የያዝነው የጥር ወር ለኢትዮጵያውያን ልዩ ስፍራ አለው፡፡ ወቅቱ ታላላቅ በዓላት የሚከበሩበት ነው፡፡በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የጥምቀት በዓል ዋናው ነው፡፡ በዋዜማው የሚከበረው የጥምቀት ከተራ በዓል፣ በማግስቱ የሚከበረውም የቃና ዘገሊላ በዓል ሌሎች የወሩ ድምቀት ናቸው፡፡
በተለይ ለጥምቀት ብዙ ይባልለታል፡፡ ለእሱ የማይደረግ እንደሌለ ለመግለጽም ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ ይባላል፡፡አባባል ይሁን እንጂ ዘንድሮም ነገር አለሙ እንደዚያው ነው፡፡ አዎን የከተራን፣ጥምቀትን ቃና ዘገሊላን በዓል የታደመ በእርግጥም ዘንድሮም እነዚህ በዓላት በክት ልብስ ደምቀው መዋላቸውን ይመሰክራል፡፡
በየጥምቀተ ባህሩ ያለው የሰው ብዛት ሲታይ በየቤቱ ሰው የቀረም አይመስል፡፡ ጭፈራው ፣ መጊያጊያጥ መኳኳሉ ይበዛል፡፡ ወጣቶች የሚፈላለጉበት አልፎም ተርፎ የሚተጫጩበት፣ የደስታና የፈንጠዝያ ወር ነው፡፡ከህጻን እስከ አዛውንት ገጠር አይል ከተማ ሁሉም ጽድት ብሎ አምሮ እና ተውቦ የጥምቀትን በዓል ያከብራል፡፡
በበዓሉ ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ አምሮና ደምቆ ነው የሚታየው፡፡ የባህል ልብሳችን ትንሳኤ የሚታየውም በእነዚህ በአላት ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በተለይ ሴቶች በእጅጉ ደምቀው ይታዩበታል፡፡ በሴቶቻችን ላይ የባህል ልብሶቻችን ብቻ አይደሉም የታዩት፡፡ የሴቶችን ልብሶች የሚያዘጋጁ ሸማኔዎች፣ እነዚህን ልቦሶች የሚያዘጋጁ ዲዛይነሮቻችንም ይታያሉ፡፡ ዲዛይነሮቻችን በእርግጥም የባህል ልብሶች ትንሳኤን አረጋግጠዋል፡፡
የሴቶቻችን የባህል ልብሶች ጥበብ ነበር የሚባሉት፡፡አሁን ደግሞ ከጥበብም ጥበብ ሆነው ረቀዋል፡፡የሰይጣን ጆሮ አይስማ ቢባልም ምን ያደረጋል ሰማውና ይህ ጥበብ የሚያበላው እንጀራ ያጓጓት ቻይናም በዚህ ስራ ውስጥ ገብታለች፡፡የባህሉን ልብስ በርካሽ ዋጋ ገበያ ውስጥ ለቃዋለች እየተባለም ይወራል፡፡ ሰውን ማልበሳቸው ባልከፋ ነበር፡፡ ሸማ በመስራት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኘውን ወገን ጦም ሊያሳድሩ መሆኑ ግን ያሳስባል፡፡በእርግጥ የኛ ሸማኔዎችና ዲዛይነሮች የሚቆልሉት ዋጋ ለቻይና መግቢያ ቀዳዳ ያበጃላት ይመስላል፡፡ታዲያ ይህን ቀዳዳ በመድፈንም ነው ቻይናን መኮነን የሚገባው፡፡
ህዝቡ ሊገዛ በሚችልበት ዋጋ ልብሱን ማቅረብ ያስፈልጋል፡፡ይህን ለማድረግ ደግሞ አመራረትን ማዘመን የግድ ይሆናል፡፡ ሁሉም ነገር በሰው ህይል በሚከናወንበት ሁኔታ ልብሱን ሰው ሊገዛ በሚችለው ዋጋ ማቅረብ አይቻልም። ቻይና በሰው ሰርታ አይደለም በርካሽ ገበያ ውስጥ የለቀቀችው፡፡በዘመናዊ መንገድ ሽምና ነውና ይታሰብበት፡፡ ብቻ የባህል ልብሱ በዓሉን ሰዎቹን እድምቋል፡፡ ያደመቁት ይድመቁ ከማለት በላይ ምንማለት ይቻላል፡፡
የጥምቀት በዓል ብቻ አይደለም የጥር ወርን የተለየ የሚያደርገወ፡፡ ከመስከረም አንስቶ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ለመጀመሪያ መንፈቀ አመት ፈተና የሚዘጋጁበትና የሚፈተኑበት ወሳኝ ወርም ነው። ከዚያም እረፍት የሚወጣበትም ነው፡፡እናም ተማሪዎች ለፈተናችሁ በሚገባ መዘጋጀት ይኖር ባቸዋል፡፡ ተረጋግተው በመፈተንም የድካማችሁን ውጤት ማየት ይኖርባችኋልና አስቡበት፡፡
የጥር ወርና ተከትለው የሚመጡት ጥቂት ወራት በተለይ ለአርሶ አደሩ የሚኖራቸው ትርጉምም ከፍተኛ ነው፡፡አርሶ አደሩ ገናውን ጥምቀቱን ወዘተ በድምቀት ያከብራል፡፡እነዚህ በአላት ከመንፈሳዊ ፋይዳቸው በተጨማሪ ወቅቱ የአዝመራ መሰብሰቢያ ወቅት እንደመሆኑ በተለይ አርሶ አደሩ ቤቱ ሙሉ መሆን የሚጀምርበት እና ጥጋብ የሚሆንበት ነው፡፡
አርሶ አደሩ በዚህ በጥር ወር በእጅጉ ይደምቃል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ብዙ ህዝብ ይደምቃል ማለት ነው፡፡ እንዴት ማለት ደግ ነው፡፡ በሀገራችን እየበዛ ያለው ከተሜነት ምን ያህል የአርሶ አደሩን ህይወት እንደቀየረው መረጃው ባይኖረኝም ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣው ከሀገራችን ህዝብ 85 በመቶው አርሶ አደር ነው ይባላል፡፡በእርግጥ ከተሜነቱ ይህን አሀዝ ዝቅ አርጎት ካልሆነ በቀር እንዳደጉት ወይም በማድግ ላይ እንደሚገኙት ሀገሮች ኢንዱስትሪው ገጠሩን ‹‹የሚገዳደርበት›› ሁኔታ የለም፡፡ ኢንዱስትሪው ገና በዳዴ ላይ እንደመሆኑ የገጠሩን ህዝብ አሀዝ ለመቀነስ አይችልም፡፡ እናም በገጠር ያለው አርሶ አደር በዚያም ተባለ በዚህ ከተሜው በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡
እርሶ አደር ሲሰራ አፈር ሲበላ ሰው መስሎ እንዲሉ ነው ኑሮው፡፡ በክረምት ወይም በስራ ወቅት እሱን የተመለከተ ምን ያህል ተጎሳቁሎ ይቆያል፡፡ እናም አርሶ አደር በክረምት ዝናብ፣ ጭቃ፣ብርድ ፣ ወዘተ ሳይል ሲያርስ ሲዘራ፣ ሲያርም ፣ሲኮተኩት፣ በበጋ እስከ ጥር ባለው ጊዜ ጸሀይና ሀሩር ሳይል ሲያጭድ፣ ሲከምር፣ ሲወቃ፣ ወዘተ. ነው የሚታየው፡፡
ይህ አርሶ አደር ከዚህ ከጥር ወር አንስቶ ወደ እርሻው እስከሚመለስ ድረስ ትንሽ ፋታ የሚያገኝ እንደመሆኑና ምርቱንም ለገበያ የሚያቀርብበት ስለሆነ ኪሱም ሞላ የሚልበት ወቅት ነውና ፈታ ማለትንም ያዘወትራል፡፡
ሰው የሚመስለው አዝመራው ከተሰበሰበ በኋላ ነው፡፡ ይህ ወቅት ደግሞ እንደየ ስነ ምህዳሩ ቢለያይም ጥር ወርን ይዞ ያለው ወቅት ነው፤ እነዚህ ወራት አርሶ አደሩ አደባባይ የሚወጣባቸው ወቅቶች ናቸው፡፡ በመስኖ እርሻ፣ በከብት እርባታ፣ በጓሮ አትክልት ልማት በአካባቢ ጥበቃ፣ ወዘተ ስራ የሚያሳልፈው ጊዜ እንዳለ ሆኖ በእነዚህ ወራት ዘና ይላል፡፡
አርሶ አደሩ በአንጻራዊ መልኩ ያርፋል ተብሎ የሚታሰበውም በእነዚህ ወቅቶች ነው፡፡ ወሩ ከእሸት ፣ከቃርሚያ ፣ወዘተ እየተወጣ አዝመራ የሚታፈስበት፤ ጎተራው የሚሞላበት፣ ገበያው የሚደራበት ነው፡፡
አርሶ አደሩ ገንዘብም መቁጠር የሚጀምረው ከዚህ ወር አንስቶ ባሉት ጥቂት ወራት ነው፡፡ በእነዚህ ወራት ያማረውን ያደርጋል፡፡ የሚላወስበት ገንዘብ የሚያገኘው በዚሁ ወቅት ነውና አመቱን ሙሉ ሲያመው የከረመውን በሽታውን ይታከማል፤ የሩቅ ለቅሶም ካለ ይደርሳል፡፡ በክረምቱ ወቅት የተበደረው ካለም እዳውን የሚከፍለው በዚሁ ወቅት እህል ሸጦ ነው፡፡
ልጁን የሚድረው፣ መልስ ቅልቅል የሚጠራው ይህንኑ ወር ይዞ ባሉት ወራት ነው፡፡ በእነዚህ ወቅቶች የሚያጨውም ያጫል፤ የሚፈላለገውም በጋብቻ የሚተሳሰረው በዚሁ ወቅት ነው፡፡
የሰርግ ዝግጅቱ ልዩ ነው፡፡ ድግሱ፣ ጥሎሹ፣ ጎጆ መውጫው፣ መሞሸሪያው፣ ጌጣ ጌጡ ብዙ ነው፡፡ ለድግሱ የሚያስፈልገው እህል ከማሳው ከጓሮው ሊገኝ ቢችልም፣ የተቀረው ወጪ ግን እህል ወይም ከብት እየተሸጠ ነው የሚሸፈነው፡፡
ወቅቱ እህል በስፋት ለገበያ የሚቀርብበት እንደ መሆኑ ዋጋው ደግሞ ለአርሶ አደሩ ብዙም አዋጭ አይደለም፡፡ ነጋዴው በዚህም በዚያም ብሎ በርካሽ እህሉን እንደሚቀበለው ይታወቃል፡፡ ሁሉንም ለመከወን ሲል ግን እህል፣ ከብት መሸጥ ይኖርበታልና ይሸጣል፡፡
ሰርጉ እንደየ እምነቱ የሚከወን ሲሆን፣ በክርስትና እምነት ተከታዩ ዘንድ ለሰርጉ ጠላው ይጠመቃል፡፡ ጠጁ ይጣላል፤ ይታረዳል፡፡ የሰርግ ጥሪውም አይነት አይነት አለው፡፡ ጥሪው በልጃችን የጋብቻ ስነ ስርዓት ላይ በመገኘት የደስታችን ተካፋይ ሁኑ የሚል ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ባዘጋጀነው ምሳ ወይም እራት ላይ ተገኙልን የሚል ሊሆንም ይችላል፡፡
ሰርግ ተበልቶና ተጠጥቶ ነፍስ ይማር አይነት ነገር ተብሎ የሚወጣበት ተዝካር አይለም፤ ሁሌም ሁሉም ቤት ባይሆንም ለሚድረው፣ ለተዳረው ትንሽም ቢሆን መስጠትን ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ሰርግ የሚሄደውም ባዶ እጁን ላይሄድ ይችላል፡፡ ለጎጆ መውጫ የሚሆን እቃ ይዞ ወይም ለአባትና እናት የሚሆን ገንዘብ ተይዞ ይኬዳል፡፡ አሁን አሁን ከተቻለ በግል አልያም በመዋጮ አንድ ነገር ይደረጋል፡፡ መጠኑ እንደቅርበቱ ይወሰናል፡፡
እናም አርሶ አደሩ ብዙ ወጪ አለበት፡፡ ማህበራዊ ጉዳይ ቢሆንም፣ ወጪን መቆጠብ ግን ይገባል፡፡ሰኔ ፣ሀምሌ እና ነሀሴ ለአርሶ አደሩ ከባድ ወቅቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የሚከብዱት ደግሞ በእቅድ ባለመመራት በሚመጣ ችግር ሳቢያ ነው፡፡ ይህን ችግር ለመፍታትም ወጪ እና ገቢ እያጤኑ በመጠን መኖር ሁነኛ መፍትሄ ነው፡፡
በአንጻሩ ወቅቱ የአዝመራ ወቅት የሚባል እንደመሆኑ ጥሩ ጥሩ ነገሮች የሚሰሩበት ከመሆኑ በተጓዳኝ ፣ ገበያ በብዛት የሚወጣበት ነው፡፡ በመሰረቱ በገበያ ላይ ብዙ ነገሮች ይገኛሉ፡፡ በዚህ ወቅት ለእርሻ ስራ የሚያስፈልገው ዘር ወይም ማዳበሪያ አይገዛም፡፡ የሁለቱ ግዥ ወደ ሰኔና ሀምሌ ነው የሚፈጸመው፡፡ በዚህ ወቅት የሚፈጸመው ግዥ የልብስ ፣ የቁሳቁስ፣ እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡በእርግጥ የከብት ግዥ ሊፈጸም ይችላል፡፡
ገበያው ገንዘብ ስለተገኘ ብቻ የማይገባ ግዥ የሚፈጸምበት ሲሆን ይታያል፡፡ ሀብት ክፉኛ የሚጠፋበት ወቅት ነው፡፡ ባለ ልክ ይጠጣል፤ ይበላል፤ ችግሩ በዚህ ብቻም አያበቃም፡፡ በመጠጥ በመነሳሳት በሚፈጸም ድርጊት ህይወት ይጠፋል፤ አካል ይጎድላል፤ በቀል ይረገዛል፤ ወዘተ.
ለስንት ልማት እርሾ የሚውል ሀብት ለፈንጠዝያ በመዋሉ ሳቢያ የአርሶ አደሩ ህይወት ወደ ኋላ ይጎተታል፡፡ አሁን አሁን እንጃ እንጂ ዱሮ በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ ወንድማማቾች አንድ አይነት ቴፕ ፣ካሴት ይገዙ ነበር ሲባል ሰምቻለሁ። ሁሉም ታዲያ ሰኔ አካባቢ እያወጡ እንደሚሸጡም ይነገር ነበር፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ አንድ አይነት ነገር ለማዳመጥ ነው ይህን ያህል ወጪ የሚወጣው፡፡ ብልህነቱ ቢኖርምን ህል ወጪን መቆጠብ እንደሚቻል ከዚህ እንረዳለን፡፡
አንዳንድ አርሶ አደሮች የሰበሰቡት ምርት የሚያልቅ አይመስላቸውም፡፡ በዚህ የተነሳም ሆድ እንዳረጉት ነው የሚለው ይረሳቸዋል፡፡ ከመቆጠብ ይልቅ ካለልክ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ፤ ሌላም ሌላም ነገር ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ አርሶ አደሮች ታዲያ ሰኔና ሀምሌ ላይ ዘር የሚቸገሩ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው በእቅድ አለመመራትን፣ የቁጠባ ባህል አለመዳበሩን ነው፡፡ ከጠንካራ አርሶ አደሮች ተሞክሮ አለመቅሰምንም ያመለክታል፡፡
አርሶ አደሩ ድግስን በጥንቃቄ መመልከት ይኖርበታል፡፡ ልጁን መዳሩ፣ ማህበር ማውጣቱ፣ ወዘተ መልካም ነው፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር አብሮ እንዲራመድ የሚያስችለው ቢሆንም አቅሙን እያየ በልክ የሚያደርግበትን ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል፡፡ የሰው ሰርግ ስበላ ኖሬ ብሎ ልጁን ድል ባለድግስ ለመዳር የሚሞክር ከሆነ ከድህነት አረንቋ ውስጥ መውጣት አይችልም፡፡የድግስ ማህበራዊ ፋይዳው ከፍተኛ ቢሆንም ጠልፎ የሚጥል መሆኑ ግን መረሳት የለበትም፡፡ ማህበራዊ ህይወት እንዳይጎሳቆልም መጠንቀቅ ይገባል፡፡
አርሶ አደሩ ለዘመናት አዝመራውን ከሰበሰበ በኋላ የእርሻ ስራ እስከሚጀመር ባሉት ወራት ስራ ፈት ሆኖ ኖሯል፡፡ በእነዚህ ወቅቶች አጥሩን ያጠባብቅ፣ ከብቶቹን ይመለከት፣ ካልሆነ በቀር ብዙም የማያላውሰው ስራ ሳይኖረው ቆይቷል፡፡አሁን እንደዚያ አይነት ነገር የለም፡፡ የመስኖ አርሻ ተፈላጊነት ጨምሯል፡፡ ወንዝ በመጥለፍ ፤ውሃ በማቆር ፣ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር እና ውሃ በማውጣት የመስኖ ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው፡፡ አርሶ አደሩ በአመት እስከ ሶስት ጊዜ የሚያመርትበት ዘመን ላይ ይገኛል፡፡
ይህን ለማድረግ አርሶ አደሩ በመስኖ ልማት ምርጥ ተሞክሮ ወዳላቸው አርሶአደሮች ሄዶ ልምድ እንዲቀስም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ልምድ ላይ በመመስረትም በክረምት ወቅት ውሃ ማጠራቀም፣ አሊያም ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በመቆፈር ወደ መስኖ ልማቱ መግባት አለበት፡፡ ይህን ስራ ለአርሶ አደሩ አንዴ ማሳየት ከተቻለ ቀጣይ አተገባበሩን እሱ ያውቅበታል፡፡
የቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት አባል በመሆን እየቆጠበ ጥሪት ማፍራት ይኖርበታል፡፡ ቁጠባው ከግብርና ስራው በተጓዳኝ የንግድ ስዎችን እና ግብርናውን በዘመናዊ መንገድ ለማካሄድ ይረዳዋል፡፡
ግብርናው መዘመን እንዳለበት ይታመናል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ አርሶ አደሩ ካለችው ሀብት እየቆጠበ ጥሪት መያዝ ሲችል ነው፡፡ ለመበደር መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ዛሬ የቁጠባ ማህበራት በየገጠሩ ገብተዋል፡፡ ከአፉ እየከፈለ በመቆጠብ ይበልጥ ሰው ሊሆን የሚችልበትን እድል ማስፋት ይኖርበታል፡፡
ነጋዴዎች ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ እንደማይሰጡ ይታወቃል፡፡ ገበያው ደላላ በደላላ ሆኗል፡፡ በእዚህ የተነሳም አርሶ አደሩ በራሱ ችግር ብቻም ሳይሆን በደላሎች ሳቢያ የልፋቱን ዋጋ ማግኘት አልቻለም፡፡ ለዚህም መፍትሄው በየአቅራቢያ ይገኛል፡፡ምርቱን ላቋቋማቸው የህብረት ስራ ማህበራት በማስረከብ ለምርቱ ተገቢውን ዋጋ ማግኘት ይችላል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥር ወር የተፋሰስ ልማት የሚጀመርበት ወቅት እየሆነ መጥቷል፡፡ የተፋሰስ ልማቱ አፈርን ይጠብቃል፡፡የደን ልማትን ለማካሄድ ያስችላል፡፡በዚህ ስራ ሀገራችን የተጎዳ መሬቷ እንዲያገግም እያደረገች ነው፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደኑ እያገገመ ሲሆን፣ የነጠፉ ምንጮች ውሃ መስጠት እየጀመሩ ነው፡፡ይህ ሁሉ በአርሶ አደሩ ጥረት የመጣ ለውጥ ነው፡፡
አርሶ አደሩ ይህን ውጤታማ የተፋሰስ ልማት አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በዚህም ለዘመናት በከንቱ ሲያልፍ የኖረው የጥር ወር መጠቀሙ ብልህነት ነው፡፡ የጥር ወርን ከእረፍትና ፈንጠዚያ በሻገር መመልከት ማለት ይሄው ነው፡፡
እናም አርሶ አደር ሆይ ጥርን ይዞ ባሉት ጥቂት ወራት አንጻራዊ እረፍት የምታገኝ ቢሆንም፣ ምርት በመሰብሰብህም ገንዘብ ማየት ብትችልም ደስታህን በልክ አድርገህ ወደፊት የምትደሰትበትን ዘመን በማሰብ ጥሪት ለማፍራት ትጋ፡፡
ገንዘብ ስር የለውም የሚለውን የአባቶችን ብሂል አስታውስ፡፡ ገንዘብ እየሰሩ በአናት በአናቱ ካልጨመሩበት እየተመዘዘ ያልቃል፡፡ እናም ጥርን የስራም የቁጠባም ወር አድርጋትና የአንተንም የቤተሰቦችህንም ህይወት ተለውጦ አይተን ደስ ይበለን፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
ዘካርያስ