የክፉ ገጽ ንባብ መንደርደሪያ፤
አሜሪካ ጣሯ በዝቷል። መከራዋም በርክቷል። በርካቶቹ ግዛቶቿ ታመዋል፤ ታምሰዋልም። የዜጎቿ ምሬትና ቁጣ ገንፍሎ አመጽ በተቀላቀለበት ሆታ አደባባይ ላይ መዋል ከጀመሩ አሥር ቀናት ተቆጥረዋል። የኮቪድ ወረርሽኝም በፊናው መቶ ሺህ ዜጎቿን ወደ መቃብር ሸኝቶ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን አልጋ ላይ እንደጣለባት ነው። ይሄም አነሰ ብሎ ሌላ መከራ እየዘነበባት እምባዋን መንታ መንታ በማፍሰስ ላይ የምትገኘው ገናናዋ አሜሪካ በጣር ላይ ነች ማለት ይቻላል። ነገሯ ሁሉ “ከአንበጣ የተረፈውን ኩብኩባ፣ ከኩብኩባ የተረፈውን ተምች፣ ከተምች የተረፈውን ዶጎብያ በልቶባት” የታላቅነቷ ክብር የመምሸት አዝማሚያ እያሳየም ይመስላል።
የበርካታ ሀገራት ዜጎች “ከጎናችሁ ነን!” እያሉ የሕዝቦቿን ቁጣ ተቀላቅለው በየአደባባዮቻቸው ድጋፋቸውን እየገለጹ ቢሆንም በሌላ አንጻርም “የወረደባት መዓት ሲያንስባት እንጂ አይበዛባትም!” እያሉ በገጠማት ክፉ አበሳ የሚሳለቁባት ወደረኞቿም አልጠፉም። በችግሯ ላይ መሳለቅ ውጤቱ የከፋ መሆኑ የገባቸው አይመስልም። ቀን በጣለው ላይ ዱላ ማሳረፍ በራስ ላይ ናዳ የመጥራት ያህል የከፋ ነው።
የአፍሪካ አሜሪካዊው ጥቁር የጆርጅ ፍሎይድ ደም በአንድ ነጭ የፖሊስ አባል ደመ ከልብ መሆኑ ሰበብ ሆኖ በሚኒሶታዋ ክፍለ ግዛት በሚኒያፖሊስ ከተማ የተቀሰቀሰው ሕዝባዊ የበቀል ቁጣ አድማሱን አስፍቶ በመላው የአሜሪካ ግዛቶች እየነደደ መሆኑ ሰሞንኛ የዓለማችን መሪ ዜና ሆኗል። ሕዝባዊው አመጽ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚደረገውን ርብርብ አዘናግቶ የሀገሪቱን መከራ እንደሚያገዝፍ ብዙዎች ሥጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። በየደረጃው የሚገኙ መሪዎቿም እርስ በእርስ እየተነቋቆሩ ሲተቻቹ ማየት አርነት ያወጣቸውን “ዴሞክራሲ” እንድንታዘበው አድርጓል።
የጆርጅ ፍሎይድ በግፍ የተለወሰ ግድያ በርግጥም የሰው ዘሮችን በሙሉ የሚያስቆጣ ድርጊት ነው። በግሌ ደግሞ ክፉውን መርዶ በሰማሁ ዕለት ስሜቴን መቆጣጠር ተስኖኝ የእንባ መዋጮዬን አድርሻለሁ። የስሜቴ መነዋወጥ ምክንያቱ ሁለት ነበር። አንድም የሰብዓዊነት ስሜት ግድ ብሎኝ ሲሆን፤ ሁለትም በሚኒሶታ ክፍለ ግዛት ውስጥ እኔም ለዓመታት የኖርኩበት ጊዜያዊ ቤቴ ስለነበር ክስተቱ ክፉኛ አሳዝኖኛል። ለክፍለ ግዛቱ ሁለቱ ውብ መንትያ ከተሞች (Twin Cities) ለሚኒያፖሊስና ለሴንት ፖል የተቀኘሁላቸውን ቅኔ መለስ ብዬ ሳነብ ብዙ ትዝታ ስሜቴን አመሰቃቅሎ ኀዘኔን በማክበድ ደብቶኝ ከርሟል።
“መተንፈስ አልቻልኩም! እባክህ አትግደለኝ!” የሚለው የንፁሁ የፍሎይድ የጣር ጩኸት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ከተጠቀሰችው ከራሄል እምባና ከንፁሁ የአቤል ደም ጋር ይመሳሰል ይመስለኛል። “የወንድሜ ጠባቂ ነኝ!” የሚል እብሪት የተጠናወታቸው ዘረኞች በጥቁሮች ላይ እየፈጸሙት ያለው ግፍ ብዙ አፍሪካ አሜሪካውያን ጥቁሮችን በአደባባይ እየሰዋ ለዘመናት ዘልቋል። የአሜሪካ የታሪክ ገጾች በርካቶቹ በዚሁ “የጠቆረ ታሪክ” የጠየሙ የሆኑትም ስለዚሁ ነው። ሰሞኑን ገንፍሎ የወጣው የሕዝብ ቁጣ የአንድ ክስተት ውጤት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ሲብላላ ኖሮ የገነፈለ እሳተ ጎሞራ ነው እየተባለ የሚነገረውም ስለዚሁ ነው። ለምስኪኑ ጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ እረፍትን፣ በኀዘን ልባቸው ለተሰበረ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ መጽናናትንና ለመላው የአሜሪካ ሕዝብ መረጋጋትን የምመኘው በቤተሰባዊ ርህራሄ ነው።
ሚኒሶታና የሰነበተ ትዝታዬ፤
የሚኒሶታን ነገር ካነሳሁ አይቀር በእነዚያ ውብ መንትያ ከተሞች በትምህርት ምክንያት በኖርኩባቸው ዓመታት አስተውላቸው የነበሩት አንዳንድ ትዝታዎቼና ገጠመኞቼ ከምን ጊዜውም በበለጠ ወለል ብለው የታዩኝ በዚህ አሳዛኝ ወቅት ነው። በዚያ ክፍለ ግዛት ውስጥ ይኖሩ ከነበሩት ቅይጥ የሰው ዘሮች መካከል (Meliting Pot እንዲሉ) ኢትዮጵያውያን ወገኖቼና ኢትዮጵያዊያነትን ክደው “አቢሲኒያዊነትን” የመረጡ የሀገሬ ልጆች ቁጥራቸው ቀላል የሚባል አልነበረም። ዛሬም ዲሞግራፊው ቢሰፋ እንጂ እንዳልጠበበ እጠረጥራለሁ። ዛሬ የኀዘን ፍራሽ ላይ የተቀመጠው የሚኒሶታ ግዛት ከወገኖቼ ቁጥር ባልተናነሰ ሁኔታ ከጎረቤት ሀገሯ ሱማሊያ የተሰደዱ ዜጎችም መኖሪያ ነበር።
ልዩነቱ የሱማሊያ ዜጎች የሰፋ የፖለቲካና የአመለካከት ልዩነት ቢኖራቸውም እንኳን በሌሎች ማኅበራዊ ተራክቧቸው መደጋገፋቸውና መረዳዳታቸው የሚያስቀና ነበር። አንድ ዜጋቸው የተጠቃና የተበደለ ከመሰላቸው “ሆ!” ብሎ የሚወጣው መላው የግዛቱ ነዋሪ ነው። ከሚኒሶታም አልፎ በሌሎች የአሜሪካ ግዛቶች ውስጥ የሚኖሩ ሱማሌያዊያንም ድጋፋቸውን የሚገልጹት በሚያስደንቅ ፍጥነትና ሁኔታ ነበር።
ሱማሌያዊ አሜሪካዊቷ ኢልሃን አብዱላሂ ኦማር የሚኒሶታን ክፍለ ግዛት በመወከል ከ2019 ጀምሮ የአሜሪካ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ወደ መሆን ክብር የመሸጋገሯ ውጤትም ከራሷ ጥረትም አልፎ የዜጎቿ የመተባበር አቅም ስለመሆኑ ለመገንዘብ አይከብድም።
በአንጻሩ በዚያው በሚኒሶታ ክፍለ ግዛት የሚኖሩት የእኔው ወገኖች በዘርና በቋንቋ፣ በጎጥና በመንደር ተቧድነው ሲናቆሩና ሲናከሱ ማየት የተለመደ ክስተት ነበር። አልፎም ተርፎ በግዛቱ ውስጥ ይገኙ በነበሩት “ኢትዮጵኌያን ሬስቶራንቶች” ውስጥ የዕለት እንጀራቸውን ሊመገቡ ጎራ ይሉ የነበሩት የአንድ እናት ልጆች ምርጫቸው በራሳቸው ዘርና ቋንቋ ባለቤትነት ወደ ተያዙት የሚያደላ ነበር።
እኔን መሰሎቹ ኢትዮጵውያን የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው በሚመረቁበት እለት በሤረኞቹ እንዲውለበለብላቸው የሚመከሩት ከፋም ለማም የሀገሪቱ ይፋዊና ብሔራዊ ሰንደቅ ዓለማ ሳይሆን ፖለቲካ በሸመናቸው ቀለማት የተፈበረኩ ጊዜ ወለድ አርማዎች እንደነበሩ ትዝ ይለኛል። በርካታ ልብ የሚሰብሩ ትዝታዎችን መቀስቀሱን ስላልወደድኩት እንጂ ብዙ ለትዝብት የሚዳርጉ ብቻ ሳይሆኑ ልብ የሚሰብሩ ጉዳዮችንም ማስታወስ ይቻል ነበር። ዛሬም ድረስ ሁኔታው እንዳልተለወጠ ወዳጆቼ በኀዘን ይገልጹልኛል። ይህ ሁኔታ የተለወጠ ዕለት ለፈጣሪ የተሳልኩትን ስዕለት የማገባው ሳይረፍድ ነው።
መለስ ብዬ የሀገሬን ደጃፍ ላንኳኳ፤
ብዙው ሀገራዊ ታሪካችን ሊጻፍና በአግባቡ ለትውልድ ሊተላለፍ ካልቻለባቸው ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ዝምታ ወዳድ መሆናችን ይሆንን እያልኩ ራሴን እጠይቃለሁ። ስንገፋ፣ ስንበደል፣ ስንበዳደል ወይንም መራራ ግፍ ሲፈጸምብን በትዕግሥት የምናልፈው “ዝም አይነቅዝም” በሚል ብሂል መፅናኛነት ነው። አፋችን ተለጉሞና ዓይናፋር ሆነን በሰላማዊ መንገድ ድምጻችንን ማሰማት የሚያዳግተንም ፈሪዎች ስለሆንን ይመስለኛል። “ማን ፈሪ አደረገን? በምን ታሪካዊ ምክንያትና ሰበብ የተነሳ?” ባይ ጠያቂ ከሞገተኝ በውይይት ለመተማመን ዝግጁ ነኝ።
አሜሪካኖች “enough is enough” የሚል አባባል አዘውትረው ይጠቀማሉ። “በቃ ብያለሁ በቃ!” እንደማለት ነው። የሰሞኑን የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ተከትሎ የገነፈለው የሕዝብ ቁጣ ለአባባላቸው እውነታነት ጥሩ ማሳያ ይመስላል። ክፋቱ ቁጣቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ከመግለጽ ይልቅ በንብረት ዘረፋ፣ ማቃጠልና ወድመት ላይ ማተኮራቸው ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው። ቁጣቸው የአንድ ዕለት ግፍ የወለደው እልህ ውጤት ሳይሆን በዓመታት ውስጥ ሲብላላ የኖረ የነጭ ዘረኝነት ትምክህት እንደሆነ ይገባኛል። የሕዝቡ ቁጣ ለዘመናት ሲዘራ የኖረው ክፉ ዘር እንደምን ለማዝመር መድረሱን የሚያመለክት ጥሩ ማመላከቻና ማስተማሪያም ጭምር ነው።
የእኛም ጉዳይ እንደዚያው ይመስለኛል። ባህላችን ይሁን ልማዳችን ብቻ አንዳቸው የጫኑብን እንደ መርግ የከበደው ሸክማችን “ዝም ባለ አፍ ዝንብ አይገባም!” አባባልን ምርጫችን አድርገን ብዙ ግፎችን አፋችንን በመለጎም እንድንሸከም ተገደን የኖርን ይመስለኛል። “ዝምታ ወርቅ ነው” እየተባልን ስንመከር፣ ወይንም “ዝም አይነቅዝም” እየተባልን ስንገሰጽ ምክሩን በእሳት ፈትነን ወርቅነቱን ከማረጋገጥ ይልቅ አለያም ዝምታ ያለመንቀዙን ለማሳየት ከመሞከር ይልቅ “እህህ!” እያሉ ማለፍን የሕይወታችን ክፍል አድርገን ኖረናል። ሲበዛም፤
“እህህን ለፈረስ ያስተማርኩ እኔ ነኝ፣
እርሱም ጥሬ ሲያምረው እኔም ሲቸግረኝ።”
እያልን በቀን ያልፋል ተስፋ መጨከናችን የተለማመድነው ሕይወታችን ነው።
ጉዳያችንን ከሚኒሶታ ትዝታ ጋር እናቆራኘውና አሁንም አንዳንድ ሀገራዊ ችግሮቻችንን እየነቀስኩ ልቆዝምባቸው። ጥቂት ሚኒሶታ ወለድ “ፖለቲከኞቻችን” በውቦቹ መንትያ ከተሞች ውስጥ እየተንፈላሰሱ በመኖር የጠመቁልንን የተንኮል ሤራ እዚህ ሀገር ውስጥ እያሳከሩበት ሕዝብ ለሕዝብ ሲያጫርሱ ስመለከት ልቤ ይደማል። እነርሱ በዘሩት ክፉ ዘር የምን ያህሉ ወገኖቻችን ደም በከንቱ ፈሶ እንደቀረ የትናንት ትዝታችን የዛሬ ኀዘናችን ነው።
“ምን ያህል ሰው ሞተ” ብሎ ንግግር መጀመሩ ለእኛ ብርቃችን አይደለም። ለሞቱት ወገኖቻችንም ፍራሽ አንጥፈን ከንፈራችንን እየመጠጥን ልቅሶ መቀመጥን ተክነንበታል። አልቅሶ እምባን በፍጥነት ማበስም የኖረ ባህላችን ነው። ስለ ሚኒሶታ ባሰብኩ ቁጥር ስለ “ኢምፓዬር” እየቦተለኩ የሚውሉ ደማቸው የእኔው ደም የሆኑት “ምንደኞች” ሁሌም ትዝ ይሉኛል። የሰላማዊ ጥሪውን ደውል ሰምተው እዚህ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላም እየሠሩ ያሉትን እኩይ ተግባራት ሳስተውል የክፋታቸው ክብደት ምን ያህል እንደሆነ ለመገመት እቸገራለሁ። ሀገራዊ በሩ በተዘጋባቸው ዓመታት እዚያው ሚኒሶታ ውስጥ ተቀምጠው የጎነጎኑትን የተንኮል ስትራቴጂ ሸክፈው ሀገር ቤት ከተመለሱ በኋላ ድርጊታቸው አፍጥጦ አዋጅ እያለ “ውስጣችን በዝምታ ከመንቀዙ የተነሳ ብቻ” በአርምሞ በማለፋችን እነሆ የዛሬያችን ቀን ከብዶብን ሸክሙ እንዳንገዳገደን አለ።
ጉዳዩ በሚኒሶታዊያን ገድለኞች ፖለቲከኞቻችን ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም። ሌሎችም አሉ እንጂ። በበረሃ ማኒፌስቷቸው ምሳር እየፈለጡ፣ እየቆረጡና እየሸነሸኑ ሀገር ሲቆረጥሙ እያስተዋልን ዝምታችን አንቅዞን አፋችንን በእጃችን ላይ ጭነን የምንታዘባቸው ሀገራዊ ጉዳዮቻችን በርካቶች ናቸው። ያለፈው እኩይ ድርጊታቸው አልበቃ ብሎ ዛሬም በንስሃ ታጥቦ ከመንጻት ይልቅ ባደፈጡበት ዋሻ ውስጥ እንደመሸጉ አሮጌ ዲሞትፎራቸውን እየወለወሉና ያፈጀ አይዲዮሎጂያቸውን እያነበነቡ የጦርነት አዋጅ በማወጅ የዕልቂት ከበሮ ሲደልቁ እያስተዋልናቸው ነው። መተላለቅን ሲዘምሩልን “አሜን!” ብለን የመቀበል ያህል በዝምታ የተሸበበው አፋችን ነቅዞ አንቅዞናል። የመንግሥት ዝምታም ከእኛ ከተራ ዜጎች ብሶ “ዝምታ ወርቅ ነው”ን መርህ የሚያራምድ ስለመሰለን ግራ ተጋብተናል።
የጦርነት ወሬ ሱስ የሆነባቸው ገድለኞች ሕዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር የሚጠምቁት የሤራ ጉሽ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየኮመጠጠ መሄዱን ስለለመድነው እንደሆንም እንጃ ብቻ በ“ዝም አይነቅዝም” ፍልስፍና ታውረን አፋችንን የለጎምን ይመስለኛል። የጆርጅ ፍሎይድ ሞት ለሚሊዮኖች የልብ ስብራት የሆነውን ያህል ለአንዳንድ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ደግሞ ዕድሉን የሥልጣን ህልም ማስፈጸሚያ መሰላል ማድረጋቸው ለትዝብት ዳርጓቸዋል። ልክ እንደኛዎቹ ጉዶች መሆኑ ነው።
የኮቪድ ወረርሽኝ እንደ ልቡ ፈንጭቶ ጥቁር ማቅ ያለበሳት የኒዮርክ ግዛት ገና ከህመሟ ሳታገግም ሌላ የሕዝብ የቁጣ ወጀብ አሳር እያበላት ይገኛል። ይህንን የአመጽ እንቅስቃሴ እንደ ዕድል በመቁጠር ዲሞክራቱ ገዢዋ አንድሪው ኩሞ ሪፓብሊካኑን የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ትራምፕን ከዳግም የምርጫ ውድድር ለማሰናከል እንደ ጥሩ ዕድል እየተጠቀሙበት ይመስላል። ሚስተር ኩሞ ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የፓርቲያቸው ተቀናቃኞችም የፕሬዚዳንቱን መውደቅ በመመኘት በየአደባባዩ ከፍና ዝቅ እያደረጉ ሲያዋርዷቸው እያስተዋልን ነው። በዚህ ሽኩቻ መሃል የአሜሪካኑ የኮቪድ አጀንዳ የተዘነጋ ይመስላል።
በንቅዘት የተሸፈነው የእኛም ዝምታ ውሎ አድሮ ጦሱ እንዳይከፋ ሥጋት ገብቶኛል። በስመ ዴሞክራሲ የሞት ድግስ እየደገሱልን የሚያደነቁሩንን “አልሞት ባይ ተጋዳይ ያረጀና ያፈጀ አይዲዮሎጂ ምርኮኞች” ከወዲሁ በያለንበት የተሸበበውን አፋችንን ገልጠን ድምጻችንን ከፍ አድርገን እያሰማን አደብ እንዲገዙ ካላደረግን በስተቀር ዝምታችን ውሎ አድሮ የአሳር ጫጩቶች መፈልፈሉ እንደማይቀር ልብ ተቀልብ ሆነን ልናስብ ይገባል።
የፎሎይድ ሞት ያስቆጣቸው የአሜሪካ ነውጠኞች ከያዟቸው መፈክሮች መካከል አንዱ ቀልቤን በሚገባ ገዝቶታል። “We have not right to remain silent” – “ዝም የማለት መብት የለንም” እንደ ማለት ነው። ዝምታችን አንቅዞን እስከ ዛሬ በርሃብ፣ በጦርነት፣ በግጭት እየተጠበስን ኖረናል። ሕዝባችን ለራስ አምላኪ ፖለቲከኞች የተመቻቸ ወንበር ሆኖ ለዘመናት የኖረው ዝምታው ሰቅዞ ስለያዘው ይመስለኛል። “Silence is the best killer” እንዲሉ።
የሰላምን ዘንባባ በመያዝ ዝምታን መስበር ይቻላል። በግሌ አመጽ የተቀላቀለበት ተቃውሞን በፍጹም አልደግፍም። የአደባባይ ጩኸትንም ብቻ የመፍትሔ መንገድ አድርጎ መራመዱን አላምንበትም። በየሙያችን፣ በየውሎ መስካችንና በየሚዲያው ድምጻችንን አጉልተን በማሰማት “ተነስ! ተዋጋ!” እያሉ ለጦርነት የሚቀሰቅሱንን የሀገርና የሕዝብ ጠላቶች አንቅረን እንደተፋናቸው ልንነግራቸው ይገባል። በተናዳፊ አንደበታቸው “ቆይ ግዴለም መስከረም ሲጠባ እንተያያለን!” እያሉ የሞት መርዶና የሽብር ስንቅ እየደገሱልን ያሉትንም አምርረን ልንገፈትራቸው ይገባል።
የኮቪድ ጦርነት ሳያንሰን ሌላ የጦርነት ቀጣና የሚቀይሱልንን “ባለ ዛሮች” አጥብቅን በድምጻችን፣ በብዕራችን፣ በጥበብ ውጤቶቻችን፣ በብዙኃን መገናኛና በየመድረኩ ላይ ጨክነን ሟርታቸውን በማምከን እርቃናቸውን ማስቀረቱ ለነገ የሚባል የቤት ሥራ መሆን አይገባውም። የጦርነት አዋጅ ሰለቸን፣ እርስ በእርስ መቧጨቁ አከሰረን እንጂ ትርፍ አላገኘንበትም። በዘርና በቋንቋ ያናከሱን ቁስል እንዳይጠግግ የክፋት አሲድ ሲነሰንሱብን እንደ አምና ካቻምና በአመጽ ሟርታቸው ተስፋ ሰንቀን ልንጋደል አይገባም። ጠንክረን እየተፋለምናቸው ከእኩይ ህልማቸው ካላነቃናቸው በስተቀር በሤራቸው ተጠልፈን ምርኮኛቸው መሆናችን አይቀሬ ይሆናል። ሰላም ይሁን!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com