79 ዓመታትን ያስቆጠረው አንጋፋው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ዛሬ ያለበት ደረጃ ለመድረስ ብዙ ሂደቶችን አልፏል፤ በርካታ ለውጦችንም አስተናግዷል። በሙያው የሰለጠኑ ጋዜጠኞች ባልነበሩበት በቀደመው ዘመን ከነበረው አሰራር በመውጣት ጋዜጣውን ለመለወጥም ሆነ ሙያውን ለማሳደግ የተከፈለው ዋጋ ቀላል አይደለም። ታዲያ አዲስ ዘመን ጋዜጣም ይሁን አጠቃላይ ሙያው በኢትዮጵያ ዘመናዊ መልክ እንዲይዝ ግንባር ቀደም ሚና ከተጫወቱት ባለሙዎች መካከል ገና በጠዋቱ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ትምህርትን በምዕራቡ ዓለም ተምረው ሙያውን ለማዘመን በዋጋ የማይተመኑ ታላላቅ አስተዋፅዖዎችን ያበረከቱት አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ አቶ ነጋሽ ገብረማርያም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ።
ነጋሽ የተወለደው በ1917 ዓ.ም አርሲ ውስጥ ነው። ሦስት ዓመት ሲሆነው እናቱ ሐረርጌ ውስጥ ይኖሩ ወደነበሩትና ፊታውራሪ አሊ ወደተባሉት አያቱ ዘንድ ወሰዱት። በዚያም እስከ 11 ዓመቱ ድረስ ቆየ። ታላቅ ወንድሙ አቶ አሰፋ ገብረማርያም በስራ ምክንያት ወደተለያዩ ስፍራዎች ሲዘዋወሩ እርሱም አብሮ ይንቀሳቀስ ነበር። በመጨረሻም መዳረሻውን አዲስ አበባ አድርጎ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገባ።
በትምህርቱ ጎበዝ የነበረው ነጋሽ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላም ብሪቲሽ ካውንስል (British Council) ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ከፍቶ ስለነበር እዚያ ገብቶ ለሁለት ዓመታት ተምሮ በዲፕሎማ ተመረቀ።
ከዚያም ወደ ጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተመድቦ ለአንድ ዓመት ያህል አስተማረ። ነጋሽ ለእረፍት ከጅማ ወደ አዲስ አበባ እንደመጣ ያጋጠመው እድል የቀደመ ምኞቱን ለማሳካት መልካም አጋጣሚን የፈጠረለት ነበር። ነጋሽ ቀደም ሲል ኮተቤ ትምህርት ቤት ገብቶ የመማር ፍላጎት ነበረው። ለእረፍት ወደ አዲስ አበባ የመጣበት ጊዜ ደግሞ ኮተቤ መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተማሪዎችን ፈትኖ ከሚቀበልበት ቀን ጋር ተገጣጠመ። ፈተናውን ተፈተነ፤ አለፈ። በተቋሙም ለሦስት ዓመታት ያህል ተምሮ ሰርቲፊኬት ተቀበለ።
ብዙም ሳይቆይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስለተከፈተ ዩኒቨርሲቲውን ተቀላቀለ። ለሁለት ዓመታት ያህል እንደተማረ በወቅቱ በወደብ አስተዳደር (Port Administration) ትምህርት የሰለጠነ የተማረ የሰው ኃይል ይፈለግ ስለነበር የንድፈ ሃሳብ ትምህርቱን አጠናቀቀ። በተግባርም ጅቡቲ፣ ምፅዋ እና ኤደን ባህረ ሰላጤን በመርከብ እየተዘዋወረ የስራውን ሁኔታ ተመለከተ። ሁሉንም ካጠናቀቀ በኋላም ሰርቲፊኬት ተቀበለ። ይሁን እንጂ የስራው አካባቢ ሞቃታማ ስለነበር በስራው ሳይቀጥል ቀረ። በዚህ ወቅት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለሁለት ዓመታት ሰርቷል።
በመቀጠልም አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ የመረጃ አገልግሎት ቢሮ የቤተ መጽሐፍትና የትርጉም ሰራተኛ በመሆን ተቀጠረ። በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥም ለሦስት ዓመታት ያህል እንደሰራ የስራ ትጋቱንና አመርቂ አፈፃፀሙን የተገነዘቡት አሜሪካዊ አለቃው «አሜሪካ አገር ለትምህርት እንላክህ ወይንስ ደመወዝ እንጨምርልህ?» የሚል ጥያቄ አቀረቡለት። ነጋሽም ወደ አሜሪካ ለትምህርት መሄድን መረጠ። በዚህም መሰረትም እ.አ.አ በ1955 ወደ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ አቀና።
ነጋሽ ሞንታና ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ለማጥናት የመረጠው ከልጅነቱ ጀምሮ ይመኘው የነበረውን ደራሲ የመሆን ሕልሙን ያሳካልኛል ያለውን ጋዜጠኝነትን ነበር። ለአንድ ዓመት ያህል ከተማረ በኋላም ተጨማሪ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ቆይቶ እንዲማር ዩኒቨርሲቲው ፈቀደለት። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶም ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን አግኝቶ ባነጋገሩት ወቅት በመንግስት በጀት ተጨማሪ ሁለት ዓመታትን ተምሮ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለስና ሙያውን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ አድርጎ እንዲያደራጅ ታዘዘ። ነጋሽም በድጋሚ ወደ አሜሪካ በመሄድ በጋዜጠኝነት የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝቶ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።
ነጋሽ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰ የተቀጠረው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ነበር። የተመደበውም የእንግሊዝኛው ‹‹ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ (The Ethiopian Herald)›› ጋዜጣ ላይ ሲሆን ምደባውም በፍላጎቱ የተከናወነ ነበር።
በወቅቱ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ አሜሪካዊው ደቪድ ታልቦት ነበሩ። ነጋሽ የእንግሊዝኛው ጋዜጣ ላይ ብዙም አልቆየም። የወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ብላታ ግርማቸው ወልደኃዋርያት « … መሻሻል የሚገባው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ስለሆነ ለምን ወደዚያ አትሄድም? …» የሚል ጥያቄ አቀረቡለት። ነጋሽም በሚኒስትሩ ሃሳብ ተስማምቶ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ መስራት ጀመረ።
የጋዜጣው ስራ ከምስረታው ጀምሮ በልምድና በፍላጎት ብቻ ይከናወን ነበር። ሰራተኞቹ (ጸሐፊዎቹ) የቤተ ክህነት ትምህርት የተማሩ እንጂ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ትምህርትና ስልጠና ያላቸው አልነበሩም። ታዲያ ይህን አሰራር በመለወጥ የጋዜጣው አቀራረብና ይዘት የሙያ መርሁን የተከተለ ማድረግ ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ትምህርትን በምዕራቡ ዓለም ተምረው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰው ነጋሽ ገብረማርያም ይጠበቅ ነበር።
ነጋሽ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅነቱን ኃላፊነት «የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት አባት» ተብለው ከሚታወቁት ከብላታ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንስ በመረከብ ወደ አሜሪካ አቅንተው የተማሩትን ዘመናዊ የጋዜጠኝነት ትምህርት ወደ ተግባር ለመቀየር ጥረታቸውን ጀመሩ። ክብደት ያላቸውና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዜናዎች አጠር ተደርገው የመጀመሪያ ገፅ ላይ እንዲሆኑ፤ ጋዜጣው አቋሙን የሚገልፅበትና ‹‹ርዕሰ አንቀጽ›› የሚል የአማርኛ ስያሜ ያለው ክፍል እንዲኖረው፤ የጋዜጣው ተቋማዊ አድራሻና የአዘጋጁ ስም በጋዜጣው ላይ እንዲገለፅ፤ የጸሐፊዎች ስም (Byline) ከጽሑፉ ርዕስ ቀጥሎ እንዲሰፍር እንዲሁም ጋዜጣው ተጨማሪ አምዶች እንዲኖሩት አደረጉ።
ቀደም ሲል በጋዜጣው ላይ ተቀላቅለው ይፃፉ የነበሩት ሃቅ/እውነት (Fact) እና የግል አስተያየት (Opinion) ልዩነት እንዳላቸው በማሳየት፤ ሁለቱ የጽሑፍ ዓይነቶች የየራሳቸው የአጻጻፍ ደንብና ቦታ እንዲቀመጥላቸውም አድርገዋል። ከዚህ በተጨማሪም ማስታወቂያዎችም ለማስታወቂያ በተመደቡ ገፆች ላይ እንዲወጡ አድርገዋል። በአጠቃላይ አቶ ነጋሽ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቀደም ሲል ከነበረው የይዘትና የአቀራረብ ቁመና በብዙ መልኩ እንዲለወጥና እንዲሻሻል አድርገውታል። የጋዜጣው ለውጥም በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
የእለት ጋዜጣው ወደ ማተሚያ ቤት ከተላከ በኋላ አቶ ነጋሽ በቢሮ ውስጥ በሰቀሉት ጥቁር ሰሌዳ ላይ በጠመኔ እየጻፉ ለወቅቱ ጋዜጠኞች የጋዜጠኝነት ስልጠና ይሰጡ ነበር። ይህ በራሳቸው ተነሳሽነት ያከናወኑት ተግባራቸውም ተወደደ። ጋዜጠኞች በየእለት ስራቸው የሚገጥሟቸውን ሙያዊ ችግሮች እንዴት መፍታት እንደሚችሉ ሲጠይቋቸው እርሳቸውም ካላቸው ልምድና በውጭ አገር ከቀሰሙት እውቀት በመነሳት ጥያቄዎቻቸውን ይመልሳሉ፤ ዘመናዊ የአጻጻፍ ስልትን ጨምሮ ሌሎች የሙያውን ሕግጋትንም ያስተምሩ ነበር።
የጋዜጣው የፊት ገፅ የንጉሰ ነገሥቱ ምስልና እርሳቸውን የተመለከቱ ጉዳዮች ብቻ በዝርዝር የሚስተናገዱበት የጋዜጣው ክፍል ነበር። ምንም እንኳ ሹማምንቱ ባይወዱትም አቶ ነጋሽ ይህን አሰራር በመቀየር ጋዜጣው ዘመናዊ/ሙያዊ መንገድን እንዲከተል ጥረት ያደርጉ ነበር። የአንባቢያን አስተያየቶች በጋዜጣው የውስጥ ገፆች ላይ ቦታ አግኝተው እንዲስተናገዱም ታግለዋል። ከብዙ ጥረት በኋላም አቶ ነጋሽ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የጀመሩት ለውጥ ጋዜጠኞችንም ሆነ የመንግሥት ሹማምንትን እያግባባ ሄደ።
ይሁን እንጂ በወቅቱ የነበረው ሳንሱር (Censorship) አቶ ነጋሽ የጋዜጠኝነትን ሙያ በፈለጉትና በተማሩት ልክ ተግባራዊ እንዲያደርጉት አላስቻላቸውም። በወቅቱ ስለ ረሃብ፣ ስለ ፍትህ መጓደል፣ ስለ ጭሰኛው መበደል፣ ስለ ኮንትሮባንድ በአጠቃላይ የንጉሰ ነገሥቱን መንግሥት ‹‹መልካም ስም›› ስለሚያጎድፉ ተግባራት መፃፍ ያስቀጣ ነበር።
አቶ ነጋሽ ስለጉዳዩ ሲያስረዱ «… ሳንሱር ከሚበረታባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የፓርላማ ውይይትን መዘገብ ነው። በፓርላማ ላይ የ‹መሬት ላራሹ› ጉዳይ ተደጋግሞ ይነሳ ነበር። የሚወያዩት ደግሞ ባለርስቶች ናቸው። ውይይቱ ውሳኔ እንዳይተላለፍበት ያዘገዩታል። ‹ይህንን ጉዳይ በቀጣይ እናየዋለን› እያሉ ይተውታል። ይህን ብሎ መጻፍ እንኳ አይቻልም ነበር …›› ብለዋል።
በወቅቱ በፊደል ግድፈትና በፎቶግራፍ አቀማመጥ የሚፈጠር ስህተት ለብርቱ ቅጣትና ግሳፄ ይዳርግ ነበር። አቶ ነጋሽ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆነው ለሁለት ዓመታት ያህል ከሰሩ በኋላ በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ችግር እንዲያጠኑ ከተመረጡት ሰዎች መካከል አንዱ ሆነው ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛወሩ። ብርሃኑ ዘሪሁን የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ሆነ።
አቶ ነጋሽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአንድ ዓመት ውጤታማ ተግባራትን ሲያከናውኑ ቆዩ። የወቅቱ ተጠባባቂ የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ሥዩም ሓረጎት « … ነጋሽ የተማረው ጋዜጠኝነት ስለሆነ ወደ ቦታው ይመለስ» ብለው ጥያቄ አቀረቡ። አቶ ነጋሽም ወደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተመልሰው ጋዜጣውን ዘመናዊ የማድረግ ጥረታቸውን ቀጠሉበት። ለሁለት ዓመታት ያህል ከሰሩ በኋላም ወደ ሬዲዮና ቴሌቪዥን መስሪያ ቤት እንዲዛወሩ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ በሙያቸው የፕሮግራም ኃላፊ፤ በሹመት ደግሞ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ምክትል ስራ አስኪያጅ ሆነው ደርግ ስልጣን እስከያዘበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል።
አቶ ነጋሽ የመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ሆነው በስራ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየፈቱና ውሳኔ እየሰጡ የራሳቸውን ፕሮግራም ከማቅረብ አልቦዘኑም። ስለጉዳዩ ሲገልፁም « … በዚህ መስሪያ ቤትም በሙያዬ የራሴን አስተዋጽኦ አበርክቼ አልፌያለሁ። አለቃ ሆኜ የሬዲዮ ተናጋሪም ነበርኩ። የሬዲዮ አድማጭ ዘና ብሎ ፕሮግራሞችን እንዲያዳምጥ፤ ጋዜጠኛውም ጥያቄዎቹ እንደ ፍርድ ቤት ደረቅ ያሉ ሳይሆን ለስለስ እና ዘና የሚያደርጉ አይነት እንዲሆኑ ጥረት አድርጌያለሁ። ‹አረፍ በል አናውጋ› የሚል ፕሮግራም ነበረኝ፤ በዚህ ፕሮግራሜ የተለያዩ ሙያተኞችን እና ታዋቂ ግለሰቦችን እንዲሁም አርሶ አደሩን ጭምር እንግዳ በማድረግ አወያያቸው ነበር። የተጠያቂዎቹን ማንነት ቀደም ብዬ አጥንቼና ተዘጋጅቼ ስለምቀርብ ጥያቄ አያጥርብኝም። ዛሬም ድረስ ጋዜጠኞቻችን ያለቀቁት ‹ሌላ የሚያክሉት አለ? ቀረ የሚሉት አለ? የሚጨምሩት አለ?› የሚሉ ጥያቄዎች እኔ ዘንድ የሉም። እውነት ለመናገር እነዚህ ጥያቄዎች የሰነፎች ናቸው …» በማለት ተናግረዋል።
«ከምሳ በኋላ» በተሰኘው ፕሮግራማቸው ደግሞ ልዩ ልዩ ጉዳዮችን በማይሰለች አቀራረብ በማቅረብ ሬዲዮ ጣቢያውን ተወዳጅ አድርገውት ነበር።
አቶ ነጋሽ በልምድ ሙያውን ለተቀላቀሉ ጋዜጠኞች እውቀታቸውን እያካፈሉ በሂደት ጥሩ ጥሩ ጋዜጠኞች እንዲፈጠሩ ጥረት አድርገዋል። « … በእርግጥ ለሙያው ማደግና ሳይንሳዊ መሰረትን ተከትሎ ዘመናዊ ጋዜጠኝነት በአገሪቱ እንዲሰፍን ጥረት አድርጌያለሁ። በጋዜጣውም ሆነ በሬዲዮው የማስበውን ያህል ለውጥ ማምጣት ግን አልቻልኩም። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ የሳንሱር ማነቆ ነው ይላሉ። ዘመኑ ወግ አጥባቂነት የተከበረበት ስለነበር አዲስ ነገር ለመስራት ሲሞከር መጯጯሁ ይበዛል። ይህንን ሁኔታ በትዕግስት በማለፍ ከሌሎች ከሚረዱኝ ባልደረቦቼ ጋር በመሆን በአቅሜ መጠነኛም ቢሆን ለውጥ አምጥቻለሁ ብዬ አስባለሁ» ብለዋል።
ወታደራዊው መንግሥት ስልጣን ከያዘ በኋላ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በስራ አስኪያጅነት እንዲመሩ የተጠየቁት አቶ ነጋሽ፤ የአስተዳደር ስራ እንደማይወዱ በመግለፅ ሹመቱን ሳይቀበሉ ቀሩ። ከዚያም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኑ። በወቅቱ በዓሉ ግርማ ወደ ዜና አገልግሎት ስለተዛወረ አብረው መስራት ጀመሩ። ጥቂት ቆይቶም በዓሉ የዜና አገልግሎት ስራ አስኪጅ ሆኖ ተሾመ፤አቶ ነጋሽ ደግሞ ወደ አገር አስተዳደር ሚኒስቴር ተዛወሩ። ጋዜጠኝነትን መልቀቅ ሳይፈልጉ እንዲዘዋወሩ ተደረገና በከተማ ልማት መስሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆነው ተመደቡ። 10 ገፅ የሚሆን በበራሪ ጽሑፍ መልክ የሚዘጋጅ መጽሔት መሰል ቅርፅ ያለው «ልማተ ከተማ» የሚባል ልሳን ያቋቋሙት በዚህ ወቅት ነበር። ይህ መጽሔት ቅርፅና ይዘቱ እየተሻሻለ ለበርካታ ዓመታት ተነቧል።
ወታደራዊ መንግሥት ቀደም ሲልም አቶ ነጋሽን አልወደዳቸውም ነበርና በ1970 ዓ.ም ጡረታ እንዲወጡ አደረጋቸው። ወታደራዊው መንግሥት አቶ ነጋሽን ያለፍላጎታቸውና ያለጊዜያቸው ጡረታ እንዲወጡ ከማድረጉ ባሻገር ለ26 ቀናት ያህል ያለ ምክንያት እንዲታሰሩና ከፍተኛ ድብደባ እንዲደርስባቸው አድርጓል።
ጡረታ ከወጡ በኋላም «ነጋዴው» የተሰኘ መጽሔት ሲቋቋም ከሌሎች የሙያው ሰዎች ጋር ሆነው ይሰሩ ጀመር። በዚህ ወቅት ነው የትያትር ድርሰት መፃፍ የጀመሩት። «የድል አጥቢያ አርበኞች» እና ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› የተሰኙ ትያትሮችን ጽፈው ተተወኑ፤ታዋቂነታቸውንም ከፍ አደረገላቸው። ‹‹የአዛውንቶች ክበብ›› የተሰኘው ትያትር በወቅቱ ተወዳጅ በመሆኑ ለተዋንያኑም ሆነ ለአቶ ነጋሽ ጥሩ ገቢ አስገኝቶላቸዋል። «ሴተኛ አዳሪ» በሚል ርዕስ ልብወለድ መጽሐፍም አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል።
አቶ ነጋሽ ሙያቸውን ለሌሎች ለማካፈል ባደረጉት ጥረት ለአጭር ጊዜም ቢሆን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ ግንኙነት ላይ ባተኮሩ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ሰጥተዋል። በአንድ የግል የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ተቋም ደግሞ ከሦስት ዓመታት በላይ ጋዜጠኝነትን ማስተማር ችለዋል።
በአንድ ወቅት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ‹‹ … በሙያው የበለጠ ለማገልገል ፍላጎትና አቅሙ ቢኖረኝም፤ የነበረው ሁኔታ እኔንም ሆነ መሰል የቀድሞ የሙያ አጋሮቼን ሊያሻግረን አልቻለም። ቢሆንም እየተንፏቀቅን፤ እየተጎዳንም፣ ባለን አቅም እየተረማመድንም የጋዜጠኝነት ሂደቱ እንዳይገታ አሁን ላለበት ደረጃ አድርሰነዋል። ጋዜጠኝነትን በአግባቡ ካልተረዱትና ሙያዊ ስነ-ምግባሩን ጠብቀው ካልተወጡት አደገኛ ነው። ጋዜጠኝነት በምላጭ ሰይፍ ላይ መሄድ ማለት ነው …›› ብለዋል።
አቶ ነጋሽ በሙያቸው ላከናወኗቸው ተግባራት እውቅናና ሽልማቶችን አግኝተዋል። ከነዚህም መካከል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የረጅም ጊዜ ሙያዊ አገልግሎት የዕውቅና ሰርተፍኬትና 20ሺ ብር ሽልማት አበርክቶላቸዋል። በጳወሎስ ኞኞ ስም በተዘጋጀ የሽልማት መርሀ ግብር ላይ የገንዘብና የእውቅና ሰርተፍኬት አግኝተዋል።
አቶ ነጋሽ ሁልጊዜም ቢሆን ዓለም አቀፋዊና አገር አቀፋዊ ሁኔታዎችን የመከታተል፣ በፅሞና ውስጥ ሆነው የማንበብና የመፃፍ እንዲሁም ስሜታቸውን በነኳቸው ጉዳዮች ላይ ግጥም የመፃፍ ልምድ አላቸው። ዘግየት ብለው ከመሰረቱት ትዳር ሁለት ልጆችን አፍርተዋል።
የኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ ዘመናዊ መልክ እንዲይዝ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወቱት አንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ አቶ ነጋሽ ገብረማርያም ሐምሌ 10 ቀን 2009 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ስርዓተ ቀብራቸውም ሐምሌ 11 ቀን 2009 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሳህሊተ ምኅረት ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
አዲስ ዘመን ሰኔ 3/2012
አንተነህ ቸሬ