እለቱ ዓርብ፣ ወሩ ግንቦት፣ ቀኑ 21፣ሁኔታው አስፈሪም አስደንጋጭም ነበር፤ምክንያቱ ደግሞ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር በኢትዮጵያ 137 የተመዘገበበት እለት ነውና።የኩላሊት ሕሙማን ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ገዳይ በሽታ ተደቅኖባቸዋል።የኮሮና ወረርሽኝ የኩላሊት እጥበት(ዲያሊሲስ) ታካሚዎች ላይ ክንዱ ፈርጣማ ነው።
ይሁን እንጂ የኩላሊት ሕሙማን አንድም አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግና ሕክምናቸውን በተገቢው በመከታተል ራሳቸውን መጠበቅና ከወረርሽኙ መከላከል እንደሚገባቸው ለመጠቆም ሁለትም ለኮሮና ወረርሽኙ ከሚደረጉት ዘርፈብዙ ርብርቦች ባልተናነሰ የእምነት አባቶች፣ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድና መንግሥታቸው፣ምሁራን፣ታዋቂ ሰዎች፣ፖለቲከኞች፣የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች እና መላው ሕብረተሰቡ ትኩረት ሰጥቶ ሊደግፋቸው እንደሚገባ ‹‹ሞት በኩላሊት ይብቃ በጎ አድራጎት ማህበር›› በእለቱ ጥሪ አቅርቧል።
የበጎ አድራጎት ማህበሩ በዓለም ላይም ሆነ በኢትዮጵያ በገዳይነቱ ቀዳሚ እየሆነ የመጣውን የኩላሊት በሽታ ሕክምና መንግሥት ብቻ የሚወጣው አይደለም።በመሆኑም በመንግሥት ሆስፒታሎች የኩላሊት እጥበት ሕክምናው ቢቻል በነጻ ካልተቻለ ደግሞ በዝቅተኛ ዋጋ መሰጠት እንዲቻል እና ምንም የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ታካሚዎች ደግሞ የሕክምና ድጋፍ በማድረግ ለልጆቻቸውና ለወገኖቻቸው ተስፋዎች እንዲሆኑ ለማድረግ አልሞ የተቋቋመ ስለመሆኑ የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ እዮብ ተወልደ መድሕን ይገልጻሉ፡፡
አቶ እዮብ የማህበሩ መስራችና የኩላሊት ታማሚ ሲሆኑ ካለፉት ስድስት ዓመታት ጀምሮ የዲያሊሲስ ሕክምና መከታተላቸው በችግሩ ስፋትና በሕብረተሰቡ የኢኮኖሚ አቅም ዙሪያ ሰፊ እገዛና ድጋፍ ኖሮ ሁሉም ትኩረት ሲሰጠው እንጂ በተናጠል አቅምና ጥረት ሊሻገሩት እንደማይቻል ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው ያስረዳሉ።በዚህ የተነሳም በአገሪቱ በርካታ ታማሚዎች መታከም እየቻሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል በማጣት ላይም ይገኛሉ። በመሆኑም መንግሥት የእነዚህ ሰዎች እጣ ፋንታ ሊያሳስበው እንጂ ሊረሳው የሚገባ ጉዳይ አይደለም ባይ ናቸው፡፡
የኩላሊት ታማሚዎች ሕክምናቸው በልመና ምጽዋት ላይ የተመሰረተ ሆኖ እስከ መቼ? ቀላል ቁጥር ያላቸው አይደሉም።በመሆኑም እንደማንኛውም ዜጋ በቂ ሕክምና በተመጣጣኝ ገንዘብ የሚያገኙባቸው እድሎች ዝግ ሆነውስ እስከመቼ ድረስ ችግሩ ይቀጥላል? ያሉት አቶ እዮብ አሁን በዓለምም ሆነ በአገራችን የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በበጎ አድራጎት ማህበራት የድጋፍ ፕሮጀክቶች በመቅረጽም ሆነ በግላቸው በመለመን የማይቀረውን የኩላሊት እጥበት ሕክምናቸውን ለሚያከናውኑ አካላት ሁኔታውን ይበልጥ ከባድ እንዲሆን አድርጎባቸዋል።በመሆኑም ‹‹ከኮቪድ 19 ተምረን ለሁሉም ገዳይ በሽታዎች ትኩረት ብንሰጥ›› ሲሉም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የሕክምና ወጪያቸውን በሕዝብ ድጋፍም ሆነ በራሳቸው በመሸፈን ሕይወታቸውን የሚያስቀጥሉ የኩላሊት ሕመምተኞች ጉዳይ ትኩረት ያሻዋል።ታካሚዎቹ የገጠማቸው የግብዓት እጥረት ከኮሮና ወረርሽኙ ጋር ተዳምሮ በሕይወት የመኖር ሕልውናቸው ላይ ስጋት ፈጥሯል በማለት ሞት በኩላሊት ይብቃ በጎ አድራጎት ማህበር ወገን ለወገኑ ይደርስ ዘንድ ድምጻቸውን በማስተጋባት ላይ ይገኛል፡፡
የኩላሊት ሕሙማን የመታከም መብት እንዳላቸው ተገንዝቦ በአቅማቸው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ከቅንነትና ለጉዳዩ ትኩረት ከመስጠት ጋር የሚያያዝ እንጂ ከአገሪቱ የእድገት አቅም ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡ለዚህ ደግሞ እንደኢትዮጵያ ለማደግ በመፍጨርጨር ላይ በሚገኙት (እንደ ኬኒያ ያሉ) ጎረቤት አገራት ለበሽታው የሰጡት ትኩረት ማሳያ እንደሆነ የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣በዚህ የተነሳ በርካታ ለአገርና ለቤተሰቦቻቸው የሚጠቅሙ ኢትዮጵያውያንን ኢትዮጵያ እንዳጣች ገልጸዋል፡፡
ከተመሰረተ ከአንድ እጅ ጣት ከፍ ያለ እድሜ ያላስቆጠረው ሞት በኩላሊት ይብቃ በጎ አድራጎት ማህበር እጃቸውን ከሚዘረጉ በጎ አድራጊዎች በሚያሰባስበው ገንዘብ በኩላሊት እጥበት ሕክምና ችግር የገጠማቸውን ይደግፋል።በመሆኑም ከአይናለም፣ከኮሪያ፣ከቅዱስ ጳውሎስ፣ከያኔት፣ከቶም፣ከጽጌረዳ፣ከቤቴል፣ከጽጌረዳ፣ከዘውዲቱ እና ከዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታሎች ጋር በመተባበር ለ135 ሰዎች ለኩላሊት እጥበት ሕክምና በድምሩ አንድ ሚሊዮን 520 ሺህ 542 ብር ወጪ ድጋፍ ማድረጉን አቶ እዮብ ተናግረዋል።አሁን ከመንግሥት እስከ ማህበረሰቡ ድረስ የሚስተዋለው የመደጋገፍና የመተጋገዝ በጎ ጅምር በገዳይ በሽታዎች ላይም ትኩረቱን አድርጎ መስራት ቢችል በምድሪቱ ለምኖ መታከምን ታሪክ ማድረግ ይችላል ብለዋል፡፡
የውስጥ ዴዌ ስፔሻሊስትና የኩላሊት ሕክምና ንኡስ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ውብሸት ጆቴ በዚህ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጊዜ የኩላሊት እጥበት(ዲያሌሲስ) ሕክምና በምን መንገድ ሊከናወን ይችላል? በታካሚዎች ላይስ የሚፈጥረው ተጽዕኖ ምን ይሆን? በሚሉት ጉዳዮች ዙሪያ ለተጠየቁት ሲመልሱ፤ የኩላሊት ዲያሌሲስ ሕክምና ለየት ያለና ከፍተኛ የሆነ ጥንቃቄን ይፈልጋል።እንደዚህ አይነት ተጓዳኝ ሕመም ባለባቸው ሰዎች ዘንድ የኮሮና ቫይረስ ተህዋሲ ኮቪድ 19 ጠንከር ይላል።በመሆኑም በተቻለ መጠን ሕክምናው በማያደርጉበት ቀን ከቤት መውጣት የለባቸውም።ወደ ሕክምናው ሲመጡና ሲመለሱም በተቻለ መጠን በግል ትራንስፖርት መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ከሌሎች ሰዎች በተለየ ሁኔታ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴዎች መቆጠብ፣ለቅሶ፣ሰርግና መሰል ማህበራዊ ክንውኖች መራቅ እንደሚገባቸው ይመክራሉ፡፡
በየሆስፒታሎች የኩላሊት ዲያሌሲስ ለሚያደርጉ ታካሚዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚደረግ የገለጹት ዶክተር ውብሸት፣ተራርቀው አገልግሎቱን እንዲያገኙ ምልክቶችን ከማስቀመጥ ጀምሮ የወረርሽኙን አጠቃላይ የታወቁ ምልክቶችና መደረግ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
ከኮሮና ቫይረስ ተህዋሲ ወረርሽኝ ዋናዋና የተለዩ ምልክቶች ጎሮሮን ማፈንና ምቾት መንሳት፣ሳል፣ራስ ምታት፣ትክትክና የመሳሰሉት በመሆናቸው እነዚህን በመለየት ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ከሌሎች ጋር ያላቸውን ንክኪዎች እንዲያቋርጡ፣እጃቸውን ወዲያው ወዲያው በሳሙና እንዲታጠቡ፣ሳኒታዘር እንዲጠቀሙና ሌሎች ጉዳዮችን በትኩረት ተገንዝበው እንዲተገብሩ ይደረጋል ነው ያሉት።ሕመምና አጠራጣሪ ሁኔታዎችን ከሐኪሞቻቸው ጋር በቅርበት በስልክ እንደሚመካከሩም ተናግረዋል፡፡
በኩላሊትና ሌሎች ተጓዳኝ በሽታዎች ባሉባቸው ሰዎች ላይ ኮሮና በእጅጉ የሚበረታና ሕይወትን የሚነጥቅ በመሆኑ እንደዋዛ ማየት እንደማይገባም ዶክተሩ መክረዋል፡፡
ከባድ የኩላሊት በሽታ ምን አይነት ነው?
ቀስ እያለ በረጅም ዓመታት ኩላሊትን በመጉዳት ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ከጊዜ በኋላ የበሽተኛው ኩላሊቶች ሙሉ በሙሉ ሥራ ያቆማሉ፡፡በሽታው ሰዎች ከሚያስቡት በላይ በማህበረሰቡ የተንሰራፋ ነው፡፡የኩላሊት ጤና ወርዶ ብቃቱ 25 በመቶ ሲደርስ አብዛኞቹ ታማሚዎች እንደሚያውቁ ባለሙያዎች ይናገራሉ።የኩላሊት መስራት ማቆም እየበረታ ሲሄድ በሰውነት ውስጥ አደገኛ መጠን ያለው ቆሻሻ እና ፈሳሽ ይከማቻል፡፡ለዚህ የሚከናወነው ሕክምናም መዳከሙን ለማቆም ወይም የሚዳከምበትን ፍጥነት ለማዘግየት የሚረዳ ነው።
ምን ምልክቶች ይታያሉ?
የኩላሊት በሽታ ከባድ ደረጃ ሲደርስ ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል፡- ደም ማነስ፣ደም የተቀላቀለበት ሽንት፣የጠቆረ ሽንት፣ንቁ አለመሆን፣የሽንት መጠን መቀነስ፣የእግር የእጅና የቁርጭምጭሚት ማበጥ፣የድካም ስሜት፣የደም ግፊት፣የእንቅልፍ እጦት፣የቆዳ ማሳከክ፣የምግብ ፍላጎት ማጣት፣ብልትን ማስነሳት መቸገር (በወንዶች ላይ)፣ሽንት ቶሎቶሎ መምጣት፣የትንፋሽ እጥረት፣ሽንት ላይ ፕሮቲን መገኘት፣በፍጥነት የሰውነት ክብደት መቀያየር እና ራስ ምታት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን ግንቦት 28/2012
ሙሐመድ ሁሴን