. ጣሊያን ከምጽዋ አዲስ አበባ የሚዘረጋውን የባቡር መስመር ጥናት ወጪ ትሸፍናለች
. ከኤምባሲዋ ግቢ የተወሰነውን ለአረንጓዴ ስፍራ ለመስጠት ወስናለች
አዲስ አበባ:- የጣሊያን ጉብኝታቸው የሁለቱን አገራት ጠንካራ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና የተሳካ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጣሊያን ቆይታቸውን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ቆይታቸው የሁለቱን አገራት ግንኙነት ያጠናከረና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ለመገናኘት ያስቻለና የተሳካ ነበር።
ከጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ ጋር የነበራቸው ቆይታ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ጠቅሰው፣ የምስራቅ አፍሪካ አገራትና ጣሊያንን በማገናኘት አብረው ወደ ልማትና ሰላም እንዲሁም ወደ አንድነት የሚያሸጋግር ፕሮጀክት ለመጀመር ያለውን ዝግጁነት ያሳየም ነው ብለዋል።
በተለይም በኢትዮጵያ በኩል ምጽዋንና አዲስ አበባን በባቡር መስመር ለማገናኘት ያለውን ፍላጎት እውን ለማድረግ የሚረዳ የመጀመሪያውን ጥናት ሙሉ ወጪ ሸፍኖ ለማስጠናትና ውጤቱን ተከትሎም በጋራ ለመስራት ያሳዩትን ዝግጁነት እኛም በከፍተኛ ክብር የተቀበልነት ነው ማለታቸውም ተገልጿል።
በሌላ በኩልም አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስና አበባ ለማድረግ በቅርቡም ብሔራዊ ቤተመንግስት ከፊሉን ግቢ ለህዝብ እይታ ክፍት ለማድረግ እቅድ አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፣ ከቤተመንግስት ያልተናነሰ ሰፋፊ ቦታን የያዙ ኤምባሲዎች የተወሰነ ቦታቸውን ለፓርክ አገልግሎት ክፍት እንዲያደርጉ ፍላጎት እንዳለ ስናሳውቅ የጣሊያን መንግስት ሀሳቡን በመቀበል ላሳየን ቀና ምላሽ ላቅያለ ምስጋና እናቀርባለን ብለዋል።
በተጨማሪም አዲስ አበባ ውስጥ ምግብ የሚቸገሩ ተማሪዎች እንዳሉና መንግስት ዳቦ ጋግሮ ማቅረብ ፍላጎት ቢኖረውም ፋብሪካ የማቆም አቅሙ ውስን በመሆኑ ይህንን ሁኔታ በመረዳት ፋብሪካው የሚቆምበትን ወጪ ለማገዝ ለገቡት ቃልም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በልጆቹና በራሳቸው ስም አመስግነዋል።
በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የተፈጠረው ሰላም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የጣሊያን መንግስት ዝግጁነቱን ማሳየቱን ገልጸው ከዚህም መካከል ተመላሽ ወታደሮችን ለማቋቋም ዝግጁነታቸውን መግለጻቸወም አስታውቀዋል።
«ጉብኝቱ የተሳካና ከእናንተ የምንፈልገውን ሁሉ እንደ ወንድምና ጠንካራ ወዳጅ አገር ያገኘንበት፤ በዚህም ልባዊ ደስታ ተሰምቶናል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ወደፊትም እዚህም እዛም በሚደረጉ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች በልማት፣ በሰላም ፣በቱሪዝምና በሌሎች ጉዳዮች ላይ አብረን እንድንሰራና ለጋራ እድገትና ሰላም አብረን እንድንቆም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ» ማለታቸውን የኤፍቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከጣሊያን በመጀመር የአውሮፓ ጉብኝታቸውን ከጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ እያደረጉ መሆኑም ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ጥር 14/2011
እፀገነት አክሊሉ