
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ትናንት በሰጠው መግለጫ የታጠቀው የድርጅቱ ሀይል ወደ ካምፕ እንዲገባ አዟል፡፡ የድርጅቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አራርሶ ቢቂላ ከኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኦነግ ያለፈውን እና ወደፊት የሚያጋጥሙትን እድሎች በማገናዘብ የትጥቅ ትግል ምዕራፍን በመዝጋት ሰላማዊ ትግልን መምረጡን ጠቅሰው፣ ይህንንም ውሳኔ የድርጅቱ አባላት፣ ታጥቆ የሚንቀሳቀሰው ሀይል እና ደጋፊዎች አክብረው መቀበል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
እርስ በእርስ መጋጨት፣ መካሰስ፣ መወነጃጀል እና መተኳኮስ ቀርቶ አሁን የተገኘው ለውጥ መሬት መያዝ አለበት ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፤ ችግሮቻችንን በውይይት እንፈታለን ሲሉም አስታውቀዋል።
ድርጅቱ የደረሰበት ውሳኔ የሚደነቅና መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ለተያያዘው ጥረት ወሳኝ ሚና የሚጫወትም ነው፡፡ ሀገሪቱ ከሰላማዊ ትግል ውጪ የፖለቲካ አቋም የሚራመድባት እንዳልሆነች የተረጋገጠበትም ነው፡፡ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ከመቆራቆስ ወጥተው ለሰላማዊ ትግል ብቻ ይበልጥ እንዲሰሩ የሚያደርግ ይሆናል፡፡
ድርጅቱ የታጣቂዎቹን እርምጃ እንዲያስቆምና ወደ ሰላማዊ ትግል እንደመጣ በኦሮሚያ ክልል መንግስት፣ በፌዴራል መንግስት እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች እና አባ ገዳዎች የተደረጉት ጥረቶች ከብዙ ጉዳት በኋላም ቢሆን ፍሬያማ መሆን ችለዋል፡፡
ድርጅቱ የትጥቅ ትግል በቃኝ ብሎ ወደ ሀገር ቤት የገባው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁንና ባለፉት ወራት ታጣቂዎቹ ከዚህ ያፈነገጠ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ በዚህም በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ ያሉ አካባቢዎች ክፉኛ ተጎድተዋል፡፡ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም መተላለፊያ አጥቶ ቆይቷል፡፡ መንግስት ይህን ችግር ለመፍታትም ከብዙ ሰላማዊ አማራጮች በኋላ ወደ እርምጃ መውሰድ የገባው፡፡
መንግስት ታጣቂዎቹ ይንቀሳቀሱ የነበሩበትን አካባቢ ሰላም ወደ ቀድሞው ለመመለስ በትኩረት እየሰራ ባለበት ወቅት ነው ድርጅቱ ሰላማዊ የትግል አማራጭን እንደሚከተል በማስታወቅ ታጣቂዎቹን ወደ ካምፕ እንዲገቡ ያዘዘው፡፡ይህም የድርጅቱ ታጣቂዎች ያደርሱ በነበረው ጥቃት ሳቢያ ሰላም አጥተው የቆዩት አካባቢዎች ህዝቦች ሰላም እንዲመለስ ያስችላል፡፡
የድርጅቱ እርምጃ በአካባቢውና በድርጅቱም ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ የተወሰደ ቢሆንም፣ ለሰላም የተከፈለ ዋጋ ነውና በአድናቆት ሊታይ ይገባል፡፡ይህን እርምጃ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የድርጅቱ ታጣቂዎች፣ አባላት እና አመራሮች ድርጅቱ ባቀረበላቸው ጥሪ መሰረት ስለ ሰላም ጠንክረው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን በከፈሉት መስዋዕትነት አዲስ የለውጥ ጎዳና ከቀየሱ ወደ አስር ወራት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ተከውነዋል፡፡የፖለቲካውን መስክ ብንመለከት እንኳ ሀገሪቱ ስትከተል በቆየችው ጠባብ የዴሞክራሲ ምህዳር ሳቢያ አመለካከታቸው በማራመዳቸው ብቻም ሳይሆን ለማራመድ በማሰባቸው ጭምር ለእስር እና ለስደት ተዳርገው የነበሩ ዜጎች ከእስር ተላቀዋል፤ ከስደት ተመልሰዋል፡፡ ነፍጥ አንስተው ጫካ የገቡትም መሳሪያቸውን እያስቀመጡ አመለካከታቸውን በነጻነት ለማራመድ ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡
ለውጡ ሀገሪቱን የሀሳብ ብዝሃነት የሚራመድባት አድርጓታል፡፡ ዛሬ በሀገሪቱ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች እየተንቀሳቀሱ ሲሆን፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያስችሉ የህግ ማሻሻያዎች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ መንግስት መጪውን ምርጫ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማድረግ ቃል ገብቶ እየሰራ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ወደ መምከር ገብተዋል፡፡
ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የተለያዩ ወገኖች በሀገሪቱ ይስተዋል የነበረውን ህገወጥ ድርጊት በማውገዝ መንግስት የህግ የበላይነትን እንዲያስከብር ሲያቀርቡ የቆዩትን ጥሪ መንግስት መመለስ ጀምሯል፡፡ በዚህም የሐገር ሀብት በመዝረፍ የተጠረጠሩ ወገኖች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል፡፡ ለሰላም መደፍረስ ምክንያት የሆኑም እንዲሁ እየተጠየቁ ናቸው፡፡
አሁን ኦነግ የደረሰበት ውሳኔ ደግሞ ይህ የመንግስት ጥረት ይበልጥ ስር እንዲያዝ ያደርጋል፡፡በተለያዩ ወገኖች ዘንድ አድሮ የነበረውን ስጋት በማስወገድም ትኩረት ወደ ልማት እንዲዞር ያደርጋል፡፡
መንግስት ኢኮኖሚው ላይ አተኩሯል፡፡ በሀገሪቱ የግብር ገቢ እየቀነሰ ነው፤ የወጪ ንግዱ የሚጠበቅበትን እየፈጸመ አይደለም፤ የብድር ጫና፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የሐገሪቱ አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው፡፡ ሀገርን የሚያሳድጋት እነዚህንና መሰል ችግሮችን በመፍታት በትክክለኛው የልማት ጎዳና መጓዝ ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ ሰላም ወሳኝ ሚና አለው፡፡ በመሆኑም ሁሉም ወገን ኦነግ እንደወሰደው እርምጃ ሁሉ ለሰላም መከበር ሚናውን መወጣት ይኖርበታል፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011