የተለያዩ ድርሳናት በቀደመው ዘመን በኢትዮጵያ ሆቴሎች እንዴት እንደተመሰረቱ መዝግበው አስቀምጠዋል። ዋነኛው የመጠንሰሳቸው ምክንያት ሰዎች (በተለይ ደግሞ ነጋዴዎችና አገር አሳሾች) ከሚያደርጉት የንግድ እንቅስቃሴ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ተግባር ጋር የተጣመረ ነው። ይህን ታሪክም ኢትዮ ኢንተርናሽናል ሆቴል ፕሮፌሽናል ኔትዎርክ በድረ ገጹ ከትቦት እናገኘዋለን።
እንደ ድረ ገጹ ዘገባ ሰዎች ከአሁን በፊት የማያውቁት ቦታ ሄደው “የመሸብኝ እንግዳ” በማለት የመጠለያ ችግራቸውን የመግለጻቸውን ሁኔታ እና የተቸገረውንም እንግዳ በተወሰነ ስፍራ የማቆየቱ አዝማሚያ ከጊዜ ብዛት ለሆቴል መጀመር ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል። በእርግጥ የሆቴሎች መስፋፋት ከሰዎች ማህበራዊ ኑሮና እድገት ጋር ተነጥሎ አይታይም። በጥቅሉ በኢትዮጵያ ለሆቴሎች መጠንሰስ ምክንያት የነበሩት ቂጣውንና ቆሎውን በስልቻ አድርገው ይጓዙ የነበሩ መንገደኞች እንደሆኑ “ ዜና ቱሪዝም መጽሔት” በህትመቱ ይገልጻል።
ታደሰ ዘውዴ የእቴጌ ጣይቱ ብጡል የህይወት ታሪክ በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንደገለጹት የኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ሆቴል እንዲታወቅ ያደረጉት እቴጌ ጣይቱ ናቸው። እቴጌ ጣይቱ በጦር ሜዳ የተዳከሙትን በምግብ እና በመጠጥ መንከባከባቸውን እንዲሁም በልብስ ነክ ሙያ ተግባረዕድ ትምህርት እንዲቀስሙ የመጡ ሰልጣኞችን ተገቢውን መስተንግዶ እንዲያገኙ ማድረጋቸው የሆቴል አገልግሎትን አስፈላጊነት ከምንም በላይ ይበልጥ እንዲረዱ አድርጓቸዋል። የእንግዳ ማረፊያን አስፈላጊ ከአደረጉት ተጨማሪ ሁኔታዎች አንዱ ከተለያየ ቦታ ለንግድ ፣ አቤቱታና ለመሳሰሉት ጉዳዮች ይመጡ የነበሩት ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደጉ እቴጌ ጣይቱ እንዲህ ያሉ እንግዶች የሚያርፍበትን ቦታ አዘጋጅተዋል፤ ይህም የኢንዱስትሪውን አስፈላጊነት ያሳየ ነበር።
እንዲህ እንዲህ እያለ አሁን የሆቴል ዘርፍ ሰፊ ገንዘብ፣ የሰው ኃይል የሚሳተፍበት እና ለአገርም ቢሆን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ አምጪ ከሆነ ሰነባብቷል። ሆኖም ይህ ዘርፍ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ስጋት በሆነው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ከባድ ፈተና ውስጥ ገብቷል። ባሳለፍነው ሳምንት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስተኛ ዓመት አምስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተግኝተው ከምክር ቤቱ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሮና ከባድ ችግር እና ኪሳራ ከአደረሰባቸው ዘርፎች መካከል የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪው አንዱ እንደሆነ መግለጻቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ዘመናት አንዴ በድል ሌላ ጊዜ ደግሞ በክፉ ቀን ተፈትነው በተባበረ ክንድ ያለፉ አገር እና ህዝቦች ናቸው። ታዲያ አሁን ወገብን ሊያስፈታ ጉልበትን ሊያላላ የሚችል ችግር ዓለምም አገሪቱም ገጥሟቸዋል። ይህንን ፈታኝ ጊዜ ለማለፍ መንግስት ዓለም ፈተናውን እየተጋፈጠ ያለበትን መንገድ ሲያጤን ቆይቷል። ከዚህ መነሻም ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ ገባ ከተባለበት እለት ጀምሮ የተለያዩ የመከላከል እና ስርጭትን የመግታት እርምጃዎች ሲወስድ ነበር። አሁንም ይህንኑ አጠናክሮ ቀጥሏል።
ወረርሽኙ በኢኮኖሚ ጡንቻቸው የዳበሩትን የዓለም አገራት ሳይቀሩ ያፍረከረከ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ በኢኮኖሚያዊ አቅማቸው ገና ለማደግ ድክ ድክ ለሚሉ አገራት ደግሞ አጋጣሚው ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› ሆኖባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህምድ ባሳለፍነው ሳምንት ለምክር ቤቱ እንዳሉት በወረርሽኙ ምክንያት ከታመሙ ተቋማት መካከል ቀዳሚውና ዋነኛው የሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ ነው።
ከግሉ ዘርፍ መካከል አንዱ የሆነው የሆቴል ኢንዱስትሪ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን፣ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት የማይተካ ሚና እንደሚጫወት ያስመሰከረ ዘርፍ ነው። በተለይ በዚህ ዘመን ከቀድሞ በተሻለ ሁኔታ የአንበሳውን ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል።
የታሪክ ሁነቶች እንደሚያስረዱት እንደ ኮቪድ 19 ያሉ ወረርሽኞችም ሲከሰቱ የዓለም ኢኮኖሚ መቀዛቀዝን የማይቀር ጉዳይ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የዋጋ አለመረጋጋት ደግሞ በአገር ውስጥ በሚወሰዱ እርምጃዎች መቀልበስ እንደማይቻል የታወቀ ነው። ቢሆንም ከዚህ ጋር ተያይዞ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ መቀነስና መከላከል የሚቻልበት አጋጣሚ አለ።
ለመሆኑ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በኢትዮጵያ ያሉ ሆቴሎች እንደሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ ምን አይነት ፈተና እያጋጠማቸው ነው? በአዲስ ዘመን የባህልና ቱሪዝም አምድ ይህን ጉዳይ ለመቃኘት ወደናል። ለዳሰሳችን እንዲያመቸን በአገራችን ከሚገኙ ሆቴሎች መካከል አንዱ በሆነው በኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ጎራ በማለት ከድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ከሆኑት አቶ ወገኔ ማቴዎስ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
ኢንተር ኮንቲኔታል ሆቴል በአዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኙ ሰመ ጥር ከሆኑ ሆቴሎች መካከል አንዱ እንደሆነ እሙን ነው። ታዲያ ይህ ሆቴል እንደ አሁኑ በወረርሽኙ ሳይፈተን መልካም የሚባል ገቢ ያለው ለብዙዎችም የስራ ዕድል የፈጠረ ነበር። ሆቴሉ በተለይ ዓለም አቀፍ ደረጃን በአሟሉት ወደ አስራ አንድ በሚሆኑ የመሰብሰቢያ አዳራሾቹ ለተለያዩ ወርክሾፖች ፣ሴሚናሮች እንዲሁም ስብሰባዎች በማከራየት ከፍተኛ ገቢ ያገኝ እንደነበር የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ወገኔ ይናገራሉ።
በተለይ ድርጅቱ ካሉት የመሰብሰቢያ አዳራሾች ከ3ሺህ በላይ ሰዎችን የሚይዘው ትልቁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በጣም ተፈላጊ እና ለድርጅቱ የገቢ ምንጭ ከሆኑት መካከል አንዱ እና ዋነኛው መሆኑን ያስረዳሉ። ሌላኛው ድርጅቱ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኝባቸው የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ኪራይም ሌላኛው የገቢ ምንጭ ነው።
እንደ ድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ገለጻ ኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ወደ 200 የሚጠጉ እንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ሲኖሩት እነዚህም ክፍሎች ከሰባ በመቶ በላይ የሚከራዩ ናቸው። በአብዛኛዎቹ የዚሁ ተጠቃሚዎች የውጭ አገር ዜጎች እንደሆኑም ጠቅሰዋል። ሌላኛው “የዌልነስ” አገልግሎት ማለትም የስፖርታዊ እንቅስቃሴ ማዘወተሪያ ስፍራ፣ የዋና ፣ እስቲም፣ ስፓ እና ተያያዥ አገልግሎትን በመስጠትም ድርጅቱ ከፍተኛ ገቢ እንደሚያገኝ አቶ ወገኔ አክለዋል።
ሆቴሉ የተለያዩ የምግብም እና የመጠጥ አቅርቦቶችንም ለእንግዶች በማቅረብ ገቢ እንደሚያገኝም ጠቅሰው ይህም ገቢ ለድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ለአገርም የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት አንጻር ሰፊ ድርሻ እንዳለው አስገንዝበዋል።
በወረርሽኙ ወቅት
“አንዳንዶች የሆቴል ስራ ተቀዛቅዟል፤ አንዳንዶች ደግሞ ቆሟል ይላሉ። ቀዝቀዝ ወይም ተዳክሟል ስንል ‹የተወሰነ ስራ አለ› የሚል ሀሳብ በውስጡ ያዘለ ነው። እውነታው ግን የሆቴል ስራ በወረርሽኝ ምክንያት ሞቷል።” በማለት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ የሆቴሉ ስራ ምን እንደሚመስል ለጠየቅናቸው ጥያቄ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ወገኔ ገለጻ፤ ኢንተርኮንቲኔታል ሆቴል ከፍተኛ ገቢ የሚያገኝባቸው የስብሰባ አዳራሾቹ ፣የዌልነስ ማዕከሉ፣ እንዲሁም የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች ጦማቸውን ማደር ከጀመሩ ሶስት ወራት አስቆጥረዋል። በስራ ዓለም ተዘጋ ሲባል ከደንበኞች ጋር ቀጣይነት ላለው ግንኙት መልካም ስለማይሆን እንጂ ድርጅቱ መዘጋት የሚገባው ደረጃ ላይ መድረሱን ይናገራሉ።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ማንኛውም ድርጅት ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ በየትኛው ደረጃ የሚሰራን ሰራተኛ መቀነስ እንደማይችል መደንገጉን ያስታወሱት አቶ ወገኔ፤ በድርጅቱ ውስጥ እየሰሩ ከነበሩት አምስት መቶ ሰራተኞች አንድ መቶ አርባውን ብቻ በመጠቀም ሌላው ቤት እንዲያርፍ ማድረጋቸውንና ለሁሉም ሰራተኛ ወርሃዊ ደመወዝ ድርጅቱ እየከፈለ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ድርጅቱ ከወረርሽኝኑ በፊት ሲሰጥ ከነበሩት አገልግሎቶች በአሁኑ ወቅት 95 ከመቶ የሚሆኑት ምንም ዓይነት ስራ እየሰሩ እንዳልሆኑ ይናገራሉ።
በአብዛኛው የሆቴሉ ደንበኞች የውጭ ዜጎች መሆናቸውን የሚናገሩት ስራ አስኪያጁ፤ አሁን ባለው ሁኔታ በረራም ስለተቋረጠ የነገውን እንኳ መተንበይ አልተቻለም ። በዚህ ሁኔታ ዘርፉ አሁን ከገጠመው በላይ ከባድ ችግር ሊገጥመው ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
የመንግስት ድጋፍ
የመጀመሪያው የኮሮና ተጠቂ ግለሰብ በአገሪቱ ከተገኘበት ዕለት እና ሰዓት ጀምሮ መንግስት ባለው ሃይል እና አቅም እየሰራ ነው። ይህም ታሪክ የማይረሳው በህብረተሰቡም የሚያስመሰግን ውለታ እና ተግባር መሆኑን ይገልጻሉ። መንግስት በወረርሽኙ በተፈተኑ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሰራቸው ስራዎች ብዛት አላቸው። የሆቴል ስራ ዘርፍም ቸል ያልተባለና የተለያዩ ድጋፎችን የተደረገበት እንደሆነም ይገልጻሉ።
እንደ አቶ ወገኔ አስተያየት አገልግሎት ሰጪ ከሆኑት ዘርፎች መካከል በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከባድ ፈተና ውስጥ የገባውን የሆቴል የስራ ዘርፍ ከችግሩ ለማውጣት መንግስት እያከናወነ ካለው ድጋፎች መካከል አንደኛው እስከ 2007 ዓ.ም የነበሩ የግብር እዳዎችን ስረዛ ማካሄድ ሲሆን፤ ሌላኛው ደግሞ ባለሀብቶች በአነስተኛ ወለድ ብድር እንዲያገኙ የተደረገበት ነው።
‹‹በቅርቡም በአነስተኛ ወለድ ብድር እንድናገኝ የተለያዩ መረጃዎችን እንድናስገባ ተነግሮን ይህንኑ አድርገናል፤ ብድሩም በቅርቡ ይሰጠናል ብለን እንጠብቃለን›› የሚሉት ስራ አስኪያጁ፤ መንግስት እያደረገ ያለው ድጋፍ አበረታች መሆኑን በመጥቀስ ድጋፉ ከዚህ በተሻለ ሁኔታ ሊደረግ እንደሚገባ ያስረዳሉ። የተለያዩ አገራት ተሞክሮ በማንሳትም የሌሎች አገራት መንግስት የሰራተኞችን ደመወዝ ከባለሀብቶች ጋር በመጋራት እየሸፈነ እንደሆነ ይናገራሉ።
በኢትዮጵያም ወረርሽኝኑ ከባድ ችግር ላደረሰባቸው ዘርፎች እንዲህ ያለ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ። ይህ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ ወጪዎችንም ቀድሞ ከአደረገው በላይ ሊጋራን ይገባል ይላሉ።
እንደ አቶ ወገኔ ገለጻ፤ ኢንተርኮንቲኔንታል በሰላሙ ወቅት የውጭ ምንዛሬ ለአገሪቱ በማስገባት የራሱን ሚና ሲጫወት ቆይቷል። ነገ ሌላ ቀን ነው። በዚህ የፈተና ወቅት ድርጅቱ ቢደገፍ ነገ በተሻለ ሁኔታ በመስራት በድህረ ኮሮና ወቅት ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በማምጣት የተለመደውን ተግባሩን እንዲቀጥል ያስችለዋል።
“እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። ብዙ መልካም እና ክፉ ጊዜያችንን በመተጋገዝ ያለፍን። የአንድ አገር ልጆች ነን” የሚሉት አቶ ወገኔ ፤ ስለሆነም ከመንግስት እና ከጤና ባለሙያዎች የሚነገረንን መልዕክት በመስማት ይህችን ቀን እንለፈው ይላሉ። ነገ ጸሐይ ትወጣለች ፤የተሻለ ቀን እናያለን በማለትም፤ እስከዛው ጊዜ ድረስ ትዕግስት ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይናገራሉ። የሀይማኖት አባቶች ምክር፣ ጸሎት ፣ልመና እና ተግሳጽንም ከንቱ ማድረግ እንደማይገባ ጠቁመዋል።
በተለይ መንግስት ከሚሰራቸው የተለያዩ ስራዎች ባሻገር ያወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስከበር ይኖርበታል የሚል ምክረ ሃሳብ ይሰጣሉ። ‹‹የወረርሽኙ መዛመት ይቀንሳል ሲባል ጭራሽ እየጨመረ እየሄደ ነው›› የሚሉት አቶ ወገኔ ህብረተሰቡ ጥንቃቄ በመተው ቸልተኛ ሆኗል ይላሉ። በመሆኑም ይህ አይነት ቸልተኝነት መቅረት እንዳለበትና የጥንቃቄ መርሆችን መከተል እንደሚያስፈልግ ይገልፃሉ። በመጨረሻም መንግስት ሌሎች ስራዎችን በጥንቃቄ እያከናወነ እንደሆነ ጠቅሰው፤ የሆቴል ዘርፉም በጥንቃቄ በከፊል እንግዶችን የሚያስተናግድበትና በረራ የሚፈቀድበት መንገድ ቢመቻች መልካም ይሆናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
አብርሃም ተወልደ