ኢትዮጵያ ከተወዳጁ አፍሪካ ዋንጫ ሦስት መሥራች ሀገራት አንዷ ብቻ ሳትሆን ውድድሩን ሦስት ጊዜ በማስተናገድም ታሪክ አላት፡፡ በዚህ ታላቅ መድረክ አንድ ጊዜም ቢሆን ድል ያጣጣመች ሀገርም ናት፡፡ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ)ን በፕሬዚዳንትነት በመምራት ‹‹የአፍሪካ ስፖርት አባት›› በሚል የሚታወቁትን ይድነቃቸው ተሰማን የመሳሰሉ በአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ ዐሻራ ያሳረፉ የስፖርት አመራሮችንም አፍርታለች፡፡
በአፍሪካ እግር ኳስ ላይ ትልቅ የታሪክ ዐሻራ ያሳረፈችው የኢትዮጵያ እግር ኳስ በጀመረበት ፈር ቀዳጅ መንገድ ለመቀጠል ተስኗታል፡፡ በተለይም ባለፉት አራት አስርተ ዓመታት ገደማ እግር ኳሳ ቁልቁል እንጂ ሽቅብ መሄድ አቅቶት በመሠረተችው አህጉራዊ የውድድር መድረክ ለመሳተፍ እንኳን ከሦስት አስርተ ዓመታት በላይ ሲፈጅባትና የበዪ ተመልካች ስትሆን ተመልክተናል።
እግር ኳሱ እንዲህ ተስፋው በሰለለበት ወቅት መንግሥት የአህጉሪቱን ትልቅ የስፖርት መድረክ የአፍሪካ ዋንጫን ከአምስት ዓመት በኋላ እኤአ በ2029 ለማዘጋጀት ሰሞኑን ለካፍ በይፋ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል።
ካፍ 46ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ባለፈው ሰኞ አዲስ አበባ ላይ ባደረገበት ወቅትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የካፍና የፊፋ ፕሬዚዳንቶችን ጨምሮ በጉባዔው ለመታደም ለመጡ ልዑካን እየተገነባ የሚገኘውን ብሔራዊ ስቴድየም አስጎብኝተዋል። በቤተመንግሥት በነበረው የእራት ግብዣ ላይም ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ የማዘጋጀት አቅም እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴም በካፍ ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት አግቶ እንዲፀድቅ ጥሪ አቅርበዋል። ይህንንም ተከትሎ የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሙሴፔ የኢትዮጵያ ጥያቄ ካፍ ባለው የአሠራር ሥርዓት እንደሚታይ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ የማስተናገድ ጥያቄዋን ያቀረበችው በትክክለኛው ጊዜ መሆኑንም ገልፀዋል። ያም ሆኖ ጥያቄው ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱ በቀጣይ ዓመት ካፍ ሞሮኮ ላይ በሚያደርገው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ይወሰናል።
ኢትዮጵያ ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት ለካፍ ገና በይፋ ጥያቄ ከማቅረቧ አስቀድሞ ብዙዎች አልተዋጠላቸውም። ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስቴድየም አጥቶ ባለፉት አራት ዓመታት ገደማ ውድድሮችን በሌሎች ሀገራት ለማድረግ መገደዱ አንዱ ምክንያት ነው። ይህ ችግር ወይም ጥያቄ ባልተመለሰበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ መነሳቷ እንደ እብደት ተቆጥሯል። የማይመስልና የማይቻል ነው ብለው የሚያምኑም ጥቂት አይደሉም።
እርግጥ ነው ትንሹን ችግር መቅረፍ ሳይቻል ሌላ ትልቅ ነገር ለማሳካት ማሰብ ለብዙዎች አሳማኝ ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከሃምሳ ሦስት ዓመት በኋላ ትልቁን አህጉራዊ ውድድር ለማሰናዳት ማሰቧ በራሱ ለስፖርቱ ትልቅ ርምጃ ነው። ደግሞም የማይቻልና ቅንጦት የሆነ ህልም አይደለም።
አዎ፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ከአምስት ዓመት በኋላ ማስተናገድ ትችላለች። ለዚህም የሚሆን አቅም አላት። መንግሥት በዚህ ደረጃ “ይቻላል” ብሎ በቁርጠኝነት መነሳቱ ዋናው ጉዳይ ነው። ቀጥሎ እንዴት? የሚለውን መጠየቅ ተገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ በቂ መልስ አለው።
ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ ከተሞች ግዙፍ ስቴድየሞችን ጀምራ ማጠናቀቅ አልቻለችም። አሁን የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ስትነሳ ግን እነዚህ ጅምር ስቴድየሞች ትልቅ አቅም እንደሚሆኗት አያከራክርም። ይህ ማለት ኢትዮጵያ በቀሪዎቹ ዓመታት የአፍሪካ ዋንጫውን ለማዘጋጀት ከዜሮ አትነሳም። የተጀመሩትን ስቴድየሞች ማጠናቀቅ ነው የሚጠበቅባት። ይህ ደግሞ ከገንዘብም ከጊዜም አኳያ ትልቅ ሚና አለው።
የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ አንድ ሀገር ሁለት 40ሺ፣ ሁለት 20ሺና ሁለት 15ሺ ተመልካች የሚይዙ ስቴድየሞችን እንዲሁም ደረጃቸውን የጠበቁ ከ12 በላይ የልምምድ ሜዳዎችን ማዘጋጀት በቂ ነው። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ በየከተሞቹ የተጀመሩ ስቴድየሞች መስፈርት አሟልተው እንዲጠናቀቁ ከማድረግ ውጭ ተጨማሪ የምትገነባው ትልቅ ፕሮጀክት አይኖርም።
እዚህ ጋር የብዙዎች ጥያቄና ስጋት ስቴድየሞቹ በጥራትና በጊዜ አይጠናቀቁም የሚል ነው። መንግሥት አሁን ካሳየው ቁርጠኝነት ወደ ኋላ ካላለ ልክ እንደኮሪደር ልማቱ ሌት ከቀን በትኩረት ከሠራ ይህም የማይቻል አይደለም። ለዚህም ፕሮጀክቶች ዝም ብሎ በዘፈቀደ መንገድ ሳይሆን በሙያው እውቀቱና ልምዱ ባላቸው ሰዎች እንዲመሩ ማድረግ ይጠበቅበታል። በዚህ ረገድ ከካፍ ጋር በቅርበት መሥራት ያስፈልጋል።
ባለፉት ዓመታት በርካታ ሀገራት የአፍሪካ ዋንጫን የማዘጋጀት እድል አግኝተው ዝግጅታቸው ከጊዜና ከጥራት አኳያ ተፈትሾ መጨረሻ ላይ እድሉን ሲነጠቁ ታዝበናል። የእኛም ተመሳሳይ እጣፋንታ እንዳይገጥመን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል። እንዲህ አይነት ችግሮች ቢገጥሙ ለሀገር ኪሳራና አንገት የሚያስደፋ ቢሆንም በሌላ መልኩ ይዞት የሚመጣ መልካም አጋጣሚ እንዳለም ማሰብ ይቻላል።
ለአፍሪካ ዋንጫው ሲባል ቆመው የነበሩ ስቴድየሞች አንድ ርምጃ መጓዛቸው እንዳለ ሆኖ፣ የሚዘጋጁ የመለማመጃ ሜዳዎችና ሌሎች መሠረተ ልማቶች የስፖርት ቤተሰቡን የዓመታት ጥያቄ ይፈታሉ። ይህም በዘላቂነት ከእግር ኳሱ በተጨማሪ በሌሎች ስፖርቶች ታዳጊዎችን በብዛት ለማፍራትና ለማነቃቃት ትልቅ ጥቅም አለው። ሀገራት ውድድሮችን ሲያዘጋጁ ከዝግጅታቸው በኋላ እነዚህን እድሎች እንደሚያገኙ ታሳቢ አድርገውም ነው።
በርካቶቹ ስቴድየሞች የሚገኙባቸው ከተሞች ከአውሮፕላን ማረፊያና ደረጃቸውን ከጠበቁ ሆቴሎች ጋር በተያያዘ ጥያቄ የሚነሳባቸው አይደሉም። ይህም አንድ ትልቅ እድል ነውና የሚናቅ አይደለም።
ካፍ እድሉን ሲሰጥ የመሠረተ ልማት መሟላትን ብቻ እንደማይመለከት ግልፅ ነው። የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት መሠረተ ልማት ከማሟላት አኳያ ኢትዮጵያ አቅሙ እንዳላት ሁሉ በቀሩት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ያለውን ሰላም ማረጋገጥ የግድ መሆኑን ማስታወስ ተገቢ ነው።
እነዚህን የቤት ሥራዎች ከተወጣን በኋላ አንድ ትልቅ ጥያቄ መመለስም ግድ ይለናል። ይህም ነገሩ ባዶ ቤት ድግስ መጋበዝ እንዳይሆን ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት ጉዳይ ነው። ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአፍሪካ ዋንጫን ማዘጋጀት ብቻ በቂ አይደለም። ከአንዴም ሦስቴ አዘጋጅተን አይተናል። ብሔራዊ ቡድኑ በተንኮታኮተበት ወቅት እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ ሳይቆርጥ ውጤት እንደሚጠብቅ ይታወቃል። በገዛ ሀገሩ ላይ በሚዘጋጅ የአፍሪካ ዋንጫ ደግሞ ይህ ጉጉቱ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ስለዚህ በቀሪ ዓመታት ዋንጫ የሚያነሳ ወይም ግማሽ ፍፃሜ የሚደርስ ቡድን መገንባት ከባድ ቢሆን እንኳን ቢያንስ እስከ ሩብ ፍፃሜ ጥሩ ፉክክር የሚያደርግ ቡድን የመገንባቱን ነገር የሚመለከታቸው አካላት ትልቅ የቤት ሥራ ሊሆን ይገባል።
ልዑል ከካምቦሎጆ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም