የሥራን ዓለም ከተቀላቀሉ ለአንድም ቀን የቅጥር ማስታወቂያ አይተውና ተወዳድረው አያውቁም። በኔዘርላንድ የልማትና ተራአዶ ድርጅት( ኤስ ኤን ቪ ) ውስጥ ከ46 ዓመታት በላይ ሠርተዋል። ከአራት አስርት ዓመታት በዘለለው የሙያ ልምዳቸው በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች በተለያዩ የሥራ ሃላፊነቶች አገልግለዋል። ጥቁርና ነጭ ብለው ቀለም ሳይሉ ከሁሉም ጋር ተዛምደው ረጅሙን የህይወት ዘመናቸውን አሳልፈዋል። በዚሁ ቆይታቸው ከተለያዩ ወገኖች እውቀት ቀስመው የራሳቸውንም ልምድ አካፍለው ተማሪም አስተማሪም ሆነዋል።
እርሳቸው የሚሠሩበት የልማት ድርጅት ድህነትን ለማጥፋት በግብርና፤ በውሃና ንፅህና፤ በታዳሽ ሃይል ላይ የተሰማራ ነው። የመንግሥት አጋዥ ሆኖ ህዝብን ያገለግላል። በተጨማሪ ለወጣቶች ሥራ ዕድል መፍጠር፤ ለሴቶች እኩል ተጠቃሚነት፤ ለአየር ንብረት ጥበቃ ለሚሠራው ሥራ የእርሳቸው ድርሻ የማይተካ ነበር – የአቶ ወርቁ ቢሆነኝ።
አቶ ወርቁ በረጅሙ የሥራ ላይ ቆይታቸው ያካበቱትን ልምዶች፣ ያጋጠማቸውን ተግዳሮት እና የወጡበትን መንገድ እንዲሁም የህይወትን ውጣ ውረድ እንዴት እንደተሻገሩትና መሰል ተሞክሯቸውን ያጫውቱን ዘንድ ለዛሬ «የህይወት ገጽታ» እንግዳችን አድርገናቸዋል።
ልጅነት
በላስታ ወልደንጉሥ ላይ በወርሐ ጥቅምት ለቤቱ ወንድልጅ ተወለደ። በዚህም ቤተሰብ ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሁሉ ደስታውን ገለጠ። አቶ ወርቁ ያደጉት፤ በአምደወርቅ ድሀና ወረዳ ነው። በማህበረሰቡ ‹‹ድሀና ›› ማለት ለድሃ መስጠት እንችላለን የሚል ትርጓሜ አለው። በቀዬው ነፍሰጡር እናት ልጇን ስትገላገል ሀብታም ድሃ ሳይባል በእኩል ትታረሳለች። የአቶ ወርቁ እናትም ይኸው ሆኖላቸዋል። ልጃቸውን ሲወልዱ በማር በወተት ታርሰዋል።
እንግዳችንም የልጅነት ዘመናቸው ወደ ታዳጊነት እስኪሸጋገር ድረስ በብዙ እንክብካቤ፣ ተግሳፅና ባህል ታርቀው ነው ያደጉት። ለሥነ ምግባራቸውና ለትጋታቸው ቤተሰቦቻቸው መልካም ምሳሌ ሆነዋል። በተለይ ደሀ ሀብታም የማይሉት ወላጆቻቸው ከሁሉም ህብረተሰብ ጋር ተግባብተውና ተከባብረው በፍቅር ኖረዋል። እርሳቸውም ይህንን ባህል አድርገው ልጅነታቸውን አሳልፈዋል።
አቶ ወርቁ ‹‹በድሀና›› ብቻ አይደለም ያደጉት። ሰቆጣ ተሻግረው አያታቸው ጋር በመሆን ብዙውን የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። ‹‹የአያት ልጅ ቅምጥል›› እንዲሉ የፈለጉትን እያገኙ የምኞታቸው እየደረሰ ልጅነታቸውን አጣጥመዋል። አያታቸው ነፃነት ስለሚሰጧቸው ደግሞ የተለያዩ ጨዋታዎችን ተጫውተው ነው ያደጉት። ትዝታውን መለስ ብለው ሲቃኙ በዘመኑ እግር ኳስና እጅ ኳስ ሲጫወቱ የልባቸው ይደርስ እንደነበር ይናገራሉ። በላስቲክ ኳስ ሠርተው ከጓደኞቻቸው ጋር በደስታ ያሳልፉ እንደነበር አይረሱትም።
ባህላዊ ጭፈራም ‹‹ውዝዋዜም›› ቢሆን ከሚወዱት መዝናኛ ውስጥ አንዱ ነው። በችሎታቸውም ቢሆን አይታሙም። በአካባቢያቸው ትልቅ ክብር የሚሰጣቸው ሙያዎች ጄኔራል፤ ሐኪም፤ አስተማሪ የመሳሰሉት ቢሆኑም እርሳቸው ጥበብ ነክ በሆኑ እውቀቶችና ሥራዎች ይማረካሉ። አወንታዊ ምልከታ ያላቸውን ሰዎች አጥብቀው ይወዳሉ። ያለምክንያት አሉታዊ ጉዳዮችን መስማት ይጠላሉ። ይህ እሳቤ በጎ ምልከታ ይዘው እንዲያድጉ አድርጓቸዋል።
ከአምደወርቅ እስከ ሆላንድ
እርሳቸው ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ልጆች ፊደል ከቆጠሩ በኋላ የቤተክርስቲያን አገልጋይ እንዲሆን ነው የሚታስበው። የአቶ ወርቁ አባትም ይህ እምነት ነበራቸው። የዘመድ አዝማድ ልጆች ተለውጠው የተሻለ ቦታ ሲደርሱ ሲመለከቱ ግን ሃሳባቸውን ለመቀየር ተገደዱ። ልጃቸው ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ከማበርታታቸውም በላይ በሚገባ ዘመናዊውን ትምህርት እንዲማሩ በአቅራቢያቸው በሚገኘው አምደወርቅ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አስገቧቸው።
ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ክፍል በአካባቢያቸው ትምህርታቸውን መከታተል ቻሉ። ቀጣዩን ክፍል ደግሞ ቆጋ እንፍራንዝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሩ። ከአምስተኛ ክፍል በኋላ ደግሞ ወደ አያታቸው ጋር በማቅናት በሰቆጣ ዋግስዩም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህር ቤት ገቡ። እስከ ስምንተኛ ክፍል ደግሞ ወደ ወልዲያ ነበር ያቀኑት። ከሦስት የመንደሩ ልጆች ጋር በመሆንም በኪራይ ቤት ውስጥ መማር ጀመሩ። ከዘጠነኛ እስከ አስራ አንደኛ ክፍል በዚያው ቆይተዋል። አስራ ሁለተኛ ክፍል የተማሩት በደሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በማታው ክፍለ ጊዜ ነበር የተከታተሉት።
እንግዳችን በወልዲያ የትምህርት ጊዜያቸውን ያሳለፉት ምግባቸውን በአህያ እየጫኑ ለሌሎች ወጪዎች ከቤተሰብ 15 ብር በወር እየተላከላቸው ነበር። የ1966 ዓም አብዮት ምክንያት ትምህርት ሲቋረጥ ለጊዜውም ቢሆን የፈተናው ቀማሽ ነበሩ። ይህ አጋጣሚ ደግሞ ወደሥራው ዓለም እንዲቀላቀሉ ሁኔታዎችን ፈጠረ። ቀን እየሠሩ ማታ መማሩን ተያያዙት።
አቶ ወርቁ የመጀመሪያ ሥራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት ኤስ ኤን ቪ በላስታ በጀመረው የቆቦ ላሊበላ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት በአስተርጓሚነት ነው። ትምህርታቸውን እየተከታተሉም እስካሁን ድረስ በዚሁ ድርጅት ውስጥ ያገለግላሉ። ውጤታማ ሰው ናቸው። ያገኙትን ዕድል ለመጠቀም አጥብቀው የሚሠሩ ትጉህ። ይህ ታታሪነታቸው በከፍተኛ ውጤት 12ኛ ክፍልን እንዲያጠናቅቁ አድርጓቸዋል። ቀጣዩን ትምህርት በፈለጋቸው መንገድ እንዲማሩም ፈር ቀዳጅ ነበር።
በወቅቱ ጉብዝናቸውን ተመልክተው በሥራ ተወጥረው ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ የሚያበረታቷቸው መልካም አስተማሪዎች ነበሩ። በዚህ ተበረታተው አለቃቸውን አሳምነው ትምህርታቸውን ለመቀጠል እንደበቁ ይናገራሉ። በድርጅቱ ቀናነትም አዲስ አበባ ትምህርታቸውን ለመከታተል እንደቻሉም ያወሳሉ።
እንግዳችን ትምህርቱን የቀጠሉት በማታ ሲሆን፤ አሠሪዎቻቸው ቤት ተከራይተውላቸው ስለነበር ምንም አልተቸገሩም። በመሆኑም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው በማታው ክፍለ ጊዜ ለሰባት ዓመታት ትምህርታቸውን ተከታተሉ። ድርጅቱ የተሻለ ተማሪ ይሆኑ ዘንድም ብዙ ይደግፏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ በቢዝነስ ማኔጅመንት በጥሩ ውጤት እንዲመረቁ እንዳገዛቸውም አውግተውናል።
ሰባት ዓመታትን በትምህርት በማሳለፋቸው የትምህርትን ጥግ እንደነኩት ያስቡ እንደነበር የሚያወሱት ባለታሪኩ፤ በሥራቸው የሚያስተዳድ ሯቸው ሰዎችን ሲመለከቱ ግን በብዙ ነገር ይበልጧቸው እንደነበር ተረዱ። ይሄ መረዳት ደግሞ በትምህርታቸው እንዲገፉ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።
አቶ ወርቁ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጀመሩ። አለቃቸው የሃሳቡ ተቃዋሚ ነበሩ። እንዳይማሩ ፈልገው ሳይሆን ደግሞ ከቦታው ለቀው ስለሚሄድ የሚያምኗቸው እርሳቸውን በመሆኑ ‹‹እኔን ተክተህ ለመሥራት የተማርከው በቂ ነው›› በሚል መነሻ ነበር። ምን ጎደለብህ ብለዋቸውም ነበር። እርሳቸው ግን ‹‹ወይ ፍንክች የአባ ቢለዋ ልጅ›› እንዲሉ በሃሳባቸው ሳይስማሙ ቀርተው በአቋማቸው ፀኑ።
በአለቃቸው አግባቢነት ቆይተውም ቢሆን ከዓመት በኋላ ወደ ትምህርት ገቡ። ሆላንድ ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ይዘው በመሄድም መምህሮቻቸው በመከሩዋቸው የትምህርት መስክ መማር ጀመሩ። ትምህርቱ ኢንዱስትሪያል ፖሊሲና ኮርፖሬት ስትራቴጂ ነበር። ትምህርት ቤቱ ደግሞ በሆላንድ የሚገኘ ማስትሪክስ ስኩል ኦፍ ማኔጅመንት ነው። አቶ ወርቁ ጥረታቸውን በስኬት ከማጠናቀቃቸውም በላይ የማዕረግ ተመራቂ ነበሩ።
ከዚያ በኋላ ግን በድጋሚ ትምህርታቸውን አልቀጠሉም። ምክንያቱ ደግሞ በድርጅቱ ሕግ የትምህርት ዕድል ሲሰጥ ለሦስት ዓመት ማገልገል ግዴታ ነው። በቀጥታ በድሮ አለቃቸው ምክር በቦትስዋና የኤስ ኤን ቪ የማኔጅመንት አማካሪ ሆነው ተመደቡ። ሥራው በየጊዜው እያስተማራቸው፤ በንባብ እውቀተታቸውን እያዳበሩና የተለያዩ ስልጠናዎችን እየወሰዱ አቅማቸውን ማጎልበት ዋና ተግባራቸው ሆነ።
አራት አስርት ዓመታትን የዘለለው ቅጥር
በ1966 ዓ.ም ነው። ዕድገት በሕብረት ዘመቻ ሲወጣ የሥራ ቅጥርም አብሮ የተጀመረው። በወቅቱ እርሳቸው ወልድያ ይማሩ ነበር። 11ኛ ክፍል የደረሱ በመሆናቸውም የዕድገት በሕብረት ዘማች መሆን ግዴታቸው ነበር። ግን ረብሻ ነበርና አልሄዱም። ትምህርት ቆሞ ጊዜው እየረዘመ ሲመጣ ከጓደኛቸው አንዱ ‹‹ምግብ ለሥራ›› ውስጥ ገባ። በዚህም ከፈረንጆች ጋር እየሠራ ጓደኞቹን ይረዳ ጀመር። አንድ ቀን ግን የሥራ ዕድል አገኘላቸውና መሥራት እንዳለባቸው ነገራቸው። በዚህም አብረው የሚኖሩት ሦስት ጓደኛማቾች ተመካከሩ።
ሥራው ከነጮች ጋር በመሆኑና እርሳቸው የአካውንቲንግ ተማሪ በመሆናቸው ማመልከቻ ጽፈው በማስገባት እንዲፈተኑ አስገደዷቸው። ጎበዝ ነበሩና ውድድሩን አሸነፉ፤ ሥራም ጀመሩ። ከዚያ በኋላ ግን ምንም አይነት ውድድር አድርገው ሆነ ማስታወቂያ አይተው ለሥራ ማመልከቻ አስገብተው አያውቁም።
‹‹እስከ አሁን ድረስ አንዱን ሳልጨርስ አዲስ ሥራ እየተሰጠኝ እዚህ ደርሻለው። ዛሬም ድረስ አለቆቼ ሆላንዳዊ ናቸው። ለዕድገቴ መሠረት ከእነሱ ያገኘሁት እምነትና መበረታታት ነው። ድርጅቱ ለቆመለት አላማ ሃያ አራት ሰዓት የሚሠሩ፤ የሰው ዕድገትን የሚመኙ መሪዎች ናቸው ዕድለኛ ነኝ›› ይላሉ ስለ ሆላንዳዊያን አለቆቻቸው ሲናገሩ።
አቶ ወርቁ የመጀመሪያ ሥራቸውን ‹‹ሀ›› ብለው የጀመሩት ኤስ ኤን ቪ በላስታ በጀመረው የቆቦ ላሊበላ የመንገድ ሥራ ፕሮጀክት ነው። ፕሮጀክቱ የአካባቢውን ተወላጆች፣ ገበሬዎች በምግብ ለሥራ በማሳተፍ ራሳቸውን እንዲችሉ አድርጓል። በዚህም መንገዱን እንዲሠራ ያመጡት መሐንዲስ በቀላሉ ከገበሬው ጋር መግባባት ስለማይችል አቶ ወርቁን በአስተርጓሚነት እንዲቀጠሩ መረጧቸው። ስለዚህም በ1966 ዓ.ም በቆቦና ላሊበላ መካከል ባለው መንገድ ዳር ካንፕ ውስጥ ሆነው የትርጉም ሥራ እየሠሩ ኑሮን ተያያዙት።
እንግዳችን፤ በእንግሊዝኛ መጻፍና መስማትን ጠንቅቀው ቢያውቁም በልምድ ማነስ ምክንያት መጀመሪያ አካባቢ ከአለቃቸው ጋር በቀላሉ መግባባት አቅቷቸው ነበር። ሆኖም ከጊዜ በኋላ የአሠሪያቸው የንግግር ድምፀት እየገባቸው በመምጣቱ በፍጥነት ከሥራው ጋር መላመድ ችለዋል።
በዚህ ሙያ ላይ በአውሮፓ አቆጠጣር እስከ 1979 የሠሩ ሲሆን፤ በ1980 ደግሞ አዲስ አበባ ሄደው የድርጅቱ አስተዳደር እንዲሆኑ አደረጓቸው። በተለያዩ የልማት ድርጅት የሚሠሩ የሆላንድ ዜጋ የሆኑ በጎ ፍቃደኞችን ለማስተዳደርም ኃላፊነት ተሰጣቸው።
በሥራ ውስጥ በአለቃና በሌላ ሠራተኛ መካከል ልዩነት አለመኖሩም ይበልጥ ለውጤታማነት እንዲተጉ እንዳደረጋቸው የሚያወሱት እንግዳችን፤ በአስተዳደርነት ለአምስት ዓመታት ሲሰሩ ከሁሉም ጋር ተግባብተው እንደነበር ያነሳሉ። በኢትዮጵያ የገጠር ሁሉን አቀፍ ዕድገት ፕሮጀክት ኦፊሰር ሆነው ሲሰሩም ይህንኑ ተግባራቸውን ነበር እውን የሚያደርጉት።
‹‹ብዙ ማወቅን የሚፈልግ ሰው ሁልጊዜ አውቃለሁ፤ አውቀዋለሁ ማለት የለበትም። ለራሱ ቀድሞ እንደሚችለው ነግሮ ለሚያሠራው ግን ከእነርሱ መማር እንደሚፈልግ ማስረዳት አለበት። ምክንያቱም ብዙዎች ያላቸውን እውቀት ሳይሸሽጉ የሚሰጡት ይህ ሲሆን ነው›› የሚሉት ባለታሪኩ፤ እነዚህ ባህሪያትን ተላብሶ መሥራት ለበለጠ የሥራ ዕድል እንደሚያሳጭም ይናገራሉ።
የተሰጠውን ተሞክሮ በተግባር ለውጦ ማሳየት መቻል ከሁሉም ሠራተኛ እንደሚጠበቅ የሚያምኑት ባለታሪኩ፤ በተሰማሩበት ውጤታማ ሥራ ሠርቶ ማሳየት ዋናው የስኬት ምልክት መሆኑን ከራሳቸው ተሞክሮ ያስረዳሉ። ይህ ደግሞ በየጊዜው የተሻለ አማራጭ እንደሚሰጥ ይመክራሉ። በምሥራቅና በደቡብ አፍሪካ ከባቢያዊ የአስተዳደር አማካሪ ለመሆንም የበቁት በዚህ ሥራቸው መሆኑንም ይገልፃሉ።
በምርሥራቅና በደቡብ አፍሪካ አካባቢ በአማካሪነት በሚሠሩበት ጊዜም በጊዚያዊ የኤስ ኤን ቪ ቦርድ ዳይሬክተር አባል ሆነውም አገልግለዋል። የሥራ ጊዜያቸው ሲጠናቀቅ ደግሞ በጋና የኤስ ኤን ቪ የመጀመርያው አፍሪካዊ ዳይሬክተር ሆነው መሥራታቸውን ቀጠሉ። ከዚያ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ ዳግም የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ከባቢያዊ የድርጅቱ ዳይሬክተር በመሆን ለሰባት ዓመታት መሥራት ችለዋል።
ቀጣዩ የሠሩበት ቦታ ዓለም አቀፍ የአመራር የትግበራ እንቅስቃሴ ፕሮግራም ማናጀርነት ነበር። በአፍሪካ፣ እስያ፣ ላቲን አሜሪካ የሚገኙ 19 አገራት የተሳተፉበት የኤስ ኤን ቪ ፕሮግራምን መርተዋል። ከዓመት ከሁለት ወር በኋላ ደግሞ ወደ አገራቸው ተመልሰው በአሁኑ ሰዓት የድርጅቱ ዳይሬክተር ሆነው እየሠሩ ይገኛሉ።
‹‹አለማወቅን ማወቅ ብዙ ጠቀሜታ አለው። ብዙ ነገሮችን ጠንክሮ ለመሥራትና ለመማር ያግዛል። እውቀት ለመገብየትም ሰፊ ዕድል ይሰጣል›› ብለው የሚያስቡት አቶ ወርቁ፤ ከላይ ያሉትን ቦታዎች ሲመሩ ከሌሎች እየተማሩ መሆኑን ይናገራሉ። በየጊዜው የተለያየ የሥራ ሃላፊነትም የተሰጠኝም ዋናው ምክንያት ‹‹አዲስ የመማሪያ ዕድል ፈጥሬ የምችለውን ስለማደርግ ነው›› ይላሉ። ከሌሎች አገር ዜጎች ጋርም በመግባባት መሥራት የቻሉት የባህል ልዩነቶች ወርቅ የሆኑ ልምዶችን እንደሚሰጡ በመረዳታቸው መሆኑን ያነሳሉ።
አቶ ወርቁ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ጡረታ ይወጣሉ። ግን ሥራቸውን ሲሰሩ ያንን እያሰቡ አይደለም። ባላቸው ዕድሜ አገራቸውንም ሆነ ድርጅታቸውን ማገልገል ይሻሉ። ዛሬም ሰፊ ሠራተኛ ያለበትን ድርጅት እንዲመሩ የተመረጡትም በአስተዳደር ከሌሎች ተምረው በለውጥ እየደገፉት ስለመጡ መሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹በተማርኩት አገሬን መጥቀም እፈልጋለሁ›› ብለው በተነሱበት ወቅት የቀድሞ አለቃቸው የዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንዲኖራቸው ከእኔ ጋር ይሥራ በማለት ማመልከቻ እስከማስገባት የደረሰው የእርሳቸው ትጋትና ውጤታማነት እንደነበር ያጫወቱን እንግዳችን፤ በድርጅቱ የመጀመርያው የኤስ ኤብ ቪ የአገር ፕሮግራም ዳይሬክተር ሃላፊነት ከተሰጣቸው አፍሪካዊ የሥራ ባልደረቦቻቸው አንዱ ሆነዋል። በዚህም ደስተኛ እንደነበሩ አይረሱትም። ይህ ትጋታቸው ደግሞ የአገራቸውን ክብር ከፍ ለማድረግ እንደተጠቀሙበት ያወሳሉ። መሥራት እንደሚችሉ ለማሳየትም ሁሉንም ሥራ በለውጥ ይመሩት እንደነበርም አጫውተውናል።
በወቅቱ ተቋማቸው አምስት አህጉር ላይ ሲሰራ የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካን እንዲመሩ ተሰጥቷቸዋል። ይህ ደግሞ 9 አገራትን ይይዝ ነበርና በሚገባ እንደለወጧቸውም አይረሱትም። የሚሠራ ሰው ይሳሳታል ብለው የሚያምኑት አቶ ወርቁ፤ በአንድ ጉዳይ ላይ ስህተት መደጋገም እንደማይገባ ይህ ከሆነ ደግሞ ውድቀትን እንደሚያስከትል ያነሳሉ። እናም ሰዎች እሳሳታለሁ ሳይሆን አሸንፋለሁ ብለው ሊሠሩ ይገባል ይላሉ። አትችልም የሚባል ነገርን መስማት ተገቢ አለመሆኑንም አይዘነጉትም። ይህ መርሐቸው እርሳቸውን አትችሉም የሚላቸው እንዳይኖር እንደረዳቸው ይናገራሉ።
እንግዳችን እሱ ልዩ ነው የሚባል ዘይቤ አይቀበሉም። ሆኖም ሁሉ ሰው እኩል ነው። ልዩነቱ ዕድሎችን የምንጠቀምበት ዘዴና ውጤት ነው። ዋናው ቀና መሆን ነው ብለው ያምናሉ። ይህ እምነታቸውና የለውጥ መሪነታቸው ደግሞ በድርጅቱ የረጅም ጊዜ አገልጋይ አስብሎ እንዲታወቁ አድርጓቸዋል።
ኢትዮጵያዊነትና ፍልስፍናቸው
‹‹ሁልጊዜ ጥረት ማድረግና ሥራዎችን በውጤት ማሳየት ከፍተኛ የሚባለውን ደረጃ ያቀዳጃል። በዚህ ደግሞ ኢትዮጵያዊያን ጠንካሮች ናቸው። እንደውም ዓለም ላይ በብዙ መስኮች ከፍተኛ ደረጃን የያዙ ኢትዮጵያዊያን በዝተዋል። በጣም የምኮራባቸውና ትልቅ ምሳሌ የሆኑኝም ብዙ ናቸው። ስለዚህ ኢትዮጵያዊነት ከልጅነት ጀምሮ ኩራት እንደሆነ ተምሬበታለሁ። ኖሬበትም አድጌያለሁ፤ አሁንም እየኖርኩበት እገኛለሁ። ያጋጠሙኝን ዕድሎች ሁሉ በአግባብ በትኩረትና በደስታ አስተዋጽኦ እንዳደርግ ዕድል የሰጠኝም ይህ ልምዴ ነው ›› ይ ላሉ።
በዚያው ልክ በዓለማችን ላይ ብዙ ደግና አዋቂ ሰዎች እንዳሉ መታመን አለበት ይላሉ። ከእነሱ ብዙ መማር እንደሚቻልም ማሰብ ተገቢ ነው። ለመማር ግን ሁሉም ሰው መጣር፣ የተሻለ ዓለም ለመገንባት መረባረብ፣ የራሱን አስተዋጽኦ ማድረግ አለበት። አለቆችም ከአደጉበት ማህበረሰብ በተጨማሪ በአመለካከት ልዩነት የሚያምኑ፤ ከስህተት መማር እንደሚቻል የሚያስቡ፤ ወደፊት እንድንተጋ የሚያበረቱ መሆን ይጠበቅባቸዋል የሚል እሳቤ አላቸው። እርሳቸው ይህንን የተላበሱ አለቆች ስለገጠሙዋቸው ማንኛውንም ቦታ በተሻለ አቅም ማለፍን ችለዋል። ሌሎችም ይህንን ቢከተሉ እንደሚደሰቱ ይናገራሉ።
አበርክቶ
‹‹ሰው መታወቅ ያለበት በሚያመጣው ለውጥና ለሌሎች ባበረከተው ነገር ነው›› የሚለው ጠንካራ አቋማቸው የሆነው ባለታሪካችን፤ ድርጅታቸው በኢትዮጵያ ላይ በሚሠራቸው ሁሉ የተሻለ ነገር እንዲያደርግ ይጥራሉ። አገሪቱ ብዙ ነገር ያላት መሆኗን በማሳየትም መታገዝ ያለበትን ጉዳይ ቀድመው ያሳያሉ።
«ድሀና አምደወርቅ ፋውንዴሽን»ን በመመስረት
ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ትምህርት ላይ፤ የተሐድሶ ሃይል፤ ንፅህና ላይና ግብርና ላይ የሠሯቸው ሥራዎች እንደ ትልቅ የልማት አስተዋጽኦ ሊወሰድ የሚችል ነው። ለዚህ ያገዛቸው ደግሞ በተለይ ጅማሮው ላይ ሁሉም አባሎች ከኪሳቸው ገንዘብ በማዋጣት እንደነበር ያስታውሳሉ። ይበልጥ ተጠቃሚነቱ እንዲያሰፋ ደግሞ በክልሉ ላይ የሚሠሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች እንዲሳተፉ ጠንክረው ሠርተዋል።
ያቋቋሙት ፋውንዴሽን የእገዛ ጅማሮውን ሀ ያለው በትምህርት ሥራ ሲሆን፤ ኮምፒውተር የሚመጣበትን መንገድ አመቻችተው ትምህርት ቤቶችን በመምረጥ ተማሪዎች ከቴክኖሎጂው ጋር እንዲተዋወቁ አድርገዋል። ከዚያ የዞኑ ትምህርት ቢሮ ቀድሞ ያመቻቸው ነገር ስለነበር በስፋት ሠርቶበት ከ26 ትምህርት ቤቶች በላይ የኮምፒውተር፣ ላቦራቶሪ ተቋቁሞ በ ኢለርኒግ (E-Learning) ተማሪዎች እንዲማሩ ተደርጓል። ንብ ማነብ ላይ መሥራት ሁለተኛው ሥራቸው ሲሆን፤ 1200 ገበሬዎችን በዘመናዊ መንገድ እንዲሰለጥኑ አድርገዋል። በእርግጥ ተቋማቸው ዋነኛ ሥራው የግብርና ሥራውንም ማገዝ ነበርና ያም እንዳገዛቸው ይናገራሉ። በተመሳሳይ አብረዋቸው የሠሩትን ግብረ ሠናይ ድርጅቶች በማስተባበርም አካባቢው ላይ ለውጥ እንዲመጣ አግዘዋል።
እነ አቶ ወርቁ በፋውንዴሽናቸው በአንደኛው አባል አማካኝነት ለአምደወርቅ ቅድመ መደበኛ በቂ የመማሪያ ዕቃዎችን አበርክተዋል፤ ወጣቶችን ሰብስበው በማሰልጠን ሀሳብ እንዲያመነጩና የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ አድርገዋል። ከወጣቶቹ በሚመነጩ ሀሳቦች የንግድ ባንክ በአምደወርቅ ከተማ እንዲከፈት አድርገዋል። ከዚያም በላይ በትራኮማ ይሰቃዩ የነበሩ ሰዎች የዓይን ብርሃናቸው እንዲመለስም ሠርተዋል። እንደውም በአንድ ጊዜ በተደረገው የ120 ሰዎች የዓይን ቀዶ ሕክምና ውስጥ 80ዎቹ የዓይን ብርሃን እንዲያገኙ ሆነዋል። በዚህም ሁልጊዜ እንደሚደሰቱ ይናገራሉ።
ኮሮና በመደማመጥ ይጠፋል
ኤስ ኤን ቪ ኢትዮጽያ በአሁኑ ጊዜ ከ15 በላይ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ከሚመለከተው የመንግሥትና የግል ተቋማት ጋር በመተባበር ይሠራል። ከፕሮጀክቶቹ መካከል ሁለት ግዙፍ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ያተኮሩ ፕሮጀክቶች ሲሆኑ፤ በርካቶችን ወደ ሥራ ያስገባል። እናም ወቅቱ ብዙ ሥራን የሚጠይቅበት በመሆኑ እንደ ድርጅት ኮሮና እጃቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ አላደረገም። የተለያዩ ተግባራትን እየከወኑ መሆናቸውን አጫውተውናል።
ዋነኛ ሥራ ከመንግሥትና ከግል ዘርፉ ጋር በመተባበር ህብረተሰቡን መጥቀም በመሆኑ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረታቸውን እንዳደረጉ ይናገራሉ። በተለይ ወቅቱ የግብርና ሥራው ላይ የሚታገዝበት በመሆኑ ሠራተኞች ራሳቸውን የሚጠብቁበትን ሁኔታ በማመቻቸት ከክልሎችና ዞኖች ጋር እየሠሩ መሆኑን አንስተዋል።
ድርጅታቸው የመጠጥ ውሃና ንጽህና መጠበቅ ላይም እንዲሁ ወቅቱ የሚጠይቀውና በስፋት የሚተገበር የማይቋረጥ በመሆኑ ከመንግሥት ጋር በመተጋገዝ እየሠሩ ነው። እንዲያውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ10ሩ ክፍለከተሞች የሚገኙ ለ90 ሺህ 128 የጎዳና ተዳዳሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ከመሥራት ባሻገር ግምታቸው ከ950 ሺህ በላይ የሆኑ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ማበርከቱንም አውግተውናል።
መልዕክት
ጠንክሮ መሥራት ዕድልን ቀና ያደርጋል፤ መንገዶችን ይከፍታል። ስኬትንም ያቀዳጃል። እናም ሰዎች ማድረግ ያለባቸው በሥራቸው ሁሉ ጠንክሮ መሥራት ነው ይላሉ። ሌላው ማህበረሰቡ የሰጠኝ ያህል ሰጥቻለሁ ብሎ ራስን መጠየቅ እንደሚገባም ያሳስባሉ። የወሰድኩትን ያህል መልሻለሁ ብሎ ለመሥራት መነሳት አገርን ይለውጣል ይላሉ።
የሥራው ውጤት በደረጃ ከፍ ማለት ሳይሆን ለህብረተሰብ በሚያስገኘው ጠቀሜታ መለካትም ሌላው ሥራችን መሆን አለበት የሚሉት ባለታሪካችን፤ ሥራ እንዲናገር መፍቀድ፣ በእውቀት ነገሮችን ማከናወን ዋነኛ ተግባራችን ልናደርገው ይገባል መልዕክታቸው ነው። ‹‹እውቀት ከጭንቀት ያላቅቃል፤ ከሰው እኩል መሆንን ይነግራል፤ አቅምን ይለያል፣ ተከታይን ያበዛል፤ ከፍታን በዚህ እየለኩ መራመድ ሥራችን እናድርገው›› የሚለው የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 7/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው