በስራ አጋጣሚ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እንቀሳቀሳለሁ። በዚህኛው ጉዞዬ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ጎራ ብየ አርባያ በለሳ እግር ጥሎኛል። በለሳ የታሪክ አምባ ነው። በለሳ ለብዙ ታጋዮች መጠጊያ ነበር። እነ ተፈራ ዋልዋ፣ በረከት ስምዖን፣ አዲሱ ለገሰ እና ሌሎችም ደርግ ሲመታቸው የተረፉት በለሳ አቅፎ ይዟቸው ነበር። የበለሳ ሕዝብ፣ ቆሎ ቆርጥሞ፣ እራፊ ለብሶ፣ ብረት ተንተርሶ፣ ጥይት አንጥፎ አስተናግዷቸዋል። እንኳን ሕዝቡ ጋራ ሸንተረሩም ባለውለታቸው ነው። ኢህዴን በአራት ሪጅን የተከፈለ የትግል መስመር ነበረው፤ (ሪጅን አንድ ጠለምት፣ ሪጅን ሁለት ወልቃይት፣ ሪጅን ሦስት በለሳ፣ ሪጅን አራት አርማጭሆ)። ዋልዋ እና አሽከር ተራሮች፣ ዳሆጭ፣ ላቫ ማርያምና የመሳሰሉት የበለሳ ምድሮች የሪጅን ሦስት (በለሳ) መጠናከሪያና መገናኛ መስመሮች ነበሩ። እናም በለሳ የጦር አውድማ ነበረች። በለሳ ላይ ከባድ ጦርነት ሲካሄድ እነ ተፈራ ከሞት ያመለጡት ዋልዋ ተራራ ላይ ተሸሽገው ነው። ተፈራ ከዋልዋ ተራራ (ዛፍ) ተሸሽጎ በመትረፉ ተፈራ ዋልዋ ተባለ።
በለሳ እና ብአዴን አሳና ባህር ነበሩ። ‹‹አሳውን ለማጥፋት ባህሩን ማድረቅ›› በሚል መርህ አርባያ በለሳ በተለያየ ጊዜ አውሮፕላን ድብደባ ተፈጽሞበታል። ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ ገፈት ቀማሽ ነበረች።
ሰኔ ሦስት ቀን 1981 ዓ.ም ዕለቱ ቅዳሜ ነበር፤ የገበያ ቀን። ከየአቅጣጫው ገበያተኞች ለመሸጥና ለመሸመት የበለሳ ወረዳ ማዕከል በሆነችው ‹‹ዙይ ሐሙሲት›› ተሰባስበዋል። እናቶች ስልቻቸውን አሸንቅለው ልጆቻቸው እንዳያለቅሱባቸው በጊዜ ለመመለስ ይዋትታሉ። ሁሉም በጊዜ ወደ ቤቱ ለመድረስ ይጣደፋል። ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ድንገት ገበያው ላይ ቦንባቸውን አዘነቡበት። ከቦንብ ድብደባው በኋላ የተገኘ ቢኖር የተቆራረጠ የሰው አካል፣ የተቀጣጠለ የእንስሳት አካላትና የወደሙ ቤቶች ነበሩ። ጀግንነት ይጎዳል እንዴ?
ብአዴን/ኢህአዴግን ሲርበው አብልተው፣ ሲጠማው አጠጥተው፣ ጠላት ሲመጣ በጀግንነታቸው መክተው፣ ጥላ ከለላ ሆነው ነበር ያሳደጉት። ዳሩ ግን፣ ለድል ያበቁት ‹‹ኢህአዴግ‹‹ የወንዝ ውሃ ከመጠጣት፣ በእግር ከመንከራተት፣ በቃሬዛ ከመሄድ፣ በዳስ ከመማር አላዳናቸውም፤ ከድህነት አረንቋ አላወጣቸውም፤ ቁስላቸውን አልሻረላቸውም። ወርቅ ላበደረ ጠጠር።
ከአዲስ አበባ በማለዳ የተነሳችው መኪናችን አባይን ተሻግራ ለምሳ ደብረማርቆስ ከተፍ አለች። ከዚያም ፍኖተሰላምን፣ እንጅባራንና ዳንግላን አልፋ አዳሯን ባህር ዳር አደረገች። በማግስቱ ካባህር ዳር ተነስታ ወረታና አዲስ ዘመን አልፋ ማክሰኝት ገባች። ከማክሰኝት ወደ ቀኝ ስትታጠፍ ፒስታ መንገድ ተቀበላት። ትንሽ እንደተጓዘች አቧራው በአፍና በአፍንጫዋ ሲገባ አስነጠሳት። እንደ ቢለዋ የሳለ ድንጋይ እግሯን ሲወጋት አነከሰች። እሾኋን ነቀልንላትና አዝግማ አርባያ ገባች። አርባያ ስንገባ መኪናችን አቧራዋን አራግፋ ገላዋን ልትታጠብ ፈለገች፤ ግን እንኳን ለእሷ ገላ መታጠቢያ ለከተማው ማህበረሰብ የሚጠጣ ውሃ የለም።
አርባያ የአሁኑ የምዕራብ በለሳ፣ የቀድሞዋ በለሳ ዋና ከተማ ስትሆን ከማክሰኝት 40 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች። (ምዕራብ በለሳ እና ምስራቅ በለሳ ተብሎ የተከፈለው በ1994 ዓ.ም ነው።)
አርባያ ከተማ መሀል አንድ ረዥም ሕንጻ ብቻውን ቁሞ ከርቀት ይታያል። አርባያ ስንደርስ በርቀት ያየነውን ህንጻ ማረፊያችን አደረግን። የሆቴሉ አስተናጋጆች ኢትዮጵያዊ ፈገግታ የተሞላበት አቀባበል አደረጉልን። የህንጻው ግቢ በተለያዩ ሐረጎችና አበቦች የተዋበ ነው። አልጋዎቹ ከታች ወደ ላይ በእያንዳዱ ፎቅ የ30 ብር ቅናሽ አላቸው። (ጉልበትን ታሳቢ ማድረጉ ልዩ ያደርገዋል።) ሂሳብ ስለሚቀንስልኝ አልጋዬን 4ኛ ፎቅ አደረኩ።
አራተኛ ፎቅ ላይ ከተማዋን ቁልቁል ስመለከት የወየቡ፣ የተጠረመሱ፣ የዘመሙ ዶሳሳ ቤቶች በነፋስ ይተራመሳሉ። ከእነዚህ የዘመሙ ደሳሳ ቤቶች መሀል ረዥም ሕንጻ መገንባቱ ሕልም ይመስላል። ከራሴ ጋር ማውራት ጀመርኩ፤ ‹‹ሕንጻውን የሚገነባው ሰው ምን ያህል ሀገር ወዳድ ቢሆን ነው፤ ይሄ ሆቴል ባይኖር እኛስ የት እናርፍ ነበር….›› የማይመለሱ ጥያቄዎችን ለራሴ አዥጎደጉዳለሁ።
ከፎቅ ወረድንና በረንዳ ላይ ተቀመጥን መጠጥ ቢጤ ያዝን።ጀግና የሚያወድሱ፣ ፈሪ የሚያንኳስሱ ሙዚቃዎች ከፍ ብለው መደመጥ ጀመሩ። የመክፈቻ ሙዚቃ ፋሲል ደመወዝ ‹‹ጎንድር›› ነው።
አርባያ በለሳ ያግድም ያግድም፣
አንጋዳው ክፉ ነው አያረማምድም!
እያለ ወልቃይት ጠገዴን፣ አርማጭሆን፣ ወገራን፣ ዳባትን፣ አዲስ ዘመንን፣ ወረታን፣ ፋርጣን፣ ጋይንትን፣ እስቴን፣ ስማዳን……. ጎንደርን በዜማ ይዞራታል።
አንዷ ወጣት ሴት ከፋሲል ሙዚቃ ጋር አንጎራጎረች፤ በአግራሞት ቀና ብየ ሳያት ‹‹አየኸኝሳ! ጀግንነት እኮ ባንጠለጠለ አይደለም›› አለችኝ። ‹‹ባንጠለጠለ አይደለም›› የሚለው አነጋገሯ አስገርሞት ባልደረባዬ በሳቅ ወደቀ።
አበቦችና ሐረጎች ከተንጣለለው ግቢ አጥር ላይ እየተሳቡ ንፋሱ በሙዚቃ እያዋዛ ሲያጫውታቸው እየተፈነከነኩ ንጹህ አየርን ለእኛ መለገስ ጀመሩ።
‹‹ደሴ ላይ ነው ቤቷ›› በሚለው ዜማ፣ “እስራኤል ነው ቤቷ (2)፣ የሚያምረው አንገቷ” ሲል አንዱ ድምጻዊ አንጎራጎረ። “አስራኤል ነው ቤቷ” በሚለው ሙዚቃ ተደምሜ ከራሴ ጋር ስሟገት ደረጄ ደገፋው ደግሞ “ዘርሽ እንዳይጠፋ ጎንደር ለዘላለም፣ ሐረግሽ ተስቦ ገባ እየሩሳሌም” ሲል ሙዚቃው በሙዚቃ ተመለሰልኝ።
በለሳዎችን ፍቅር እንጂ ጠብ አያሸንፋቸውም። ክብራቸው ሲነካ የጀግንነት ዛራቸው ይነሳባቸውና “አካኪ ዘራፍ” ይላሉ። በለሴዎች ተኩሰው ከሚስቱ ሞትን ይመርጣሉ። ለዚያ ነው “አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት፣ እያደር ይፈጃል እንደ እግር እሳት” ሲሉ የሚሸልሉት። ተኩስ ትምህርት ቤታቸው ነው። አንድ የበለሳ ወጣት ጎጆ ሲቀልስ ከበሬ እኩል ጠመንጃ ሊኖረው ይገባል።
ከአርባያ በስተምስራቅ በኩል 20 ኬሎ ሜትር ርቀት አሽከር ተራራ አካባቢ ከአንድ ወጣት ጋር ጨዋታ ጀምረናል። ወይብላ ማርያም፣ ማጫ እስጢፋኖስ፣ ከአለት ተፈልፍሎ የተሰራው ገዳም ወርቅአምባ ጊዮርጊስ….. ስላሉት ታሪካዊ መስህቦች፣ አጼ ልብነድንግልና ግራኝ አህመድ በለሳ እንዳረፉ አጫወተኝ።
ጨዋታችን እንዲህና እንዲያ እያለ ተኩስ ችሎታ ላይ ደረሰ። ‹‹አባቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢላማ ካለማመደኝ በኋላ አንዲት ወፍ ደረቷ ላይ ያለውን ጥቁር ምልክት እንድመታ ነገረኝ፤ አልሜ ተኩሼ አንገቷን በጠስኩት፤ እንድትመታው ያዘዝኩህን ምልክት አልመታህም ብሎ አባቴ ተቆጣኝ›› አለኝ።
መጠጡን በአበቦች መዓዛ እና በሙዚቃ እያማግን ስንበላ እንዱን ፍልቅልቅ ታዳጊ ‹‹ቄሴ›› ብለው ሲጠሩት ሰማን። በተደጋጋሚ ‹‹ቄሴ›› እያሉ ይጠሩታል፤ እኛም ለማረጋገጥ ‹‹ቄሴ›› ብለን ጠርተን ጭማሪ አልነው፤ ጣታችን ወደ ቢራ ጠርሙሳችን እየቀሰርን። ልጁ ገና ለአቅመ መታዘዝ የደረሰ አይመስልም። ፈጣኑ ቄሴ ወዲያውኑ እያብከነከነ አመጣው። ቄሴ አጠቃላይ ሁኔታው ያልተበረዘ የገጠር ልጅ ነው።
ስለ ቄሴ ፍጥነትና ቅልጥፍና ሳወጣ ሳወርድ እንደተቀመጥኩ ጋምቤላ ደረስኩ፤ ጋምቤላ አልጋ የያዝንበት አንድ ሰፊ ግቢ። ግቢው ከስፋቱ የተነሳ ነዳጅ ማደያ ይመስላል። ሆቴሉን በበላይነት የሚመራው ወጣት ‹‹ትንሹ›› ብሎ ሲጣራ ከ12 ዓመት የማይበልጥና የደስደስ ያለው ልጅ ፈጥኖ መጣ፤ ‹‹ትን……ሹ›› ብሎ ሲጠራው የልጁን ትልቅነት አሳይቶ ነው፤ በርግጥም ትንሹ ታዛዥና ትሁት ልጅ ነው። ቢራ ይታዘዛል፣ ጠርሙስ ይሰበስባል፤ አልጋ ያስይዛል፤ ለመኪና መቆሚያ ቦታ ያመቻቻል፡ትንሹ ከደራ ሐሙሲት ነው ከአንድ አሽከርካሪ ጋር ወደ ጋምቤላ ሄዶ ለምዶ የቀረው። እድሜያቸው፣ ትህትናቸው፣ ፍጥነታቸው፣ ፍልቅልቅነታቸው፣ ገራገርነታቸው፣ የዋህነታቸው….‹‹ትንሹ እና ቄሴ›› ብዙ ነገራቸው ይመሳሰላል። ገና በለጋነታቸው ከስራ ጋር ተቆራኝተዋል። ሁለቱም የማደግ እና የሚንቦገቦግ ተስፋ ከፊታቸው ላይ ይነበባል። እነዚህ ሁለት እንቡጦች ናፍቀውኛል።
ለምን ቄሴ እንደተባለ ጠየቅነው። የቆሎ ተማሪ ነበር፤ አንድ ቀን በእንተማርያም…..ብሎ በሩ ላይ ሲቆም ፍልቅልቅነቱ የማረካቸው የሆቴሉ ባለቤት ከሆቴሉ እየሰራ ይማር ዘንድ ሲጠይቁት ይስማማል። ትምህርቱ የሰኞን ጸሎት ጨርሶ ወደ ማክሰኞ መግባቱን ሲናገራቸው ‹‹ቄሴ›› ብለንሀል አሉት።
ቄሴ የማይሰራው የለውም፤ እስከሚታዘዝ አይጠብቅም። የእቃ ዕጣቢ መድፋት፣ ውሃ መቅዳት (ከመኪና ማውረድ)፣ ቢራ መታዘዝ፣ የቢራ ሳጥንና ጠርሙስ መሰብሰብ፣ የእንጀራ መጋገሪያ ማገዶ ማቅረብ፣ የወንበሮችን ልብስ ማልበስ፣ ቆርኪ መድፋት እና ሌሎች ስራዎችን አስቦ በየእለቱ ያከናውናል። ትጉህነቱ ከአንድ ‹‹እንቁ ኢትዮጵያዊ›› ተጋብቶበት መሆኑን ነገረን። ታዳጊው ሰውየውን የገለጸበት ሁኔታ ማረከኝና አፈላልጌ አናግረው ዘንድ ሕሌናዬ አስገደደኝ።
እናም፤ ይህን ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ በአካል አግኝቻቸው ተገልጦ የማያልቅና ጣፋጭ የህይወት ተሞክሯቸውን አጫውተውኛል። በርግጥም ግብረገብነታቸው፣ ጨዋነታቸው፣ ታታሪነታቸው፣ ቁርጠኝነታቸው፣ ለሀገር ተቆርቋሪነታቸው፣ ትሁትነታቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸው፣……..ሁለንተናቸው ይህን ሰው ‹‹እንቁ ኢትዮጵያዊ›› ያሰኛቸዋል። ከአንደበታቸው የሚፈልቁ ቃላት ከማር ከወተት ይጥማሉ፤ አይጠገቡም። የድምጽ መቅረጫዬ 72 ደቂቃ የፈጀውን ቃለመጠየቅ እየቀዳች ጠጣችው፤ እያጣጣመች። ብዕሬም የዚህን እንቁ ኢትዮጵያዊ ቃላት ስትከትብ በደስታ ተፍነከነከች። ታዲያ እኒህ እንቁ ኢትዮጵያዊ ማን ናቸው?
አማረ ዓለሙ ይባላሉ። በቀድሞው በለሳ ወረዳ (አሁን ምዕራብ በለሳ) ማጫ አቡነ እስጢፋኖስ፣ አዲስ ዓለም ቀበሌ ነው ተወልደው ያደጉት። እስከ 6ኛ ክፍል እዚያው በለሳ ተምረዋል። ከ1970 በፊት በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ትምህርት ብዙ መግፋት ስላላስቻላቸው ወደ እርሻ ተሰማሩ።
በህይወታቸው ላይ ትልቅ አሻራ ስላሳረፈች ከበለሳ ወደ ጎንደር የሄዱባት ቀን አዕምሯቸው ላይ ታትማለች፤ ታህሣሥ 29 ቀን 1979። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ልማትና የክርስቲያን ተራድኦ “world vision Ethiopia” ድጋፍ፣ ቀን የተለያዩ የሙያ ዕደ ጥበብ፣ ማታ ደግሞ ትምህርታቸውን ተማሩ። ለ9 ወር በተሰጠው የተግባረ ዕድ ስልጠና ከ80 ሰልጣኞች 1ኛ ሆነው ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው በጀርመን ተራድኦ ድርጅት አማካኝነት ሰላሌ አውራጃ ሂደው አሰልጣኝ ሆኑ። ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ሲቆጣጠር ወደ ጎንደር መጥተው 347 ብር መነሻ ይዘው በ1983 ዓ.ም ወደ ንግዱ ዓለም ተቀላቀሉ።
የቤተክህነት ትምህርትም ቀስመዋል። መንፈሳዊ ትጥቅ ታጥቀው ከቤተክርስቲያን ከወጡ በኋላ ራሳቸውን ከመቻል አልፈው በሺዎች ለሚቆጠሩ የተማሩና ያልተማሩ ዜጎች የስራ ዕድል ስለፈጠሩላቸው እና መንፈሳዊ እና ልማታዊ ስራ በአንድ በማከናወናቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ‹‹ሊቀ አዕምሮ አማረ ዓለሙ›› የሚል ማዕረግ እንካችሁ አለቻቸው። እሰየው ይገባቸዋል።
በእርግጥም ሊቀ አዕምሮ አማረ ዓለሙ ያልተሳተፉበት ዘርፍ አለ ለማለት አያስደፍርም። በግብርና፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በትምህርት፣ በሆቴልና ቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪ፣ በንግድ፣ በትራንስፖርት፣ በኢንቨስትመንት፣ በበጎ አድራጎት፣ በሰላምና ጸጥታ ዘርፍ….በሁሉም መስመር ተጠምደዋል።
የበለሳ ሁለንተናዊ ጉዳይ እንደ እግር እሳት ያንገበግባቸው ሊቀ አዕምሮ አማረ በአዲስ አበባ እና በውጭ ሀገራት ሰርተው ያፈሩትን ንብረት ፈሰስ አድርገው እየሰሩ ነው። አንገት የተሰራው አዙሮ ለማየት ነው እንዲሉ ያደጉበትን የበለሳን ሕዝብ ለመደገፍ የተደላደለ ኑሯቸውን ትተው ከከተማ ወደ ገጠር ዘምተው የልማት አርበኛ ሆነዋል።
የሰው ልጅ ከፈጣሪ በተሰጠው አካል ሊሰራበት እንደሚገባ ይህን ይመክራሉ። ‹‹አፋችን መልካም እንድንናገርበት፣ እግራችን ወደ ጥሩ መንገድ እንድንራመድበት፣ እጃችን እንድንጨብጥበት፣ ዓይናችን ጥሩ ነገር እንድናይበት፤ በአጠቃላይ ጥሩ ነገር ሰርተን እንድናልፍ ነው የተፈጠርነው።››
አርቆ አሳቢው ሊቀ አዕምሮ አማረ፣ ‹‹ኢትዮጵያን የሚያስፈልጋት ረዥም ተራማጅ እግር፣ አሻግሮ የሚያይ ዓይን፣ አርቆ የሚያስብ አዕምሮ ነው።›› ይላሉ።
‹‹ሀገር የሚለማው፣ የለማ አዕምሮ ሲፈጠር ነው›› የሚሉት እኒህ እንቁ ኢትዮጵያዊ፣ የሰውን አዕምሮ አስተሳሰብ በመቀየር ላይ ናቸው። ማህበረሰቡን ለማስተማር ሳር የማያበቅል አሲዳማ እና የተራቆተ መሬት ጠየቁ፤ ተሰጣቸውም። ቦታውን በ17 ሺህ ያህል ቆርቆሮ አጥረው አፈር ማከም ጀመሩ። የወንዙን ውሃ በሞተር እየሳቡ በመቶ ሺህ የሚቆጠር አትክልትና ፍራፍሬ አለሙበት። ስኳር ድንች፣ ሽንኩርት፣ ድንች፣ ቃሪያ፣ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ፣ በርበሬ በማልማት ከሆቴሉ አገልግሎት አልፎ የአርባያ ነዋሪ አትክልት የመመገብ ልምድ እንዲዳብር በተመጣጣኝ ዋጋ ያቀርቡለታል። ሙዝ፣ ብርቱካን፣ አፕል፣ አቮካዶ፣ማንጎ፣ ፓፓዬ፣ ጌሾ፣ ቡና…..እንዲሁም ዝግባ፣ ሾላ፣ ዋንዛ፣ የጠመንጃ ዛፍ፣ ችብሃ በማልማት ተፈጥሮን ለመመለስና ለማደስ ይታገላሉ። እዚያው ንብ ያንባሉ። ዕፅዋት በማግኘታቸው ወፎች ይዘምራሉ። ሊቀ አዕምሮን በመዝሙራቸው እያወደሱ ይገኛሉ።
አንድ ስራ ተመጋጋቢ መሆን አለበት ይላሉ ሊቀ አዕምሮ አማረ። የእርሻውን ተረፈ ምርት ለእንስሳቱ፣ የእንስሳቱን ተረፈ ምርት ደግሞ ለእርሻው በማዳበሪያነት እንዲውል አድርገውታል።
ያስገነቡት የእንስሳት ማድለቢያ እጅግ ዘመናዊ ነው።ከእስራኤል ሀገር ነው ተሞክረውን ያመጡት። በፌዴራልም ሆነ በክልል እንዲህ ዓይነት ዘመናዊ የተቀናጀ ትልቅ ማድለቢያ ያለ አይመስለኝም። ከማድለብ ባሻገር ለወተት ሀብት ልማት፣ ዶሮ፣ ፍየል፣ በግ እርባታ ታሳቢ ተደርጎ የተሰራ ነው። እንዴት እንደሚያደልብ ለገበሬው አሳይተው ያደለበውን በጥሩ ዋጋ ይረከቡታል።
እያንዳዱን ስራ በባለሙያ ያስመራሉ። የሰው ጤና የሚጠበቀው የእንስሳት ጤና ሲጠበቅ ነው የሚሉት ሊቀ አዕምሮ አማረ እንስሳቱ በየጊዜው ክብደታቸው፣ ሙቀታቸውና አጠቃላይ ጤንነታቸውን የሚከታተሉ ዶክተሮች (ሀኪሞች) ቀጥረዋል። የአካባቢውን ስነ ምህዳር በባለሙያ አስጠንተነዋል፣ ለእንስሳቱ ምቹ ስለመሆኑ ውሃውን እስራኤል አገር ልከው አስመርምረውታል። ከመቶ በላይ በሬዎች እያደለቡ ነው። ከሺህ በላይ በሬዎችን ማድለብ የቅርብ ጊዜ እቅዳቸው ነው። በተጨማሪም አሳ ለማምረት እና ለማህበረሰቡ መዝናኛ የሚሆን ተፈጥሯዊ ባህር ለመስራት ውሃ ለመሙላት ቋጥኝ እያስፈለፈሉ ይገኛሉ።
ዕጽዋትን ለመታደግ ብሎም አካባቢ ጥበቃ ላይ አዳዲስ ስልቶችን እየቀየሱ ስለመሆናቸው እንዲህ ይላሉ። ‹‹ሰው ሲኖር መሰረታዊ ነገሮች ያስፈልገዋል፤ የሰው ልጅ ምግቡን ለማብሰል ዛፍ ሲቆርጥ አትቁረጥ ቢሉት አይሰማም፤ ሌላ አማራጭ ማቅረብ ያስፈልጋል።››
በመሆኑም የከብቶችን ተረፈምርትና እበት ሌላ አዲስ ቴክኖሎጂ በመጨመር ከሰልንና እንጨትን የሚተካ ኩበት(ጥፍጥፍ) ለህብረተሰቡ በቅናሽ ዋጋ በማቅረብ ዛፎች እንዳይቆረጡ እያደረጉ ይገኛሉ።
‹‹ለአንድ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልገው ውሃ፣ መሬት፣ የሰው ጉልበትና ሰላም ነው። አንድ ኢንቨስትመንት ውጤታማ የማይሆነው ከህብረተሰቡ ስለማይጀምር ነው። መጀመሪያ አካባቢውን የሚጠቅም ነገር ሰርቶ ማህበረሰቡን ማስለመድ ያስፈልጋል።›› ይላሉ ሊቀ አዕምሮ። እናም ትምህርት ቤት፣ የቀበሌ አዳራሽ፣ መንፈሳዊ ተቋም ሰርተዋል።
ለትምህርት ካላቸው ቁጭት የተነሳ ጎንደር ከተማ ‹‹ትውልድ አማረ›› የተባለ የግል ትምህርት ቤት ከፍተው ለማህበረሰቡ ጥራት ያለው ትምህርት ተደራሽ እያደረጉ ነው።
በ1983 ዓ.ም በ347 ብር የወጠኑት ንግድ ዛሬ ላይ ሀብታቸው ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። ቢሊየነር መሆኑን ብቻውን በቂ አይደለም የሚሉት ሊቀ አዕምሮ አለሙ ‹‹ሀብት የሚባለው ከባንክ ቤት የተቆጠረ ገንዘብ አይደለም፤ ለማህበረሰቡ የሰጠው አገልግሎትና የፈጠረው የስራ ዕድል ሲሰላ ነው›› ይላሉ። በግብርና፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ከብት በማድለብ፣ በትምህርት፣ በንግድ፣ በሆቴል፣ በሱቅ እና በሌሎች ዘርፎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የስራ ዕድል ፈጥረዋል።ያም ሆኖ ‹‹ይህን በመስራት ትልቅ አያሰኘኝም፤ ገና ብዙ መስራት ይጠበቅብኛል›› ይላሉ ሰውየው። በርግጥም ከቱጃርነታቸው የበለጠ ትህትናቸው፣ ታታሪነታቸው፣ ቁርጠኝነታቸው፣ አርቆ አሳቢነታቸው እና መንፈሳዊ ጥንካሬያቸው ያጓጓል።
ባለሀብት፣ የተማረ ወይም የከተማ ሰው ወደታች ወርዶ አይሰራም ብለው ለሚያስቡ እኝህ ሰው ናሙና ናቸው። ማለዳ ለሆቴሉ ውሃ በመኪናቸው ይቀዳሉ፤ ቀን በዶማና በአካፋ አፈር ይቆፍራሉ። ሊቀ አዕምሮ ሁሌም ባተሌ ናቸው፤ ለእንቅልፍ ጊዜ የላቸውም። እንኳን ቢሊየነር ሆነው ሁለት እና ሶሰት መቶ ሺህ ብር ያላቸው ባለሀብቶች አፈርንና ጭቃን ይጸየፋሉ፣ የድንቁርና ምልክትም ይመስላለቸዋል። ከግብርናው ዓለም እየራቁ፣ ግብርናን እየናቁ መጨረሻ ላይ ገጠር መፈጠራቸውን ይዘነጋሉ።
ስጋ በዘመናዊ ቄራ እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ በማቀነባበር ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማምጣት እየሰሩ ነው። ዶሴ ይዤ በየቢሮው ባለው ቢሮካራሲ እንዳልንከራተት መንግስት ቢያግዘኝ በጣናና በአባይ ተፋሰስ ዙሪያ በግብርናው ዘርፍ በሰፊው ለመስራት አቅድ አለኝ ይላሉ።
ጠላታችን የሆነው ድህነትን ቂም ይዘውበታል። ‹‹የየትኛውም ፖለቲካ አባል አይደለሁም፤ የኔ ፖለቲካ ከድህነት ጋር ጦርነት መግጠም ነው።›› በማለት ድህነትን ለማስወገድ በለሳ ላይ እንደዘመቱ ይናገራሉ።
ማህበረሰቡ ዛሬም እንደ ድሮው በጦር መሳሪያ መመካቱ ያሳሰባላቸው ሊቀ አዕምሮ አማረ ‹‹በለሳ አሁንም የእርስ በእርስ ግዲያ አለ፤ እጁ ከመሳሪያ፣ ጣቱ ከምላጭ አልወጣም። ሀገራችን ለማልማት የሚያስፈልገው ጦር መሳሪያ የያዘ ሰራዊት ሳይሆን ዶማ እና አካፋ የያዘና መሬትን ወደ ገነት የሚቀይር ነው።›› ሰላም ከሌለ የቆረስነውን አንጎርስም፣ የጎረስነውን አንውጠውም የሚሉት ይህ እንቁ ኢትዮጵያዊ ወንጀልን ለማጥፋት ከፖሊስ፣ ከጸጥታ፣ ከፍትህ፣ ከአቃቢ ህግ፣ ከፍርድ ቤት፣ ከአስተዳደር የተውጣጡ ደም አድራቂ ሽማግሌዎች ለማቋቋም የራሳቸው ደመወዝ፣ ቢሮ እና ተሽከርካሪ በመመደብ የወንጀል ቅድመ መከላከል ስራ ለመስራት እያመቻቹ ነው። በመሆኑም ይህ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ልጅ፣ የተንኮልን ግንብ እየናዱ የአብሮነትን ገመድ እየገመዱ ይገኛሉ።
ሊቀ አዕምሮ አማረ የአብራካቸው ክፋይ የሆኑ ሊቀ አዕምሮዎችን አፍርተዋል። በዚህም ‹‹ከኢንቨስትመንቴ የበለጠ በልጆቼ ተሳክቶልኛል። በትምህርታቸው የጎበዙ፣ በጎ የሚያስቡ፣ የማይዋሹ፣ የማይቀጥፉ፣ የማይሰርቁ፣ በስነ ምግባር የታነጹ ልጆች ፈጥሪያለሁ›› ይላሉ።
ከምንም በላይ ሰውን መቅረጽ ይበልጣል የሚል ፍልስፍና ያላቸው ሊቀ አዕምሮ አራት ልጆች ያሏቸው ሲሆን አንዷ ዶክተር፣ አንዱ ኢንጂነር፣ ሁለት ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ናቸው።
ይህ እንቁ ኢትዮጵያዊ፣ ከስጋ ልጆቻቸው ባሻገር እንደ ልጆቻቸው ተንከባክበው በቋሚነት የሚያስተምሯው 104 ተማሪዎች አሉ። (86 በ1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣18 በዩኒቨርስቲዎች)። ሊቀ አዕምሮ አማረ፣ “የሰው መጀመሪያ ሀብቱ ጉልበቱ ነው፤ ከመሞቱ በፊት ጉልበቱን ወደ ስራ መመንዘር አለበት” በማለት ይመክራሉ። አክለውም “ሰው ለምን ይቀመጣል፤ ድንጋይ አይደለ አይከሰከስ፣ ለኩረት ወይም ለግንብ አይሆንም፣ በሕይወት እያለ ትውልድ የሚቀባበለው የስራ ሐውልት መስራት ይኖርበታል።›› ይላሉ።
ትውልዱ አስተሳሰቡ ካልዳበረና ጉልበቱን ካልሰራበት በተደጋጋሚ እየሞተ መሆኑን እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ። ‹‹አንድ ጊዜ መሞት ተፈጥሯዊ ነው፤ ዳሩ ግን አንድ ሰው በየቀኑ መሞት የለበትም”።…..›› ለዚህ ደግሞ ሰው ከራሱ መታረቅ ይኖርበታል፤ ከሰው ጋር የተጣላን ሰው፣ ሰው ወይም ሕግ ያስታርቀዋል። ከራሱ ጋር የተጣላን ሰው ማን ያስታርቀዋል?››
በመጨረሻም፣ ይህ እንቁ ኢትዮጵያዊ ለማመን የሚከብድ ንግግር እንዲህ ሲሉ ተናገሩ። ‹‹ሰው የተቋጠረ አፈር ነው፤ መቼ እንደሚፈርስ አይታወቅም። ሞት ያልተከፈለ ዕዳ ነው። እኔም እዳዬን መቼ እንደምከፍል አላወቅም፤ ሰው ይሞታል፤ ሕይወት ግን ይቀጥላል። ልጆቼን ሳሳድጋቸው የአዕምሮ ዕውቀት ነው የማስታጥቃቸው፤ በየትኛውም ዓለም ካሉ ተቋማት እንደፍላጎታቸው አስተምራቸዋለሁ ነገር ግን ሀብቴን ለልጆቼ አላወርሳቸውም፤ ውርስ ደካማ ያደርጋል። ልጆቼ ከፈለጉ እንደማንኛውም ሰራተኛ (ደመወዝተኛ) ሆነው በድርጅቶቼ መስራት ይችላሉ፤ መጨረሻ ላይ ሀብትና ንብረቴን ለሀገሬ ነው የማወርሰው፤ ልጆቼም አምነውበታል።” እንቁ ኢትዮጵያዊ ይሏል እንዲህ ነው።
ስንቶቻችን ላሳደገን ማህበረሰብ ውለታውን እየከፈልን ይሆን? እራሳችንን እንጠይቅ።
ልጆቹስ ቢሆኑ የሰው ልጅ በውርስ እየተናቆረ ባለበት ዘመን፣ አባታቸው ሀብትና ንብረቱን ለሕዝብ አወርሳለሁ ሲል መስማማታቸው [እንቁ ኢትዮጵያዊያን] አያሰኛቸውምን?
ቸር ያሰማንማ!
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
ባህሩ ሰጠኝ (የኮሙዩንኬሽን ባለሙያ)