የመንግስት የህትመት መገናኛ ብዙኃን ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የተመሰረተው በ1933 ዓ.ም ነው። ድርጅቱ በአገሪቷ ውስጥ በአማርኛ ቋንቋ ‹‹አዲስ ዘመን›› የተባለውን እለታዊ ጋዜጣ የሚያሳትም ብቸኛው ተቋም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይም በሳምንት ለስድስት ቀናት በእንግሊዘኛ ቋንቋ የሚታተም ‹‹ዘ ኢትዮጵያ ሔራልድ›› በመባል የሚታወቀውን ጋዜጣ የሚያሳትም ሲሆን፣ በተጨማሪም በአፋን ኦሮሞ ‹‹በሪሳ›› እና በአረብኛ ‹‹አል ዓለም›› የተባሉ ጋዜጦችንም በሳምንት አንድ ጊዜ ለህትመት ያበቃል፡፡ በሁለት ወር አንዴ ለንባብ የምትበቃ ዘመን መጽሄትም የድርጅቱ አንዷና ተነባቢ የህትመት ውጤት ናት። ከእነዚህ የድርጅቱ ህትመቶች መካከል አዲስ ዘመን ጋዜጣ አንጋፋው ሲሆን፣ ዘንድሮ 79ኛ ዓመቱ ላይ ይገኛል፡፡ የዚህን ጋዜጣ 79ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አመራር ከሆኑት የህክምና፣ የስነልቦና እና የሥነ-መለኮት ባለሙያው ዶክተር ወዳጄነህ ማህረነ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገን እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሲያስቡ በቅድሚያ ወደ አዕምርዎ የሚመጣው ነገር ምንድን ነው?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሳስብ ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው አንደኛ ስልጣኔ ነው። ምክንያቱም የአዲስ ዘመን ጅማሮ የስልጣኔ ጅማሮ ነው። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ወደ ሐሳቤ የሚመጣው ስነ ጽሑፍ ነው። በርካታ የአገሪቱ ጉምቱ ጸሐፍትን የምናውቃቸው በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ነው። በዚህም መሰረት ታዋቂ የኢትዮጵያ ስነ ጽሑፍ ጸሐፊዎች ጅማሬያቸውን ያደረጉት ከአዲስ ዘመን ስለሆነ ሁለቱ ነገሮች ናቸው ወደሐሳቤ የሚመጡት።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዘመን በአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ ለቋንቋና ለስነ ጽሑፍ ያበረከተውን አስተዋጽኦ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ከስነ ጽሑፍ አንጻር ብዙዎቻችን የምናከብራቸውን የስነ ጽሁፍ ሰዎችን አበርክቶልናል። ለአብነት ያህል እነ በዓሉ ግርማ፣ ብርሃኑ ዘሪሁን፣ ጳውሎስ ኞኞ፣ ስብሀት ገብረእግዚአብሄር እና ሌሎችም መነሻቸው አዲስ ዘመን እንደሆነ አውቃለሁ። እናም አዲስ ዘመን ብዙ ጸሐፍት ጅማሬያቸው የነበረና ብዕራቸውንም ያሰሉበት ቦታና የእነርሱም አሻራ የሚገኝበት ስፍራ እንደሆነ እረዳለሁ። አሁንም ደግሞ ለቋንቋ እድገት አዲስ ዘመን ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ብዙዎቹ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በቋንቋ አጠቃቀሙ ለሌሎችም መገናኛ ብዙሃን የመለኪያ ያህል ነው የሚሉ አሉና እዚህስ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ልክ ነው፤ እኔ ቢያንስ አዲስ ዘመን እና ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድን በየቀኑ አገኛለሁ። እናም በጋዜጦቹ ላይ የማስተውለው ደረጃውን የጠበቀ ቋንቋ ነው። በጣም ትክክለኛ ቋንቋ የምታገኚው በእነዚህ ጋዜጦች ላይ ነው። ደግሞም ሌሎች እንደምንጭ አድርገው ሲውስዱም አስተውያለሁ። ብዙ ጊዜ አዲስ ዘመን ተጠቅሶ የሚወሰድበትም ሁኔታ አለ። ይህ ግን በአዲስ ዘመን ብቻ አይደለም። በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጋዜጦች እንዲህ አይነት አስተዋጽኦ ነበራቸው ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- በአብነት የሚጠቅሷቸው ይኖሩ ይሆን?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- አዎ! ወደኋላ ልመለስና የሰው ልጅ በጽሑፍ መረጃ የማሰራጨት ፍላጎት የሚጀምረው ከክርስቶስ ልደት በፊት ነው። ገና ከክርስቶስ ልደት በፊት የሰው ልጅ በድንጋይ፣ በፓፒረስ፣ በተሰራ የበግ ቆዳ ላይ እየጻፈ መረጃዎችን የማሰራጨት ፍላጎት ነበረው፤ እናም ያንንም ሲያደርግ ቆይቷል። ቀጥሎም እኤአ 1440 በጉተንበርግ ማተሚያ ማሽኖች ተሰሩ። በዚህም መልክ የታተሙ የህትመት ውጤቶች መሰራጨት ጀመሩ።
እንደሚታወቀውም የመጀመሪያው ጋዜጣ የታተመው እኤአ በ1605 ሲሆን፣ ያሳተሙትም ጀርመኖች ናቸው። ስያሜውም ‹‹ዘ ሪሌሽን›› የሚል ነበር። በዚህም ሳምንታዊ የሆነው የመጀመሪያው በጀርመንኛ የታተመ ጋዜጣ ወጣ። ስድስት አስርት ዓመታት ቆይቶ ደግሞ እኤአ በ1665 ላይ እንግሊዞች ወደጋዜጣው ህትመት መምጣት ቻሉ። በዚህም መሰረት የመጀመሪያውን ‹‹ዘ ኦክስፎርድ ጋዜት›› የሚባል ጋዜጣን አሳተሙ። ከዛ ቀይረው የለንደን ጋዜጣ (ለነደንስ ጋዜት) ሲሉ በመሰየም ማሳተም ጀመሩ። በዚህ መልኩ የጋዜጣው ህትመት እያደገና እየሰፋ መምጣት ቻለ። ሁሉም ግን የስልጣኔያቸው አንዱ መሰረት አድርገው ነው የወሰዱት። በዚህም እንግሊዞችም ሆኖ ሌሎቹ ለጋዜጣ ያላቸው ቦታ በጣም አስደናቂ ነው። ለዴሞክራሲ ማደግ ጋዜጣ ከፍ ያለ ቦታ አለው። የህብረተሰብን አስተሳሰብም ለመገንባትም ሆነ የአስተሳሰብ ልህቀትን ለማምጣት ጋዜጣ የማይናቅ ሚና አለው። ያደጉ አገሮችም ለዚህ የተጠቀሙት ጋዜጣን ነው።
ወደ እኛ አገርም ስንመጣ የወቅቱ የአገሪቱ መሪ አጼ ኃይለስላሴ ከስደት ሲመለሱ በስደት የነበሩበት አገር ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ይመስለኛል። ምክንያቱ የቆዩት ጋዜጣ በስፋት የሚነበብበት አገር ነው። በ1933 ከስደት ሲመለሱ በተመለሱ በሳምንት ውስጥ ነው አዲስ ዘመን ጋዜጣ የተጀመረው። በዚህም ደግሞ ምን አይነት ትኩረት እንደሰጡ ነው የሚያሳየው።
በሳምንታ ውስጥ ከንግግራቸው ላይ ተወስዶ ‹‹ይህ የአዲስ ዘመን መክፈቻ ነው፤ የአዲስ ዘመን ጅማሬ ነው›› ብለው ነው ንግግር ያደረጉት። ከዛ ጋዜጣው እንዲታተም ትዕዛዝ ሲወጣ ያቺው የእርሳቸው ቃል ተወስዳ ‹‹አዲስ ዘመን›› ተብሎ ጋዜጣው ተጀመረ። ይህ የሚያሳየው እንዳልኩሽ በቆዩበት አገር የጋዜጣ ትርጉም ገብቷቸው ስለነበር ነው። ይህ ማለት ጋዜጣ እና ስልጣኔ ያላቸውን ግንኙነት በአግባቡ ተረድተዋል ማለት ነው።
አንድ ህዝብ ሲሰለጥን ጋዜጣ ማንበብ እንዳለበት ገብቷቸዋል። እና በዓለም ዙሪያ ስልጣኔና ጋዜጣ የተያያዙ ናቸው። የሰለጠነ ህዝብ ጋዜጣ ያነባል፤ ጋዜጣ የሚያነብ ህዝብ ደግሞ ይሰለጥናል። ስለሰለጠንኩ ጋዜጣ አነባለሁ፤ ጋዜጣ በማንበቤ ደግሞ የበለጠ ሰለጥናለሁ። እናም ለሰው ልጅ ስልጣኔ ዴሞክራሲ ላላቸው አገሮች እድገት፣ ለአስተሳሰብም ልህቀት ጋዜጦች የነበራው ሚና ከፍተኛ ነው።
ብዙ አገሮች እስካሁንም ድረስ ጠዋት ሲነሱ ከቡና ጋር የሚቀርብላቸው ጋዜጣ ነው። አጼ ኃይለስላሴም ጠዋት ላይ ጋዜጣ ከቡና ጋር ይቀርብላቸው ነበር የሚል አንብቤያለሁ። ቡናቸው ሲቀርብ ጋዜጣም አብሮ እንደሚቀርብላቸው ይገለጻል። አሁንም ድረስ በሰለጠነው ዓለም ሆቴል አርፈሽ ጠዋት ላይ የሆቴልሽን በር ስትከፍቺ ጋዜጣ ወድቆ ታያለሽ። በዚህ መልኩ ጋዜጣን ማንበብ አንድ ትልቅ ባህል ሆኖ ነው የቆየው። አሁን ደግሞ በኦንላይንም ሰዎች ይከታተሉታል። ሰዎች በዚህ መልኩ መረጃ በማግኘታቸውም ሰልጥነዋል ማለት ይቻላል።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዘመን ሰነድን ከመሰነድ አኳያ ያበረከተውን ፋይዳ እንዴት ይገልጹታል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ወደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲመጣ በየኮሪደሩ በፎቶግራፍ የተቀመጡ ታሪኮች ሌላ ቦታ የማይገኙ ናቸው። አንዳንድ ሰዎች የኢትዮጵያ ታሪክ የየቀን ማስታወሻ የያዘ ሰነድ ነው ይሉታል። በእርግጥም አዲስ ዘመን የኢትዮጵያን የየቀን ማስታወሻ የያዘ ሰነድ ነው። ስለሆነም የኢትዮጵያን ሙሉ ታሪክ የሚፈለግ ሰው አዲስ ዘመን መታተም ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን ታሪክ ጋዜጣው ላይ ያገኘዋል። ስለዚህ ታሪክን ሰንዶ በማስቀመጥ አንጻር አዲስ ዘመን የነበረውና ያለው ሚና እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው።
ሌላው ጋዜጦችም ይሁኑ ሌሎቹ ብሮድካስት ሚዲያዎች ስራ ይጀመሩና ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይቆማሉ። ለአዲስ ዘመን 79 ዓመት ያለማቋረጥ መሄድ ማለት እጅግ በጣም አስደናቂ ነገር ነው። ከዚህ በኋላም እንደሚቀጥል ይታወቃል። ደግሞም በይዘቱ እየተሻሻለ፣ ፎርማቱን እየቀያየረ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እያደገ ያለ ጋዜጣ መሆኑን አያለሁ፡፡
በአሁኑ ወቅት ብዝሃነትን በስፋት እናይበታለን። በድርጅቱ በሚካሄደው ሪፎርም ጋዜጣው በጣም እየተሻሻለ እና በህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እያደገ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል። ለምንድን ነው ቢባል ባለፉት ጊዜያት እንደነዚህ አይነት ሚዲያ ዎችን የነበሩ መንግስታት የፕሮፓጋንዳ ማሽን አድርገው የመጠቀም ፍላጎት አላቸው። ደግሞም ተጠቅ መውበታል። ይህ አይነቱ አካሄድ ግን አሁን እንደተለወጠ ነው ፡፡
ለአብነት ያህል ባለፈው ሳምንት ካየኋቸው ጋዜጦች ፊት ገጽ ላይ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ፎቶግራፋቸውና ሐሳባቸው በስፋት ወጥቶ አስተውያለሁ። ዋና ዋና ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚባሉ መሪዎቻቸውና የተናገሩት ንግግር በስፋት እየተስተናገዱ ነው። ቁንጽል የሆነ ሐሳባቸው ብቻ ሳይሆን የተናገሩት ሐሳብ ሳይቆረጥ በመውጣት ላይ እንደሆነ ማስተዋል ችያለሁ።
ምሁራን ሆነው የመንግስት ደጋፊ የሆኑ እንዲሁም ደጋፊ ያልሆኑም እድሉ ተሰጥቷቸው ጋዜጣው ላይ ጽሑፋቸውን አንብቤያለሁ። ይህ በጋዜጣው ላይ ያለውን ለውጥ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነቱን እንዲጨምር ያደርገዋል። ዝም ብሎ የመንግስትን ሐሳብ እየወሰደ የሚያስተላልፍ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ሳይሆን ብዝሃነትንና የተለያዩ ሐሳቦችን የሚያስተናግድ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ጋዜጣ በመሆን እየመጣ ያለ እንደሆነ ነው እያየሁ ነው ያለሁት። እናም በዚህ ደግሞ በጣም ተደስቻለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት የህትመት ውጤቶችን ጊዜው እየፈተናቸው ይገኛል፤ በተለይም የማህበራዊ ትስስር ገጽ፣ ዩቲዩብና መሰል መረጃ መቀበያና ማስተላለፊያ ዘዴዎች ይጠቀሳሉና ይህንን ፈተና አዲስ ዘመን እንዴት ነው መወጣት ያለበት ብለው ያምናሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ፈተናው ዓለም አቀፍ ነው። በአሁኑ ሰዓት አሜሪካ ውስጥ 1 ሺህ 330 የሚያህሉ ጋዜጦች ይታተማሉ። ከአምስት ዓመት በፊት 1 ሺህ 500 በላይ ነበሩ። ስለዚህ ከህትመት የወጡ ጋዜጦች አሉ። እነዚህ የጠቀስሻቸው ሚዲያዎች በአጠቃላይ በህትመት ላይ ያላቸው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም። ነገር ግን እስካሁን ተጽዕኖው ቢኖርም ጋዜጦችን የማህበራዊ ሚዲያው ሊተካቸው እንደማይችል ይታመናል፤ አንደኛ ጋዜጣ ይዞ ማንበብ የራሱ የሆነ ባህል አለው። የራሱ የሆነ ፍቅር አለው፡፡
ለምሳሌ የተለያዩ የመጽሐፍት አይነቶች የእጅ ስልኬ ላይ አሉ። ነገር ግን ወረቀቱን አሊያም መጽሐፉን ገልጬ ገጾቹን እያየሁ እንደማነበው አይሆንልኝም። ልክ ወረቀቱን አሊያም መጽሐፉን ገልጬ የማንበውን አይነት ስሜት ሊተኩልኝ አልቻሉም። ለታተመው የበለጠ ፍቅር አለኝ። ልክ እንደዛው የጋዜጦችም ፍቅር አሁንም አልጠፋም። አሁንም ቢሆን ህዝቡ ጋዜጣን ማንበብ ይወዳል። አውሮፓ እኮ በየባቡሩ ላይ ሳይቀር ሰው የጠዋት አሊያም የምሽት ጋዜጣ እያነበበ ነው የሚሄደው። እናም ያንን ማሳየት ያስፈልጋል። አሁን የመጡት አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ሙሉ በመሉ ጋዜጣን ሊያስቀሩት አይችሉም።
አዲስ ዘመን፡- ምናልባትም በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ የሚቀርቡ መረጃዎች ከእውነትነታቸው አንጻር ሙሉ ለሙሉ ለማመን ስለሚቸግር ይሆን ሰው ለማመሳከር ወደጋዜጣው የሚመጣው?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- አዎ! እንዲያው ለተወዳጅነቱም አንዱ ተዓማኒ በመሆኑም ጭምር ነው። የተረጋገጠ ማስረጃ ሪፖርተሩ አምጥቶ፤ ከአርታኢው ጋር ተነጋግሮ በተቀመጠው የኤዲቶሪያል ፖሊሲ አማካይነት ታይቶ እንደ አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጽሑፍ ይዞ ስለሚወጣ የተሳሳተ መረጃ የመውጣቱ እድሉ በጣም አነስተኛ ነው። ለምሳሌ ፌስቡክ ላይ አንድ ዜና ባነብ ወዲያውኑ እውነት ነው ብዬ አልቀበልም። ጋዜጣ ላይ የማነበው መረጃ ግን ትክክለኛ መረጃ እንደሆነ አድርጌ ነው የምወስደው። ስለዚህ ጋዜጣ የማንበብ ባህሉ ማደግ አለበት ብዬ ነው የማምነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የቦርድ አመራር መሆንዎ ይታወቃል፤ በቦርድ አመራርነትዎ ተቋሙን ሲቀላቀሉ የጠበቁትን ያህል ሆኖ ነው ያገኙት?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- የድርጅቱ የቦርድ አባል ሆኜ ስሾም ደስተኛ ነበርኩ። እኔ ስነ ጽሑፍ እወዳለሁ። በጣም ከምወዳቸው የስነ ጽሁፍ ሰዎች መካል ደግሞ አስቀድሜ ልጠቅስ እንደሞከርኩት የማደንቃቸው ሰዎች እና ከልጅነቴ ጀምሮ ስራዎቻቸውን የማነብላቸው ሰዎች ናቸው። ስለዚህም የእነሱ ዱካ ያረፈበት ቦታ ላይ መግባቴ አስደስቶኛል፡፡
እንደ አዲስ ዘመን 79 ዓመት የቆየ እድሜ ያለው ጋዜጣ የሚያትም፣ ዘ ኢትዮጵያ ሄራልድን፣ በሪሳን፣ ዘመን መጽሄትን እንዲሁም ዓል አለምን የሚያሳትም ድርጅት ለኔ በጣም ትልቅ ነው። እና በተቋሙ የቦርድ አባል በመሆኔ ደስ ብሎኛል። የተቀበልኩትም በደስታ ነው።
ከገባሁ በኋላም ያየሁት የድርጅቱ ሰራተኞች በጣም በትጋት እንደሚሰሩና ከሚሰሩትም በታች እየተከፈላቸው ነው። የሚከፈላቸው አነስተኛ ደመወዝ ቢሆንም ስራውን በጥራት እንደሚሰሩ ነው ማስተዋል የቻልኩት። ድርጅቱ እንደማንኛውም ድርጅት የራሱ የሆኑ ችግሮች ይኖሩታል። ችግሮቹን ደግሞ ከቦርዱም ጋር ተነጋሮ ሲፈታና መግባባት ላይ ሲደርስ አይቻለሁ፡፡
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በቀጣይ የራሱ ማተሚያ ቤት እንዲኖረው ያልማል። ይህ በጣም አስፈላጊ ነው። ተቋሙ ማተሚያ ቤት ኖሮት የራሱን ጋዜጦች በራሱ ሲያትም ማየት እፈልጋለሁ። እኛ በቦርድ አባልነት ከገባን በኋላ እንኳን ጋዜጦች ላይ የምናየው የይዘትም ሆነ የቅርጽ ለውጥ አለ። እናም በሪፎርም ሂደት ላይ ያለ ድርጅት እንደሆነ አስተውለናል። እንዲሁም ጥሩ አመራሮች ያሉት ድርጅት እንደሆነም ተገንዝበናል። እኔ ለአዲስ ዘመን አዲስ ዘመን መጥቶለታል ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፡- ለአዲስ ዘመን አዲስ ዘመን መጥቶለታል ካሉ የዚህ መገለጫው ምን ይሆን?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- የጋዜጣው ይዘት በራሱ ለውጥ አሳይቷል፤ አስቀድሜ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በአግባቡ ማስተናገዱ የመንግስት ሚዲያ ሆኖ እያለ የሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ያለ አድልዎ የሚስተናገዱበትና እያተስተናገዱበት ያለ ጋዜጣ በመሆኑም ነው። የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው እና ምሁራንም እዚህ ጋዜጣ ላይ በነጻነት ጽፈው ማየት የየዕለት ነገር ሆኗል፤ መንግስትን የሚደግፍ ህዝብ እንኳ ቢሆን እኮ ጋዜጣው በየዕለቱ መንግስትን ብቻ ሲያወድስ ማየትን አይፈልግም። ስለዚህ አዲስ ዘመን አሁን ላይ የተለያየ ሐሳብን የሚያስተናግድ ጋዜጣ እየሆነ ነው የመጣው። ይህ በመሆኑ ለእኔ እዲስ ተስፋ ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ ተቀባይነቱ እየጨመረ ይመጣል። የሚታተመውም ቁጥር እየጨመረ፣ ህዝቡም እየወደደው ይመጣል።
አዲስ ዘመን፡- እርስዎ የድርጅቱ የቦርድ አመራር እንደመሆንዎ ድርጅቱ በቀጣይ የያዘውን እቅድ እንዲያሳካ ስራ አመራር ቦርዱ ምን ለመስራት ተዘጋጅቷል?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ቦርዱ አንዱ እቅዱ ድርጅቱ የሚያካሂደውን የለውጥ ሂደት ስራውን ማገዝ ነው። ድርጅቱ ሪፎርም ላይ ነው። የሰራተኞችና የአመራሩ የተባበረ መንፈስ እንዲኖር፣ መግባባት እንዲሰፍን የስራው ቦታ ለስራ ሳቢና ምቹ እንዲሆን ነው የቦርዱ የመጀመሪያው ስራ። አንድ ሰራተኛ ወደስራው ሲሄድ ደስ እያለው ሊሆን ይገባል። ችግር እንኳ ቢኖር በመነጋገር መግባባት እንዲኖር ማድረግ ነው ብዬ አምናለሁ።
ሁለተኛው ደግሞ እየተደረገ ያለውን ሪፎርም በተለይ በህትመት ውጤቶቹ ላይ ያለውን ለውጥ ማገዝ ነው። ሶስተኛው እኔ ራሴ በጣም ትኩረት እንዲሰጠው የምፈለገውና ሊሰጠው የሚገባው በተለይ የቦርድ አባል ሆኜ ከመግባቴ በፊት በድርጅቱ ሰራተኞች ዘንድ ትልቅ ቅሬታ እነደነበር የማውቀው ነገር አለ። ይኸውም በክፍያ በኩል ከሌሎች አቻ ድርጅቶች ጋር ሲተያይ የድርጅቱ ሰራተኞች የወር ደመወዛቸው አነስተኛ ነው። ይህ ደግሞ መስተካከል አለበት፤ ምክንያቱም ድርጅቱ እያተረፈ ነው። እስካተረፈ ድረስና ወጪውን መቋቋም እስከቻለ ድረስ የሰራተኞቹ ኑሮ መለወጥ አለበት። ለሰራተኛው ለስራ መነሳሳት እጅግ አስፈላጊ ነው። አንድ መስሪያ ቤት ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ስራውን ደስ እያላቸው መስራት አለባቸው። ለኑሯቸው የሚሆን በቂ ገቢ ማግኘት አለባቸው። አነስተኛም ቢሆን ከሚያገኟት ላይ መቆጠብም መቻል አለባቸው። የኑሮ ደረጃቸውም መለወጥ አለበት። አሁን ያለው አዲሱ ቦርድ በዚህ ያምናል። ስለዚህም የደመወዝ መሻሻያ መደረግ አለበት። የድርጅቱ ሰራኞች በጣም ትልቅ ስራ እየሰሩ በጣም ትንሽ እየተከፈላቸው ያሉ ስለሆኑ የደመወዝ ማስተካከያ መኖር አለበት። የስራ አካባቢ ያማረ መሆን አለበት የሚል እምነት ቦርዱ አለው።
አዲስ ዘመን፡- በእርግጥም እርስዎ እንዳሉት የክፍያው ጉዳይ የሰራተኛው ዋና ጥያቄ ነው፤ ብዙ ሰርቶ ትንሽ የሚከፈለው መሆኑ የሚቀጥለው ታዲያ እስከ መቼ ነው?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- በመጀመሪያው የስብሰባ ቀን ያነሳሁት ነገር ቢኖር ይህን አሁን ያነሳነውን ሐሳብ ነው። ቅድሚያ ተሰጥቶት መስተካከል ያለበት የሰራተኞቹ የኑሮ ሁኔታ እና መስተካከል ያለበት ደመወዛቸው ነው። በመሆኑም ይህ ሐሳብ በፍጥነት እንዲተገበር ነው ያቀረብኩት። ያገኘሁት መልስ ደግሞ የድርጅቱ መዋቅር በአዲስ አደረጃጀት የተሰራ በመሆኑ በቦርዱ ይጸድቃል የሚል ነው። እሱ ከጸደቀ በኋላ የሚከተለው ደመወዙን የማስተካከል ስራ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የፎቶ ግራፍና የጋዜጣ ክምችት ያለው ተቋም ነው፤ ይህ ሀብት ለአገራዊ ፋይዳ እንዲውል ምን ማድረግ ይገባል ይላሉ?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- አሁን ድርጅቱ ያለበት ቦታ ጠባብ ነው። ስለዚህም ድርጅቱ ሰፊ ቦታ ቢያገኝ ማተሚያ ቤቱንም ሰርቶ ያለውን ሀብት ለእይታ የሚያቀርብበት እንደ ኤግዚቢሽን አይነት ቦታ ቢኖረው ታሪክን የሚያወሱ የተለያየ ዘመን ፎቶዎችን እንዲሁም በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የታተሙ ስራዎችን ቢያቀርብ የሚጎበኝ ድርጅት ቢሆን የበለጠ ፋይዳ አለው።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በትንሽ ቦታ ያለ ነገር ግን በጣም ትልቅ የሆነ ድርጅት ነው። በጣም ትልቅ አገራዊ ስራ የሰራ፣ ታሪክን በትንሽ ቦታ ላይ አከማችቶ ያለ ትልቅ ድርጅት ነው። ስለዚህ ብዙ ትኩረት የሚስያፈልገው ድርጅት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሽግግርና በቀውስ ጊዜ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸው ምን መሆን አለበት?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- ያለፈው የለውጥ ጊዜ አለ፤ ከፊታችን ያለው ጊዜ ደግሞ ከበድ የሚል ይመስለኛል። ሊጎዳን የሚችለው ዋናው ነገር የመረጃ መዛባት ነው ብዬ አምናለሁ። የመረጃ ፍሰት፣ እውነ ተኛነት በጣም ያስፈልጋል፤ ጊዜው ወሳኝ ነው። እናም የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎች የህዝብም ሆኑ የግል ሚዲያዎች በከፍተኛ ትጋትና ጥራት ትክክለኛውን መረጃ በማቅረብ በከፍተኛ ኃላፊነት ሊሰሩ የሚገባበት ወቅት ነው።
ምክንያቱም በፌስቡክና በዩቲዩብ መረጃዎች ከሄድን የተሳሳቱ መረጃዎች ሊሆኑ ይችላሉና ህዝብን ወደማጋጨት፣ እልቂትን ወደማምጣት ሊወስዱ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ህዝብ የዋህ ይሆናል፤ ደጋግሞ የሚሰማውን ነገር ያምናል። ይህን መመከት የሚቻለው ደግሞ አሁን ባሉት ሚዲያዎች አማካይነት ነው። እና ያልተዛባ ሁሉን ያማካለ እውነተኛ የሆነና ተቀባይነት ያለው መረጃ ቶሎ ቶሎ በማቅረብ በኩል የሚዲያዎች ሚና ከበፊቱም የበለጠ ነው ብዬ ነው የማምነው።
አሁን በፊት ለፊታችን ባሉ ወራት ውስጥ የሚዲያው ሚና በጣም ከፍተኛ ነው ብዬም እጠብቃለሁ። በተለይ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲከባበር በማድረግ፣ ህዝብ ሊያጋጩ የሚፈበረኩ ተንኮሎችን በማጋለጥና ትክክል እንዳልሆኑ በማሳየት ህዝቡ የሚፈልገውን ሰላም እንዲያገኝ መስራትም ይጠበቅባቸዋል የሚል እምነት አለኝ። ህዝቡ ሰላምን፣ በልቶ ማደርን፣ ዴሞክራሲን እንዲሁም መልካም አስተዳደርን ነው የሚፈለገው። ብጥብጥም ሆነ የማንም ደም እንዲፈስ አይፈልግም። ምክንያቱም አገሪቱ ገና በልታ የማደር ጥያቄ ላይ ናት። ከዚህ አንጻር ሰላምን የሚያሰፍን ነገር ቢሰራ መልካም ነው የሚል አተያይ አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ግጭትን የሚቆሰቁሱ ብሎም አንድነትን የሚያናጉ አንዳንድ ሚዲያዎች አሉ ይባላልና ለእነዚህ የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- የመገናኛ ብዙሃንም ሆኑ የፖለቲካ መሪዎች እንደ እኔ ምኞት ወደ ብስለትና አስተሳሰብ ልህቀት ቢመጡ እላለሁ። ምክንያቱም የሚለኮሰው እሳት ለኳሹን መልሶ ማቃጠሉ አይቀርም። ያ እንዳይሆን ግን በትዕግስትና የአስተሳሰብን አድማስ በማስፋት ራሳቸውን ለህዝባቸው ሲሉና የሚጎዳውን ህዝባቸውን በማሰብ ለእነሱ ሲሉ በብስለት ያላቸውን አስተሳሰብ ቢያራምዱ ለሁላችንም ይጠቅማል ብዬ አምናለሁ፡፡
እንታገልለታለን የሚሉት ህዝብ መልሶ የሚጎዳ ከሆነ አይጠቅሙትም፤ ይጎዱታልና። ግጭት ቢነሳ፤ ደምም ቢፈስ የሚጠቀም ማንም የለም። ስለዚህ የፖለቲካ መሪዎቻችን አስተዋይ ይሁኑ ማለት እፈልጋለሁ። እውነት ለመናገር ደግሞ ብዙዎቹ የተማሩ ናቸው። ነገር ግን መማር ብቻ በራሱ በቂ አይደለም። አንድ መሪ አዕምሮው ብቻ ሳይሆን ልብም ያስፈልገዋል። ስለዚህ በአዕምሮው ብቻ ሳይሆን በልቡም መምራት አለበት። አዕምሮ በመረጃ የተሞላ ሆኖ ልቡ ደግሞ መልካም ካልሆነ አስቸጋሪ ነው። እንዳልኩሽ ብዙዎቹ መሪዎች የእውቀት ችግር የለባቸውም። ነገር ግን ልባቸውን አስተካክለው ለሚቀጥለው ትውልድም ሆነ ለህዝቡ መልካም እንዲሆንለት ሊያስቡ ይገባል። ወደዚህ ማስተዋልና የልብ ስፋት ቢመጡ ደግሞ ደስታዬ ወሰን አይኖረውም።
አዲስ ዘመን፡- አዲስ ዘመን 79ኛ ዓመቱን እያከበረ ነውና ከዚህ ጋር ተያይዞ እንደ ድርጅቱ የቦርድ አመራርነትዎ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ዶክተር ወዳጄነህ፡- በመጀመሪያ እነዛን የድርጅቱን ትጉ ሰራኞች እንኳን ለ79ኛ ዓመት አደረሳችሁ ማለት እወዳለሁ። የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ጌትነት እንደነገሩኝ ከሆነ ደግሞ አዲስ ዘመን እስከ 80ኛው በዓሉ ድረስ ዓመቱን ሙሉ በዓሉ የሚታሰብ ነው የሚሆነው። ጋዜጣውን በአዲስ መልክ ለህዝብ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። ያሉትን የህትመት ውጤቶች በሙሉ ማስተዋወቅ አለብን። በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ወሳኝ ታሪክን የያዘ ነው። ስለዚህም በዓሉን በደስታ እናከብራለን። ለ80ኛ ዓመት በዓሉ ደግሞ እግዚአብሄር በሰላም ያድርሰን እላለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለሰጡን ጊዜ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር ወዳጄነህ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 30/2012
አስቴር ኤልያስ