ብዙ ጊዜ በሀገራችን “የአመለካከት ችግር” የሚል ሐረግ ሲነሳ ይደመጣል። በተለይ ፖለቲከኞች “የአመለካከት ችግር”ን የራሳቸውን ሐሳብ ማቀንቀን ያልቻሉ ወይም ያልፈልጉ ሰዎችን የሚገልጹበት ነው። አንድ ሰው ፖለቲከኞች የሚያቀነቅኑትን ሐሳብ ካላቀነቀነ ወይም ካልደገፈ የአመለካከት ችግር አለበት ይባላል። የእነርሱን ሐሳብ አለማቀንቀኑ በሐሳብ የተለየ የሚያደርገው ብቻ ሳይሆን አንዳንዴ በሀገር ወይም በሕዝብ ጠላትነት እንዲፈረጅ ያደርገዋል። በሀገራችን ዜጎች የተለየ ሐሳብ ስለነበራቸው ብቻ “ሀገርን የሚያፈርሱ፤ መንግሥታዊ ሥርዓትን የሚደረምሱ ምሕረት የለሽ ጠላት ናቸው” ተብለው በጥይት ተደብድበዋል። በአስተሳሰብ አለመብሰል ሀገራችን ውድ ዋጋ ከፍላለች። አሁንም እየከፈለች ነው። በዚህ ዝግጅት ውስጥ ምክንያት (reason) በሰው ልጅ አስተሳሰብ ውስጥ ያለውን ቦታና ከዚሁ አንጻር የኢትዮጵያን ሕዝብ የአስተሳሰብ ዕድገት በግርድፉ መቃኘት ይሞክራል።
አስተሳሰብ እጅግ ሰፊና ውስብስብ ትርጉም ያለው ጽንሰ-ሐሳብ ነው። አመለካከት ደግሞ አንድ ለየት ያለ ነገር የሚገለጽበት አስተሳሰብ ነው። አስተሳሰብ ያወቅናቸውንና የተረዳናቸውን ነገሮች በጽንሰ-ሐሳብነት ቀርጸን በቋንቋ የምንገልጸው ነው። ዕውቀት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ወሳኙ ጉዳይ የምናውቀውን ነገር ምንነት በምን ያህል ጥልቀት እንደምናውቅ ነው። ለምሳሌ ድንጋይ ዛፍ አለመሆኑንና ዛፍም ድንጋይ አለመሆኑን ማወቅ አያስቸግርም። ጤናማ የስሜት ሕዋሳት ያለው ሰው ሁሉ ይህን ልዩነት መረዳት ይችላል። ነገር ግን ድንጋይን ከዛፍ ወይም ዛፍን ከድንጋይ የሚለዩ ባሕርያትን ማወቅ ጥልቅ ግንዛቤን ይጠይቃል። ስለድንጋይ በቂ ዕውቀት ያለው ሰው ልዩ መገለጫውን ምክንያታዊ በሆኑ መንገዶች ሊገልጽ ይችላል። ይህ ሰው ሌላው ሰው የማያውቀውን ያውቃል ወይም ሌላው ሰው ማድረግ የማይችለውን ያደርጋል ማለት ነው – በዕውቀቱ ምክንያት።
አስተሳሰብ ብርሃን ወይም ጨለማ ሊሆን ይችላል። ላቅ ያለ ምክንያታዊ አቅም ያለው አስተሳሰብ ብርሃን ነው – ማወቅ የምንፈልገውን ነገር በተሻለ መንገድ ስለሚያሳየን። ደካማ ምክንያታዊ አቅም ያለው አስተሳሰብ ጨለማ ወይም የደበዘዘ ነው- ነገሮችን በሚፈለገው መልክ ሊያሳየን ስለማይችል። በስሜት ሕዋሳቶች ማወቅ የምንችለው እጅግ በጣም ውስን ነገሮችን ነው። በምክንያታዊ አስተሳሰብ ግን የተወሳሰበ ነገርን መረዳት እንችላለን። ብዙ ዓይነት አስተሳሰቦች አሉ። በተጨባጭ የሚታዩ ነገሮችን የሚገልጹ አስተሳሰቦች አሉ። በተጨባጭ የማይዳሰሱ ነገር ግን ለሰዎች ማንነትና ምንነት፤ ስለ ሰዎች ስብዕናና ችሎታ፤ ግንኙነትና ድርጊት፤ ባሕርይና ጠባይ የሚገልጹ ረቂቅ አስተሳሰቦችም አሉ። የሁሉም አሳማኝነት የሚረጋገጠው ባላቸው ምክንያታዊ አቅም ነው።
አስተሳሰብ እጅግ ጠቃሚ ነው፤ እጅግ ጎጂም ነው። ጎጂ የሚሆነው ችግርን መፍታት፤ ጥያቄን መመለስና አገልግሎት መስጠት ካልቻለ ነው። ሰዎችን ከማዋደድ ይልቅ የሚያጣላ፤ ከማቀራረብ ይልቅ የሚያራርቅ፤ ከማስተሳሰር ይልቅ የሚያፋታ ከሆነ ነው። ለሰው አቅም ከመፍጠር ይልቅ አቅም የሚያሳጣ፤ የሰውን ዕድገት ወደፊት ከመውሰድ ይልቅ ወደ ኋላ የሚመልስ ሲሆን ነው። በምክንያት የዳበረ አእምሮ ባብዛኛው ጥቅምን እንጂ ጉዳትን አይመርጥም፤ የሚበጅን እንጂ የማይበጅን ነገር አይቀበልም። የሰው አእምሮ ከተሻለ ወይም ላቅ ካለ ሐሳብ ለመድረስ ምክንያት የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉት። ለምን? እንዴት? በምን? የት? ወዴት? ምን ያህል? ብሎ በሚያነሳቸው ጥያቄዎች አማካይነት ከውጭ ወደ ውስጥ፤ ከቀላል ወደ ጥልቅና ረቂቅ ግንዛቤ ይገባል። ለእነዚህ ጥያቄዎች ጥርጣሬ የማያስነሱ ማስረጃ ያላቸው መልሶችን ይፈልጋል።
ምክንያት ውስብስብና ሰፊ ጽንሰ-ሃሳብ ነው። በቀላሉ ትርጉም መስጠት ያስቸግራል። በውስብስብነቱ ለሁለት መክፈል እንችላለን። ምክንያት በተፈጥሮ ሥርዓት ውስጥ ይገኛል። መንስኤ ከሚለው ፅንሰ-ሀሳብ ጋር የተቀራረበ ትርጉም አለው። ይህ ዓይነቱ ምክንያት ከኛ አእምሮ ውጭ ነው። በራሱ ለሁለት ሊከፈል ይችላል – አስፈላጊና አጋጣሚ በመባል። ለሁሉም ነገር መኖር፤ መንቀሳቀስ፤ መፈጠርና አለመፈጠር ምክንያት አለ – አስፈላጊ ወይም አጋጣሚ ምክንያት። ሌላው ምክንያት በሰው አእምሮ ውስጥ ያለ ነው። ይህ ጽሑፍ የሚያተኩረው በአእምሮ ውስጥ ባለውና በሚኖረው ምክንያት ላይ ነው። ከላይ የተጠቀሱ ጥያቄዎችን በመሣሪያነት በመጠቀም ነገሮችን መፈተሽ የሚያስችለን ምክንያት ነው።
ምክንያት ለሰው ልጅ ብርሃን የሚሰጥ ነው። በሁለቱ ዓይኖቻችን ማየት የማንችላቸውን ነገሮች የሚያሳየን የአእምሮ ብርሃን ነው። በቂ ምክንያት ወይም ምክንያታዊ አቅም ያለው ሰው በዓይኖቹ አይቶ፤ በጆሮው ሰምቶ፤ በአፍንጫው አሽትቶ፤ በምላሱ ቀምሶና በእጆቹ ደስሶ ከሚያገኘው ዕውቀት የሚልቅ ዕውቀት በምክንያት ያገኛል። በጥቅሉ የነገሮችን ውጫዊ ገጽታ አልፈን ውስጣዊ ምንነታቸውን መረዳት የሚያስችል ስለሆነ ጥልቅ መሣሪያ ነው። እንደ ሰው ማመን፤ መታመንና መተማመን የምንችለው በምክንያት ነው። የሆነውን ነገር ለማመን ወይም ላለማመን፤ ለመቀበል ወይም ላለመቀበል፤ ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ምክንያትን በማረጋገጫ መሣሪያነት መጠቀም የግድ ይላል። ባጭሩ ለምንሆነውና ለምንሰራው፤ ለምንገምተውና ለምናስበው፤ ለምንፈጽመውና ለምንተገብረው ነገር ሁሉ ምክንያትን እንጠቀማለን፡:
በሕይወት ዘመናችን ብዙ ማወቅ የሚኖሩብን ነገሮች አሉ። በዓለም ላይ የምናገኛቸው ስፍር-ቁጥር የሌላቸው ቁስአካላዊና መንፈሳዊ ነገሮች ናቸው። አቅም ስለማይፈቅድ ሁሉንም ማወቅ አንችልም። ብዙ ጊዜ ለማወቅ የምንገደደው ከሰው ሕይወት ጋር ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆነ ቁርኝት ያላቸውን ነው። በቅድሚያ በቀጥታም ወይም በተዘዋዋሪ የሚጠቅሙን ወይም የሚጎዱን፤ የሚያስደስቱን ወይም የሚያሳዝኑን ማወቅ እንፈልጋለን። ለማወቅ የምንገደደው ከኛ ውጭ ስለሆኑ ነገሮች ብቻ አይደለም፤ በራሳችን ውስጥ ስላሉትና ስለራሳችን ማንነትም ጭምር ነው። ከጥንት ጀምሮ ፈላስፎች ራስን ስለማወቅ አጥብቀው አስተምረዋል፤ ያስተምራሉ። ለዚህ ዋና ምክንያት ራሱ ምክንያት ነው። በእያንዳንዳችን ውስጥ ያለ አቅም ነው – ምክንያት። ዕድገታችንና ውድቀታችንን የሚዘውረው እርሱ ነው።
የሰውን ልጅ ከሌሎች ፍጡራን ልዩ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱና ዋነኛው አእምሮ ወይም ምክኑያ ነው። አእምሮ ወይም ምክኑያ ለሰው ልጅ የማሰብ፤ የማወቅ፤ የመመርመርና የመመራመር፤ የመተርጎምና የመፍጠር፤ የማጥናትና የመገምገም፤ የመገመትና የማስላት፤ የመግለፅና የማሳወቅ፤ የመተንተንና የማብራራት አቅም ሰጥቶታል። ምክንያት የሚፈጠረው በበለፀገው የአእምሮ ክፍል ውስጥ ነው። ሥራው ላቅ ያለና ጥልቅ የሆነ ነው። ሁሌ ማስረጃንና ማረጋገጫን መሠረት ያደርጋል። ከእውነት ለመድረስ ሥነ-አመክኖያዊ ዘዴን ይጠቀማል። በዚህ የሚበጀንን ከማይበጀን፤ የሚጠቅመንን ከሚጎዳን፤ እውነትን ከውሸት፤ ልማትን ከጥፋት ባጭሩ መልካምን ከመጥፎ መለየት የምንችለው በምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው። በእርግጥ ምክንያት በመሠረታዊ ባሕርይው ሀሳብ ነው። ማንኛውም ሐሳብ ግን ምክንያት ሊሆን አይችልም – ሁሉም ዓይነት ሐሳብ ማረጋገጫ ወይም ማሳመኛ የሚፈልግ ባለመሆኑ።
የሰው ልጅ ያለ እርስ በእርስ መኖር ስለማይችል ማሕበራዊ እንስሳ ነው። አብሮ የሚኖረው በሐሳብ መግባባትና መረዳዳት ስለሚችል ነው። እኔ የማስበውንና የምሰራውን ሌላው ሰው በሐሳብ፤ በቋንቋና በተግባር ተረድቶ ይቀበላል። ሌሎች የሚያስቡትንና የሚሰሩትን እኔም ተረድቼ እቀበላለሁ። አንዱ ሌላውን መረዳትና መቀበል የሚችለው ምክንያታዊ አስተሳሰብ በመካከላቸው በሚፈጥረው እምነት ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ከሌላው ጋር የሚግባባው በቋንቋ በሚገለጽ አስተሳሰብ ነው። በምክንያት የሚታገዝ ሐሳብ አጠራጣሪና አሻሚ የመሆን አጋጣሚው ዝቅተኛ ስለሆነ ቅቡልነት አለው።
ሰዎች ልዩነቶች አሏቸው – የሚያቀራርቡ ወይም የሚያራርቁ፤ የሚያፋቅሩ ወይም የሚያጣሉ ልዩነቶች። በሳል ምክንያት ካለ ልዩነቶች ችግር የመሆን ዕድላቸው ዝቅተኛ ነው። ይልቁንም ሀብቶች፤ ውበቶችና ጉልበቶች የመሆን አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው። ለምሳሌ ባልና ሚስት በፆታ ይለያያሉ። ይህ ተፈጥሮአዊ ልዩነት ነው። ልዩነቱ በባሕርይው የሚያፈላልግና የሚያስተሳስር እንጂ የሚያቃርን አይደለም። እንበልና እኔና አንተ የማናስወግዳቸው ልዩነቶች አሉን። እኔ አንተን መሆን አልችልም፤ አንተም እኔን መሆን አትችልም። ነገር ግን ደግሞ እኔና አንተ ያለ እርስ በእርስ መኖር አንችልም። ይህ ማለት ልዩነት ብቻ ሳይሆን አንድነትም አለን። የማንጋራቸው ነገሮች ያሉንን ያህል የምንጋራቸው ነገሮችም አሉ። በልዩነት ምክንያት መራራቅ ቢኖርም በምንጋራቸው ነገሮች እንቀራረባለን። ምናልባት የሚያቃርኑ ነገሮች አንድ ከሚያደርጉን አይለው ከተገኙ ደግሞ የሚያቻችል ምክንያታዊ አስተሳሰብ አለ። ምክንያት የእነዚህን ልዩነቶች እውነትነት በግልጽ ያሳያል።
በዓለም ላይ ብዙ የሚመሳሰሉና ለይቶ ለማወቅ የሚያስቸግሩ ነገሮች አሉ – ጠቃሚ መስለው የሚጎዱ፤ የሚጎዱ መስለው የሚጠቅሙ ነገሮች። ሰዎች አንዳንዴ ውሸትን እውነት ወይም እውነትን ውሸት አስመስለው ሲያቀርቡ እናስተውላለን። ይህ ማለት ሰዎች እውነትን በውሸት ወይም ውሸትን በእውነት በመሸፈን የሚፈልጉትን ነገር ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነት ውዥንብር የሚፈጠረው አንድም ካለማወቅ አሊያም ድብቅ ፍላጎትን እውን ለማድረግ ሲፈለግ ነው። ውዥንብርን፤ ማደናገርን፤ ማስመሰልንና ማሳሳትን በመቋቋም እውነትን መረዳት የምንችለው በምክንያት ነው።
ዕውቀት ሃሳብ ነው። ማንኛውም ሃሳብ ግን ዕውቀት አይደለም። የዕውቀት ደም ሥር ምክንያት ነው። በሰው ዕውቀት ውስጥ ስለሚታሰበውና ስለሚባለው ነገር በቂ መረጃና ማስረጃ፤ ማረጋገጫና መተማመኛ አለ። ሰው ስለሆነውና ስለሚሆነው፤ ስለተናገረውና ስለሚናገረው በቂ ምክንያት ከሌለው ሐሳቡ ቅቡልነት ያጣል። በቂ ምክንያት በሌለበት ማንም ስለሚያስበውም ሆነ ስለሚሰራው መተማመን አይችልም። ሐሳብ አሳማኝ ሆኖ ቅቡልነት ማግኘት የሚችለው በምክንያት በመረጃና ማስረጃ የተደገፈ ሲሆን ነው። በዚህ ከሌሎች ሐሳቦችና እምነቶች የሚለየው። መደመጥ ወይም መሰማት፤ ተቀባይነት ማግኘት ወይም ማጣት የሚፈጠረው በሚቀርበው ምክንያት ጥንካሬና ጥልቀት ነው።
ስለውጫዊ ዓለምም ሆነ በውስጣችን ስላሉት ነገሮች መረጃ የምናገኘው በተለያዩ መንገዶች ነው። ያየናቸውንና የሰማናቸውን፤ በስሜት ሕዋሳቶቻችን ያገኘናቸውንና የተረዳናቸውን መረጃዎች አደራጅተንና አቀናብረን ወደ ጽንሰ-ሐሳብነት የምናሳድገው በምክንያት ነው። ባጭሩ ምክንያት የተቀነባበረና የተደራጀ የአስተሳሰብ ሥርዓት መፍጠር የሚያስችል አእምሮአዊ አቅም ነው። የፈጠራ ሥራዎች የሚሰሩት፤ ጥናትና ምርምሮች የሚካሄዱት፤ አዳዲስ ግኝቶች፤ ምርቶችና ዕውቀቶች የሚመነጩት በምክንያት ኃይል ነው። ቀላል ምሳሌ እንውሰድ። መኪና የሰው ስሪት እንጂ የተፈጥሮ ሕግ ውጤት አይደለም። የተሰራው በመቶዎች በሚቆጠሩ ብረታብረቶች፣ ሽቦዎች፣ ፕላስቲኮች፤ ጎማዎች፤ ክሮች፤ ቱቦዎች፣ መስታወቶች ወዘተ ነው። ነዳጅ፤ ውሃ፤ ዘይት፤ አየር፤ ኤሌክትሪክ በውስጡ በመተላለፍና በመመላለስ ለመኪናው ሕይወትና ጉልበት ይሰጣሉ።
እነዚህ ነገሮች ተሰካክተውና ተቆላልፈው፤ ተሳስረውና ተቀናብረው የተቀመጡት በምክንያት ነው። ያለ ምክንያት የሚቀመጥ ነገር ፈጽሞ አይኖርም። ያለ ምክንያት የተቀመጠና የጎደለ ነገር ካለ ለመኪናው ደህንነት አደጋ ሊሆን ይችላል – ልክ እንደ ሰውነታችን። በአካላችን ውስጥ አየር፤ ደም፤ ውሃ፤ ምግብና የመሳሰሉትን የሚመላልሱ ቧምቧዎች፤ ምግብ የሚፈጩ፤ ደም የሚያጠሩና ቆሻሻ የሚያስወግዱ ነገሮች አሉ። የሰው ምክንያት መኪናን በሰው ሰውነት አምሳያ እንዲሰራ አስችሎታል። ስለዚህ የሰው ልጅ የሚያመርታቸው ነገሮች ሁሉ በምክንያት መሪነት የተቀነባበሩ ናቸው።
ንድፈ-ሀሳቦችንና ርዕዮተዓለሞችን፤ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን መፍጠር፤ ማመንጨትና ማደራጀት የምንችለው በምክንያት በመታገዝ ነው። ዛሬ የምናውቃቸው ሳይንሶች፤ ማቲማቲክስ፤ ሎጅክ፤ ፍልስፍናና ጥበብ የምንላቸው የዕውቀት ዘርፎች ሁሉ በምክንያት የታነፁ ናቸው። የተፈጥሮ ሳይንሶችን ብንወስድ የተፈጥሮ ሕግጋትን አሰራር፤ የመንስኤና የውጤትን ግንኙነት የሚገልጹ ወይም የሚያብራሩ ናቸው። በዓለም ላይ የምናያቸውና የሰው ልጅ ያፈራቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ሁሉ የሰው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ውጤቶች ናቸው። ለዚህ ነው ቀደም ሲል ምክንያት የሰው ልጅ ዕድገትና ምጥቀት የደም ሥር ነው ያልነው። ሁሉም እርሱን መሠረት አድርገው የተደራጁ ናቸው።
ለመሆኑ የሰው ልጅ ምክንያታዊ አቅሙን በሚገባ ተጠቅሟል? ዛሬ በዓለም ላይ የምናያቸው ውስብስብ ችግሮች ሰው ያለውን ምክንያታዊ አቅሙን ላለመጠቀሙ ተጨባጭ ማስረጃ ናቸው። ይህን አቅሙን አውጥቶ ቢጠቀም ኖሮ ዛሬ የዚች ዓለም ገጽታ በእጅጉ ከዚህ የተሻለ ይሆን ነበር። ከምክንያት የዕድገት ደረጃዎች አንጻር ሰውን ለሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል። አንዱ በምክንያት የሚታገዝ ነው። ሁለተኛው እምቅ ምክንያታዊ አቅም ያለው ነገር ግን ይህን አቅም ባለማጎልበቱ ባብዛኛው ስሜታዊ አስተሳሰብን የሚጠቀም ነው።
የበሰለ ወይም የበለፀገ ምክንያት የሚያለማ፤ የሚያሳድግ፤ ምቾትና ሰላም የሚፈጥር፤ ፍቅርና ትብብር የሚያሰፍን ይሆናል። ባንጻሩ ኢ-ምክንያት ወይም ባብዛኛው በስሜት ላይ የተመሠረተ እምነት ወይም አስተሳሰብ ስለሆነ የሚያጠፋ፤ ለጦርነትና አመፅ የሚያነሳሳ ነው። ለዚህ ነው የዛሬው ዓለም ባንድ በኩል ፍቅርና ሰላም፤ በሌላ በኩል ጥላቻና አመፅን የምታስተናግደው። ባንድ በኩል መተባበርና መደጋገፍ አለ፤ በሌላ በኩል መጣጣል አለ። ከዚህ ምክንያት በኢ-ምክንያት ላይ የበላይነት መቀዳጀት አለመቻሉን እንረዳለን። በሁለቱ መካከል ጦርነት አለ።
ምክንያት በትኖና ተንትኖ፤ ነጥሎና ለይቶ መግለጽ የሚችል ነው። እውነትን ከውሸት፤ ተገቢ የሆነውን ተገቢ ካልሆነው፤ መለየት የሚያስችል ቢሆንም ራሱ በተፈለገው መጠንና ዓይነት ባለማደጉ በኢ-ምክንያት ላይ የበላይነት መቀዳጀት አልቻለም። ስለዚህ መስራት የነበረበትን ያህል አልሰራም። ሰውን ማሳደግ በነበረበት መጠንና ዓይነት አላሳደገም። የሰው ምክንያታዊ አቅም የሚያድገው አእምሮው መበልፀግ ሲችል ነው። አእምሮ የሚበለጽገው በብዙ መንገዶች ነው – በመጠየቅ፤ በመማር፤ በመማማር፤ በመመራመር፤ በማጥናትና በመለማመድ ነው። ከሁሉም በላይ የትምህርት ተቋማት ዋና ዓላማ የሰውን አእምሮ በምክንያት ማበልፀግ ነው።
ኢትዮጵና ምክንያታዊ አስተሳሰብ
የኢትዮጵያን ሕዝብ አስተሳሰብ ምክንያታዊና ምክንያታዊ ያልሆኑ በማለት ለሁለት ብንከፍል፤ በግምት ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆነው ምክንያታዊ ያልሆነ ነው። ይህ ማለት የሀገራችን የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካ፤ የባሕልና ማሕበራዊ ሕይወት የሚያንቀሳቅሰው ምክንያታዊ ባልሆነ አስተሳሰብ ነው። አስተሳሰብ የሁሉም የሕይወት ገጽታዎች እስትንፋስ ነው። በመልካምነት ወይም በመጥፎነት በሰዎች መብትና ፍላጎት፤ ጥቅምና ክብር፤ ነፃነትና ማንነት ውስጥ የሚገለጽ ነው። የአስተሳሰብ ድህነት የድህነቶች ሁሉ እናት ነው። የኢኮኖሚ፤ የፖለቲካ፤ የማሕበራዊና ባሕላዊ ችግሮቻችን መሠረታዊ ምንጭና ግንድ ይኸው ነው።
እጅግ ግዙፍ የሆነ የአስተሳሰብ ችግር አለብን። አላዋቂነት ወይም ማይምነት፤ በስሜት መገፋትና በደመ-ነፍስ መንቀሳቀስ ብዙ ኪሳራ አድርሶብናል። እዚህ ግባ የማይባል ነገር ሁሉ ሲያገዳድለን ኖሯል። ዛሬም ቢሆን ከዚያ ታሪክ አልወጣንም። የፖለቲካ ሥርዓቶች በተለያዩ ጊዜያት በርካታ ርዕዮተዓለማዊ አስተሳሰቦችን አደጉ ከሚባሉ ሀገሮች አስገብተዋል። ችግሮችን የመፍታትና ጥያቄዎችን መመለስ የሚያስችል አቅም ግን አልፈጠሩልንም። እንዲያውም ያልታሰቡ ችግሮች ፈጠሩብን። ለዚህም ምክንያቶች ይኖራሉ። አንድም አጠቃቀማቸውን አለማወቅ፤ አሊያም የሀገራችን እሴትና ትውፊት ጋር አለመጣጣም ይሆናል። ሁሉንም ሞክረናል። ከችጋር የሚያስጥለን አልተገኘም። ያለን ብቸኛ ምርጫ በሌሎች የሰላ አስተሳሰብ ላይ ከመነታረክ የራሳችንን ኢምክንያታዊ አስተሳሰብን ማበለፀጉ ላይ ብናተኩር ይመረጣል።
ምክንያታዊ አስተሳሰብ አላቸው የሚባሉት የተማሩ ዜጎች ናቸው። እነዚህ በቁጥር ጥቂት ናቸው። ከእነርሱ ራሱ በሰል ያለ ምክንያታዊ አስተሳሰብ ያላቸው ሁሉም አይደሉም። በዚህ ስሌት በሀገራችን የተንሰራፋው የአስተሳሰብ ኋላቀርነት እጅግ ግዙፍ ነው። ይህ እንዴት ሊወገድ ይችላል የሚለውን ጥያቄ መመለስም ያስቸግራል። መጀመሪያ አለማወቃችንን እንወቅ። በመማር ራሳችንን ካለማወቅ ነፃ ለማውጣት እንትጋ። ሳናውቅ “እናውቃለን” ብለን ዋጋ በሚያስከፍል ነገር ውስጥ አንግባ። በእርግጥ አስተሳሰብ ይለማል። ከአፈራችን የበቀለ፤ ከሕዝባችን ባሕል፤ እሴትና ትውፊት የመነጨ አስተሳሰብ በዘመናዊ ምክንያቶች ኮትኩቶ ማነጽ ምርጫችን መሆን ይገባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ጠና ደዎ(ፒ.ኤች.ዲ