አኒታ ጳውሎስ የተባለች ያኔ የአሶሽየትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ የነበረች ከዐሥር ዓመት በፊት አንድ ጥያቄ ጠይቃ ነበር። ጥያቄው የቀረበው ሚሊኒየም ጽሕፈት ቤት ይባል ለነበረው ተቋም አንድ የሥራ ኃላፊ ነበር። በወቅቱ ኃላፊው ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ሺህ ዓመት (ሚሊኒየም) ለመቀበል ሰባት ሚሊየን አካባቢ ሀገር በቀል ችግኞች መትከሏን ማስታወቃቸው ነበር ጋዜጠኛዋን ጥያቄ እንድትጠይቅ ያደረጋት። በወቅቱ ከጥያቄ ይልቅ ወደ ሙግትነት የተቀየረ መሆኑን አስታውሳሁ። ይሔን ያህል መትከላችሁን እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል? ቆጥራችኋል ወይ?… የሚሉ ነበሩ ሙግታዊ ጥያቄዎቿ።
ከጋዜጠኛዋ የቁጥር ጥያቄ ይልቅ ያኔም ሆነ አሁን የሚያሳስበኝ የምንተክላቸው ሀገር በቀል ችግኞች ብዛት ሳይሆን ምን ያህሉ ፀደቁ የሚለው ነው። መትከሉ ብቻ በቂ አይደለም። የተተከሉት ችግኞች ጸድቀው ዛፎች ሲሆኑ ተመናምኖ የነበረው የሀገራችን የደን ሽፋን ማንሰራራቱ ነው ዋናው። ከሦስት በመቶ በታች ወርዶ ነበር የተባለው ወደ ዐሥር በመቶ እና ከዚያ በላይ የሚሔደው የደን ሽፋናችን ችግኝ በመትከል ብቻ ሳይሆን በመንከባከብም ጭምር ነው የሚጨምረው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ከአራት ቢሊየን በላይ ሀገር በቀል ችግኞች ተክላለች። ከነዚህ ውስጥ 350 ሚሊየን ያክሉ በአንድ ቀን የተተከሉ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ክብረወሰንም የያዙ ናቸው። ዘንድሮም አምስት ቢሊየን ችግኞች ለመትከል አቅዳለች። ከነዚህ አብዛኞቹ ሀገር በቀል እንደሚሆኑ ይታመናል።
በሀገሪቱ ከዚያም በፊት እና በኋላ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ችግኞች ተተክለዋል። በአብዮቱ ጊዜ ማለትም በወታደራዊው መንግሥት ጊዜ ተተክለው እስካሁንም የዘለቁትን እና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን ጽድ የሚበዛባቸውን ደኖች እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል። ከነዚህ ጫካዎች (ደኖች) አንዱ በጅማ መስመር የሚገኘው በተለምዶ በቀለ ጫካ የሚ ባለው ነው።
በቀለ ጫካም ሆነ መሰል ደኖች ከዚህ የደረሱት ችግኞች ተተክለው ብቻ አይደለም- እንክብካቤ እና ጥበቃ ተደርጎላቸው እንጂ። በወቅቱ ችግኝ ተከላ የሚሸፈኑ ቦታዎች ነቀላ እንዳይከናውን በብዙ ቦታዎች ጥበቃ ነበራቸው- የደን ልማት ጥበቃ። ደን መንጥሮ ችግኝ ነቅሎ የተገኘ ሰውም በሕግ ይቀጣ ነበር። ጥፋቱን ያከናነወኑት በሰው ይዞታነት ያሉ እንስሳትም ቢሆኑ በቁጥጥር ሥር ውለው ባለቤቶቻቸው እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር። የተተከሉትም ሥር ይዘው በውሃ ራሳቸውን እስኪችሉ በየወቅቱ በዘመቻ ውሃ ይጠጡ ነበር። ተከላውም ብዙውን ጊዜ በክረምት ይከናወናል።
አሁንም ችግኝ ተከላ የሚከናወነው ከሞላ ጎደል በክረምት ነው። በደረቁ የበጋ ወቅት የተተከሉትን ችግኞች ከሞላ ጎደል ዞር ብሎ የሚያያቸው ጠፋ እንጂ። በተለያዩ መሥርያ ቤቶች በየዓመቱ ክረምት ሀገር በቀል ችግኞች በብዛት ይተከላሉ። የየተቋማቱም የማስታወቂያ ሰሌዳዎች በችግኝ ተከላ ፎቶግራፎች ይሞላሉ። በዚህ ጊዜ በጭቃ የላቆጡ እጆች፣ የተንፈራጠጡ እግሮች፣ አረንጓዴ ዘመቻ የሚሉ ቲሸርቶች እና ኮፍያዎች ማየቱ የተለመደ ነው።
እንዲህ አይነት ፎቶዎች ለቁጥር እስኪ ታክቱኝ ድረስ አይቻለሁ። ችግኙን ውሃ በማጠጣት የሚንከባከቡ ችግኝ ተካዮችም ሆነ ፎቶግራፎች ከጠቅላይ ሚንስትሩ በስተቀር አላየሁም። ይህ ከችግኝ ማጽደቅ ይልቅ ችግኝ ተከላ ላይ ብቻ ሙጥኝ ማለታችንን ያሳያል። መቶ ተክሎ ጥሎ ከመሔድ አንድ ተክሎ እሷኑ ተንከባክቦ ለዐቅመ ዛፍ ማብቃት ይሻላል እላለሁ። እናንተስ?
ችግኝ ተከላን አስመልክቶ እየተተኮረ ያለው ቁጥር ላይ ይመስላል። የአሶሴትድ ፕሬስ ጋዜጠኛዋ እንደጠየቀችው ስንት እንደተከላችሁ እንዴት አወቃችሁ ማለት ብቻ አይበቃም። ይኼን ያህል ተክለናል ማለትም መልስ አይደለም። ዐሥርም፣ መቶም ፣ ሺህም፣ ሚሊየን ሆነ ቢሊየን መትከል ይቻላል። ምን ያሉ ያዙ ጸደቁ ነው ቁምነገሩ። የድንቃድንቅ መዝገቡም በአንድ ቀን ይህን ያህል ተተከለ ከሚለው የቁጥር ክብረወሰን ይልቅ ምን ያህሉ ያዘ በሚለው ላይ የሚያተኩርበት አማራጭ ላይ ቢያተኩር አልያም አንድ ሚሊየን በአንድ ሰዓት ተክለህ ነበር አንዱም ስላልጸደቀ የሰጠሁህን ክብረወሰን ነጥቄሃለሁ ማለት ቢችል ! ወይን ደግሞ አንድ ሚሊየን ተክላችሁ ዘጠኝ መቶ ሺው ስለበቀለ ተጨማሪ ክብረወሰን እንካችሁ ቢባል ደግሞ እጅግ ያማረ ይሆናል።
በሌላ በኩል ብዙ ጊዜ ችግኝ የምንተክለው በሀምሌ ወር ከዚያም አለፍ ሲል በነሐሴ ወር ነው። ይህ በራሱ ምንም አይነት ችግር የለበትም። ችግሩ የሚመጣው ተክለን ዞር ስንል፣ የተከልነውን ሳንንከባከብ ስንቀር ነው። ተክሎ ዞር ብቻ ከሆነ ይህን አይነት ችግኝ ተከላ ነቀላ ማለት ነው። ከነሃሴ ተከትለው በሚመጡት ወራት እንደ አየሩ እርጥበት እና ድርቀት ውሃ ማጠጣት ሲኖርብን ብዙ ጊዜ ከመትከል የዘለለ ሚና አይኖረንም። ችግን በብዛት መትከላችን የሚበረታታ ቢሆንም መንከባከባችን ደግሞ የበለጠ ይበረታታል። ይህ ሲሆን አምና በተከልናቸው አራት ቢሊየን ችግኞች ለሀገራችንም ሆነ ለዓለማችን አረንጓዴ ምጣኔ ሀብት የበኩላችንን አስተዋጽዖ አደረግን ማለት ነው። ግማሽ ያህሉ እንኳን ቢይዝ የተሻለ ነገር ይኖረናል። እሩብ ያህሉ እንኳ ቢይዙ በጥቂት ዓመታት ውስጥ አንድ ቢሊየን ዛፎች ይኖሩናል ማለት ነው።
ዘንድሮም ከዚያ የሚልቅ ችግኝ ለመትከል ባለፈው ዓርብ የዓመቱ የችግኝ ተከላ መርሐግብር ተጀምሯል። የዘንድሮውን ስንጨምርበት የሚይዙ ችግኞች ቁጥር ለአረንጓዴ ምጣኔ ሀብታችንም ገንቢ አስተዋጽዖ አለው። እጽዋት ደግሞ እንስሳት አይደሉም። አንዴ ራሳቸውን እስኪችሉ ከተንከባከብናቸው ከእንስሳት ንክኪ ከጠበቅናቸው ቀለብ ስፈሩልኝ፣ ውሃ አጠጡኝ ብዙም አይሉንም። ጥቅማቸው ግን ለሁላችንም ይሆናል። ጥቅማቸው ለምድራችን ሁሉ እንዲሆን ችግኝ ተከላ ብቻ በቂ አይደለም፤ ራሳቸውን እስኪችሉ ሥር እስኪሰዱ መንከባከብ እንጂ!
ይህን ለማድረግ አልተጠቀምንበትም እንጂ ባሕላችን አንድ መንገድ አለው። በብዙ የሀገራች ባህሎች እና ሐይማኖቶች ዛፍ ሕይወት ነው፣ ችግኝ የዛፍ መጀመሪያ ነው የሚል ጠንካራ እሳቤ አለ። ስለዚህም እንደባህላችን ችግኞችን ተንከባክበን ዛፍ እናድርጋቸው።
አዲስ ዘመን ሰኔ 6/2012
መልካሙ ተክሌ (melkamutekle@gmail.com)