ጉዞ ወደ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025

አሁን ባለንበት ዘመን ያለ ቴክኖሎጂ ህይወት ፈታኝ ነው። ከግለሰብም አልፎ ሀገራትም ያለ ቴክኖሎጂ ያሰቡትን እ ድገት እ ና ብ ልጽግና ማ ረጋገጥ አ ይችሉም። ለዚህ ነው ከበለጸጉት እስከታዳጊ ሀገራት ድረስ ቴክኖሎጂን ለማልማትና ለመጠቀም ትኩረት ሰጥተው በመስራት ላይ የሚገኙት።

ኢትዮጵያ ለቴክኖሎጂ ትኩረት ከሰጡ ሀገራት አንዷ ነች። ስትራቴጂክ የእድገት ዘርፎች በሚል በፖሊሲ ደረጃ ልዩ ትኩረት ከሰጠቻቸው ዘርፎች ውስጥ ቴክኖሎጂን አንዱ የትኩረት አቅጣጫ አድርጋ መውሰዷም ለዚህ ነው። ዲጂታል ኢትዮጵያ የሚለው መርሃ ግብር በመቅረጽም በ2025 በሁሉም ዘርፍ ቴክኖሎጂ መሪ ሆኖ እንዲወጣ እየተሰራ ነው።

በርግጥ ቴክኖሎጂ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከግብርና እና ከሌሎች ዘርፎች አንፃር የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። የአጠቃቀም ሂደቱን ብንመለከት ደግሞ እንደ ዘርፎቹ አይነት ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድም ይለያያል፣ የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎችም እንዲሁ እንደ አገልግሎቱ አይነትና ስፋት ይለያያሉ። እንደ ኢትዮጵያ ላሉና በማደግ ላይ ለሚገኙ ሀገራት ደግሞ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ሥራ ፋይዳው ከምንለው በላይ ትልቅ ነው።

ኢትዮጵያም የዲጂታል ዓለምን ለመቀላቀል የሚያስችላትን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተቀብላ ዲጂታላይዜሽን ለማስፋፋት የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሰራች ነው። አሁን ላይ ሥራው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበላይነት እየመራው ይገኛል።

የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ዲጂታላይዜሽንን በማስፋፋት ረገድ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ሥራ ላይ እንዲውል ተደርጎ በርካታ ሥራዎች መስራት ተችሏል። በዚህም ከ526 በላይ የሆኑ የመንግሥት አገልግሎቶች በኤሌክትሮኒክስ መንገድ እንዲፈጸሙ፤ የክፍያ ሥርዓቶችም በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ሥርዓት እንዲሆኑ እና የተለያዩ መተግበሪያዎች እንዲለሙ ተደርጓል።

በዲጂታል ቴክኖሎጂው በኩል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ሊያሰፉ የሚችሉ ሥራዎችን መስራት ተችሏል። ባለፈው ወር መጨረሻም የዲጂታል ሳምንት በማካሄድ በዲጂታል ዙሪያ የተሰሩ ሥራዎችን ኅብረተሰቡ እንዲረዳቸውና እንዲገነዘባቸው ማድረግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተሰርተዋል ።

ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ ከተሰሩ ሥራዎች አንዱ ፤ የመንግሥት አገልግሎቶችን ሙሉ በሙሉ በኤሌክትሮኒክስ ለመተግበር የሚያስችለው ስትራቴጂ አንዱ ነው። ስትራቴጂው በቀጣይ አምስት ዓመት የኤሌክትሮኒክስ ዘርፉ የሚመራበትን አቅጣጫ ለማመላከት ታልሞ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ስትራቴጂውን አጠናቅቆ ተግባራዊ ለማድረግ ያስችል ዘንድ የመጨረሻ ግብዓት ማሰባሰብ ተችሏል።

ስትራቴጂው በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል ነው፤ የመሰረተ ልማት ግንባታ፣ የመተግበሪያ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ አወቃቀር እና በጀትን አካትቶ የያዘ መሆኑ ተገልጿል። ስትራቴጂው ከ2016 እስከ 2020 ዓ.ም ተግባር ላይ የሚውል መሆኑም ተመላክቷል።

እንደ ሀገር በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂና በአዲስ የፈጠራ ሥራ መታገዝ የግድ ሆኗል፤ ያለቴክኖሎጂ ያለሙበት መድረስ ከባድ እየሆነ መጥቷል። ከእነዚህ ዘመን አፍራሽ የቴክኖሎጂ ዘርፎች መካከል አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ወይም የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቀዳሚውን ስፍራ እየያዘ መጥቷል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ዘርፎች ምርታማነትን ለመጨመር እንዲሁም አምራች እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስተሳሰር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ነው። ሰው ሰራሽ አስተውሎት/artificial intelligence/ በአሁኑ ወቅት በትምህርት፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣በደህንነት እና በግብርና ዘርፎች ምርታማነትን እና ቅልጥፍናን ለመጨመር ቁልፍ ቴክኖሎጂ ሆኖ እያገለገለ ነው።

በኢኮኖሚው ረገድም መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ የዚህ ቴክኖሎጂ ድርሻ በዓለም ገበያ 350 ቢሊዮን ዶላር በላይ ደርሷል። ይህ ቴክኖሎጂ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን እና ህይወታችንም ሰፊ ድርሻ እየያዘ  መጥቷል። ያደጉትም ሆነ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቴክኖሎጂው በሚያስፈልጋቸው ዘርፎች እንደ አስፈላጊነቱ እየተጠቀሙበት ችግሮቻቸውን እየፈቱ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ትገኛለች። የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን በመጠቀም የግብርና፣ የጤና፣ የደህንነት፣ እና መሰል ዘርፎችን አቅም ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።

ሰው ሰራሽ አስተውሎት ማሽን ወይም ኮምፒዩተር የሰው ልጆችን ተክቶ ማመዛዘን፣ መማር፣ ማቀድ እና ፈጠራዎችን ማከናወን እንዲችል የሚያደርግ ነው። በዚህ ሁኔታ ማሽኖቹ አካባቢያቸውን እንዲገነዘቡ፣ የተገነዘቡትን እንዲተነትኑ ፣ ችግሮችን እንዲፈቱ እና አንድ የተወሰነ ግብ እንዲደርሱ ለማድረግ ያስችላቸዋል።

ይህም በተለይ የሰዎችን ንክኪ በመቀነስ ለምርት መጨመር፣ የጊዜ አጠቃቀምን ለማሻሻል፣ ብልሹ አሰራሮችን ለማስወገድ እና ውስብስብ ስራዎችን ያለ ከፍተኛ ወጪ ለመፈፀም ያስችላል። ከጊዜ አንፃርም ያለማቋረጥ እና ያለ ምንም እረፍት ይሰራል ይህም የህብረተሰብን ኑሮ የሀገርን ዕድገት እንደሚያቀላጥፍ ያስረዳል።

በ2030፣ 50 በመቶ የሚሆነው ስራ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ እንደሚተካ ይጠበቃል። በ2020 አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኮቪድ 19 ለማጥናት ጥቅም ላይ ውሏል። 2030- አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ለዓለም ኢኮኖሚ 15.7 ቢሊዮን ዶላር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ይጠበቃል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና አገልግሎት የጥራት እና ተደራሽነት ውስንነት አለበት። በታዳጊ ሀገራት ደግሞ ችግሩ ሰፊ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያም ይህንን ችግር ለመቅረፍና የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ጥቅም ላይ ለማዋል መረባረብ የግድ እንደሚሉት እሙን ነው።

ይህ ቴክኖሎጂ በሁሉም ዘርፎች ሰፊ ተግባራት ያሉት በመሆኑ ከቅንጦት ይልቅ ለህብረተሰብ ያለው አስፈላጊነት ግንዛቤ እያገኘ መጥቷል፤ ቴክኖሎጂው በተለይ በአፍሪካ ከባድ በሽታዎችን ለማስወገድ፣ የጤና እንክብካቤን እና ትምህርትን ለማሻሻል፣ ድህነትን ለመቀነስ እና በአህጉሪቱ ለሚታየው የምግብ እጥረት የላቁ መፍትሔዎችን ለማምጣት የሚያግዝ በመሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ይገባል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ ለቴክኖሎጂ የሰጠው ትኩረት ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ዓለም ካለችበት ነበራዊ ሁኔታ አንፃርና ሌሎች ሀገራት በዘርፉ ከደረሱበት ልህቀት አኳያ አሁንም ብዙ መሥራት ይጠበቃል። በተለይ የመንግሥት ተቋማት ላይ ያለው የቴክኖሎጂ ፍላጐት አሁንም ገና በመሆኑ ችግሩን ለመቅረፍ መረባረብ ተገቢና አስፈላጊ ነው።

ተቋማት ቴክኖሎጂን ተጠቅመው የአገልግሎት አሰጣጣቸውን እንዲያዘምኑ በፖሊሲ ደረጃ አቅጣጫዎች ቢኖሩም በተግባራዊነቱ ላይ አሁንም ክፍተት ስለመኖሩ በተጨባጭ የሚስተዋል ነው። ተቋማት ከለመዱት አሰራር ተላቀው የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አሁንም በትኩረት መሥራት ይጠበቅባቸዋል፤ ለዚህ ደግሞ እራሳቸውን በሁለንተናዊ መልኩ ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።

ክብረአብ

 አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You