለፈችውን ውሳኔ ማንሳት አይደለም ማሰብ ከጀመረች በአንገቷ ገመድ እያጠለቀች መሆኑን ማወቅ ይገባታል›› ብለዋል።
በእርግጥ ‹‹ከወረርሽኙ ሁለንተናዊ ቀውስ ለማገገም ዓመታት ይወስድባታል›› የተባለችውና ከድህነት ጋር ሰርክ ስሟ የሚነሳው አህጉራችን አፍሪካም ቫይረሱም ሆነ ቫይረሱን ለመከላከል በምትተገብራቸው ውሳኔዎች አማካኝነት ክፉኛ መቁሰሏ አይቀሬ ነው።
ከእርስ በእርስ አጋርነት ይቅል ምእራባውያን ላይ ጥገኛ የሆኑት አፍሪካውያን ድንበር መዝጋት፣በረራ መሰረዝና ማቋረጥን ጨምሮ የሚወስዷቸው ጠንካራ የመከላከል ተግባራት ቫይረሱን ለመቆጣጠርና ለመከላከል ከፍተኛ ፋይዳ ቢኖራቸውም፣ በተቃራኒው በአህጉሪቱ ኢኮኖሚያ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ግን በቀላሉ የሚገለፅ አይደለም።
ይሁንና ‹‹ከበጣም መጥፎ መጥፎውን መምረጥ›› እንደሚባለው በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ምድር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭት በከፍተኛ ፍጥነት መስፋፋትን ተከትሎ 43 አገራት ድንበሮቻቸውን ሙሉ በሙሉ ዝግ ማድረጋቸው ታውቋል።
በዚህም በተጨማሪም 54 የአፍሪካ አገራት የተገደበ ሕዝባዊ ስብሰባን ተግባራዊ ያደረጉ ሲሆን 38 የሚሆኑት በመላው አገሪቱ የትምህርት ተቋማትን ዘግተዋል። 41 አገራት ህዝባቸው የፊት ጭንብል እንዲያደርግ አስገዳጅ ህግ አውጥተዋል። 35ቱ ሀገሮች የምሽት የሰዓት እላፊ ማወጃቸውን የአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (ሲዲሲ) ገልጿል።
ይሁንና አፍሪካ ምድር ወረርሽኙን ለመከላከል ተግባራዊ የሚደረጉ ውሳኔዎች በአግባቡ ተግባራዊ አለመሆን ሚሊዮኖችን ከማትረፍ ይልቅ መቀጠፍም እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው። እናም የውሳኔዎቹ እድሜ እናዳይረዝም የአገራቱ መንግስታት ጥናት ላይ በተመሰረተ መልኩ ጠንካራ የመከላከል ስራቸውን ማስቀጠል፣ ሁኔታዎችን እየቃኙም ውሳኔዎችን ማስተላለፍ እንደሚኖርባቸው ተጠቁማል። ከሁሉም በላይ ዜጎች ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረትና ማገዝ ብሎም ለሚተላለፉ ውሳኔዎች ተገዢ መሆን ይኖርባቸዋልም›› ተብሏል።
ከሁሉም በላይ ግን በአንድ አገር የሚከሰተው ማናቸውም ቀውስም ተወደደም ተጠላ በድፍን ዓለም ተፅዕኖ ማሳደሩ የማይቀር መሆኑንና ሁሉም አገራት ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው እስካልተረጋገጠም አንድ አገር ሙሉ በሙሉ ነፃ ነኝ ማለት እንደማይቻለው አፅእኖት ሰጥተውታል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 11/2012
ታምራት ተስፋዬ