ከ ወራት ሁሉ የበዓል ሀብታም ማነው ቢባል፤ ጥር ይመስለኛል። በተለይ ለክርስትና እምነት ተከታዮች። በጥቅሉ ደግሞ ከበዓላቱ በአንድም በሌላም መልኩ ደስታውን ለሚጋሩ፣ ክዋኔውን ለሚወዱና በኢትዮጵያዊነት ለሚኮሩ የደስታ ወቅት ነው። የሚያገቡ፣ የሚጋቡና የሚያጋቡ፤ ግራ የሚያጋቡትን ሳይጨምር፤ እንዲሁም ነጋዴዎችና ባለሆቴሎችም ጥሩ ትርፍ የሚያካብቱበት ይመስለኛል፤ ወርሃ ጥር።
ከጥምቀት መልስ፤ ጥቂት የማይባሉ ጎረምሶችና ጎልማሶችን ሰብሰብ ብለው በሆቴሎችና መጠጥ ቤቶች በር ላይ ማየት የተለመደ ሆኗል። የጥንቶቹ ሎሚ ተወራውረውና ተጫጭተው ሲሽኮረማመሙ ነበር መሰለኝ ጊዜውን የሚያሳልፉት። በእርግጥ ሰብሰብ ብለውም በሳቅና በጨዋታ ጊዜውን ተናፋቂ ሳያደርጉት አይቀርም። አስቡታ! በየዓመቱ ለጥምቀት ብለው ተቀጣጥረው የሚገናኙ ሰዎችኮ አሉ።
ያኔስ ሩጫው እንደዛሬ አልነበረም፤ ቢያንስ ቀና ብሎ ለመተያየት ጊዜ ይተርፋል። አሁን ቀና ብለን ብንሄድ እንኳ የኑሮን ሂሳብ እየሠራን ሆነና እርስ በእርስ መተያየት የለም። እንዲህ ቀልብን ሰብሰብ አድርጎ መተያያ ጊዜም ጥምቀት ሆነ። ታቦታቱን ሸኝቶ ወደ የቤት ከመመለስ ይልቅ፤ በዓመት አንዴ ያገኙትን ሰው እስኪጠግቡት ለማውራት፤ ያለፈውን ጊዜ እንደውሃ ኮለል እያደረጉ ለመንገር የት ይኬድ? ለዛ ይመስለኛል፤ ብዙ መጠጥ ቤቶችና ሆቴሎች አካባቢ ብዙ ሰዎች ሰብሰብ ብለው የምናየው፤ ወይም ሰብሰብ ብለን የምንታየው።
መቼም ጥምቀት አንድ ጊዜ መሆኑ እንጂ፤ የቢራ አስተዋዋቂዎች ሳይጠቀሙበት አይቀሩም ነበር። አሁንስ ምን ቀራቸው? በነገራችን ላይ ግን ከጥምቀት በዓል የሚመለሱ ሰዎች፤ እነዛ መጠጥ ቤቶች ባይኖሩ ወይም «መጠጥ የለንም» ቢሏቸው እንኳ፤ መሰባሰባቸውን አይተውትም። በእርግጠኝነት እላችኋለሁ፤ አብዛኞቹ በዓመት አንዴ በከተራና በጥምቀት የሚገናኙ ስለሚሆኑ፤ አጋጣሚዋን ለናፍቆታቸው መወጫ ማድረግ ስለሚፈልጉ ነው የሚሰባሰቡት።
ብቻ ነገሬ ዞሮ ዞሮ ማረፊያው መጠጥ ላይ ነው። ይሄ የመጠጥ ወሬ ሳይሰለቻችሁ ይቀራል? አዎን! «በየቀኑ በየስርጭቱ መካከል የሚሰማውን ማስታወቂያ መቼ ነው አዋጁ የሚያስቆምልን?» ለሚለው ጥያቄ መልስ ያለው ካልሆነ ስለዚህ ጉዳይ ምንም ዓይነት ነገር መስማት የማይፈልግ ብዙ ሰው አለ። እኔን ግን ጠይቁኝ፤ «ምን ስትይ ጥምቀትን ሰበብ አድርገሽና ዙሪያ ዙሪያውን ታከሽ የመጠጥን ነገር አነሳሽው?» በሉኝ። «የሰለቸኝንና የታከተኝን፤ አልፎም መሰልቸቱን ለምደን የተውነውን ጉዳይ ምን ስትይ አነሳሽብን?» በሉኝ።
እንዲህ ነው፤ ፔንስልቫንያ በተባለች አንድ የአሜሪካ ግዛት ውስጥ የሆነ ነው ብሎ ዩፒአይ የተባለ ድረገጽ ከሳምንት በፊት ያስነበበው ዜና ቢስበኝ ነው። ዜናው የ«አፋልጉኝ» ይዘት ያለው ስለሆነና፤ የተፈለገውም ሰው ምንአልባት ከዚህ ከእኛ መዲና የሚገኝ ከሆነ፤ ወደ ፔንስልቫንያ እንዲላክ ጥያቄ ለማቅረብም ጭምር ነው። ማን ያውቃል? ሰው በምን በኩል ኑሮው እንደሚቀየር’ኮ አይታወቅም።
የፔንስልቫንያ ፖሊስ ነው አፋልጉኝ ያለው። ተፈላጊው እንዲህ ያለ ነው፤
* ጾታ፤ ተለይቶ አልተቀመጠም። ይህ ማለት ደግሞ ተፈላጊው «ሰው» ስለሆነ፤ ለወንድ እንዲሁም ለሴት እድሉ ክፍት ነው።
* ብዛት፤ ሦስት።
* ተፈላጊ ችሎታ፤ የተማረ ያልተማረ አይልም፤ ዲግሪ በብዛትም በደረጃም አይጠየቅም። በጎ ፈቃደኛና አደገኛ ጠጪ መሆን ብቻ በቂ ነው።
* የተፈላጊ የሥራ ድርሻ /ጊዜአዊ ቢሆንም/፤ እኔ ነኝ ባሉ ጉደኛና ከፍተኛ የአልኮል መጠን ያላቸውን መጠጦች ጠጥቶ፤ አቅልን እስኪስቱ መስከር ነው።
የከተማዋ ፖሊስ እንዲህ ያለ በጎ ፈቃደኛ መፈለጉን በማኅበራዊ ድረገጹ ወይም በፌስቡክ ይፋ ያደረገው፤ ለተግባራዊ ስልጠና የሚውል «ሰካራም» ፈልጎ ነው። ስልጠናው ለፖሊስ አዛዦች እንዲሰጥ የታቀደ ሲሆን፤ በመስክ እንቅስቃሴ ላይ ጠጥቶ እያሽከረከረ ነው ብለው የጠረጠሩትንና ጠጥቶ ሲያሽከረክር ያገኙትን ሰው እንዴት መያዝና መቆጣጠር እንደሚቻሉ በተግባር ለማሳየት ያለመ ነው። በአንድ ቃል፤ መልመጃ ሊያደርጉት ነው ማለት ነው።
ጣቢያው ፈቃደኞቹ የሚመዘገቡበትን ቀን አብሮ ይፋ አድርጓል። ቀኑን እንወቀው ካላችሁ፤ በእኛ በኢትዮጵያውያን የቀን መቁጠሪያ የካቲት ማብቂያ አካባቢ ነው። «መጠጡን እንደልብ ስለማቅረብ አታስቡ፤ በመጠጣትና በመስከር ለሚባክን ጊዜ ግን ምንም ዓይነት ካሳ አልከፍልም» ብሏል፤ ስልጠናውን ያዘጋጀው የፖሊስ ጣቢያው ሥራ ክፍል።
ታዲያ ግን የበጎ ፈቃደኞች እድሜ ክልል ከ25 እስከ 40 እንዲሆን ተጠይቋል። «ከዚህ ቀደም የፍርድ ቤት ጣጣና ክስ የሌለበት» ሲልም ክፍሉ በጣቢያው ድረ-ገጽ አክሏል። ብቻ «ጥምብዝ ብሎ ለመስከር ፈቃደኛ የሆነ» የሚለው ደመቅ ተደርጎ የተሰመረበት ነው። «የአንድ ቀን የመጠጥ ወጪዬን ይሸፍኑልኝ እንጂ፤ እንኳን ጠጥቶ ስለማሽከርከር ለምን ስለሰውነት ክፍሎች ማስተማሪያ አያደርጉኝም!!» የሚል ይኖራል፤ ማን ያውቃል?
ታዲያ እንደ ባለማስታወቂያዎቹ ፍላጎት፤ በጎ ፈቃደኛው መጠጦቹን ጠጥቶ ከሰከረና ፖሊሶቹም የተፈለገውን የተግባር ስልጠናው ካገኙ በኋላ እየተወላገዱ መሄድ የለም። «ሲጠጣ ወይም ስትጠጣ አብሬ ነበርኩ፤ በበጎ ፈቃድ ጠጠቶ ወይም ጠጥታ ያለፈቃዱ ወይም ያለፈቃዷ አደጋ ውስጥ እንዳይገባ ወይም እንዳትገባ፤ ኃላፊነቱን ወስጄ እጠብቀዋለሁ ወይም እጠብቃታለሁ» ብሎ ቃል የሚገባ፤ ስካር የማይወድ፤ እንደ «ሹም ሹፌር» ያለ ሰው አብሮ ሊኖር ይገባል ተብሏል።
እንግዲህ የበጎነት ዓይነት አለው። ማስተማሪያና መልመጃ ለመሆንም እንዲህ ያለ በጎ ፈቃድ ሊጠየቅ ይችላል። መቼም እነዛ የፔንስልቫንያ ፖሊስ አሰልጣኞች፤ ምሽት ላይ ወልገድ ወልገድ የሚል አጥተው አይመስለኝም። እዚህ እኛ አገር መጥተው እግሩ በነዳጅ መስጫውና በፍሬን ላይ እየተንገዳገደበት አደጋ የሚያደርሱ፤ ጠጪዎችና መኪና አደጋ አድራሾችን ቢመለከቱ፤ ተግባራዊ ስልጠናውን በአፋጣኝ ወደ አገሬ ያመጡት ነበር።
እዚህ ላይ፤ በፔንስልቫንያ «ፈቃደኛ የሆነ መልመጃ ሰካራም» እስኪፈለግ ድረስ መሆኑ ገረመን እንጂ፤ ጠጥቶ የማሽከርከር ነገርስ በእርግጥ ሁሉም አገር ላይ ተመሳሳይ ችግር እንደሆነ ነው የሚነገረው። የሰው ልጅ ሁሉ መነሻው አንድ ስለመሆኑና ዘሩ ከአንድ አዳም እንደሆነ ማስረጃ ይዘው ለመሟገት የሚደክሙ፤ እንዲህ ያለ የሰው ልጅን አስቸጋሪነት ቢጠቅሱ እርፍ የሚሉ አይመስላችሁም? ሰላም!
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
ሊድያ ተስፋዬ