የፖለቲካ ምህዳር ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን በእጅጉ ሲያነጋግር ኖሯል፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የፖለቲካ ምህዳር መጥበብ እንዳይንቀሳቀሱ እግር ከወርች እንዳሰራቸው በመጥቀስ ሁሌም መንግስት ምህዳሩን እንዲያሰፋ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡
ገዥው ፓርቲ ችግሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ ነው ያለው እንጂ በሀገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ጥበት የለም እያለ የፓርቲዎቹን አቤቱታ ሲያጣጥል ቆይቷል፡፡ይህን እያለም አምስት ምርጫዎችንም አካሂዷል፡፡ በአንዳንዶቹ ምርጫዎችም ብቻውን እያሸነፈ ሀገሪቱን መርቷል፡፡
በሀገሪቱ ባለፈው አመት አጋማሽ ላይ ለውጥ ከመምጣቱ አስቀድሞ በነበሩት ሁለት እና ሶስት ዓመታት በየአቅጣጫው ተቀጣጥሎ የነበረው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ኢህአዴግ የፖለቲካ ምህዳር ጥበት መኖሩን እንዲቀበል አርጎታል፡፡ የምርጫ ምህዳር መጥበቡን እያመነ የመጣበት ሁኔታ ታይቷል፡፡ ይህንንም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በመወያየት አንዳንድ አዋጆች የሚሻሻሉበትን መንገድ መጥረግ ጀምሮም እንደነበር ይታወሳል፡፡ ለእዚህም የምርጫ ህጉን ለማሻሻል የተደረገውን ሙከራ መጥቀስ ይቻላል፡፡
የህዝብ ድምጽ መባከን የለበትም፤ በሚል የምርጫ ህጉን ለማሻሻል የሚያስችል ስምምነት ላይም ተደርሶም ነበር፡፡ በዚህም የምርጫ ሥነ ሥርዓቱ ከአብላጫ ድምጽ ወደ ቅይጥ የምርጫ ሥርዓት የሚመጣበት ሁኔታ ላይ ተደርሶም ነበር፡፡
ይህ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የመነጋገር እርምጃ በጸረ ሽብር ህጉ እንዲሁም በምርጫ ቦርድ ላይም ተጀምሮ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ይሁንና ኢህአዴግ እነዚህ ህጎች ምንም የማይወጣላቸው ናቸው ብሎ አጥብቆ ተከራክሮባቸዋል፡፡ በሀገሪቱ የተቀጣጠለውን ቁጣና አመጽ ተከትሎ የመጣው ለውጥ የዴሞክራሲ ምህዳርን የማስፋቱ ጉዳይ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ወሳኙ መሆኑን አስምሮበታል፡፡ በዚህም መሰረት የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ ከመሆናቸው በተጓዳኝ ህጎችን የማሻሻል ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበትም ነው፡፡
ለውጡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ሳቢያ በሀገር ውስጥ ታስረው የነበሩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን በመፍታት ፣ መሳሪያ አንስተው ይዋጉ የነበሩትን እንዲሁም በውጭ ሀገር ይንቀሳቀሱ የነበሩትን የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እንዲሁም አክቲቪስቶች ወደ ሀገራቸው ገብተው አመለካ ከታቸውን በነጻነት እንዲያራምዱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል፡፡
መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የማይከናወኑ ተግባሮች እንደሌሉ በተደጋጋሚ ሲያረጋግጥ በቆየው መሰረትም አላሰራ ያሉ ህጎችን የማሻሻሉ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ቀደም ሲል ኢህአዴግ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ሲወያይባቸው የነበሩትን የምርጫ ህጉን ፣የጸረ ሽብር ህጉን፣ የበጎ አድራጎትና ማህበራትን ህግን ጨምሮ ሌሎች ህጎችን ለማሻሻል እየተሰራ ነው፡፡
ለዚህ ስራም መንግስት በጠቅላይ አቃቤ ህግ የህግና ፍትሕ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ አቋቁሟል፡፡ ምክር ቤቱም የጸረ ሽበር ህጉን ጨምሮ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ገንባታ አንቅፋት ናቸው ተብለው የተለዩ አዋጆችንና ደንቦችን ለማሻሸል የሚረዱ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በእስከ አሁኑ ስራውም በርካታ ውጤታማ የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ መቻሉን የአማካሪ ጉባኤው ጽህፈት ቤት ጊዜያዊ አስተባባሪ አቶ አብዱላጢፍ ከድር ይናገራሉ።
የአማካሪ ጉባኤው መቋቋም
እንደ አቶ አብዱላጢፍ ገለጻ ፤ አማካሪ ጉባኤው የተቋቋመው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል በተውጣጡ ባለሙያዎች ነው፡፡ ባለሙያዎቹ በትምህርት ዝግጅታቸውም ከሁለተኛ ዲግሪ በላይ ባላቸውና በስራውም ብዙ ልምድ ያካበቱ እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል። በሌላ በኩል ደግሞ በዳኝነትና በጥብቅና ስራ የረጅም ዓመት ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችም እንዲካተቱ ተደርጓል፡፡ በመሆኑም የሙያና የብቃታቸው ጉዳይ የተረጋገጠ ነው።
እነዚህ ባለሙያዎች ደግሞ በጽህፈት ቤቱ ስራቸውን የሚያከናውኑት በትርፍ ጊዜያቸውና በነጻ መሆኑን ጠቅሰው፣ በስራቸው ዘጠኝ የስራ ክፍሎችን በመያዝ ለአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠቅም ተግባር እያከናወኑ ስለመሆኑ ይገልጻሉ።
ሥልጣንና ሃላፊነት
የጽህፈት ቤቱ ሥልጣንና ሃላፊነት ባለሙያዎቹንና ምሁራን ስራቸውን ቀልጣፋ ማድረግ፣ ማስተባበር፣ ቴክኒካል ድጋፍ መስጠትና የስራ አቅዳቸውን እንዲያዘጋጁ ማገዝ መከታታል ለአፈጻጸሙ የሚያስፈልጋቸውን የጥናትና ምርምር ስራ ማከናወንና ሌሎች ተዛማጅ ተግባራትን ማከናወን መሆኑን ያብራራሉ።
እስከ አሁን እንዲሻሻሉ ለጉባኤው የቀረቡና በመታየት ላይ ያሉ ህጎች በተለያየ ደረጃ ላይ ናቸው ያሉት አቶ አብዱላጢፍ፤ በተለይም ጉባኤው እንደተቋቋመ በሰኔና ሀምሌ ወሮች ውስጥ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ከመሆናቸውም በላይ አፋኝ ናቸው የተባሉ ህጎችን አይቶ እንዲያሻሽል ማድረግ የመጀመሪያው የስራ ትዕዛዙ ስለነበር በእዚሁ መሰረትም የጸረ ሽብር ህጉ፣ የሲቪል ማህበረሰብ እና የበጎ አድራጎት ህግ ፣ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ህጎችን ከህገ መንግስቱና ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር ያላቸውን አንድነትና ልዩነት በመፈተሽም ማሻሻያ እንዲደረግባቸው እየተሰራ ነው።
እያንዳንዱን ህግ በተገቢው ሁኔታ የማየትና የመፈተሽ እንዲሁም ከህገ መንግስቱና ከሌሎች ተያያዥ ህጎች ጋር የማመሳከሩ ስራ በጥንቃቄ እየተከናወነ ይገኛል።
እየተሻሻሉ ያሉ ህጎች
በአሁኑ ወቅትም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ረቂቅ አዋጅን የሚያሻሽለው ቡድን ስራውን ጨርሶ ረቂቅ አዋጁን ለጠቅላይ አቃቤ ህግ እና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ልኳል፡፡ እዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ተመክሮበት እንደሚጸድቅ ይጠበቃል ይላሉ።
ሌላው እየተሻሻለ የሚገኘው የጸረ ሽብር ህጉ መሆኑን ጊዜያዊ አስተባባሪው ጠቅሰው፣ የማሻሻሉ ስራ እጅግ አከራካሪ ሆኖ እንዳገኙት ይገልጻሉ፡፡
በአዋጁ ላይ በመርህ ደረጃ አሁን ባሉም መደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ህጎች ውስጥ ሽብርን ለመቆጣጠርም ሆነ ለመከላከል የሚያስችሉ በቂ ህጎች አሉ ብለው የሚከራከሩ ወገኖች መኖራቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ህጉ የሽብር ተግባርን ከመከላከል ይልቅ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ያጠባል እና አያስፈልግም የሚሉ ወገኖች እንዳሉም ያመለክታሉ፡፡ እነዚህ ወገኖች ሲሰራበት የነበረውም ይሄው ነው እንደሚሉ ይጠቅሳሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህጉ በብዙ አገሮች እንዳለ በመጥቀስ፣ የጸረ ሽብር ህግ እየተዳደሩና ችግሩም ሲከሰት በመደበኛው የወንጀለኛ ህጎች እያስተናገዱት ይገኛሉ የሚል ነው።
የጸረ ሽብር ህጉ ለስራ አስፈጻሚው በተለይም ደግሞ ለጸጥታ አካላት በምርመራ፣ በመረጃ አሰባሰብ እንዲሁም በሌሎች ተዛማጅ ስራዎች ላይ ከመደበኛው አሰራር በተለየ ሥልጣንና ሃላፊነት ይሰጣል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ የዳበረና ጠንካራ የፍትህ ተቋማት በሌሉበት ሰፊ ስልጣን መገኘቱ በጣም አደገኛ ከመሆኑም በላይ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በማለትም ለጊዜው የጸረ ሽብር ህግ ባይኖረን ብለው የሚከራከሩ አካላትም እንዳሉም ያብራራሉ።
ይህ ግን በጽህፈት ቤቱም ሆነ በአማካሪ ጉባኤው አያስፈልግም የሚል ድምዳሜ ላይ አልተደረሰም፤ ሆኖም የሚነሳውን ክርክር በጥናት ላይ እንዲንጸባረቅ በማድረግና ለጊዜውም ቢሆን በርካታ የቁጥጥር ሥርዓቶች ተቀምጠውለት በስራ ላይ ቢውል የሚል አቅጣጫ በመኖሩ በዚህ መሰረት ያሉትን ክፍተቶች የሚያሻሽል ረቂቅ እየተዘጋጀ መሆኑን ይጠቁማሉ። በቅርቡ የተረቀቀው የማረሚያ ቤቶች የማቋቋሚያ አዋጅ በድጋሚ አልቆ ለመንግስት መቅረቡን ይጠቅሳሉ፡፡
አዋጁን አሁንም በወንጀል ሥርዓት ላይ የሚሰራ የጥናት ቡድን እንደገና እንዲያየው እንዲደረግና ቶሎ ማሻሻያ እንዲያደርግበት የሚል ትእዛዝ በመተላለፉ ለቡድኑ መላኩን ያብራራሉ። ይህ ካለቀ በኋላ በድጋሚ የመጣና ቡድኑም በስራው መካከል አስገብቶ ይሰራዋል። ከዚህ አንጻር ሲታይ ስራው ጥሩ ከመሆኑ በተጨማሪ .ባለሙያዎቹም በፍጹም ፍቃደኝነትና ተነሳሽነት እየሰሩ ይገኛሉ ይላሉ ።
በአሁኑ ወቅት እንዲሻሻሉ በርካታ ህጎች መቅረባቸውን ጊዜያዊ አስተባባሪው ጠቅሰው፣ ከእነዚህ መካከልም ትልቅና ራሱን የቻለው በአምስት መጽሀፎች የተከፈለው የንግድ ህግ ፣ ሚዲያን የሚመለከቱ ሶስት የሚደርሱ ዋና ዋና አዋጆች እንዳሉ ይጠቁማሉ፣ በተጨማሪም አዋጆች ብቻ ሳይሆኑ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣቸው መታየት ያለባቸው ደንቦችና መመሪያዎች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ።
እንደ ጊዜያዊ አስተባባሪው ገለጻ፤ ትልቅ ትኩረትን በሚፈልገው የምርጫ ህጉ ላይ በተሻለ ፍጥነት ሰፊ ስራ እየተሰራ ነው። የምርጫ ቦርድን ለማቋቋም እንደገና የወጣው ረቂቅም ስራው ተጠናቅቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል። በቀጣይም የምርጫው ዋና ህግ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስነ ምግባር ደንብም አለ፡፡ እነዚህን ለማሻሻልም ጊዜውን ከግምት ውስጥ በማስገባት የስራ ቡድኑ የማሻሻያ ረቂቆችን ወደ ማዘጋጀት ገብቷል፤ ይህም በተቻለ ፍጥነት ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለሚመለከተው አካል ይቀርባል።
የአማካሪ ጉባኤው መተዳደሪያ ደንብ
በሌላ በኩል ደግሞ አማካሪ ጉባኤው መተዳደሪያ ደንብ በማዘጋጀት ማጽደቁን ጊዜያዊ አስተባባሪው ይገልጻሉ፡፡ የህብረተሰብ ተሳትፎ ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ይናገራሉ። በዚህም መሰረት ስራውን ከጀመረ አንስቶ ለምሳሌ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ህጎች ረቂቅ ሲዘጋጅ ችግሮቹ ሲለዩና የመፍትሔ ሃሳብ ሲሰበሰብ በሁሉም ክልሎች ተከታታይ የሆኑ የባለድርሻ አካላትና የህዝብ የምክከር መድረኮች ተደርገዋል። በጸረ ሽብር ህጉ ላይም እስከ አሁን ድረስ ከአምስት ያላነሱና የተለያዩ ደረጃዎች ያሏቸው መድረኮች ተዘጋጅተው ህብረተሰቡም ተሳታፊ ሆኗል።
የዴሞክራሲ ተቋማትን ህግ ለማሻሻልም በተለይም ከምርጫ ህጉ ጋር በተያያዘ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል ያሉት አስተባባሪው፣ ረቂቅ ደረጃ ላይ ከደረሰም በኋላ በነበሩ ተመሳሳይ መድረኮች ተሳትፎ ተደርጎባቸዋል ይላሉ።
ውጤታማነት
አቶ አብዲላጢፍ እንደሚሉት፤ ጽህፈት ቤቱ እያከናወነ ያለው ተግባር እስከ አሁን ውጤታማ ነው፡፡ እንደ አማካሪ ጉባኤም ሆኖ ስራውን በተሳካ ሁኔታ እየሰራ ነው። ሁሉም ስራዎች በታሰበውና በታቀደው ልክ እየሄዱ ላይሆን ይችላል፡፡ ስራው ወደ ኋላ ተጎትቶም ሊሆን ይችላል፤ የጸረ ሽብር ህጉን ለአብነት በመጥቀስ ሲያብራሩም ህጉ በአሁኑ ወቅት ይጠናቀቃል ተብሎ ታስቦ እንደነበር አስታውሰው፣ የመዘግየት ነገር እንደታየበት ያመለክታሉ፡፡ አብዛኛው ስራ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ።
የስራው ባለቤቶች በትርፍ ጊዜያቸው የሚሰሩ ከመሆኑ አንጻር አንዳንድ ጊዜ ጥልቅ የሆነ ጥናት ለማዘጋጀት መረጃ ለመሰብሰብ አስቸጋሪ ይሆናል፤ በሙሉ ጊዜያቸው ስራውን የሚያከናውኑ አካላትን ለማግኘት እየተሞከረ ከመሆኑም በላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሰዎችን ቀጥረው እንዲሰጡ ለማድረግም እየተሞከረ መሆኑን ነው የተናገሩት።
አሁን እየታየ ያለው የለውጥ መንገድ ብዙዎችን ያነሳሳ ከመሆኑ አንጻር ሌሎች ተጨማሪ ህጎች ይሻሻላሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ ደግሞ እነዚህ በትርፍ ጊዜያቸው እያገለገሉ የሚገኙት ምሁራንና ባለሙያዎችም ለስራው ከፍተኛ የሆነ ተነሳሽነት ያላቸው በመሆኑ ዝግጅቱ ምሉዕና ጥሩ ነው ለማለት ያስደፍራል ይላሉ።የህግ ማሻሻያ ብቻውን የዴሞክራሲና የነጻነት መንገድን ላያረጋግጥ እንደሚችል ተናግረው፣ ማሻሻሉ ግን በራሱ አንድ እርምጃ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰቡ ተሳትፎ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ያመለክታሉ። ህገ መንግስትን ማሻሻል የሚፈልጉ ጥያቄዎች እንዳሉም ጥናቶች ጠቅሰው ጊዜያዊ አስተባባሪው ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
እፀገነት አክሊሉ