እውነተኛ ዴሞክራሲ ባለበት ሀገር ሚዲያ ከመንግስትና ከማኅበረሰብ ገለልተኛ ታዛቢ ሆኖ ያገለግላል። መገናኛ ብዙሃን ባይኖሩ ዜጎች የመንግስት ኃላፊዎች የሥልጣን አጠቃቀም ግንዛቤ አይኖራቸውም። ዴሞክራሲ በሌለባቸው ሀገራት ጋዜጠኞች ይደበደባሉ፣ ይታሰራሉ እና የሚዲያ ነፃነት ይታፈናል። እነዚህ አስፀያፊ ተግባራት የሀገር ገፅታ ወይም የባለሥልጣናት ግድያና ሥም እንዳይጎድፍ ለመጠበቅ በሚል የሚፈፀሙ ናቸው።
መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች የመናገር ነፃነትን ያካትታሉ። እነዚህ መብቶች መረጃ የማግኘት፣ የመስጠትና የማጋራት እና ሃሳብንና መረጃን ለሚዲያና ለሌሎች ማጋራት ያካትታል። ሚዲያዎች በዴሞክራሲ በበለፀጉ ሀገራት ውጤታማ ናቸው። በእነዚህ ሀገራት ያሉ ህገ-መንግስቶች ህግ አውጪው የመንግስት አካል የመናገር ነፃነት የሚገድቡ ህጎች እንዳያወጣ ይከለክላሉ።
ሚዲያው ሁለት ሥራዎች አሉት። አንደኛው ህዝቡን ማሳወቅ ነው። ሁለተኛው ደግሞ የመንግስት ባህሪን መታዘብና መመርመር ነው። ይሁን እንጂ መንግስትና ሚዲያ ያላቸው ግንኙነት አንዳንዴ አስቸጋሪና ጠላትነት እንዳለበት መረጃዎች ያሳያሉ። የመናገር ነፃነት በሚዲያ በመጠኑ ሊገደብ ይገባል። ትንሽ እሳት ትልቅ ስፍራን ሊያጠፋ እንደሚችል ሁሉ የተሳሳተ መረጃ ከፍተኛ ጥፋት ሊያመጣ ይችላል። የጋዜጠኝነት ስታንዳርዶች ደረጃቸውን መታዘብ ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ሚዲያ በመናገር ነፃነት ሰበብ ችግር ሳይፈጥሩ የሚዲያ ህግና ደንብ እንዳይጥሱ ያደርጋቸዋል።
በዴሞክራሲ በበለፀጉ ሀገራት የጋዜጠኝነት ስታንዳርዶች ደረጃ የማይታዘቡ ሚድያዎች በህዝብ ታማኝነታቸውን ያጣሉ። መንግስት በህግ ከመጠየቅ አስቀድመው አንባቢያንና ተመልካቾች ጋዜጦችንና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ከማንበብና ከመመልከት ይቆጠባሉ። የዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋዜጠኝነትን አወሳስቧል። የኢትዮጵያም ሚዲያም የዚሁ ሰለባ ነው። ቴክኖሎጂ ጋዜጠኞች ዜናዎችን የሚሸፍኑበትን አካሄድ ወደ ስሜት ቀስቃሽነት አዘንብሏል።
በዚህ ዘመን መረጃ በአብዛኛው በዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ በአነስተኛ ክፍያ ወይም በነፃ ስለሚገኝና በፍጥነት መሰራጨቱ በጋዜጠኝነት ላይ ጫና አሳድሯል። ሰበርና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ አድርጓል። ይህ ሁኔታ ህብረተሰቡ ለዜና መረጃዎች ያለውን አተያይ እና የጋዜጠኞች አዘጋገብ ከተለመደው አሠራር ለውጥ እንዲያደርጉ ገፋፍቷል።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ሚዲያው በሚፈለገው ልክ ማደግ አልቻለም። ሚዲያው በብዙ ውስብስብ ችግሮች ተከቧል። ሚዲያው አንባብያንን እና የማስታወቂያ ገቢን እያጣ ሄዷል። የህትመት ወጪዎች ከፍተኛ መሆን፣ የንባብ ባህል አለማደግ እና የሠለጠነ የሰው ኋይል አለመኖር ዘርፉ በሚፈለገው መጠን እንዳያድግ አድርጓል።
በዓለም ላይ የሚዲያው ኢንዱስትሪ በፍጥነት እያደገ ሲሆን በሀገራችን በኢትዮጵያ ግን አላደገም ማለት ይቻላል። ወደፊት የሚሆነውም መገመት ከባድ ነው። ይሁን እንጂ አንዳንድ አሁን እየታዩ ያሉ ለውጦች መልካም ዕድል እንዳለ ያሳያል። የፖለቲካ የመጫወቻ ሜዳ እየተከፈተ ነው። የፖለቲካ መሪዎች እና ጋዜጠኞች በይቅርታ መፈታት እና ክሳቸው መሠረዙ የሐሳብ በነፃነት አለ ለማለት ይቻላል። ፅንፈኛና ያልተለመደም ሐሳብ ያላቸው ዜጎች እና የሚዲያ ተቋማት ሳይቀር ያለገደብ እንዲናገሩ መደረጉ መልካም የሚባል ነው።
መረጃና ሐሳብ በሰፊው መሰራጨት መቻል ሀገርን ለማሻገርና የፖለቲካ ባህል በአዲስ መልኩ ለማነፅ ይረዳል። ለተለያዩ አመለካከቶች የተጋለጠና የነቃ ህብረተሰብ ሲኖር ሀገራዊ የፖለቲካ ሥሪቱ አመርቂ ይሆናል። ይህ እንዲሆን ደግሞ ሚዲያ ከማንም በላይ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።
የሚዲያ ተቋማት የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ባለሀብቶች የራሳቸውን ፍላጎት ጋዜጠኞች እንዲሸፍኑ ያደርጋሉ። ይህ ደግሞ የዘገባ ዓይነቱ የመንግስትን ፖሊሲዎች የሚያርሙ ከመሆን ይልቅ የባለቤትነት ድርሻ ያላቸው ባለሀብቶች ፍላጎት ማራገቢያ ይሆናሉ።
ሚዲያ ባለው ተደራሽነት ሰፊ የታዳሚ ብዛት አለው። ይህ መሆኑ መረጃ ለሰፊው ህብረተሰብ እንዲደርስ ይረዳል። ተፅዕኖ ፈጣሪነቱም በዚሁ ልክ ይጨምራል። ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ደግሞ የበለጠ ናቸው።
ዜና ማሳራጫ ሚዲያዎች የመንግስት ባለስልጣናት የሥልጣን አጠቃቀማቸው በህግ ከተደነገገው ውስጥ መሆኑን ክትትል በማድረግ መልካም አስተዋፅኦ ያደርጋሉ። በዚህም ምክንያት የመንግስት ባለስልጣናት የሚዲያዎች መረጃ አሰረጫጨት መብቶች ላይ የሥራ ፍቃድ አሰጣጥ ቀላልና የተሣለጠ ማድረግ ያስፈልጋል።
ጋዜጠኝነት ዜጎች በማህበረሰባቸው፣ በሀገራቸው፣ በአህጉራቸው እና በዓለም ላይ የሚያግባባቸውና የሚያሳስባቸው ጉዳዮችን ያሳውቃል። ይህም ዓለም ሐሳብና ሀቅ ያጠላባት እና ዴሞክራሲ የሰፈነባት የተሻለች እንድትሆን ይረዳል።
ጋዜጠኝነት የሥነ-ፅሑፍ ዘርፍ ሲሆን አዲስ የተከሰቱ እና ሰዎች የማያውቋቸው ነገሮችን ያሳውቃል። በዚህ የሙያ ዘርፍ የተሠማሩ ሰዎች ጋዜጠኞች ይባላሉ። ጋዜጠኞች በጋዜጣ፣ መፅሔት፣ ድህረ-ገፆች፣ ቴለቪዥን እና ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ ይሠራሉ። ብርቱ ጋዜጠኞች ዕለት-ተዕለት ማንበብ እና መረጃ ማነፍነፍ የሚወዱ እና ዓለም ላይ ያሉ ሁኔታዎችን የሚከታተሉ ናቸው።
በቀደመው ሁኔታ ሀገራችን ኢትዮጵያ ሚዲያዎች በሁለት ፅንፍ የቆሙ ናቸው። የመንግስት ሚዲያዎች የመንግስት ፍላጎትን ይወግናሉ። በሚዲያ የሚተላለፉ ስርጭቶች ሥልጣን ላይ ላለው መንግስት የወገኑ ናቸው። የመንግስትን ክፍተት እና ፍላጎት የሚፃረሩ ሐሳቦችን አያስተላልፉም። የግል ሚዲያዎች ደግሞ ሥልጣን ላይ ላለው መንግስት የሚቃወሙ ሐሳቦችን አብዝተው ያስተላልፋሉ። ከእነዚህ ውጪ ያሉ ሚዲያዎች ደግሞ መዝናኛ ፕሮግራሞች ላይ ያተኩራሉ። በእነዚህ ሚዲያዎች የሚሠሩ ጋዜጠኞችም በተቋማቱ ፍላጎት ሥራቸውን እንዲሠሩ ይገደዳሉ።
እንግዲህ ከላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት የሀገራችን ሚዲያ በሚፈለገው መንገድ ማደግ አለመቻሉን ያሳያል። በመንግስት በኩል የሚዲያ ነፃነት እንዲያድግ መልካም የሚባል አስተዋፅዖ እየታየ ቢሆንም ከፅንፈኝነት የፀዳ ሚዛናዊነት ለመፍጠር ብዙ ሥራዎች ይቀራሉ። ከዚህ በተጨማሪም የሀገራችን ቁልፍ እና ትኩረት ያልተሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር አለባቸውም እላለሁ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 29/2012
በላይ አበራ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲ