
አለማችን ከስድስት ወራት በፊት የነበራት ሁለንተናዊ ጤና ዛሬ ተለውጣል ።በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የሚታየው፣ የሚሰማውና እየሆነ ያለው በእጅጉ ተለውጦ፣ ከማስደሰት ይልቅ የሚያሳቅቅ ሆኗል።ኮቪድ 19ኝም በቴክኖሎጂ የመጠቁ፣ በኢኮኖሚ የበለፀጉና በህክምና አገልግሎት አቅርቦትም ሆነ ጥራት ከፊተኞቹ ተርታ ስማቸው የሚጠራላቸው አገራትም ሳይቀር አቅም አሳጥቷል፡፡
በመላው አለም የሚገኙ አገራት የወረርሽኙን ስርጭትና ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ ከተቻላቸው ድል ለማድረግ ይረዳናል በሚል የሰዎች እንቅስቃሴ መገደባቸውና ድንበራቸውን መጠርቀማቸውም ከሁሉ በላይ የአለም ኢኮኖሚን ገፅታ በእጅጉ ለውጦታል፡፡
የአየር ትራንስፖርት ተቋርጦ አውሮፕላኖች ከሰማይ ወደ ምድር መውረዳቸው፣ በየእለቱ በሺዎች በሚቆጠሩ ተጓዧች የሚጨናነቁ አየር መንገዶችና የቱሪስት መዳረሻዎች ሰው አልባ መሆናቸው፣ ኮንፈረንሶች፣ ኮንሰርቶች፣ የስፖርት ውድድሮች እንዲሁም ሌሎች ግዙፍ ሁነቶች መሰረዛቸው ብሎም ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች ባዛሮች፣ ካፌዎች ዝግ መሆናቸውም አለምአቀፉን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ካረንቲን ውስጥ ከቶታል፡፡
ይህ ክስተትም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን አቅም ተማምነው ውለው የሚያድሩ አገራት ከዘርፉ የሚያገኙትን ረብጣ ገንዘብ እንዲያጡ በማስገደድ ብቻ ሳይወሰን በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎቻቸውን ስራ አልባ አድርጎባቸዋል፡፡የአለም ቱሪዝም ድርጅትም፣በዚህ አመት አለም አቀፍ የቱሪስት ቁጥር ከስልሳ እስከ ሰማንያ በመቶ እንደሚቀንስ ይፋ አድርጓል፡፡በቀውሱም ዘርፉ በቀጥታ በፈጠራቸው ስራዎች የተሰማሩ ከመቶ ሃያ ሚሊየን በላይ ሰዎች አደጋ ውስጥ እንደሚወድቁም ጠቁሟል፡፡
ወረርሽኙ ይበልጥ የበረታባቸው አውሮፓውያኑ አገራት በተለይ ጣሊያን፣ስፔንና ፈረንሳይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪያቸው በኮሮና ክፉ ቅጣት ተቀጥቷል፡፡አለም ላይ ምርጥ የተሰኙና ለወትሮው በበርካቶች የሚጨናነቁ የቱሪስት መስህቦችና መዳረሻዎቻቸውም ሰው ናፍቋቸው ተከርችመው ውለው አድረዋል፡፡ወራትንም አስቆጥረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወረርሽኙ ለወራት ከቆየበት አውሮፓ ፊቱን በማዞር ወደ ሌላ አህጉር በሚያስደነግጥ ፍጥነት በመገስገስና በመዛመት ላይ መሆኑ ታዲያ ጭንቅ ውስጥ ለቆዩት እነዚህና ሌሎች አገራት ትልቅ እፎይታ የሰጣቸው መስሏል፡፡
ግሪክና ስፔን የመሳሰሉ አንዳንድ አገራትም የተንኮታኮተ ኢኮኖሚያቸውን ከወደቀበት ለማንሳት ይረዳቸው ዘንድ ቀደም ሲል የወረርሽኙን ስርጭትና ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ ያስተላለፉትን ውሳኔዎች ማንሳት ጀምረዋል፡፡በተለይ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ የላቀ ስማ ያላቸው አገራት ‹‹በከፍተኛ ጥንቃቄ ቱሪስቶችን ለመቀበል ደፋ ቀና እያልን በመሆኑ መጥታችሁ ጎብኙን›› የሚል ጥሪ በማቅረብ ተጠምደዋል፡፡
ይህን ያስተዋሉ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃንም ሁለት አይነት አቋም አንፀባርቀዋል፡፡አንዳንዶች ዘርፉ ከሞት አፋፍ ተመልሶ በዳግም ትንሳኤ ላይ ስለመሆኑ አስረድተዋል።በርካቶች ደግሞ ‹‹ሌላው ቀርቶ ኢንዱስትሪው በሚቀጥሉት 18 ወራት ከራስ ምታቱ መሻር ከቻለ ትልቅ ስኬት ነው›› በማለት ብርቱ ሙግት ገጥመዋል፡፡
በተለይ የሁለተኛው እሳቤ አቀንቃኞች‹‹በአንዳንድ አገራት አለምአቀፍ ቀርቶ የአገር ውስጥ በረራዎች እንኳን በቅጡ አለመጀመራቸው እንዲሁም የበርካታ ቱሪስቶች ምርጫ የሆኑ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና የመዝናና ስፍራዎች ሙሉ በሙሉ ስራ ለመጀመር በሚያስችል ደረጃ ላይ አለመሆናቸው ኢንዱስትሪው አገገመ ለማለት ጊዜው በጣም ገና እንደሆነ በቂ ምስክር ይሆናል››እያሉ ነው ፡፡
የወረርሽኙን ስርጭት እንዴት መግታት ይቻላል የሚለው እስካልታወቀና የዚህ ፈተና መልስ የሚርቅ ከሆነም ዘርፉን ለመታደግ አስቸጋሪ መሆኑንና ኢንዱስትሪውን ዳግም ወደ ቀደመ ተክለ ቁመናው ለመመለስም ምናልባት የተጠቀሰው ጊዜ ራሱ በቂ ሊሆን እንደማይችል ገምተዋል፡፡
በርካታ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃንም አውሮፓን ማእከል ካደረገው ከዚህ ሙግት ይልቅ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኙ ለሌላ ጥፋት አህጉር መቀየሩ እጅጉና አሳስቧቸዋል፡፡ወረርሽኙ በተለይ በሌሎች አህጉራት ላይ የሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በአውሮፓ ምድር ካስመለከተውም የላቀና አሳሳቢ እንደሚሆን የሚገልፁት እነዚህ አካላት፣ በተለይ በቱሪዝም ኢንዱስትሪ ረገድ ለአፍሪካ መጪው ጊዜ ፈታኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በእርግጥም አለምአቀፍ ቱሪስትና ተጓዦችን መሰረት ያደረገውና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲራል ራማፉሳ፣‹‹አዲሱ ወርቅ››ሲሉ የሚያሞካሹት የአፍሪካ ቱሪዝም፣ ለአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ብሎም በህዝቦች የሚሰጠው ድጋፍ እጅጉን ግዙፍ ነው፡፡
ለአብነት ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና እኤአ በ2019 ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው አንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊየን ዶላር ገቢ ማግኘቷንና ዘርፉ አምስት ነጥብ አምስት በመቶ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻን እንደሚወስድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃም የቱሪዝም ዘርፉ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ ለመሳሰሉ አገራት በተናጥል አንድ ሚሊየን ለሚሆኑ ዜጎቻቸው የስራ ዋስትና መሆኑን ያመላክታል፡፡እንደ ሲቼልስ፣ ኬፕ ቨርዲ፣ ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንስፔ እንዲሁም ሞርሺየስን ለመሳሰሉ አገራት ደግሞ ከጠቅላላው የስራ እድል 20 በመቶ ድርሻ እንዳለው ይነገራል፡፡
አፍሪካም በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የበርካታ ቱሪስቶች ቀዳሚ ምርጫ መሆን መጀመሯ ይገለፃል።የአለም የቱሪዝም ድርጅት መረጃም ከሁለት አመት በፊት 67 ሚሊየን አለም አቀፍ ቱሪስቶች አፍሪካን መጎብኘታቸውንና አህጉሪቱም 38 ቢሊየን ዶላር ገቢ መሰብሰቧን ይጠቁማል፡፡
ድርጅቱ ይህ አለም አቀፍ የቱሪስቶች ፍሰት በ2019 በአራት ነጥብ ሁለት በ2020 ደግሞ ከሶስት እስከ አምስት በመቶ እንደሚጨምር ግምቱን አስቀምጦ ነበር፡፡ይህን ለማለቱ ምክንያትም የአህጉሪቱ የኢኮኖሚ እድገት እየጨመረ መምጣት.፣የአየር ትራንስፖርት ተደራሽነት እንዲሁም የዲጂታል ቴክኖሎጂው መጎልበትና ቪዛ ለማግኘት ቀላል መሆኑን በዋቢነት አስቀምጧል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ግን ይህን የድርጅቱ ግምት ፉርሽ አድርጎታል፡፡‹‹ወረርሽኙ የአፍሪካን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ክፉኛ በማንኮታኮት በርካታ ረብጣ ገንዘብ ነጥቋልም›› ተብሏል፡፡የተባበሩት መንግስታት ሪፖርትም በወረርሽኙ ምክንያት የአፍሪካ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ በቀጥታና በተዘዋዋሪ ፈጥሮት የነበረውን ሁለት ሚሊየን የስራ እድል ይነጥቃል ››ብሏል፡፡
የአፍሪካ ዋይልድ ላይፍ ፋውንዴሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ፣ካዱ ኪዌ ሰቡናይ፣ወረርሽኙ የአፍሪካ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በማንኮታኮት በተለይ በገጠር ለሚኖሩ ዜጎችና የዱር የእንስሳት ጥበቃና እንክብካቤ ስራዎች ላይ ከባድ ፈተና መጋረጡን በስፋት አትተዋል፡፡
ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ የጥበቃና የእንክብካቤ ስራዎች የሚሰሩት ከጎብኚዎች በሚገኝ ገቢ እንደመሆኑ የእነርሱ መቅረት እንስሳቶቹን ለረሃብና ለተለያዩ ጉዳቶች ከማጋለጥ ባሻገር ማእከላቱንም ለመዝጋት እያንደረደራቸው ይገኛል፡፡
እስካሁን ባለው ሂደት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአህጉሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ያሉበትን ገሃድ ችግሮችና ደካማ ጎኖች ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱ የሚያመላክቱ ምሁራን በአንፃሩ፣በአሁን ወቅትም ሆነ ከኮቪድ ቀውስ ማግስት የአፍሪካ ቱሪዝም ተጨማሪ የቤት ስራ እንዳሉበት አፅንኦት ሰጥተው በማስረዳት ተጠምደዋል፡፡
ሲ ኤን ኤን ፀሐፊ አይሻ ሳሉዲን፣ያነጋገረቻቸው የደቡብ አፍሪካ የቱሪዝም ቦርድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሲሳ ሾና ፣የወረርሽኙን መዳከም ተከትሎ ድንበሮች ሙሉ በሙሉ ቢከፈቱ እንኳን የጉዞ እንቅስቃሴው ከወትሮው በተለየ ዘገምተኛ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን እንደሚገባና አፍሪካም ይህን መንቀራፈፍ ፈር ለማስያዝ ራሷን ማደስ እንደሚኖርባት አብራርተዋል፡፡
‹‹የጉዞ እንቅስቃሴው የሚጀመረው ቀስ በቀስ ከመሆኑ ባሻገር ሰዎች ከአገራቸው ከመውጣት ይልቅ የእንቅስቃሴ ነጻነቱን ለማጣጣም ቅድሚያ በአገራቸው ከተሞች መንቀሳቀስን ያስቀድማሉ፣ይህ እስከሆነም ከአህጉራችን ውጪ የሚገኙ ቱሪስቶችን ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ ይወስዳል›› ብለዋል፡፡
ዋና ስራ አስፈፃሚው ይህን ፈተና ለመሻገር አፍሪካውያን አገራት ማድረግ አለባቸው የሚሉትን ሲያመላክቱም፣‹‹ከኮሮና ወረርሽኝ ማግስት በርካታ አገራት ቱሪስቶችን ወደ ራሳቸው ለመጥራት እርስ በእርስ ብርቱ ፉክክር ውስጥ መግባታቸው አይቀሬ ነው፣ይህ እስከሆነም አፍሪካውያን ከሁሉ በላይ መዳረሻዎቻቸውን ይበልጥ አማላይ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል››ብለዋል፡፡
አፍሪካውያን አገራት የወቅቱንና ቀጣዩን ትውልድ ጎብኚ ፍላጎትና ስሜት በጠበቀ መልኩ የቱሪዝም አገልግሎት ስለማሻሻልና ዘርፉ ይበልጡን ተጠቃሚ ለመሆን ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥተውታል፡፡በአሁኑ ወቅት አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ዲጂታላይዝድ እየሆኑ መምጣታቸውን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን መከወን ለዚህም በእጅጉ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አስምረውበታል፡፡
በጋና ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስ ትምህርት መምህሩ ኮቢ ሜንሻም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የአፍሪካ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ያሉበትን ገሃድ ችግሮችና ደካማ ጎኖች ቁልጭ አድርጎ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡‹‹እኛ ምእራባውያን ሙሉ በሙሉ ጥገኛ ሆነን ቆይተናል፤ ይህ በራሱ አደጋውን ከፍተኛ ያደርገዋል የሚሉት መምህሩ፤ ኮቪድ 19 መከሰትም የአህጉሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ይበልጥ ማሻሻል ፣የአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን በአህጉር አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማሳለጥ እና ማስተዋወቅ ግድ እንደሚል ትልቅ ትምህርት መስጠቱን አብራርተዋል፡፡
ኢሳኩ አዳም እና አልበርት ኪምባ የተባሉ የዘርፉ ምሁራን ዘ ኮንቨርዜሽን ላይ ባሰፈሩት ሰፊ ሀተታ፣የአፍሪካ ቱሪዝም ከኮሮና ወረርሽኙ ቁስል ለማገገም ስለሚያስፈልጉት የመፍትሄ አቅጣጫዎችም አመላክተዋል፡፡
አገራት ማድረግ ከሚኖርባቸው ዋነኛ ተግባራት መካከል በተለይ በወረርሽኙ ስጋትና በተዛባ አመለካከት በተለያዩ የቱሪስት መዳረሻዎች ቦታዎች አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ጎብኚዎችን በአግባቡ ያለማስተናገድ ብሎም የማግለል አዝማሚያ ሊያስመለክቱ ስለሚችሉ፣እነርሱን የማስተማርና የማረም ተግባር ማከናወን የግድ ይላል›› ብለዋል፡፡
እንደ ባለሙያዎቹ ምክር ሃሳብ፣የጎብኚዎችን እምነት ለማግኘትና ምርጫ ለመሆን ወረርሽኙ ነባራዊ ሁኔታና ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር ያለውን መሻሻል በየእለቱ ማሳወቅ ያረዳል፤ለዚህም መደበኛና የተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በመጠቀም ልዩ ልዩ ማስታወቂያዎችን መስራት ይገባል፡፡
አገራት የዘርፉ ተዋናዮች ተስፋ ሳይቆርጡ በስራቸው እንዲቀጥሉ ለማድረግ የታክስ ማሻሻያን ጨምሮ የተለያዩ የቅናሽ ማበረታቻዎችን መስጠት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡የአገር ውስጥ ብሎም አህጉራዊ የቱሪዝም ጉዞ ትስስር እንዲጠናከር፣ ማስታወቂያዎችን መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
ምንም ያህል የወረርሽኙ ቆይታ ቢረዝም በዘርፉ ውስጥ የተሰማሩ ሠራተኞችን መቀነስ ከባድ ስህተት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ይህን እሳቤ የሚጋሩት ግብፃዊው የቱሪዝም ባለሙያው አቲፍ አብዱላቲፍም፣ ከስራ የሚርቁ ሠራተኞች ቁጥር ከተበራከተ ወረርሽኙ መፍትሄ አግኝቶ ዘርፉ ወደ ቀድሞ ተክለ ቁመናው በሚመለስበት ጊዜ የሰለጠኑ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች እጦት ሊያሰቃየው ይችላል›› ብለዋል፡፡
አፍሪካውያን ከሁሉ በላይ አስደማሚና ውብ የቱሪስት መዳረሻዎቻቸውን ይበልጥ ማስተዋወቅና ገበያ ማፈላለግ እንዳለባቸው ባለሙያዎቹ አፅንኦት ሰጥተውታል፡፡‹‹በተለይ የቱሪስቶች ምርጫ የሆኑ አገራት ጎብኚዎችን ለማግኘት ብርቱ ፉክክር ስለሚያደርጉ አፍሪካውያን ከሌላው ጊዜ በተሻለ ልቀው መታየትና ምስላቸውን መሸጥ አለባቸው››ተብሏል፡፡
ኢትዮጵያ በአለም ላይ ከፖስት ኮቪድ19 በኋላ የቱሪስት መዳረሻ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ አገራት ከግንባር ቀደሞቹ አንዷ ናት፡፡ምስራቅ አፍሪካዋ ትልቅ አገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ መሪነት የጀመረቻቸው አስደማሚ ፕሮጀክቶችም በአለም ስታንዳርድ ተወዳዳሪ ብቻ ሳይሆን ቀዳሚም ከሚባሉት ውስጥ ሆነዋል።አገሪቱም በአሁኑ ወቅት መዳረሻዎቻቸውን ይበልጥ አማላይ በማድረግና ማራኪ መልኳን በማስተዋወቅ ላይ ትገኛለች:: ሌላው በአለም አቀፍ ደረጃ አፍሪካውያን ሊያደርጉት ይገባል የተባለው አብይ ጉዳይ ቢኖር ለደህንነት በተለይም ለጤና ንፅህና ቅድሚያ መስጠት ነው፡፡ከሁሉም በላይ የጉብኝት መዳረሻ ቦታዎችንና ሆቴሎችን የፀረ ተህዋሲያን በመርጨት ለጎብኚዎች ምቹ ከባቢን መፍጠር አለባቸው ተብሏል፡፡
ግብፅና ኢትዮጵያን የመሳሰሉ አገራትም ይህን የፀረ ተህዋሲያን ርጭት በማስጀመር ቀዳሚ ሆነዋል።ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት አንጋፋውን ብሄራዊ ሙዚየሟን ፀረ ተህዋሲያን በመርጨት ለጎብኚዎች የጤና ደህንነት እንደምትጨነቅ አሳይታለች፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2012
ታምራት ተስፋዬ