ለአገር ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ልዩና ሳቢ ማበረታቻዎች ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ያስገነዝባሉ።
በወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ዘላለም እጅጉ የግሉ ዘርፍ ለበርካታ ዓመታት ምንም ዓይነት ማበረታቻ ሳይደረግለት እንዲያውም ተገድቦ መቆየቱን ያስታውሳሉ፡፡ ማንሰራራት ከጀመረም ጥቂት ዓመታት ብቻ መቆጠራቸውን አስታውሰው፣ ዘርፉ ከ50 እስከ 70 ዓመታት ትልቅ ድጋፍ ሲያደርጉ ከቆዩ አገራት ጋርም አይነጻጸርም ይላሉ፡፡
ዘርፉ ይህ ውስንነት እያለበትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጥ እየታየበት መሆኑን ጠቅሰው፣ይህ ግን አገሪቱ ከሚያስፈልጋት አንጻር ሲታይ በጣም ውስን እንደሆነም ነው የሚጠቁሙት። በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ያለው የግል ባለሀብት ሚና ያን ያህል አመርቂ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ በምጣኔ ሀብት ዕድገቱ ውስጥም እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ እጅግ በጣም ውስን መሆኑን ያመለክታሉ።
ሌላው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ዶክተር አሰፋ አድማሱ እንደሚሉት፤ አብዛኛው የሀገር ውስጥ ባለሀብት በመባል የሚታወቀው በአገልግሎት ዘርፉ ውስጥ እየሰራ ያለው ነው፡፡ ባለሀብቱ በዚህ ዘርፍ ላይ ለመሰማራቱ አንዱ ምክንያት ዘርፉ ወጪን በአጭር ጊዜ ሸፍኖ ትርፋማ መሆን የሚያስችል በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡ በመንግስት በኩል ሲደረግ የቆየው ማበረታቻም አንድ ዓይነት መሆኑን በመጥቀስ፣ ይህም ባለሀብቱ አድካሚ ወደ ሆነው አምራች ኢንዱስትሪ መግባት እንዳይፈልግ አድርጎታል ሲሉ ያብራራሉ።
የአምራች ኢንዱስትሪው ብዙ ስራ እንደሚጠይቅ፣ እውቀት እንደሚፈልግ፣ ሊሳካም ላይሳካም የሚችልና አደጋ (ኪሳራ) ያለው መሆኑን አብራርተው፣ ለዚህ ዘርፍ ከመንግሰት የሚሰጠውም ማበረታቻ የተለየ አለመሆኑ ባለሀብቱ ሙሉ አቅሙንና ጊዜውን አገልግሎት ዘርፉ ላይ እንዲያደርግ ምክንያት መሆኑን ይናገራሉ።
በዶክተር አሰፋ ሃሳብ የሚስማሙት ዶክተር ዘላለም እንደሚሉት ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በራሱ ከፍተኛ ሀብት እና የሰለጠነ የሰው ሃይል ይፈልጋል፡፡ የሰለጠነ የሰው ሃይል ከአገር ውስጥ የሚገኝበት ሁኔታ ቢኖርም ከውጭ ማስመጣት የግድ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ በውጭ አገር ካሉ ባለሀብቶች ጋር በትብብር መስራትን ይጠይቃል፤ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር እነዚህን ማድረግ አለመቻሉ የግል ዘርፉ እንዲዳከም ውጤታማ እንዳይሆን አድርገውታል።
ዘርፉን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች እንዳሉ የሚናገሩት ዶክተር ዘላለም፣ በተግባር የሚታየው ግን የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ባለው ሁኔታ የመስሪያ ቦታ ለማግኘት ችግር ይገጥም እንደነበር፣ የኢንቨስትመንት ፍቃድ ለማውጣት፣ እቃዎችን ከውጭ አስመጥቶ ስራ ለመጀመር ፣ ሰራተኛ ለመቅጠር የሚወስደው ጊዜና የሚባክነው ሀብትና ጉልበት ከፍተኛ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ ይህም ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዳይገቡ እንደሚያደርግ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች ተጋፍጦ ማለፍ ቢቻል እንኳን ትርፋማነቱ አጠያያቂ ይሆናል›› የሚሉት ዶክተር ዘላለም፣ ችግሩ ዘርፉ በምጣኔ ሀብት እድገቱ ላይ መወጣት ያለበትን ሚና እንዳይወጣ እንዳደረገም ይገልጻሉ።
ዶክተር አሰፋ በበኩላቸው መንግስት የሚያወጣቸው ፖሊሲዎችና የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት የሚያከናውናቸው ስራዎች ጥሩ መሆናቸውን ተናግረው፣ የሚፈለገውን ውጤት ማስገኘት እንዳልቻሉ ያመለክታሉ፡፡ ፖሊሲዎቹን እንዲያስፈጽሙ የተቋቋሙ ቢሮዎች ሃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣቸው፣ በየጊዜው የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች አለመደረጋቸው ማበረታቻዎቹና ፖሊሲዎቹ ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርገዋል ይላሉ፡፡
ባለሀብቱ የአገልግሎት ዘርፉን ሙጥኝ ያለው መደበቂያም ስለሆነ ነው የሚሉት ዶክተር አሰፋ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ግን መደበቂያ አለመሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፉ ባለሀብቱ ከግብርም ሆነ ከሌላ ወጪን ከሚጠይቁ ነገር ግን ለአገር ኢኮኖሚ ዋልታና ማገር ከሆኑ አሰራሮች ሊደበቅ እንደማይችል ይጠቅሳሉ፡፡ በዚህ የተነሳም ባለሀብቱ ወደ ዘርፉ ለመግባት ፍላጎቱ አናሳ መሆኑን ያመለክታሉ።
አሁን ባለው ሁኔታ የግሉ ዘርፍ አገልግሎቱን ሙጥኝ ማለቱ ምክንያታዊና ትክክለኛ አካሄድ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ሁኔታ መቀየር የሚቻለው የመንግስት ማበረታቻዎች ለየት ያሉና ሳቢ ሲሆኑ ነው ይላሉ፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ዘርፉ ከአገልግሎት ሰጪነት ይወጣል ብሎ መጠበቅ የዋህነት መሆኑን ያስገነዝባሉ።
መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ ማበረታቻዎችን ማድረጉን እየገለጸ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማበረታቻው ለአገልግሎቱም ለማኑፋክቸሪንጉም አንድ አይነት ከሆነ ምኑን ማበረታቻ ሆነ ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ የግሉን ዘርፍ ለአገር ምጣኔ ሀብታዊ እድገትም ሚና አለው ካልን የተለየ እና እውነተኛ የማበረታቻ ድጋፍ ሊደረግ ይገባል ይላሉ።
ዶክተር አሰፋ በቀጣይ ከቀረጥ ነጻ የማስገባት መብት ወይንም ከግብር ነጻ የመሆን መብት ከተፈጠረ የአምራች ኢንዱስትሪውን ኮታ ከፍ ማድረግ እንደሚገባ፣ በአገልግሎት ዘርፉ ላይም ቅጣት (ፔናሊቲ) ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ ያመለክታሉ፡፡ ይህን በማድረግ የአገለግሎት ዘርፉ የባለሀብቱ መደበቂያ እንዳይሆን በማድረግ አቋራጭ መንገድን መዝጋት እንደሚገባ ያስገነዝባሉ ።
ዶክተር ዘላለም የባለሀብቱን ተሳትፎ ለማጎልበት የውጭ ምንዛሪውን ችግር በመፍታት፣ የመሬት አቅርቦቱን ምቹና ቀልጣፋ በማድረግ፣ በኢንቨስትመንት ፈቃድ አሰጣጥ በኩል የሚታዩ ውጣ ውረዶችን በመቀነስ፣ የወጪ ንግድ አስገዳጅ ሁኔታዎችን (ፎርማሊቲዎችን) በማጥበብ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ከስር ከስር መፍታት ያስፈልጋል ሲሉ ያብራራሉ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በቅርቡ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ባለፉት 15 ዓመታት በአማካይ በ10 በመቶ እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፣ዕድገቱን ማስቀጠል የሚቻለው ግን የግል ዘርፉን ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል የኢንቨስትመንት ምህዳር ሲፈጠር ነው። ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ለግል ዘርፉ ዕድገት ምቹ ያልሆነ አሰራር ለመቀየር የሚያስችል አዲስ ኢንሼቲቭ (የሪፎርም እንቅስቃሴም) መጀመሩን ይጠቁማሉ። ከማሻሻያ ስራዎቹ መካከልም በዋነኛነት በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት_ የሚከናወኑ ስራዎች ሙሉ ለሙሉ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዙ እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚሁ መሰረት በየሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ይጠቁማሉ፡፡ ከሚቀጥሉት አራት ወራት እስከ 3 ዓመታት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑ የአጭር፣ የመካከለኛና ረጅም ጊዜ እቅዶች መታቀዳቸውን ይገልጻሉ።
መንግስት የግሉ ሴክተር በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ዕድገት ላይ ጉልህ ሚና እንዲጫወት ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ሀገሪቱ በርካታ ማበረታቸዎችን አድርጋለች፡፡ ባለሀብቱ ዛሬም እዚያው አገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ነው ያለው፡፡
በቀጣይም በተደረጉት ማበረታቻዎች ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ እንዲሁም የሌሎች በኢትዮጵያ ደረጃ የሚገኙ ሀገሮችን ተሞክሮ በመቅሰም አሁንም ባለሀብቱን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ለመሳብ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ለዘርፉ ልዩ ማበረታቻዎችን በማድረግ የኖረበትን የአገልግሎት ዘርፍ ለቆ እንዲወጣ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ባለሀብቱ የአገልግሎት ዘርፉን ሙጥኝ እንዲል ያደረጉ አሰራሮችም እየተፈተሹ በአቋራጭ የመበልጸጊያ መንገዶች ሊዘጉ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
በእፀገነት አክሊሉ