“ዴሞክራሲ” የሚለው ቃል ከእንግሊዝኛው የተወሰደ ቢሆንም መሰረቱ ግሪክ እንደሆነ የተለያዩ ድርሳናት ይገልፃሉ። በዚህ ፍቺው ደግሞ “ዴሞ” እና “ክራሲ” ከሚሉ ሁለት ጥምር ቃላት የተመሰረተ እንደሆነ ያወሳሉ። እነዚህ ሁለት ቃላት ደግሞ ህዝብና አስተዳደር ማለት ናቸው። ከዚህ በመነሳትም ዴሞክራሲ ለሚለው ቃል የህዝብ አስተዳደር የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል።
የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ ይህ ቢሆንም በዓለም ላይ የአገራት የጎራ መለያ ከሆነ ሰነባብቷል። በተለይ ራሷን የዴሞክራሲ ጠበቃ አድርጋ የምትመለከተው አሜሪካና አጋሮቿ ይህንን ቃል የግላቸው በማድረግ በዚህ ሂደት ውስጥ አይደሉም ብለው የሚያስቧቸውን አገራት ለመጨቆንና ከዚያም አልፎ ለማፈራረስ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ መስፈርቶች ተግባራዊ የሚደረጉት በሌሎች ላይ ነው። ስለዴሞክራሲ የምታስተምረው ራሷ አሜሪካም ጭምር ምን ያህል ዴሞክራሲን እንደምትጥስ ግን የሰሞኑ የዘረኝነት ውዝግብ አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
ድርሳናቱ እንደሚያመለክቱት በዓለም ላይ የተለያዩ የዴሞክራሲ አይነቶች አሉ። ከነዚህም መካከል በአብዛኛው የሚጠቀሱት የቀጥታ ዴሞክራሲ /Direct Democracy/፣ የውክልና ዴሞክራሲ/Reperesentative Democracy/፣ አሳታፊ ዴሞክራሲ /Participatory Democracy/፣ የብዙሃነት ዴሞክራሲ፣ የልሂቃን ዴሞክራሲ፣ ፓርላሜንታዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ወዘተ በሚል ይከፍሏቸዋል። ነገር ግን አብዛኞቹ የሚያነሷቸው የዴሞክራሲ አይነቶች አሳታፊ፣ የብዙሃት እና የልሂቃን የሚሉ የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳቦችን ነው። ያም ሆነ ይህ ሁሉም የየራሱ ፍልስፍናዊ መሰረት ቢኖረውም ዴሞክራሲ ለሰው ልጅ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ መለስ ስንል ደግሞ ዴሞክራሲ የሚለው ጽንሰ ሃሳብ በመንግስታትና በፓርቲዎች መነገር ከጀመረ ከከግማሽ ምዕተ አመት መሻገሩን እናገኛለን። በዚህ ረገድ በተለይ ከደርግ መንግስት ጀምሮ ስለዴሞክራሲ ያልተወራበት ጊዜ አለ ለማለት አይቻልም። ከዚህም አልፎ በዴሞክራሲ ስም የሚምሉና የሚገዘቱ ፓርቲዎችም ቁጥራቸው እየሰፋ መጥቷል። በተግባር ግን ወደ መሬት የወረደበት ጊዜ አለ ለማለት አያስደፍርም። ህብረተሰቡም ቢሆን ይህንን የዴሞክራሲ ባህል ተለማምዶ ከመተግበር አንጻር ሰፊ ክፍተት እንዳለበት ይታወቃል።
ነገር ግን የዴሞክራሲን ተግባራዊ ለማድረግ ከመንግታት ቁርጠኝነት ባሻገር የዜጎችና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁርጠኝነትም ወሳኝ ሚና አለው። ለዚህ ደግሞ አሁን ያለንበት ጊዜ አብይ ምስክር ሊሆን ይችላል። ባለፉት ሁለት አመታት በአገራችን ያየነው ሰፊ የዴሞክራሲ ምህዳር ዴሞክራሲውን በሚፈለገው ልክ ለምን አላሳደገም ስንል ዴሞክራሲ በመንግስት ቁርጠኝነት ብቻ የማይመጣ መሆኑን ሊያሳየን ይችላል። ከዚህ አንጻር በአገራችን በነዚህ ጊዜያት ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተለይ ከፓርቲዎች መብዛትና ከዴሞክራሲ ተግባራዊነት ጋር አያይዘን እንቃኝ።
በአሁኑ ዘመን በዓለም ላይ ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ እየሆኑ ከሚገኙ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ግንባር ቀደሙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ቢሆንም ይህም ቢሆን ፖለቲካዊ አንድምታ እየያዘ ከሚዲያ ሚዲያ መሽከርከሩ አልቀረም። በአገራችንም ቢሆን ኮሮና ፖለቲካውን በተወሰነ ደረጃ አደብ ቢያስገዛም ሙሉ ለሙሉ አላስቀረውም። አልፎ አልፎ ቀዳዳ ሲገኝ ኮሮናን በመርሳት ፖለቲካውን ማጦዝ ያለ ነው። በዚህ ዘመን እንደ አሸን የፈሉትን ሚዲያዎች የቀን ውሎ ስንመለከት በአብዛኛው ከዚህ የወቅቱ አጀንዳ ጋር የተቆራኙ ናቸው። ዛሬ ዛሬ በየትኛውም መደበኛ ሚዲያ ወይም በማህበራዊ ሚዲያውም ጭምር ከኮሮና ባሻገር ስለፖለቲካ ሳይነገር የሚዋልበት እለት አይኖርም። እናም ለዛሬ በተለይ መነሻችን ፖለቲካው ስለሆነ በዚሁ ዙሪያ ሃሳቦችን እናነሳለን።
የአለምን የፖለቲካ ጭብጥ ስንመለከት እንደ አህጉሩ ደረጃ፣ እንደአገራቱ አቅምና ፖለቲካዊ ብቃት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አቅም የተለያየ ነው። ለምሳሌ እኛ የምገኝበት የአፍሪካ ቀጣና የፖለቲካ ውሎ በአብዛኛው ከውስጥ ሰላምና ከግጭት ጋር የተያያዘ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ በተለይ አፍሪካውያን ገና ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያልተሸጋገሩ፣ ድህነትና ኋላቀርነት የህዝቦች ዋነኛ መገለጫ በመሆኑና ከርስ በርስ ግጭት ጋር ተያይዞ ውስጣዊ የፖለቲካ ጡዘታቸው የእለት ተዕለት አጀንዳ ሲሆን ይስተዋላል።
ኢትዮጵያም በዚህ የአፍሪካ ቀጠና የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ ትገኛለች። አገሪቷ ላለፉት አምስት አስርት አመታት በተለያዩ የውስጥ ችግሮች የተነሳ ያልተረጋጋ የፖለቲካ አውድ ውስጥ ቆይታለች። አንዱ አጋጥሞት ስልጣን ላይ ሲወጣ ያን ያልተቀበለው ሃይል ነፍጥ አንግቦ ጫካ ሲገባና ትርምስ ሲፈጥር፣ እሱም ሲሳካለት በራሱ መንገድ በመጓዝ አገሪቱን ከመለወጥ ይልቅ በቢሮክራሲውና በውስጥ ሽኩቻ ታጥሮ ዳግም ለሌላ ፍልሚያ ሲዘጋጅ እና በዚህ የማያባራ አዙሪት ውስጥ ሆነን እነሆ ድህነትንም ሳናሸንፍ፣ የተረጋጋ ፖለቲካዊ ስርዓትም ሳንፈጥር ባለንበት መርገጥ ግድ ብሎናል።
ለዚህ አንዱ የ1960ዎቹ የአገራችን ፖለቲካ ትልቅ ማሳያ ሊሆን ይችላል። የቀደመው የፊውዳል ስርዓት በህዝብ እንቢተኝነት ተገርስሶ ደርግ ወደስልጣን ቢወጣም አምባገነን ከመሆን ያገደው አልነበረም። በወቅቱ በተለይ ዴሞክራሲ የሚለው ቃል እዚህም እዚያም እንደአሸን የፈላበትና ይህን የስማቸው ማጣፈጫ ያደረጉ የፖለቲካ ሃይሎች ተፈጥረው ርስ በርሳቸውም ሆነ ስልጣን ላይ ካለው ሃይል ጋር መስማማት ሳይችሉ የሚፈለገውን ለውጥ ሳያመጡና ለህዝብም አንዳች ቁምነገር ሳይፈይዱ አለፉ።
ደርግም ቢሆን አምባገንነቱን አጠንክሮ በመቀጠል ዴሞክራሲ የሚለውን ቅጥያ እንደያዘ ቢቀጥልም ከስም ውጭ በተግባር የማያውቀውን ዴሞክራሲ ለህዝብ ሊያደርስ አልቻለም። በዚህ የተነሳ ህዝቡ ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ ከማለት አልዳነም።
ደርግን ገርስሶ ስልጣን የያዘው ኢህአዴግም ቢሆን ወደ መጀመርያው አካባቢ ለዴሞክራሲ የተሻለ መንገድ የተጓዘበት ሁኔታ ነበር። በተለይ ሃሳብን በነጻነት ከመግለፅ ጀምሮ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተወዳድረው የፖለቲካ ስልጣን እንዲይዙ እየማለ ሲገዙት ኖሯል። በዚህ የተነሳ ጥቂት የማይባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተፈልፍለው የፖለቲካ ፓርቲ ግሽበት የፈጠሩበት ሁኔታ በስፋት ተስተውሏል።
በተለይ ኢህአዴግ እየቆየ ሲመጣ በአንድ በኩል ዴሞክራሲያዊ ነው ለመባል ብቻ በርካታ ፓርቲዎች እንዲፈለፈሉ ቢያደርግም ለህዝቡ አማራጭ እድሎችን ይዘው መቅረብ ያልቻሉትና የተፈጠሩበትን የህዝብ ዓላማ ተገንዝበው ለዚያ የሚሰሩት ግን በጣም አነስተኛ ነበሩ። አብዛኞቹ ፓርቲዎች መድረኩን ብቻ ለማሞቅ፣ አንዳንዶቹም ምርጫ ሲቃረብ ብቻ የሚፈጠሩና ስለፖለቲካ ምን ግንዛቤ የሌላቸው ፓርቲዎች ናቸው።
በዚህ የተነሳ ባለፉት ሁለት አስር አመታት የፓቲዎቻችን ቁጥር በአብዛኛው ከአንድ መቶ የሚልቅ እንደነበር ይታወቃል። እነዚህ ፓርቲዎች ግን አንዱ ከሌላው ጋር በምን አይነት ልዩነት እንደተፈጠረ የሚያውቅ የለም፤ እነሱም የሚያውቁ አይመስልም። ሌላው ቢቀር አሁን በተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት እንኳን ለህዝቡ ምን ፈየዱ ስንል መልሳችን ምንም የሚል ይሆናል። ለዚህ አንድ ማሳያ ላንሳ።
በ2002 ዓ.ም ምርጫ ሲቃረብ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጓቸው የውይይት መድረኮች ላይ የመገኘት እድል አግኝቼ ነበር። በወቅቱ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በቀረበው ጥሪ መሰረት ከአንድ መቶ በላይ አመራሮች ነበሩ። ውይይት ለማድረግ በተሞከረበት ወቅት ከነዚህ የፖለቲካ አመራሮች ሲነሱ የነበረው ሃሳብና የነዚህን አመራሮች የፖለቲካዊ ብቃትና የግንዛቤ ሁኔታ ስመለከት በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ተስፋ ቆረጥኩ። በአብዛኛው የሚነሱት ጉዳዮች የግል ፍላጎትን ለማሟላት አልያም ስልጣን ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ነበሩ።
በወቅቱ እውን አንዳንዶቹ ፓርቲዎች በአጋጣሚ ማሸነፍ ቢችሉ እንዴት ነው ህዝብን መምራት የሚችሉት የሚለው የብዙዎች የኔ ቢጤዎቹ ጥያቄ ነበር። አንዳንዶቹ እንኳንስ ህዝብን ሊመሩ ቤተሰባቸውን በአግባቡ ስለመምራታቸው ጥያቄን የሚያጭር ነበር። ስለፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከህይወት ልምድ ተምረው ማገናዘብ የሚችሉ የማይመስሉ የፓርቲ አመራሮችን በዚያ ሁኔታ ተሰባስበው በአገር ጉዳይ ላይ ለመወሰን ሲቀመጡ ላየ ዴሞክራሲ ገደል መግባቱን ያረጋግጣል። የዴሞክራሲ ጥማትንም ያናጥባል።
በእንደዚህ አይነት ሁኔታ በአንድ አገር ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈጠራቸው እውን ለአገር ጠቀሜታ ይኖረዋል? የሚለው አጠያያቂ ሲሆን በተለይ በእንደእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ለህዝብ ምንም አይነት ፋይዳ የሌላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች መፈልፈላቸው ከትንሷ የአገር ኢኮኖሚ ላይ ለመቀራመት ካልሆነ በስተቀር ለህዝብ ጠቀሜታ አለው የሚል እምነት ያሳጣል።
አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ በአብዛኛው ሁለት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ ሆነው እናገኛቸዋለን። ፌዴራሊዝም እና አሃዳዊ ስርዓት። ፌዴራሊዝም የሚሉት ፓርቲዎች በአብዛኛው ብሄር ላይ ተንጠልጥለው “የኔ ብሄር በዚህ ጊዜ እንዲህ ሆኗል፤ ስለዚህ ከዚህ ጭቆና ለመውጣት እኔ አስፈልገዋለሁ” የሚል እንድምታ ያለው ሃሳብ ሲያቀነቅኑ ሌሎቹ ደግሞ “አሁን አገራችን በመፍረስ መንገድ ላይ ናት፤ ለዚህ ምክንያት ደግሞ አገራዊ አንድነት በመጥፋቱ ነው፤ ስለዚህ አገራዊ አንድነት እኔ ከሌለሁ አይመጣም” የሚል ጩኸት ያሰማሉ። ከነዚህ ሁለት ፅንፍ የወጡ ሃይሎች በተቃራኒ የቆሙና ሁለቱንም አቻችለው ለመሄድ የሚሞክሩ ፓርቲዎችም መኖራቸው ግን አይካድም፤ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም።
በርግጥ የአገራችን ህዝብ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ልቆ ሄዷል። አንዳንዶቹ ቢያንስ እንኳን ከህዝቡ ስልቦና ጋር አብረው መራመድ ያልቻሉና ላለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥኑ እንደሆኑ ማየት ይቻላል። ለዚህም አንዱ ማሳያ በዚህ ዘመን አንተ እንዲህ ሆነሃልና ተነስ ተዋጋ እስከማለት መድረሳቸው ነው።
በዚህ ሰው አልባ ድሮኖች በሚዋጉበት ዘመን ህዝብና ህዝብን በማጫረስ ትርፍ ለማግኘት የሚቀሰቅሱ ፓርቲዎችን ስናይ ከዚህ ውጭ ምን ልንል እችላለን።
አሁን በአገራችን የመጣው ለውጥ ካስገኘልን በረከቶች አንዱ የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት እንደሆነ ብዙዎች የሚስማሙ ይመስለኛል። ለምሳሌ በተለያዩ መንገዶች እስርና ተጠያቂነትን ፈርተው ከአገር ለቀው የኮበለሉ የፖለቲካ ሃይሎችና ግለሰቦች ጭምር ተመልሰው እንደልብ መንቀሳቀስ እና ከዚያም አልፎ እንደልብ መናገር የቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ይህችን የዴሞክራሲ ጭላንጭል እንዳናሰፋ በእንጭጩ ለመቅጨት የሚጥሩ አካላት በስፋት ተፈጥረዋል። በተለይ ለዘመናት አብሮ የኖረውን ህዝብ በመከፋፈልና አንዱ በሌላው ላይ ጥቃት እንዲፈጽም በማነሳሳት በአገሪቱ አለመረጋጋት እንዲፈጠር የተለያዩ አካላት እየሰሩ ይገኛሉ። ይህ ደግሞ የዴሞክራሲ ጠላት ነው።
አሁን አሁን በአገራችን በሚፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ ትልቁን ሚና የሚጫወቱት ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አክቲቪስቶችና ጊዜያቸውን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያፈሱ ስራ ፈቶች ናቸው። እነዚህ ሃይሎች በአገሪቱ የመጣውን ለውጥ በአንድ በኩል እንዲቀለበስና አገሪቱ ወደአለመረጋጋት እንድትገባ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለህዝብ እናስባለን በሚል ለራስ የፖለቲካ ትርፍ የሚደረጉ ሩጫዎች ናቸው።
በዚህ ሁሉ መሃል ግን ከአንድ መቶ የዘለሉት የፖለቲካ ፓርቲዎቻን ይህን አገራዊ ችግር ለመፍታት ከመጣር ይልቅ ሌላ ሩጫ ላይ ናቸው። አብዛኞቹም ከአገራዊ ሰላም መደፍረስ ይልቅ የራሳቸው ህልውና የሚያሳስባቸው ናቸው።
ለምሳሌ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ ማስፈረም ያለባቸውን የህዝብ ቁጥር ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ትልቅ መነጋገሪያ አጀንዳ እንደፈጠሩ ማየቱ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በቅርቡ ደግሞ ከኮሮና መከሰት ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማራዘም መወሰኑን ተከትሎ ያዙኝ ልቀቁኝ የሚሉ ፓርቲዎችና ግለሰቦች ታይተዋል። አንዳንዶቹም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ስልጣን ለመያዝ የሚዳክሩ ናቸው። ከፊሎቹ ደግሞ የጠፋ ድምጻቸው በዚህ አጋጣሚ እንዲሰማላቸው የሚታገሉ ናቸው። ምርጫ ከሰኔ ሰላሳ በኋላ መንግስት የለም ከሚለው አስተሳሰብ ብቻዬንም ቢሆን ምርጫ አካሄዳለሁ እስከሚለው አመለካከት ድረስ የታዩ ልዩነቶችም የዚሁ ማሳያዎች ናቸው። በአጠቃላይ በዚህ ወቅት የታየው ትርምስ እውን ዴሞክራሲን እየተለማመድን ወይስ እያጠፋን የሚል ጥያቄን ያጭራል።
በሌላ በኩል እነዚህ ፓርቲዎች እውን የሚከተሉት ርዕዮተዓለም አለ ወይ ብሎ ጥያቄ ለሚያነሳ አካል መልስ ሊያጣ ይችላል። ምክንያቱም እነዚህን ሁሉ ሊያስተናግድ የሚችል የተለያየ ሃሳብ የለምና። ከላይ እንዳነሳነው የዴሞክራሲ መገለጫዎች በራሳቸው ውስን ናቸው። ከዚያ ውጭ ካሆነ በስተቀር።
የሚገርመው አንዳንዳንዶቹ የፓርቲ አመራሮች ፓርቲን ትልቁ የገቢ ምንጭ ማድረጋቸው ነው። ለአንዳንዶቹ የፖለቲካ ፓርቲ ማለት ትልቁ የንግድ ተቋማቸው ነው። ትርፋቸው የሚለካው በህልውናቸውና በፓርቲው ውስጥ ባላቸው ስልጣን ልክ በመሆኑ ያን ማጣት አይሆንላቸውም። ለዚህ ነው አንዳንዶቹ ተዋሃዱ ሲባሉ ፈጽሞ የማይዋጥላቸው። መዋሃድ የሚለው የዶክተር አብይ ምክር ለአንዳንዶቹ የመሪነት ቦታውን የሚያሳጣቸው በመሆኑ አይፈልጉትም። የመሪነት ቦታውን ካልያዙ ደግሞ የሚፈልጉትን ለማግኘት ይቸገራሉ። በዚህ የተነሳ ከፓርቲ መሪነት ሲነሱ አዲስ ፓርቲ ወደማቋቋም የሄዱ እንዳሉም አይተናል።
ለዚህ ነው አንዳንዶቹ በሊቀመንበርነት ስልጣናቸው ላይ ሙጭጭ ብለው ለበርካታ አመታት የኖሩት። ይህንን ቦታቸውን በሆነ አጋጣሚ ከቢሮ ቢቀሩ እንኳን አያምኑትም። በዚህ የተነሳ ማህተሙን በኪሳቸው ይዘው የሚዞሩም እንዳሉ ይገለፃል። የካዝና ቁልፍን ማን ጥሎ ይሄዳል።
ነገር ግን አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ ከነዚህ የፖለቲካ ፓርቲዎች በላይ ነው። በዚህ የተነሳ እነሱን መደገፍ ማለት ገንዘቡን መርጨት መሆኑን ስለሚገነዘብ የገንዘብ ድጋፍ አያደርም። እነሱም ቢሆኑ የሃብት ምንጭ አድርገው የሚጠቀሙት ህዝብን ሳይሆን መንግስትን ነው። ይህ ገንዘብ ደግሞ በተዘዋዋሪ የህዝብ በመሆኑ በቀጣይ በትክክል ለህዝብ ከማይሰሩና ህዝብ ከማይፈልጋቸው ፓርቲዎች መንግስት እጁን መሰብሰብ አለበት።
በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እንዳሉት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት ቀለብ የሚሰፈርላቸው ናቸው። በመሆኑም መንግስት እነዚህን ጡረተኞች ከሚደግፍ ገንዘቡን ለሌላ ተግባር ቢያውለው የተሻለ ዴሞክራሲን ማረጋገጥ ይችላል።
ኢትዮጵያ አሁን ባለው ሁኔታ የሚያስፈልጋት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን በርካታ ባለሃብት ወይም የስራ እድል የሚፈጥሩ ዜጎችን ነው። ይህ ማለት ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች አያስፈልጉም ማለት አይደለም። ጥቂት ሃቀኛና ለህዝብ ጥቅም የቆሙ የፖለቲካ ድርጅቶች በቂ ናቸው። ከዚህ ውጭ ግን አንዳንዶቹ ፓርቲዎች ተደራጅተው ወደ ስራ ቢገቡ ወይም እስካሁን ያካበቱትን ሃብት አውጥተው በኢንቨስትመንት ቢሰማሩና ለሌሎች ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው የስራ እድል ቢፈጥሩ ከፓርቲ ስራ በላይ ነውና ቢያስቡበት መልካም ነው።
ይህ ባይሆንላቸው ደግሞ አርፈው መቀመጥም አንድ ነገር ነው። በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚገኙ እድሎችን ተጠቅመው ግጭት ለመፍጠር ከመጣር ወይም በፓርቲ ስም ህዝብን ከማደናገር ዝም ብሎ በያዙት ስራ ላይ ቢሳተፉ መልካም ነው። ምክንቱያም አሁን አገራችን ሁለት ነገር ያስፈልጋታል። አንደኛ ሰላም፤ ሁለተኛ ደግሞ ከዚህ ህዝቦቿ ከኮሮና ቫይረስ ተጠብቀው ችግሩን በማለፍ ነገ ለልማትና ለብልጽግና ዝግጁ መሆን። እነዚህ ጉዳዮች ከተስተካከሉ ኢትዮጵያ በህዝቦቿ ጥረት ከድህነት ለመውጣት በቂ አቅም አላት።
አዲስ ዘመን ሰኔ 5/2012
ውቤ ከልደታ