ዘንድሮ “መራዘም” ብሎ ቃል ክብሪት ሆኗል። ባሳለፍነው ሳምንት የፌደሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የህዝብና ቤት ቆጠራው መራዘም ያልተዋጠላቸውና የተዋጠላቸው የምክር ቤቱ አባላት ተረት ተታኩሰዋል። አንዲት የምክር ቤቱ አባል “እንኳን ዘንቦብሽ ድሮም ጤዛ ነሽ” በማለት ቆጠራው መራዘሙን ሲተቹ ፤ ሌላ የምክር ቤት አባል “ለማያቅሽ ታጠኚ” ብለው እርፍ አሉ።
ከዚህ ቀደምም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫውን ለማራዘም ባደረገው ውይይት ሃሳቡን የተቃወሙ የምክር ቤቱ አባል “ሊበሏት ያሰቧትን አሞራ ጅግራ ነሽ ይሏታል” ብለው ተርተው ነበር። ለትችቱ ምላሽ የሰጡ ሌላ የምክር ቤቱ አባል ደግሞ “ጅብ የማያውቁት አገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል” ብለው ተርተዋል። የመልስ ምቱ ይበልጥ ጠንክሮ “ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ” እና “አዛኝ ቅቤ አንጓች” ታክለዋል።
በርግጥ ምክር ቤቶቹ ለተረትና ምሳሌዎች አዲስ አይደሉም። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር ተፈቅዶላቸው ፓርላማ የገቡ ጥቂት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በገዢው ፓርቲ ሰዎች በሚተኮሱ ተረቶች ሲቆስሉ ኖረዋል። ልዩነቱ ያኔ ተራች መንግስት ነበር። የያኔዎቹ የተቃውሞ ጎራ ሰዎች እንኳን ለብሽሽቅ ተረት የሚወክሉትን ህዝብ ጥያቄ ለማቅረብ የማትበቃ ሁለት ደቂቃ ነበር የሚሰጣቸው። ከዛ ሃሳባቸው ሳያልቅ ሰዓታቸው ያልቃል ፤ አይ ዴሞክራሲ !
ዛሬ ደግሞ ተረት ተራቹ ተቃዋሚው ቡድን ሆኗል። የፌዴራል መንግስቱን የተቆጣጠረው ገዢ ፓርቲም “እሾህን በእሾህ” አይነት ስትራቴጂ ቀይሷል። ሁኔታዎች በዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ የሁለቱ ምክር ቤት አባሎች ከሕገመንግስቱ እኩል ለተረት መጽሐፍት ትኩረት መስጠት መጀመራቸው አይቀሬ ነው።
ድሮ ድሮ ጎበዝ ተማሪ ፈተና ዛሬ ሆነ ነገ ጭንቁ አልነበረም። ዛሬ ግን መቶ ከመቶ እያገኘ ሲደፍን የኖረ “ተማሪ” ፈተናው ከተራዘመ ሞቼ እገኛለሁ የሚልበት ዘመን ላይ ደርሰናል። አገር አቀፍ የፈተናዎች ድርጅት የሚያወጣውን ፈተና ትቶ ራሱ ላወጣው ጥያቄ ራሱ መልስ ሰጥቶ ራሱ ራይት ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ዳሩ በአስጠኚ ፈንታ ተፈታኝ ተቀጥሮላቸው የተማሩ “ምሁራን” እራሳቸው የሚፈተኑበት ጊዜ ሲመጣ ቁጭ ብለው ይጠብቃሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው። እንዲህ ባለ ፈተና ሰርተፍኬት አግኝቶ ወደ ቀጣዩ ክፍል ማለፍ ይችል ይሆን? ይህ ጥያቄ ከባድ ስለሆነ ብተወው ይሻለኛል፤ ጊዜ ወይም መከላከያ ይመልሱታል።
የወቅቱ የአዝማሪዎች መንቶ ግጥም ፣ ተራዝሟል ስላሉ ምርጫና ቆጠራ ዩ ኤን ይድረስልን ኤዩም ይጠራ… የሚል ሆኗል።
“ተራዝሟል” በሚል ቃል ምክንያት በየመንደሩ እስጥ አገባ ውስጥ እየተገባ ነው። ለአንዱ ሚስቱ በክረምቱ መግቢያ ሽርሽር ልትወስደው ቃል ትገባለታለች። በኋላ በኮሮና ምክንያት አራዝሜዋለው አለችው። ባል ሆዬ እጁን አጣጥፎ ሊቀመጥ ነው … “ትዳራችን ከመበተኑ በፊት ጣልቃ ገብታችሁ አንድ ነገር አድርጉ” ብሎ ለተባበሩት መንግሥታትና ለአፍሪካ ህብረት አቤት አለላችኋ !
የምርጫው መራዘም ያስነሳው አቧራ ለሳምንታት ከባቢ አየሩ ላይ ሲቆይ ብልጭ ብሎብኝ “ትንቢትና ምርጫ” በሚል ርዕስ በጻፍኩት አጭር ጽሑፍ የአንድ “ነብይ”ን ትንቢት አስታውሼ ነበር። ከዓመታት በፊት አንድ “ነብይ” “በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ይጠለፋል” ብሎ “ትንቢት” ተናገረ። በኋላ ይሆናል ያለው ሳይሆን ዓመቱ ተጠናቀቀ። “ነብዩ” አይኑን በጨው አጥቦ “ትንቢቴን ወደቀጣዩ ዓመት አራዝሜዋለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ ማንም ምንም አላለም። ዛሬ ግን ምርጫው ይራዘማል ሲባል ያዙኝ ልቀቁኝ ባዩ በዝቷል። ትንቢት በሚራዘምበት አገር ምርጫ ቢራዘም ምን ይገርማል ?
በበኩሌ በዚህ ወቅት የኮሮና ቆይታ እንዳይራዘም ብቻ ነው ጭንቀቴ። እንዴ ምን ነካን ? ፈጣሪ ዕድሜያችንን ያርዝምልን እንጂ ገና ብዙ ነገር ሲራዘም እናያለን። ማራዘም የረዘመ ንትርክ ውስጥ ሲነክር ያየሁት በያዝነው ዓመት ነው። ቀደም ባለው ዘመን የዕድሜ ማራዘሚያ የማይወጋ ዘርፍ አልነበረም። ይህን ስል ግን አንድን ነገር ማራዘም ምንም ችግር አያመጣም ማለቴ አይደለም። በተለይ ብረት ምጣድ ላይ ለተቀመጡ ምጡ ከባድ ነው። አንዳንድ ድርጅቶች በዓመቱ መጀመሪያ ላይ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ የያዙትን ቀጠሮ እንደ ምርጫ ቦርድ “የቅድመ ዝግጅት ስራዎች አልተጠናቀቁም” በሚል እያራዘሙ ሐምሌ ሲያደርሱት እያንዳንዱ ወር የዓመታትን ያህል እንደሚረዝም የደረሰበት ያውቀዋል።
እናንተዬ ምርጫን ግን በዚህ ልክ መናፈቅ ነበረብን ? ምርጫ እኮ ለኛ ብርቅ አይደለም። ማነው በየአምስት ዓመቱ ብቻ ይመጣል ያለው? ምርጫ ለአፍታ እንኳን የማይለየን (ምናልባት እኛ የማናስተውለው) የምንደምቅበት አሊያም የምንደበዝዝበት የየዕለት እጣችን ነው።
የሚዲያዎቻችን ዜናና “ልዩ ዝግጅት” ማጠንጠኛ የምርጫውን መራዘም መደገፍና መንቀፍ ላይ ከሆነ ሰነባብቷል። ታክሲ ውስጥ በተከፈተ ሬዲዮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ ብልጽግና ምርጫ የሚያስፈራው ፓርቲ ስላልሆነ ምርጫው እንዲራዘም አይፈልግም ነበር። በዚህ ምክንያት ወይዘሪት ቡርቱካን ሚደቅሳ ስራቸውን ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ባልተለመደ ሁኔታ ጠንከር ያለ የቃላት ልውውጥ አድርገናል ሲሉ ትሰማለህ።
የቴሌቪዥን ጣቢያህን በቀየርክ ቁጥር አገር የቀየርክ ያህል ግራ ትጋባለህ። አንዱ ጣቢያ ላይ “አምባገነናዊ የቡድን በስልጣን ላይ የመቆየት ፍላጎት ለማርካት ሲባል የህዝብን የመወሰን ስልጣን መደፍጠጥ ፈፅሞ አይቻልም!” የሚል ርዕሰ አመጽ ያጋጥምሃል። ምን ተፈጠረ ብለህ ጆሮህን ስትሰጥ “የፈዴራል መንግስትን ስልጣን የተቆጣጠረው አካል ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ያሳየው ማን አለበኝነትና ንቀት ዛሬም … በተከበረው ምክር ቤታችን ላይ መድገሙ የአምባገነንነት ባህሪው የከፋ ጫፍ ላይ መድረሱን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው።” ብለው ጭብጡን ያስጨብጡሃል። ለጥቆ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ሥልጣንና ሃላፊነት ጠንቅቀን እናውቃለን ብለውህ የኢፌዴሪ ህገ- መንግስትንና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅን ጠቅሰው ሲያበቁ “ ምክር ቤታችን የራስን እድል የመወሰን ያልተገደበ ስልጣን ስላለው የወሰነውን ውሳኔ ተግባራዊ ከማድረግ የሚከለክለው ማንም ሃይል ሊኖር አይችልም።” ብለው ያስገርሙሃል።
እንደ እኔ እጅህ የማያርፍ ከሆነ ደግሞ የሪሞትህን ቁጥሮች ስትጫን በፕሌን ወይም በመርከብ ሳትጫን ሌላ አገር ትገኛለህ። እዚያ ደግሞ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተከስተው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን አደጋ ለማስወገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ በሚል የቀረበው ጥሪ “ጩኸቴን ቀሙኝ ካልሆነ በስተቀር እንዲህ ያለ ግፍ፣ አፈና እና ግድያ ያለው ከሳሹ በመሸገበት ክልል ነው” ሲሉ ትሰማለህ።
ስክሪን ሰልችቶህ ጋዜጣ ስትገልጥ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ያገኙሃል። እኔ ሦስተኛ ዲግሪዬን የሠራሁት በተላላፊ በሽታዎች ዙሪያ ነው። እንደባለሙያ ስመለከተው የኮሮና ቫይረስ እጅግ አደገኛ የሆነ ቫይረስ ነው። በዓለም ላይ እንደታየውም ለበርካታ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል። ይህንንም በአግባቡ ስለምረዳ ምርጫው መተላለፍ እንዳለበት እኔም ሆንኩኝ ፓርቲዬ ጽኑ አቋም ይዘናል። ምርጫ አካሂዳለሁ የሚለውን ቡድን በተመለከተ የሚያሳፍር ነገር ነው እየሰማሁ ያለሁት። ልምድ እንዳለው ፖለቲከኛ ሆነው አላገኘኋቸውም ይሉሃል። ይህን ጊዜ ፕሮፌሰሩ የወቀሷቸው ሰዎች ሰባተኛ ዲግሪያቸውንም በተላላፊ በሽታ ላይ ቢሰሩ ምርጫ ለማካሄድ መቋመጣቸውን እንደማይተው ትረዳና ሌላ ፕላኔት ላይ ነው እንዴ የሚኖሩት ትላለህ።
ምርጫ እናካሂዳለን ባዮቹ እንደ ተሞክሮ የሚያዩት የቡሩንዲን ምርጫ ነው። 42 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘውባት እያለ በወረርሽኙ ላይ የሚሰሩ የዓለም ጤና ድርጅት ባለሙያዎችን ከአገሯ አባርራ ምርጫ ያካሄደችው ቡሩንዲ ውሎ ሳያድር ለድፍረቷ ዋጋ ከፍላለች። የሀገሪቱን ህገ መንግሥት በመጣስ ለሶስተኛ የሥልጣን ዘመን የተወዳደሩት ፕሬዚደንት ንኩሩንዚዛ በኮሮና ቫይረስ ሞተዋል ፤ የበሽታው ስርጭትም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ‹‹ብልህ በሌሎች ጥፋት ይማራል›› እንዲሉ አበው እኛ ከቡሩንዲ ብንማርስ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 10/2012
የትናየት ፈሩ
ትንቢት በሚራዘምበት አገር ምርጫ ቢራዘም ምን ይገርማል?