
ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለም ሀገራትን ደኅንነት እየፈተነ ከሚገኘው ወንጀሎች ውስጥ አንዱ በዜጎች መነገድና ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ዜጎችን ድንበር ማሻገር ነው። በመሆኑም ይህን ወንጀል በመመርመርና በማስቀጣት ደረጃ ሊያሠራ የሚችል ሥርዓት መዘርጋት ተቀዳሚው ተግባር መሆን የሚገባው ጉዳይ ነው። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ በኩል የተጀማመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸው የማይካድ ቢሆንም፤ እንቅስቃሴዎቹ በቂ አይደለም የሚሉ ምሑራንም አሉ። ይህን ጉዳይ አስመልክተን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የምርመራ ቡድን በትናንትናው ክፍል ሦስት ዕትሙ ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ማስቆም አሊያም መቀነስ ያልተቻለው ለምንድን ነው? ከዚህ አኳያስ የሀገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? ሲል ጠይቆ ያጠናቀረውን መረጃ አስነብቧል። በዛሬው ዕለት ዕትሙ ደግሞ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረገው ፍልሰት በግለሰብ፣ በቤተሰብና በሀገር ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከግምት ገብቶ መንግሥት እያከናወነ ያለው ሥራ ምንድን ነው? ሲል ጠይቆ ያጠናቀረውን የምርመራ ዘገባ እነሆ ብሏል።
ክፍል አራት
ኢ-መደበኛ ፍልሰትን ለመቀነስ ምን ተከናወነ?
በኢትዮጵያ ያለው የፍልሰት ሁኔታ በጣም ውስብስብ፣ በየጊዜው የሚለዋወጥና በከፍተኛ ሁኔታ ሀገሪቱን ለችግር እየዳረገ ያለ ነው ይላሉ ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው። እንደሚታወሰው በሊቢያ ላይ ዜጎቻችን በአረመኔውና በጨካኙ ቡድን ከታረዱ በኋላ መንግሥት የወሰደው ትልቁ ርምጃ ቢኖር ሕግ ማውጣት ነው ሲሉ ይጠቅሳሉ።
አቶ አብርሃም እንደሚሉት፤ ከዚያ በፊት የነበረው በወንጀል ሕግ ውስጥ “ሰውን ለሥራ ወደውጭ ሀገር መላክ” የሚል አንድ አንቀጽ ብቻ ነው። ክስ ሲከሰስም የነበረው በዚህ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 598/3 መሠረት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን በ2012 ዓ.ም ላይ አሁን ያለው አዋጅ ቁጥር 1178/2012 ወጣ። ይህ አዋጅ ጥቅል በሆነ መልኩ አንደኛ ወንጀሎቹን በጣም በዝርዝር የያዘ ሲሆን፣ ድንጋጌዎቹንም እስከ ሞት ቅጣት ድረስ ያስቀመጠ ነው።
አዋጁ፣ ወንጀሎቹን መደንገግ ብቻ ሳይሆን ወንጀሎቹን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ያተኮረ ስትራቴጂም አስቀምጧል። እንዲህ ሲባል ፎር ፒስ (four ps) ማለትም አንደኛው ወንጀሎቹን መከላከል ላይ ሲሆን፣ ሁለተኛው የተጎጂዎች ጥበቃ እና ድጋፍ ነው። ይህ መልሶ ማቋቋምን ይጨምራል፤ ምክንያቱም በጣም ብዙ ሰዎችን የሚጎዳ ስለሆነ በጣም ወሳኝ ጉዳይ አድርጎ ይዞታል። ሦስተኛው የምርመራ እና ክርክር ሲሆን፣ አራተኛው ደግሞ ትብብርና አጋርነት ነው። ሕጉ የወጣው ወንጀሎችን በእነዚህ አራት መንገዶች እንከላከላለን በሚል ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
ይህ በመሆኑ ተቋማትም በአግባቡ እንዲደራጁ ዕድል ሰጥቷል። በተለይ 2014 የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት መቋቋም እጅግ በጣም ትልቅ ርምጃ ነው ማለት ይቻላል። ይህ የትብብር አደረጃጀት በሕጉ መሠረት ብሔራዊ ምክር ቤቱ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲመራ ያደረገ ሲሆን፣ ምክር ቤቱ ክልሎችንም የያዘ ነው።
በፌዴራል ደረጃ ደግሞ ፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራው የትብብር ጥምረት ተቋቁሟል የሚሉት አቶ አብርሃም፣ የሚመለከታቸው ሀገር አቀፍ ተቋማትና በዓለም አቀፍ ደረጃ አጋሮችም ያሉበት ነው ሲሉ አስረድተዋል። ይህንን ክልሎችም እንዲያቋቁሙ ሕጉ ይፈቅዳል። ከዚህ የተነሳ ያቋቋሙ ክልሎች ያሉ ሲሆኑ፣ ያላቋቋሙ ክልሎችም መኖራቸውን አቶ አብርሃም አመልክተዋል።
በዋናነት ከ70 በመቶ በላይ የሆኑ ፍልሰተኞች እና ከ70 በመቶ በላይ ተመላሾች ደግሞ የሚገቡባቸው ክልሎች ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ናቸው ያሉት ኃላፊው፣ እንዲያውም ደቡብ ክልልን ሲጨመር ስሌቱ ወደ 80 በመቶ ይደርሳል ብለዋል። ይህ ማለት እነዚህ ክልሎች ላይ የሚሠራው ሥራ በጣም ቁልፍ ነው። አፋርና ሱማሌ መውጫ ክልሎች ስለሆኑ የችግሩ ገፈት ቀማሾች ናቸው። የሚፈልሱትን ድንበር ላይ ይዘው እስከሚመልሱ የሚያበሉትና የሚያጠጡት እንዲሁም የሚመልሱት እነርሱ ናቸው። ያንን ማድረግ ካልቻሉ ግን ዜጋው ሲፈልስ እያዩ ሊያልፉ ይችላሉ ብለዋል።
አቶ አብርሃም እንደሚያስረዱት፤ ሕጉ ከወጣ እንኳ አምስት ዓመት ያህል አስቆጥሯል፤ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ነበረብን። በእርግጥ ጉዳዩ የመንግሥት ጉዳይ ወደመሆን ተሸጋግሯል። አሁንም የሚቀር ነገር ቢኖርም መንግሥት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት አሳይቶበታል። ይህ በጎረቤት ሀገራትም የለም። በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የሚመራ በአዋጅ የተቋቋመ አደረጃጀት የለም። ምክንያቱም የሚያቋቁሙት ወይ የመግባቢያ ስምምነት (MOU) ነው፤ ወይም ደግሞ በአስተዳደራዊ ውሳኔ ነው።
የእኛ ግን የተቋቋመው በአዋጅ ነው። አዋጁ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ትልቅ ሥልጣን ሰጥቶታል። ይህ ትልቅ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ነው። በዚህ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ልክ ክልሎች እና የተቋማት አመራሮች መሥራት ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን በደንብ አጢኖ መያዝ ያስፈልጋል። ይህ ጉዳይ የመንግሥት ዓይነተኛ አጀንዳ መሆኑን መረዳት የሚቻለው ጉዳዩ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠረጴዛ ላይ ካሉት ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው አጀንዳ መሆኑ ነውና ጥሩ ርምጃ ነው ይላሉ።
አሁን ችግራችን ከሌሎቹም ሀገሮች በላይ በመሆኑ እየሠራን ያለነው ብዙ ሥራ ከጉዳቱ አኳያ አነስ ያለ ይሁን እንጂ በቅጣት ረገድ እስከ 25 ዓመት የማስቀጣት፣ ንብረቶችን አግዶ ምርመራ የማድረግ ጅምሮቹ መልካም ናቸው። ከምንም በላይ ደግሞ ወደውጭ ሀገር የሚሔዱ ዜጎቻችን ቁጥር ዘንድሮ ከፍ ማለቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሰው በሞያሌ፣ ጋላፊ እና ደወሌ በኩል ሊወጣ የነበረው መዳን ችሏል ማለት ነው። ይህ ሊበረታታ የተገባው ነገር ነው። ነገር ግን እየተሠራ ካለው ሥራ እና እየተፈጸመ ካለው ወንጀል አንጻር በቂ አይደለም ይላሉ።
ግንዛቤ ፈጠራችን ምን ይመስላል? ምን አይነት ለውጥ አመጣ የሚለው ላይ መሠራት አለበት። ደላሎቹ የሚፈጥሩት ግንዛቤ ፈጠራ ወጣቶች ሀገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ የሚያደርግ ከሆነ እኛ የምንፈጥረው ግንዛቤ ፈጠራ ወጣቶቹ ሀገራቸውን ጥለው እንዳይሄዱና ከሔዱም በሕጋዊ መንገድ እንዲሔዱ ለምን አላደረጋችሁም የሚለውን በአግባቡ ማየት ይኖርብናል የሚሉት ኃላፊው፣ እዚህ ላይ መሥራት የሚጠይቅ ሲሆን እኛም ዕቅዶችን ይዘን እየሠራን ነው ብለዋል። አንዳንድ ተቋማት በደንብ እየሠሩ ሲሆን፣ ለምሳሌ ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባው የሚመራ ምክር ቤት አቋቁመው፤ በሕግ እየሠሩ ነው። ይህ በጣም ትልቅ ሥራ ነው፤ ነገር ግን ድሬዳዋ መሸጋገሪያ እንደመሆኗ አንጻር አሁንም ችግሩ በጣም ከፍተኛ ነው ብለዋል።
አቶ አብርሃም እንደሚሉት፤ በቅርቡ አንድ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመላሾች የኢኮኖሚ ዳግም ውሕደት (Economic Reintegration) ላይ ውይይት ለማድረግ ትልቅ መድረክ ማዘጋጀት ነው። መንግሥት አሁን እየሠራ ባለው መንገድ ብቻ መሆን አይችልም። ባንኮቻችንን፣ የግል ዘርፉን፣ የመቅጠር አቅም ያላቸውን ኢንዱስትሪ ፓርኮችን እዚህ ሥራ ላይ ማሳተፍ ያስፈልጋል። ምክንያቱም እነርሱ የሌሉበት የዳግም ውሕደቱ ሥራ ለውጥ የለውም። እነርሱን ካልያዝን የሚፈጠረው የሥራ ዕድል በጣም አነስተኛ ይሆናል። በቂ ካልሆነ ደግሞ ተመልሰው ይሄዳሉ። ስለዚህ ይህንን ለመምራት የተለየ ዕቅድ ይፈልጋል።
ለአንድ የእግር ኳስ ጨዋታ በሚሊዮን የሚቆጠር ብር አውጥተው ስፖንሰር የሚያደርጉ ባንኮች፤ ለተመላሽ ስደተኞች እነርሱን ያማከለ የብድር አሰጣጥ፣ የወለድ ቅነሳ እና የአከፋፈል ሥርዓት ወይም ደግሞ የተለየ ሥርዓት እንዲቀርጹ ካላደረግናቸው አሁንም መልሰን ችግር ውስጥ መግባታችን የማይቀር ነው። ምክንያቱም ባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና ቀጣሪ ድርጅቶች ስንቱን የመዝናኛ መርሐግብር ሲደግፉ እናያለን? ሲሉ አቶ አብርሃም ይጠይቃሉ።
ሌላው ሥራው የሀገር ውስጥ ትብብርን ብቻ ሳይሆን የውጭ ሀገራትንም ትብብር ይፈልጋል። በመሆኑም አሁን እሱን ጀምረናል። በተለይ ጂቡቲ ላይ የጋራ ወንጀል ምርመራ ቡድን አቋቁመን ለመሥራት የሁለትዮሽ ስምምነት ተፈራርመናል። ይህን ገና ተግባራዊ አላደረግነውም። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ አቤቱታ (ፕሮአክቲቭ) ምርመራ ማድረግ ይፈልጋል። እንዲህም ሲባል ስልክ መጥለፍ፣ በመስመሩ ውስጥ ያሉ ደላሎዎች እነማን ናቸው? የሚለውን የኢንተለጀንስ ሥራ መሥራት ማለት ነው። ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ቢሯችን ድረስ መጥተው አቤቱታ እያቀረቡ ብቻ የጉዳዩን ክብደትና የሚያደርሰውን ጉዳት መሥራት አይቻልም።
ከኬንያ ጋር ደግሞ እንዲሁ ውይይት አድርገናል የሚሉት የሴክሬታሪያት ኃላፊው፣ ከማላዊ ጋርም ተስማምተናል፤ ማላዊ እንደሚታወቀው አንደኛው ማለፊያ ነው ብለዋል። ከታንዛኒያ ጋርም እንዲሁ እንቀጥላለን፤ እስከ ደቡብ አፍሪካ ድረስ እንሔድበታለን። ሳዑዲ ዓረቢያ ድረስ ለመሔድ እንሞክራለን ሲሉም አብራርተዋል።
በጥቅሉ ዓለም አቀፍ ትብብሩን ለማጠናከር ጥረት እያደረግን ነው።
የክህሎት ግንባታ ወሳኝ ነው፤ ምክንያቱም በአሁኑ ወቅት ወንጀሉም ስርቆቱም የሚተገበርበት መንገድ እየረቀቀ መጥቷል።
ወንጀለኞች ከሚከተሏቸው የምልመላና የገንዘብ ማዘዋወሪያ ዘዴዎች አንጻር ሥልጠና መስጠትና መመሪያዎች ማዘጋጀት የግድ ይላል። ስለሆነም ዓቃቤ ሕጎችና ፖሊሲዎች የሚመሩባቸውን በመሥራት ላይ እንገኛለን። ይህ ማለት ሥልጠናም ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ነው። ምክንያቱም ቀድመናቸው ካልሔድን እነርሱም የራሳቸውን ስልት ለመንደፍ ፈጣን ናቸው ብለዋል።
እርሳቸው እንደሚሉት፤ ፍልሰት ለልማት ትልቅ አስተዋፅዖ ያለው መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በሌሎች ሀገሮች ጥቅል ሀገራዊ ምርታቸው (ጂዲፒ) ላይ ትልቅ አስተዋፅዖ አበርክቷል፤ ሀገራቱ አድገዋልም። በተለይ እንደእኛ የቤት ሠራተኞችን ብቻ ሳይሆን የተማሩ እና ክህሎት ያላቸውን ሰዎች እየላኩ ወደሀገራቸው በሚልኩ የውጭ ምንዛሪ ተጠቃሚ እየሆኑ ነው። በእርግጥ ወደሀገራችንም ከወርቅም በላይ የሚላከው ከፍተኛ ገንዘብ ነው። ስለዚህ ወንጀለኞችን ተከላክለን መደበኛ ብናደርገው መጨረሻ የውጭ ምንዛሪያችን ይጨምራል። ኤሌክትሪክ፣ ቡና እና ወርቅ ሸጠን ከምናገኘው ገንዘብ በላይ ውጭ ሀገር ያለው ኢትዮጵያዊ ለእናቱ ቡና መግዣ ብሎ የሚልከው ገንዘብ ሲጠራቀም አሁን ከሚላከው ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ይሆናል።
ከአቶ አብርሃም በተጨማሪ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረገውን ጉዞ ለመቀነስ በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ምንድን ነው? ስንል በተመሳሳይ ለተለያዩ ምሑራንም ጥያቄ አቅርበንላቸዋል። ምሑራኑን አንድ የሚያስማማቸው ነገር ቢኖር ኢትዮጵያ ሕጋዊ በሆነ መንገድ፤ ሰዎች ወደውጭ ሀገር ለሥራ እንዲሔዱ የማድረግ ጅማሬዋ መልካም መሆኑ ነው። ከረጅም ጊዜ በኋላ በመንግሥት እገዛና በመንግሥት ማሕቀፍ ውስጥ ሰዎች የሥራ ዕድል ፍለጋ ወደ ተለያየ ሀገር እንዲሄዱ የማድረግ ጅማሮ የሚበረታታ፤ የሚመሰገንም ሲሆን፣ ትልቅ ሥራና ተነሳሽነት እንደሆነም ያመለክታሉ። አንዳንዶቹም የአዋጅ መውጣትም የሚበረታታ ነው ይላሉ።
በአንጻሩ ደግሞ ሙከራዎች ቢኖሩም በመንግሥት እየተሠራ ያለው ሥራ በምንም መልኩ ከ10 ወይም 20 በመቶ የሚበልጥ አይደለም የሚሉ ምሑራን አልታጡም። በርካታ ሰው ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሀገር አቋርጦ ሲሄድ መንግሥት ይህን ኢ-መደበኛ ፍልሰት እንዴት ማየት ይሳነዋል ሲሉ የሚጠይቁም አሉ። ዜጎች ከመነሻቸው ጀምሮ የባሕር ጠረፍ እስኪደርሱ ድረስ ቁጥጥር አለማድረጉ ከምን የመጣ ነው ሲሉም ያክላሉ።
ካነጋገርናቸው ምሑራን መካከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አርትስ ኤንድ ሂዩማኒቲስ መምህር እና አጥኝ ጉዲና በሹዳ (ዶ/ር) እንደሚሉት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ የሚባል ነው። ሰው ወደ ውጭ ለመሄድ ሕጋዊ በሆነ መንገድ እንዲሆን ማድረግ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። በዚያው ልክ ደግሞ ሲሄዱ እንዳይቸገሩ ያለውንም የሥራ ባሕሪ እንዲያውቁ የሚደረገው እንቅስቃሴ መልካም ነው። ሚዲያዎችም በቂ ነው ማለት ባንችልም ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ጥሩ የሚባሉ ናቸው።
የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲው አመራርና አስተዳደር ኮሌጅ ምክትል ዲን፣ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ዕድል ፈጠራ አማካሪ፣ የቦርድ አባልና ፍልሰትና ልማት ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር መሐመድ ዓሊ፣ በበኩላቸው፤ ኢ-መደበኛ የሆነውን የፍልሰት ሁኔታ ለመከላከል ያለው ርቀት ኢትዮጵያ በአዋጅ ደረጃ በተለያየ ጊዜ እንዳሻሻለችው የሚታወቅ ነው።
በሰው መነገድ (trafficking) እና ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር (smuggling) እነዚህን ሁለቱን ለመከላከል የሚያስችል አዋጅ ወጥቷል። የአቅም፣ የመተባበር፣ የመተጋገዝ መረጃ የመሰጣጣት ክፍተቶች አሉ። እነዚያን የማስተካከል ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። ክፍተቶችን ለይቶ መሥራት ይጠይቃል።
መንግሥት አሁን ገጠሪቱ የኢትዮጵያን ክፍል በማልማት ላይ ይገኛል የሚሉት ደግሞ ዲፕሎማቱና ኢኮኖሚስቱ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ናቸው። ወጣቶችም በማኅበር ተደራጀተው እየሠሩ ነው። ነገር ግን ኑሯቸው የከተማን አይመስልም።
ስለዚህ የከተማን እንዲመስል መሥራት የተገባ ነው። በተለይም መሠረተ ልማት በማሟላት እና በተመሳሳይ መዝናኛዎችም በማመቻቸት የከተማን ይዘት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል።
ለምሳሌ በሲውዘርላንድ ሰዎች በከተማ ከመኖር ይልቅ ገጠራማውን ክፍል ይመርጣሉ። ምክንያቱም ከተማ ያለው ነገር ሁሉ በገጠራማው ስፍራም አለ። ስለዚህ ገጠሩን ጥለው ወደ ከተማ የሚሰደዱት ለምንድን ነው? የወጣቶች መንደር ተብሎ እስከተገነባ ድረስ ወጣቶቹ የሚወዱትንና የሚፈልጉትን ማግኘት የሚችሉበት ዓይነት መሆን አለበት ይላሉ።
በሌላ በኩል በጣም በርካታ ሰው ሀገር አቋርጦ ሲሄድ መንግሥት ይህን ኢ-መደበኛ ፍልሰት እንዴት ማየት ይሳነዋል ሲሉ የሚጠይቁት አምባሳደር ጥሩነህ፣ ደኅንነቱ እራሱ ዜጎች ከመነሻቸው ጀምሮ የባሕር ጠረፍ እስኪደርሱ ድረስ ቁጥጥር አለማድረጉ ከየት የመጣ ነው? ይላሉ። በእርግጥ ይላሉ ዲፕሎማቱ፣ ቁጥጥሩ ብቻውን ስደቱን ሊያስቀር አይችልም። ነገር ግን ዜጋው ሕይወቱን ተስፋ ቢስ አድርጎ በሚሰደድበት ጊዜ እራሱን ለባሕር፣ ለበረሃ እና ለጨካኝ ሰዎች ከሚሰጥ ይልቅ የተሻለ ኑሮ እዚህ መኖር እንዲችል ማመቻቸት እንደሚሻል ያመለክታሉ። ከተመቻቸና ቁጥጥሩ በመንግሥት አማካይነት ከጠበቀ መቀነስ እንደሚቻል ያስረዳሉ።
በመንግሥት በኩል የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ እንደሆነ ይታመናል የሚሉት ደግሞ የጅማ ዩኒቨርስቲ በማኅበራዊ ሳይንስና ሂዩማኒቲስ ኮሌጅ የሲዮሶሎጂ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ነጋ ጅባት (ዶ/ር) ሲሆን፣ መንግሥት ሲባል የመንግሥት መዋቅር የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ናቸው ይላሉ። የክልል መንግሥት ስንል ከክልል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው አካል ነው። ይህ መንግሥት ደግሞ ሕዝብን እንዲመራና እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ተሰጥቶታል።
በተለይ በሊቢያ ከተከሰተ ችግር ወዲህ መንግሥት በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ይላሉ። በሀገር አቀፍ ደረጃ የተዋቀረ የትብብር ኃይል አለ። ስለሆነም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አንድ ላይ ሆነው በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙ ያስገነዝባሉ።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በመንግሥት በኩል የፖሊሲ ቀረጻ ሙከራዎች ነበሩ። ፖሊሲ ከተረቀቀ ቆይቷል። ነገር ግን ፖሊሲው ከተረቀቀ ረጅም ጊዜ ሆኖታል። እስካሁን መፅደቅ ነበረበት። እንዲያም ሆኖ ፖሊሲ እንዲኖር መንግሥት ቁርጠኝነት ማሳየቱ ጥሩ ነው። ነገር ግን በሚፈለገው ፍጥነት ተጠናቅቆ ወደሥራ አለመግባቱ አንዱ ክፍተት ነው።
ምክንያቱም ፖሊሲ ሁሉንም ነገር ይመራል። እንዴት መመራት አለበት የሚለውን ምላሽ የሚሰጥ ነው። የፖሊሲ አለመኖሩ በራሱ መንግሥት በሚያደርጋቸው ጥረቶች ላይ የራሱ ችግር ሊኖረው ይችላል። ሆኖም ግን ስትራቴጂዎች ተቀርጸው ሕግ ወጥቶ የትብብር አካላትም ተቋቁሞ ከፌዴራል መንግሥት ጀምሮ እስከ ወረዳና ቀበሌ ድረስ የሚሔድ መዋቅር ተዘርግቷል። ከዚህ አንጻር የሚደረግ ጥረት አለ። ስለዚህ እሱ ሊበረታታ ይገባል። ነገር ግን በቀበሌ አካባቢ የመታወቂያ አሰጣጥ ጀምሮ ኢሚግሬሽን አካባቢ ጭምር ክፍተት እንዳለ የሚያሳይ ነገር አለ።
በፕሮግራም ደረጃ ተቀርጾ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ነው። የሰው ኃይሉንም በዚያ ደረጃ አሠልጥኖ መላክ ላይ እና የውጭ ጉዞ መጀመሩ ላይ ብዙ ጥሩ ነገሮች ያሉት ነው። ይሁንና እሱ ላይም ክፍተቶች አሉ።
አሁንም በበቂ ሳያሠለጥኑ ፈቃድ ብቻ አግኝተው በውጭ ሀገር ስምሪት ላይ የተሳተፉ አካላት አሉ። እነዚህም አሁን የሚወሰዱት ሕጋዊ አካል ተደርገው ነው። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በገንዘብ ላይ የሚያተኩሩበት ጊዜ አለ። ሥልጠና ሳይሰጡ ገንዘብ በመውሰድ ሰርተፊኬት መስጠት አለ። ስለዚህ ምናልባት ሥልጠናዎቹ ብዙ ጊዜ የሚሰጡት በግል ተቋማት ነውና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በአካባቢው ባሉ ከዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ጋር በመሆን ሥልጠናው ቢያያዝ ካሪኩለምም ተቀርጾለት አግባብ የሆነ አሰጣጥ እንዲሰጥ ቢደረግ ጥሩ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምን ያህል መዝገቦች ተከፈቱ? ምን ያህሉስ ውሳኔ አገኙ? ውሳኔውስ እስከምን ድረስ የሚያስቀጣ ነው? ስንል ለፌዴራል ፖሊስ ጥያቄ ባቀረብንበት ወቅት እንዳስረዳው፤ በሰዎች መነገድ እና ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ከማሻገር ወንጀሎች አንጻር ከተበዳዮች፣ ከቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ከተለያዩ አካላት የሚቀርቡ ጥቆማዎችን መነሻ በማድረግ የወንጀል ምርመራ ተካሂዷል። በተለይ በ2016 በጀት ዓመት ለረጅም ዓመታት በምርመራ ላይ የቆዩ ውዝፍ መዛግብትን ለማጥራት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ በዚህም በዓመቱ ውስጥ በርካታ መዛግብትን አጣርቶ ለዓቃቢ ሕግ በመላክ ከዚህ ቀደም ከነበረው የተሻለ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ተችሏል።
ለአብነት ያህል ያለፉት ሦስት ዓመታት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በ2015 በጀት ዓመት የቀረበ ጥቆማ 176 ምርመራቸው ተጠናቆ ለዓቃቢሕግ የተላከ 47፣ በቁጥጥር ስር የዋለ ተጠርጣሪ ብዛት 58 ነው። በ2016 በጀት ዓመት የቀረበ ጥቆማ 214፣ ምርመራቸው ተጠናቅቆ ለዓቃቢሕግ የተላከ 209 ሲሆን፣ በቁጥጥር ስር የዋለ ተጠርጣሪ ብዛት 72 ነው።
በተገባደደው በ2017 በጀት ዓመት የቀረበ ጥቆማ 132 ሲሆን፣ ምርመራቸው ተጠናቅቆ ለዓቃቢሕግ የተላከ 117፣ በቁጥጥር ስር የዋለ ተጠርጣሪ ብዛት ደግሞ 130 ነው።
በሰዎች የመነገድ እና ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ጥቆማዎች በአዋጅ ቁጥር 1178/12 ላይ የተመላከቱትን ወንጀሎች ማለትም በሰዎች መነገድ፣ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር እና በሕገወጥ መንገድ ዜጎችን ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር መላክ እንዲሁም ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በተመለከተ ምርመራ የማድረግ ኃላፊነት የተጣለበት ሲሆን፣ በዋናነት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሥራውን ለማሳለጥ ያስችል ዘንድ ሁለት የምርመራ ክፍሎች ተቋቁመዋል። የምርመራ መዝገቦቹን የየዕለት የሥራ እንቅስቃሴ፤ ጠንካራ እና ደካማ ጎን እየተገመገመና አስተያየት እየተሰጠ እንዲሁም ከዓቃቢ ሕግ ጋር በመነጋገር በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ በከፍተኛ ኃላፊዎች ይገኛል።
በሰው መነገድና በሕገወጥ መንገድ ሰዎችን ድንበር ማሻገር ወንጀል ክስ ጉዳይ ምርመራ ሲጣራባቸው የነበሩና በ2016 እና በ2017 በጀት ዓመት 43 የምርመራ መዝገቦች በፍርድ ቤት ውሳኔ ያገኙ ሲሆን፣ ከነዚህም ውስጥ በ18 የምርመራ መዝገቦች በ29 ተከሳሾች ላይ ከአንድ ዓመት እስከ 25 ዓመታት ፅኑ እስራት እና ከሁለት ሺህ ብር እስከ 410 ሺህ የኢትዮጵያ ብር የገንዘብ መቀጮ በከፍተኛ ኃላፊዎች ተቀጥተዋል።
በሌላ በኩል በ2017 በጀት ዓመት በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር 35 የምርመራ መዝገቦች ለዓቃቢሕግ የተላኩ መዝገቦች በዓቃቢ ሕግ በኩል ክስ ተከፍቶባቸው በክርክር ሂደት ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ከታሰሩ ተጠርጣሪዎች መካከል ተከስሰው በፍርድ ቤት ዋስትና የተለቀቁትን ሳይጨምር 14 ተጠርጣሪዎች ወደ ማረሚያ ቤት ተልከዋል።
ቅንጅታዊ ሥራን በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስ ምላሽ እንደሚያስረዳው፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የበላይነት፤ በፍትሕ ሚኒስቴር ራሱን የቻለ በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች ጋር ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራር የሚያሳልጥ ተቋም በማስተባበር ላይ ይገኛል። በሰዎች የመነገድና ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎች የመመርመራና የመክሰስ የፌዴራል የሕግ አስፈፃሚ አካላት ስልጣን በመሆኑ (የአዋጅ 1178/2012 አንቀጽ 41)፣ የክልል የህግ አስፈፃሚ አካላት ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀሎቹን እንዲመረምሩ ውክልና በሚሰጣቸው ጊዜ በክልሎችም ተፈጻሚ ይሆናል።
ወድ አንባቢያን በነገው ዕለት የመጨረሻውና ክፍል አምስት የሚቀጥል ይሆናል።
በኢፕድ የምርመራ ቡድን
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም