በየግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት እያደገ እንደመጣ ይታወቃል፡፡ይሁንና ዘርፉ እየጨመረ የመጣው የግብርና ምርት ፍላጎት ለማርካት አልቻለም፡፡በዚህ የተነሳም ሀገራችን የዳቦ ስንዴ በየአመቱ ከውጪ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በመመደብ እያስገባች ትገኛለች፡፡የእህል ዋጋ እየጨመረ ነው፤ለእዚህ አንዱ ምክንያት የአቅርቦትና ፍላጎት አለመመጣጠን እንደሆነ ይገለጻል፡፡ችግሩን ለመፍታት መንግስት በአቅርቦት ላይ እንደሚሰራ በተደጋጋሚ ሲያረጋግጥ ቆይቷል፡፡
መንግስት ችግሩን ለመፍታት አንዱ መፍትሄ በመስኖ ላይ አተኩሮ መስራት መሆኑን በመገንዘብ በዚህ አመት በቆላማ አካባቢዎች ስንዴ በመስኖ እንዲለማ እያደረገ ነው፡፡በዚህም ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እየታዩ መሆናቸውን ከመስክ ምልከታ ዘገባዎች መረዳት ተችሏል፡፡ግብርናውንም ለማዘመን እየሰራ ይገኛል፡፡በቅርቡ ለአርሶ አደሮች የቀረቡ ትራክተሮች የቀረቡበትን ሁኔታ በአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በያዝነው የመኸር ወቅትም በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡ መንግስት አርሶ አደሩ እና ባለሀብቶች መሬታቸውን በሙሉ አርሰው በዘር እንዲሸፍኑ እያሳሰበ ይገኛል፡፡ባለፉት ወራትም የማሳ ዝግጅት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ቀድመው የሚዘሩ የሰብል አይነቶችም ተዘርተዋል፡፡
እነሆ አሁን ደግሞ ሰኔ ግም ብሏል፡፡ ሰኔ አርሶ አደሩ በመኸር ግብርና ስራ በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠመድበት ወቅት ነው፡፡በዚህ ወር ያልተሰራ መቼም አይሰራም፡፡ምክንያቱ ደግሞ ዘር የሚጀመርበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡በግንቦት የተሰነጠቀው ማሳ በሰኔ እንዲለሰልስ እየተደረገ በዘር ይሸፈናል፡፡ዘንድሮ በግንቦት የነበረው ዝናብ ለእርሻ ጥሩ እንደሆነም የግብርና ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡ ፡ጸሀዩም ዝናቡም ምቹ ነበሩ፡፡ ይህን ምቹ ሁኔታ በሰኔ ወር በሚገባ በመስራት ይበልጥ ማሳመር ይገባል፡፡ ሰነፍ ገበሬ በሰኔ ይሞታል እንዲሉ ሰነፍ ገበሬ ካልሆነ በቀር ሁሉም አርሶ አደር ሰኔን በጉጉት ይጠብቃል ፤በሚገባም ይጠቀምበታል፡፡
ከሰኔ ወር አንስቶ ባሉት ወራት በሚገባ ሳያርሱ፣ሳይጎለጉሉና በዘር ሳይሸፍኑ የመኸር አዝመራ ማፈስ አይቻልም፡፡አንድ ሰኔ በተለያየ ምክንያት ካመለጠ በቀላሉ ሊካካስ ስለማይችልም ነው ‹‹አንድ ሰኔ የገደለውን አስር ሰኔ አይመልሰውም›› እየተባለ የሚገለጸው፡፡
ሀገራችን ኢኮኖሚዋ አሁንም በግብርና ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ግብርናችን በዝናብ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑም የዝናብ ወቅት እና ዘር መዝራት የሚጀመርበትን ይህን ወር በሚገባ መጠቀም የህልውና ጉዳይ ነው፡፡በመሆኑም አርሶ አደሩ የግብርና ባለሙያውና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሙሉ ሙሉ ጊዜያቸውን በግብርናው ስራ ላይ ማዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡
እንደሚታወቀው ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ አለም ኢኮኖሚዋ ክፉኛ ደቋል፡፡በዚህ የተነሳም መግዛት ሆነ መሸጥም አስቸጋሪ ሆኗል ፡፡ ኮሮኖ መቼ እንደሚያበቃ አለመታወቁ ደግሞ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል ፡፡ መንግስታትም ችግሩ ብዙ ዋጋ ሳያስከፍለን ለመቆጣጠር ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡ ፡
ለዚህም ሲባል በኢኮኖሚው ዘርፍ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው፡፡ የግብርናው ዘርፍ ከኢኮኖሚው ዘርፎች አንዱ እና ዋንኛው ከመሆኑ አንጻር ለተያዘው የመኸር ወቅት አዝመራ የሚውል ማዳበሪያ በከፍተኛ ወጪ ከውጪ በመግዛት ከሁሉም በላይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ሲያጓጉዝ ቆይቷል ፡፡ ከዚህም ባለፈ አንድም መሬት ጦም ማደር የለበትም በሚል መንግስት በባለሀብቶች የተያዙ መሬቶች ሳይቀሩ በሰብል እንዲሸፈኑ እያደረገ ይገኛል ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ትናንት ከህዝብ ተወካዮችም ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ይህንኑ አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ አመቱን ሙሉ ዝናብ አግኝተናል፤ግንቦት የክረምት ያህል ሆኖልናል ይህንን የተሻለ አጋጣሚ ወደ ተሻለ እድል መለወጥ እንደሚጠበቅብን፤ በመኸርና በበልግ እርሻ ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አመልክተዋል ፡፡ ይህ የመንግስት ቁርጠኝነትና ዝግጅት ፍሬያማ እንዲሆን አርሶ አደሮች፣የግብርና ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል፡፡
መንግስት ግብርናውን ከዝናብ ጥገኝነት ለማውጣት በመስኖ ላይ በትኩረት ለመስራት በስፋት እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ይህ ግን ገና በጅምር ላይ ያለ እንደመሆኑ ዝናብን አሟጦ በመጠቀም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በትኩረት መስራት ያስፈልጋል፡፡ይህን የመንግስት ጥረት የመኸር ወቅቱን በሚገባ በመጠቀም ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ይገባል፡፡ ለእዚህ ደግሞ የተያዘውን ሰኔ ወርን በሚገባ መጠቀም የግድ ነው፡፡
የኮሮና ወረርሽኝ እድሜ መቼ እንደሚያጥር ካለመታወቁ ጋር በተያያዘ ሁሉም በእጁ ያለውን ይዞ ሊቆይ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለ ሆኖ ፤ የትራንስፖርት እና ሌሎች ችግሮች ተጨምረውበት እህል ከውጪ ገዝቶ ለማስገባት እንኳን አዳጋች ሊሆን እንደሚችል አለም አቀፍ ስጋት አለ ። ይህንን ሥጋት ወደ መልካም አጋጣሚ ለመለወጥ በእጃችን ያለውን መፍትሄ፤ መሬቶቻችንን በሙሉ በሚገባ በማረስና በማለስለስ በዘር መሸፈን ይጠበቅብናል ፡፡ ይህንን ማድረግ ለዛሬ ከፍታችን ያለውን ችግር በብቃት ለመወጣት ፤ለነገ ደግሞ የተሻለ ውጤታማ ተሞክሮ ባለቤት ያደርገናል ። ሰኔ ግም ብሏል፤እንጠቀምበት፡፡
አዲስ ዘመን ሰኔ 2/2012