በፈረንጆቹ አዲስ አመት መገባደጃ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ፅንፈኛውን የአይ ኤስ አይ ኤስ ቡድን እየወጋ ያለው 2ሺ የሚጠጋ የአሜሪካ ወታደር ድል በመጎናፀፉ ከቀጣናው ለቆ መውጣት እንዳለበት ውሳኔ ማስተላለፋቸው ይታወቃል፡፡ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱት ወታደሮችም ከቤተሰቦቻው ጋር እንዲሚገናኙና ርዝራዦቹ የአይ ኤስ አይ ኤስ ተዋጊዎች በቀሪዎቹ የአሜሪካ ወታደሮች እንደሚደመሰሱ አስታውቀዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ውሳኔ ከአሜሪካ ጋር በጥምረት አይ ኤስ አይ ኤስን እየወጉ ያሉ ሃይሎችንና በተለይም የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስትር ጂም ማሲስን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን ያስቆጣ ሲሆን በሶሪያ አይ ኤስ አይ ኤስን የሚወጋው የአሜሪካ ሃይል ልዩ መልእክተኛ በሬት ጉርክም የዶናልድ ትራምፕን ከሶሪያ እንውጣ ጥያቄ ተከትሎ ከስራ ሃላፊነታቸው በገዛ ፍቃዳቸው ለቀዋል፡፡
አንካራ ሽብርተኛ ነው ብላ የምታስበውና በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ የሚገኘው የአሜሪካ ኩርዲሽ ጥምር ሃይል የአሜሪካ ወታደሮች ከስፍራው ይለቃሉ ተብሎ በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ሃይሉ ለቱርክ ጥቃት ተጋላጭ ይሆናል በሚል ቀጣናው ውጥረት ውስጥ መግባቱን አልጀዚራ ትናንት ዘግቧል፡፡ ኩርዶቹ የሶሪያን መንግስት ለመደገፍና በተለይም በሰሜን ሶሪያ የምትገኘውን ማንቢጅ የተሰኘችውን ቁልፍ ከተማ ከቱርክ ጥቃት ለመከላከል ማድፈጣቸውንም ዘገባው ጠቁሟል።
እንደዘገባው ከሆነ የሶርያ የመንግስት ሃይል በቅርቡ በከተማዋ አቅራቢያ ታይቶ የነበረ ሲሆን ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነው የሰብአዊ መብት ቃኚ ቡድን የመንግስት ሃይሉ ከአሜሪካ ሃይል ጋር ግጭት ውስጥ ላለመግባት በሚል ከአካባቢው ማፈግፈጉን አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሳምንት በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ በኩርዶች ቁጥጥር ስር በምትገኘው ማንቢጅ ከተማ በደረሰ የቦምብ ጥቃት አራት የአሜሪካ የጦር ሃላፊዎች መገደላቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ይህን ተከትሎ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፒት ጣሂብ ኤርዶጋን የከተማዋን ፀጥታ ጉዳይ ለእኔ ተውት ሲሉ ትናንት ለአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልክ ሹክ ብለዋቸዋል፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ኤርዶጋን ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር በነበራቸው የስልክ መልእክት ልውውጥ እንደተናገሩት በማንቢጅ የአሜሪካ ሃይል ላይ የደረሰው ጥቃት የአሜሪካ ሃይል ከቀጣናው ይወጣል መባሉን ተከትሎ ፅንፈኛው የአይ ኤስ አይ ኤስ ቡድን አሁንም ተፅእኖው እንዳለ ለማሳየት የሰነዘረው ትንኮሳ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
በሳምንቱ መጨረሻ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባልተጠበቀ ሁኔታ 2 ሺ የአሜሪካን ወታደሮች ከሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ለቀው መውጣት እንዳለባቸውና ፅንፈኛው የአይ ኤስ አይ ኤስ ቡድን ሽንፈት እንደተከናነበ በይፋ የገለፁ ቢሆንም ይህ ሃሳባቸው ግን በመከላከያ ሚኒስቴር ሃላፊዎችና በአማካሪዎቻቸው ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘም፡፡ የአሜሪካን ከፍተኛ ባለስልጣናት ትራምፕ ውሳኔያቸውን ዳግም እንዲያጤኑና ወታደሮቹን ከሶሪያ ከማስወጣታቸው በፊት ቅድመ ሁኔታዎች እንዲያስቀምጡ ቢጎቶጉቷቸውም ቱርክ በበኩሏ የአሜሪካ ኩርዲሽ ጥምር ሃይልን ደህንነት ለመጠበቅ ዝግጁ ነኝ ስትል ተደምጣለች፡፡
የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ባለፈው ቅዳሜ ባደረጉት የስልክ መልእክት ልውውጥ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ በተፈጠረው የቀጣናው ውጥረት ዙሪያና በኩርድ ተዋጊዎች እጣ ፋንታ ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል፡፡ መሪዎቹ ባደረጉት የስልክ ውይይት አንድምታ ዙሪያም ተንታኞች የተለያዩ ሃሳቦችን እያንፀባረቁ ይገኛሉ፡፡
በኦክላሃማ ዩኒቨርሲቲ የመካከለኛው ምስራቅ የጥናት ማእከል ዳይሬክተር ጆሹዋ ሌንዲስ ‹‹የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሲፒት ጣኢብ ኤርዶጋን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ወታደሮች በሶሪያ መቆየት እንደማይፈልጉ በማወቃቸው ከፕሬዚዳንቱ የደህንነትና የውጭ ፖሊሲ ሃላፊዎች ጋር ከማውራት ይልቅ በቀጥታ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመነጋገር ፈልገዋል›› ሲሉ ለአልጀዚራ ገልፀዋል፡፡ ሆኖም በትራምፕ ዙሪያ ያሉ ሰዎች የአሜሪካን ሃይል በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ቆይቶ ፅንፈኛውን የአይ ኤስ አይ ኤስ ቡድንን እንዲወጋና የኩርድ ተዋጊዎችን እንዲጠብቅ ፍላጎታቸው ነው›› ሲሉ ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የአረብ ምርምርና ፖሊሲ ጥናት ማእከል የፖሊሲ ትንተና ዳይሬክተር ማርዋም ካብላን በበኩላቸው እንደሚገልፁት ከዋሽንግተን መራሹ የኩርድ ሚሊሻ ጋር ጥምረት የፈጠረው አሜሪካ መራሹ የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ሃይል (YPJ) ማንቢጅ የተሰኘችውን ከተማ ከፅንፈኛው እስላማዊ ቡድን አይ ኤስ አይ ኤስ በ2016 ተረክቧል፡፡ አንካራ ደግሞ በአሜሪካ የሚደገፈውን የኩርድ ተዋጊ ሚሊሻ ቡድን እንደ አሸባሪና በቱርክ ከአስር ዓመታት በላይ መሳሪያ ካነሳው የኩርዲስታን ሰራተኞች ፓርቲ (PKK) እንደ አንዱ ተቀፅላ አድርጋ ትቆጥረዋለች፡፡ የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ሃይል ከቦታው ለቆ ይውጣ ውሳኔ ደግሞ የቀጣናውን ውጥረት አባብሷል፡፡
የአልጀዚራው ዘጋቢ ኦስማን ቢን ጃቪድ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው የስልክ መልእክት ልውውጥ በሁለቱ የሰሜን እትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት አባል ሀገራት መካከል በዋሽንግተን መራሹ የኩርድ ተዋጊዎች ጉዳይ የተፈጠረውን የቃላት ጦርነት ተክትሎ የተከሰተውን ልዩነት ለመድፈን መሆኑን የጠቆሙ ሲሆን፤ የአሜሪካ ሃይል ከቀጣናው የሚወጣ ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ገልፀዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቱርክ ወታደሮች ቀጣናውን ስለሚፈልጉትና አሜሪካ መራሹ የኩርድ ተዋጊዎችም ከተማዋ በቱርክ መንግስት ቁጥጥር ስር እንዳትወድቅ በመፈለጋቸው የማንጂብ ከተማ የሁለቱ ሀገራት አጨቃጫቂ ቦታ ሆናለች ሲሉም ዘጋቢው ገልፀዋል፡፡ የአሜሪካ ሃይል ቀጣናውን ሲለቅ አልያም ቀጣናው ከአሜሪካና ቱርክ ውጪ የሚሆን ከሆነ ምንአልባት የኩርድ ተዋጊዎቹ ከሶሪያ የመንግስት ሃይል ጋር ሊቀላቀሉ እንደሚችሉም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
አሜሪካ መራሹ የኩርድ ተዋጊዎች ባለፈው ወር የሶሪያውን ፕሬዚዳንት በሽር አላሳድ ሃይል አካባቢውን እንዲጎበኝ ጥሪ ማቅረባቸው ምን አልባትም የቱርክ ሃይል ቦታውን እንዳይቆጣጠር ፍላጎት ስላላቸውና ከሶሪያ የመንግስት ሃይሎች ጋር ለመሆን ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ነው ሲሉ ኦስማን ቢን ጃቪድ ገልፀዋል፡፡
በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገውን የስልክ መልእከት ልውውጥ ተከትሎ ኤርዶጋን የማንጂብ ከተማን ደህንነት ለማስጠበቅ ያላቸውን ፍላጎት በተመለከተ ከነጩ ቤተመንግስት የተገለፀ ነገር ባይኖርም ሁለቱ መሪዎች በቀጣናው በሚፈልጉት ደህንነት ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በስልክ መልእክት ልውውጡ ወቅት በሶሪያ የቀረውን የአይ ኤስ አይ ኤስ የሽብር ቡድን ማሸነፍ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን እንዳሰመሩብት የነጩ ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ ሳራ ሳንደርስ ገልፀዋል፡፡ ሁለቱ መሪዎች ለሰሜን ምስራቅ ሶሪያ አሳሳቢ የደህንነት ጉዳይ አደራዳሪ መፍትሄ ለማምጣት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ መስማማታቸውንም ገልፀዋል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የጋራ ንግድ ልውውጥ ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ መስማማ ታቸውንም ቃል አቀባዩዋ ገልፀዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ ቱርክ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ በሚገኙ የኩርድ ተዋጊዎች ላይ ጥቃት እንዳትፈጽምና ጥቃቱን የምትፈፅም ከሆነም ለኢኮኖሚዋ ስጋት ሊሆን እንደሚችል ማስጠንቀቃቸውን ዘገባዎች ያስታወሱ ሲሆን የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሜቭለት ካቩሶግሎ በምላሻቸው ይህ ምንም የሚያስፈራ ጉዳይ እንዳልሆነና በቱርክ ኢኮኖሚ ላይም ምንም አይነት ስጋት የሚያሳድር እንዳልሆነ ገልፀዋል፡፡
የስልክ መልእክት ለውውጡን አስመልክቶ የቱርክ ፕሬዚዳንት ፅህፈት ቤት በበኩሉ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ሁለቱ መሪዎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው ሃላፊዎቻቸው መካከል ቀልጣፋ ውይይት በማድረግ በሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ተስማሚ ቀጣና ለመፍጠር መስማማታቸውን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ነገሩ ሳይሰፋ ተስማሚ ቀጣና መፈጠር እንዳለበትም በተመሳሳይ የጠቆሙ ሲሆን አሜሪካ መራሹ የሶሪያ ዴሞክሪያሳዊ ሃይል በበኩሉ ተስማሚ ቀጣና ለመፍጠር ዝግጅት መደረጉ የከፋ ባይሆንም የአሜሪካን ሃይል ከስፍራው የሚለቅ ከሆነ ግን አንካራ በቀጣናው አዲስ ጥቃት እንድትፈፀም አድል ሊፈጥርላት እንደሚችል ስጋቱን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
አስናቀ ፀጋዬ