የመንግስት የሥልጣን ጊዜ እንዲራዘም እና ዘንድሮ ይካሄድ የነበረው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ በኮሮና ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) ምክንያት እንዲራዘም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ጸደቀ፡፡ በተቋማት ላይ እምነት ሊኖርና ትችት ሲቀርብ መረጃ ላይ ሊመሰረተ እንደሚገባም ተጠቁሟል፡፡
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ትናንት ተጀምሯል፡፡ ምርጫን በሚመለከት የተመለከተው ምክር ቤቱ፤ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በአራት አባላት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ እና በ114 አብላጫ ድምጽ አጽድቋል፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ (ኮቪድ 19) የሕዝብ ጤና ስጋት ሆኖ ባለበትና የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጸንቶ በሚቆይባቸው ጊዜያት እና ከተነሳም በኋላ አዲስ ምርጫ ተካሂዶ የስልጣን ርክክብ እስኪፈጸም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የክልል ምክር ቤቶችና የፌዴራልና የክልል አስፈጻሚ አካላት የስራ ዘመን እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡
የኮቪድ 19 ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ወረርሽኝ አለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የጤና ድርጅቶች የሚያወጡትን
መረጃ መሰረት በማድረግ የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የሳይንሱ ማህበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበትና ይህም በሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ከዘጠኝ ወራት እስከ አንድ አመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሄድም በህገ መንግስት ትርጉም እና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡
የሁሉም ክልል አባላት በተወከሉበት የተከፈተው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት 6ኛውን አገራዊ ምርጫ ስለማራዘም አስመልክቶ አጣሪ ጉባኤው የህገመንግስት ትርጉም ጉዳይ ላይ ውይይት አድርጓል፡፡
በእለቱም ህገ መንግስቱ የመንግስት የስልጣን ጊዜ ገደብን በግልጽ አስቀምጦ ሳለ ወደ ህገ መንግስታዊ ትርጓሜ መገባቱ አስፈላጊ አይደለም የሚል ሃሳብ ተነስቷል፡፡ ምርጫውን ማራዘም ህገ መንግስትን እንደመጣስ እንደሚቆጠር፣ ህገመንግስት ከተጣሰ ደግሞ አገር እንደሚፈርስ እንዲሁም ሂደቱ የህዝብን ሉአላዊ ስልጣን መጣስ ይሆናል በማለት ከምክር ቤት አባላት የተነሳ ክርክርም ተደምጧል፡፡
ህገመንግስቱ አምስት አመት ብሎ ያስቀመጠው የሥልጣን ገደብ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መምጣት፣ መተርጎም አልነበረበትም ተገቢም አይደለም የሚል ክርክር ተነስቷል፡፡ ወረርሽኙ አደገኛ ቢሆንም ጥንቃቄ በማድረግ ማካሄድ ይቻላል፣ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርገው ካካሄዱ አገራት ተሞክሮ ተቀምሮ መካሄድ ነበረበት የሚል ሃሳብ ተነስቶም ነበረ፡፡ መንግስት ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅት አልነበረውም፣ በአጭር ጊዜ የተካሄደና ብዙ ባለሙያዎች ያልተሳተፉበት ነው ሲሉም ሂደቱን ተቃውመውታል ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ መንግስት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ አቋም ይዞና የጊዜ ሰሌዳም ወጥቶ እንደነበረ፣ የተከሰተውን ወረርሽኝ ተከትሎም በክልልና በፌዴራል ምርጫ ለማካሄድ ስልጣን ያለው ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል የውሳኔ ሃሳብ ማቅረቡ ተነስቷል፡፡
የተለያዩ አማራጮች ቀርበው የሕገ መንግስት ትርጉም የሚለው ተመርጦ ስልጣን ላለው የህገ መንግስት አጣሪ ጉባኤ መመራቱም ተጠቁሟል፡፡ ‹‹ምርጫ እንዲካሄድ የምንከራከረውን ያህል ለሕዝብ ደህንነትና ጤና መከራከር ይገባናል›› በማለትም ከምክር ቤት አባላቱ ሃሳብ ቀርቧል፡፡
ነጻ ፍትሃዊና አሳታፊ ምርጫ ለማድረግ አስቻይ አይደለም፣ ትርጓሜ መጠየቁ እጅግ በጣም ትክክለኛ ነው፣ የሕዝብና የአገር ደህንነት መቅደም አለበት በሚል የህገ መንግስትና ማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ደግፈው በርካታ አባላት ተከራክረዋል፡፡
ትርጉም አያስፈልግም የሚለው ሕግን ካለማወቅ የሚመነጭ መሆኑንም የጠቆሙም ነበሩ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ባለፉት 27 ዓመታት በተደጋጋሚ ሲጣስ እንደነበረ በማመልከትም፤ ውሳኔው ጉባኤው በተሰጠው ስልጣን መሰረት የቀረበ በመሆኑ ተቀባይነት አለውም ብለዋል፡፡
ለህዝብና ለአገር ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባል፣ ምርጫ ማካሄድ የሚቻለው ህዝብ ሲኖር ነው፣ አስቸኳይ ጊዜ በታወጀበትና የሕዝብ እንቅስቃሴ በተገደበበት ሁኔታ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ያስቸግራል፣ የትኛውም ክልል ለእዚህ አደጋ መዳረግ የለበትም፤ ህገ መንግስት ከተጣሰ አገር ይፈርሳል የሚለው ሃሳብ ሌላ ዓላማ አለው የሚሉና መሰል ሃሳቦችም ተነስተዋል ፡፡
የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ፤ ጉባኤው በተሰጠው ስልጣን ተጠቅሞ ከባለሙያዎች ማብራሪያ መውሰዱን፣ ከህግ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተቋማት ማሳተፉንና በዘርፉ ከፍተኛ እውቀትና ልምድ ያላቸውን፣ ምርምር የሰሩ፣ ህገ መንግስቱ ሲረቀቅ የተሳተፉና የህገ መንግስት ባለሙያዎችን መጋበዛቸውን አስታውቀዋል፡፡ከ30 በላይ ባለሙያዎች ተሳትፎ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ለ20 ቀናት በተደረገው ውይይት ሶስት ሃሳብ መነሳቱን የጠቆሙት ወይዘሮ መአዛ፤ ጉባኤው ጉዳዩን ለማየት ስልጣን የለውም፣ ህገ መንግስቱ ግልጽ በመሆኑ ህገ መንግስት ትርጉም አያስፈልግም የሚልና አገሪቱ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር የምትገኝ በመሆኗ የታገዱ መብቶችን በመጠቀም ምርጫ ማራዘም ይቻላል የሚሉ አስተያየቶች መቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡
ከሕገ መንግስት መፍትሄ ይገኛል ብሎ መነሳት ትክክል መሆኑን፣ በእዚህ ሂደት ደግሞ የዳበረ ልምድ አለመኖሩን አንስተዋል፡፡ ሕገ መንግስት የሚተነተንና የሚስፋፋ ሰነድ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻም የመንግስት ስልጣን መራዘም እና የጤና ሚኒስቴር፣ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የሳይንሱ ማህበረሰብ አካላት ወረርሽኙ የሕዝብ ጤና ስጋት አለመሆኑን ካረጋገጡበትና ይህም በምክር ቤት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ ከዘጠኝ ወራት እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርጫው እንዲካሄድ የውሳኔ ሃሳቡ መቅረቡን አመልክተዋል፡፡
በተቋማት ላይ እምነት ሊኖር ይገባል ያሉት ወይዘሮ መአዛ፤ አጣሪ ጉባኤው በከፍተኛ ሃላፊነት እና የህግ መተርጎም ስራ ተግባሩን ማከናወኑን አመልክተዋል፡፡ ገና በዴሞክራሲ ጅምር ላይ የምትገኝ አገር እንደመሆናችን ትችት ሲቀርብ መረጃ ላይ የተመሰረተ ቢሆን የተሻለ ይሆናል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 4/2012
ዘላለም ግዛው