የኮሪደር ልማቱ እና ተጨባጭ ትሩፋቶቹ

አዲስ አበባ የዓለም ሦስተኛ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን በተጨባጭ የሚያረጋግጡ አሻራዎችን በሁሉም ረገድ ማኖሯን እንደቀጠለች ነው። የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ከመሆኗም ባሻገር የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ የሆነችው መዲናዋ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፋዊ ውሳኔዎች የሚተላለፉባት፤የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል ሆናም እያገለገለች ትገኛለች። የባለ ብዙ የትብብር መድረክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቅርንጫፍ መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ የዓለም የዲፕሎማቲክ ልዑካን መሰብሰቢያና መኖሪያም ጭምር ነች።

ከምስረታዋ ጊዜ አንስቶ ከተማዋ፤ በአዝጋሚ የለውጥ ሂደት አልፋ አሁን ወደምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ ደርሳለች። በወርሀ መጋቢት 2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ወሳኝ የገፅታ ግንባታና ፈጣን ‹‹የስማርት ሲቲ›› የለውጥ ተግባራትን በጊዜ የለንም መንፈስ እያከናወነች ትገኛለች፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃም ሆነ በርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ፤ ለዘመናት የልማት ሥራዎችን በሚፈለገው ፍጥነትና ጊዜ ጀምሮ መጨረስ አዳጋች ነበር። አዳዲስ የልማት ሥራዎችን ደረጃ በደረጃ መጀመርን ጨምሮ ቅንጅታዊ የፕሮጀክት አመራር ውስንነት በጉልህ ይስተዋልም ነበር። ከዚያም አልፎ በየአካባቢው የብሶትና የህዝባዊ ቁጣም ምንጭ መሆኑ የቅርብ ግዜ ትዝታ ነው።

የፕሮጀክቶች አመራር ክፍተት፣ ብክነትና ምዝበራ በተደጋጋሚ ከማጋጠሙ የተነሳ፤ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎችና ምሁራን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት ተደጋጋሚ ወቀሳ ይሰነዘር እንደነበር የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው። ለዚህም የዓባይ ግድብን ጨምሮ፤ ሌሎችም ወሳኝ ሀገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች የገጠማቸው ችግርና በዋቢነት ማንሳት ይቻላል፡፡

ለዚህ ነው የለውጡ አመራር ከላይ ያነሳሁትን ጉልህ ችግር ሊያሻሽል የሚያስችል ስር ነቀል ለውጥ ለማድረግ የተገደደው። በተለይ ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስን ማእከል ያደረጉ መሻሻሎች መታየት መጀመራቸው የነበረውን ጉድለት በጉልህ ያመላከተ ሆኗል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከተደረገው የመንግሥት ለውጥ ወዲህ፤ የነዋሪውን ሁለተናዊ የልማት ተጠቃሚነትን ጨምሮ በምርጫ ወቅት ለህዝቡ የገባቸውን ቃሎች ደረጃ በደረጃ በተግባር ለመፈጸም እንዲያስችለው ዘርፈ ብዙ የከተማ ልማት ዕቅዶችን ፤ግዜ ወስዶና በጥናት ለይቶ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

በሁለንተናዊ መልኩ ከተማዋ ወደ ፈጣን የለውጥ ሂደት እንድትገባ ለማስቻል እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም እርምጃዎችን ተከተሎ በርካታ ወሳኝ የልማት ስራዎች ባልተለመደ መልኩ በተጨባጭ መታየት ጀምረዋል። በአንድ የምርጫ ዘመን ቀርቶ ፤ በተያዘላቸው የግዜ ሰሌዳ ተፈጽመው የማያውቁ የልማት ሥራዎች ከለውጡ በኋላ ከ60ና 90 ቀናት ባጠረ ግዜ ተፈጽመው፤ ለታለመላቸው ህዝባዊ አገልግሎት ክፍት ማድረግ እየተለመደ መጥቷል።

የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት፡ ገጽታና ደረጃ በሚፈለገው ልክ ማሻሻል እንዲቻል በሁሉም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ የስማርት ሲቲ የከተማ ልማት የሪፎርም ተግባራት ፤በጥብቅ የፕሮጀክት አመራር ስነ ምግባር እየተመሩ ነው። ከወትሮ በተለየ መንገድ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የስማርት ሲቲ የከተማ ልማት ተግባራት፤ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ጨምሮ የሌሎች ሀገራትን የከተማ ልማት ልምድና ተሞክሮ ከከተማዋ አሁናዊ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማጣጣም የሚተገበሩ ናቸው።

የልማት እቅዶቹ በሰው ተኮር የልማት መርህ የነዋሪዎችን ደህንነት በጠበቀ መልኩ የሚከናወኑ መሆናቸው፣ ከፕሮጀክቶቹ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆንበትን እድል እየፈጠረ ነው። የኮሪደር ልማቱ “ሰውነትን በሚያስቀድም መርህ“ የሚከናወን መሆኑም ለዚህ ተጨባጭ ማሳያ ነው።

ቀደም ባለው ወቅት ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ የኮሪደር ልማት ስራዎች፣ አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ ዓለም አቀፍ የኮንፈረንስ ማዕከላት (ማሻሻያ የተደረገባቸውን ጨምሮ) እንደ አዲስ ተገንብተው ለህዝባዊ አገልግሎት ክፍት በመደረግ ላይ ያሉ የጤና መሰረተ-ልማቶች ፣ የኢንቨስትመንት እና ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በአጠቃላይ በከተማዋ የስማርት ሲቲ የከተማ ልማት ፕሮግራም ማሕቀፍ ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው።

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማዋ ተግባራዊ እየተደረጉ ያሉ የከተማ ልማት ዕቅዶች አሁናዊ አፈጻጸም፤ ጀምሮ በጥብቅ ስነምግባር ተቀናጅቶ የመጨረስን አዲሰ የፕሮጀክት አመራር ልምድ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያስተዋወቀ ያለ ነው። በሁሉም ረገድ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች በይበልጥ በግዜ የለንም መንፈስ ተጠናክረው የሚቀጥሉ ስለመሆናቸው በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ ሲነገር ተደምጧል።

ለዚህም ተጨባጭ ማሳያ የሚሆነው፣ በአንድ የምርጫ ዘመን እንኳን በተያዘላቸው የግዜ ሰሌዳ ተፈጽመው የማያውቁ የልማት ሥራዎች ከስልሳና ዘጠና ቀናት ባጠረ ግዜ፤ ተጠናቀው ለታለመላቸው ህዝባዊ አገልግሎት ክፍት መደረግ የመቻላቸው ጉዳይ ነው። ለአብነት ያክል በከተማ አስተዳደሩ በተከታታይ ዓመታት ተገንብተው ለአገልግሎት ብቁ የተደረጉ ወደ 30 ሺ ገደማ ልዩ ልዩ የልማት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው፤የነዋሪውን የኑሮ ጫና በዘላቂነት ለማቃለልም ያላቸው ጠቀሜታም ከፍ ያለ ነው፡፡

እነዚህ የልማት ሥራዎች የከተማዋን ጎስቋላ ገፅታ በሚፈለገው አግባብ እየለወጡ ያሉ፤ ከወትሮ በተሻለ ሰፋፊ የስራ ዕድሎችን የፈጠሩ፤ ወሳኝ የመንግሥት አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ያሳለጡ ናቸው። የከተማዋን ገቢ ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ ስለመሆናቸውም በተደጋጋሚ ተገልጿል። በከተማዋ አዲስና እየዳበረ ያለውን አሁናዊ የፕሮጀክቶች የስራ አፈጻጸም ያስገኟቸው ውጤቶች በቀናነት መመልከት ከተቻለ ከተማዋ፤ በሁሉን አቀፍ የለውጥ ሂደት ላይ መሆኗን በልኩ መረዳትና ማድነቅ እንዲሁም መደገፍ ለሚፈልግ አካል ብዙም የሚከብድ አይደለም።

ከለውጡ ማግስት አንስቶ በተከታታይ በፕሮጀክቶች አመራርና አስተዳደር ረገድ በተጨባጭ የታየው ስኬትና ውጤት ሊመዘገብ የቻለው መንግሥት የመፈፀም አቅሙን በማሳደጉ፤ ብክነትን መቀነስ መቻሉን ጨምሮ የልማት አጋሮችን እና የነዋሪውን ሁለንተናዊ አቅም አስተባብሮ መጠቀም በመቻሉ ነው። ለዚህ ከንቲባዋ ለከተማው ምክር ቤት የ2016 ዓ.ም የስራ አፈጻጸምን በማስመልከት በሰጡት ማብራሪያ በግልጽ አስቀምጠውታል። ይህንኑ ጀምሮ የመጨረስ አዲስና እየዳበረ የመጣውን የፕሮጀክት አመራር ልምድ ተከትሎ፤ ከንቲባ አዳነች የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራምን ጨምሮ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት ልዩ ልዩ የማበረታቻ ሽልማቶችን መቀበላቸውም ይታወሳል።

የከተማዋ የኮሪደር ልማት ትግበራ፤ የጎረቤት ሩዋንዳ ኪጋሊ ከተማን ጨምሮ የሌሎችንም ዓለም አቀፍ ከተሞች ተሞክሮዎችን ዋቢ አድርጎ እንደሚፈጸም ከመሆኑም ባሻገር፤ ከከተማዋ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ነው። ከተማ አስተዳደሩ የኮሪደር ልማት በሚያልፍባቸው መዳረሻዎች ካሳ፣ ተለዋጭ ቦታና በየደረጃው የሚገኙ ቤቶችን አስቀድሞ እያቀረበ ያለ ስለመሆኑ የልማቱ ተነሽዎች በተለያዩ ጊዜያት ለሚዲያ አካላት ከሰጧቸው ምስክርነቶች መረዳት የሚቻል ይሆናል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ አጠቃላይ ግንባታቸው ተጠናቆ ለህዝባዊ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ክፍት ተደርገው ከነበሩት አምስቱም የኮሪደር ልማት መዳረሻዎች መካከል ከአራት ኪሎ በመስቀል አደባባይ አድርጎ እስከ ቦሌ ድልድይ (7 ኪሎ ሜትር) ፤ ከቦሌ አየር መንገድ እስከ መገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ (4 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር) ፤ ከመገናኛ ዲያስፖራ አደባባይ በአራት ኪሎ አድርጎ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ድረስ (6 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር)፤ ከፒያሳ ዓድዋ ድል መታሰቢያ ዙሪያ፣ በለገሃር ሜክሲኮ፣ በሳርቤት አድርጎ እስከ ወሎሰፈር (10 ኪሎ ሜትር) ባለው የተከናወኑና አሁንም እየተሰሩ የሚገኙ የልማት ሥራዎች በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በአምስቱም የኮሪደር ልማት መዳረሻዎች፤ ከ240 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ እና በተጓዳኝ በፕሮግራም ማሕቀፉ ተካተው የተከናወኑ መሰል መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ 70 የከተማዋን የውስጥ ውበት ከመልካም የአየር ንብረት ጠባይ ጋር አዳምረው መንፈስን የማደስ አቅም ያላቸው የህዝብ መናፈሻዎች ተገንብተው የከተማዋ ነዋሪ ከቤተሰቡ ጋር ባመቸው ሰዓት ሁሉ እየተገለገለባቸው ነው፡፡

ከተማዋን በሁሉም ረገድ ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንድትሆን ለማስቻል የተያዘውን ራዕይ ከማሳካት አኳያ፤ የከተማዋን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ወደ ላቀ ምዕራፍ ለማሸጋገር የሚረዱ የፍሳሽ ማስተላለፊያዎች፣ በአይነታቸው ልዩ የከተማዋን ሰላማዊነት የሚያፀኑ የደህንነት ካሜራዎች፣ የብልህ ትራንስፖርት ስርዓት (intelli­gent transport system) በመሬት ውስጥ የመዘርጋት ስራ ፣ ከ400 የሚልቁ ህንጻዎች ዕድሳትን ጨምሮ ወጥ የቀለምና የመብራት ስራዎች እና ሌሎች ተያያዥ ተግባራት ዘመን ተሻጋሪ አገልግሎት እንዲሰጡ ሆነው በላቀ ጥራት እየተሰሩ ስለመሆናቸው ከተማ አስተዳደሩ የሚያወጣቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ከከተማ አስተዳደሩ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው ፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ፤ ለኮሪደር ልማት ፕሮግራም ተነሺዎች 6 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ካሳ ተከፍሏል። ለልማቱ ተነሺዎች በተቀላጠፈ አኳኃን ለሁለት ሺህ 538 ቦታዎች (33 ነጥብ 4 ሄክታር) ምትክ መሬት በከተማው የመሬት ልማት ማኔጅመት ቢሮ በኩል ተላልፏ። በሌላ መልኩ የልማት ሥራው ለከተማዋ ነዋሪዎች ይዞት በመጣው መልካም ዕድል ፤ እጅግ ጎስቁለው ለመኖር አመቺ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ በንግድ ቤቶች ውስጥ የነበሩ በርካታ የልማት ተነሺዎች ምቹ የመኖሪያ እና መስሪያ ቦታ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡

በአገልግሎትና በአቅርቦት ሥራ ላይ የተሰማሩ ብዙሃን የንግዱ ማህበረሰብ አካላት፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በልማቱ ሳቢያ የተፈጠረው ሰፊ የገበያ ትስስር አካል በመደረጋቸው ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልና ተጠቃሚነትን በከተማዋ እንዲሰፍን እያስቻለ የሚገኝ የልማት ስራም መሆኑ ተጨማሪ ማስረጃ ሳያሻው በፍሬው የሚታይ ነው።

ከሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት መጀመር አስቀድሞ፤ በቅርቡ ተመርቆ ለህዝባዊ አገልግሎት ክፍት የተደረገው የአፍሪካ ፣የኢትዮጵያና የአዲስ አበባ መግቢያ በር ተደርጎ የሚታየው የቦሌ መንገዶች የልማት ኮሪደር ፕሮግራም ርዕሰ መዲናዋ አዲስ አበባ የንግድ፣ የቱሪዝም ፣ የዓለም አቀፍ ኮንፈረንስና የልዩ ልዩ የስማርት ሲቲ አገልግሎቶች ማዕከል በተጨባጭ እየሆነች መምጣቷን ያረጋገጠም ሥራ መሆኑ የበርካቶችን ምስክርነት እያገኘ ነው።

የቦሌ መንገዶች፣ የልማት ኮሪደር ሥራ ወደ ቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ እና ወደሌሎችም የከተማዋ አካባቢዎች በትራንስፖርት የሚደረግን ጉዞ በእጅጉ የተቀላጠፈ እንዲሆን አስችሏል። በቦሌ መንገዶች የኮሪደር ልማት ፕሮግራም ማሕቀፍ የተገነቡ፤ ልዩ ልዩ የቢዝነስ ማዕከላት፣ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች እና ሱቆች የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በእጅጉ መሳብ ችለዋል። በዚህም በአካባቢው የሚከናወኑ ልዩ ልዩ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የምሽቱን ክፍለ ግዜ ጨምሮ፤ ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት እንዲታይባቸው ከመሆኑም ባሻገር ፤መጪው ግዜ ለከተማዋ ብሩህ መሆኑን አመላካች ተደርጎ ተወስዷል፡፡

በኮሪደር ልማት መርሀ-ግብር በከተማዋ ተግባራዊ ከሚደረጉ ዝርዝር የልማት ሥራዎች መካከል የመንገድ ኮሪደር ልማት፤ የወንዝ ዳርቻዎች አዋሳኝ የተፋሰስ ልማት ፣ የብስክሌትና ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ልማት ፣ ዘመናዊ የትራንስፖርት ተርሚናሎች ግንባታ ፣ አገናኝ የኮሪደር ልማት ድልድዮች፣ ማሳለጫዎችና የመጋቢ መንገዶች ልማት፤ የመንገድ ዳር የህዝብ መፀዳጃ ቤቶች፤ ፋውንቴይኖች እና የህዝብ መናፈሻ ስፍራዎች፤ ወጥ የህንጻ ቀለምና የከተማ ማብራት፤ ደረጃቸውን የጠበቁ ፓርኪንጎች፣ የመኪና መጫኛና ማውረጃ አገልግሎቶችን ጨምሮ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ያካተቱ ናቸው።

በጋዜጠኛና ሲኒየር የኮሙኒኬሽን

ባለሙያ ላንዱዘር አሥራት

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You