ክበባትን በአዲስ የማደራጀቱ ተግባር

ከመደበኛው መማር ማስተማር ሂደት በተጓዳኝ በትምህርት ቤቶች የሚቋቋሙ ክበባት በራሳቸው የመማማሪያ መድረክ ናቸው። ተማሪን ከተማሪ፤ ተማሪን ከመምህሩ፤ ተማሪን ከአስተዳደሩ ብሎም ተማሪን ከማኅበረሰቡ ጋር ድልድይ ሆነው ያቀራርባሉ። የእርስ በርስ መስተጋብሩንም ያጠናክራል። የእያንዳንዱን ተማሪ ስብዕና በመቅረጽም በኩል የማይተካ ሚናን ይጫወታል። በተለይ ለተማሪዎች የወደፊት ራዕይን በማመላከት በኩል ድርሻቸው ጉልህ ስለመሆኑ ያነጋገርናቸው ተማሪዎችና የትምህርት አመራሮች ይናገራሉ።

በዳግማዊ ምኒልክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ዜማ ወርቁ ደግሞ ለዚህ ምስክር ናት። ዜማ በልጅነታቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ሳሉ በትምህርት ቤታቸው ሚኒ ሚዲያ ክበብ ይሠሩ የነበሩ እና አሁን ጋዜጠኞች የሆኑ ብዙ ሰዎች እንዳሉ ታውቃለች። ለዚህ መሠረታቸው ደግሞ በክበባቱ ውስጥ ያላቸው እንቅስቃሴ እንደሆነም ሰምታለች። እርሷም እነርሱን አብነት አድርጋ የራሷን ራዕይ ሰንቃ እየተንቀሳቀሰች እንደሆነ ታነሳለች።

“እያንዳንዳችን የተፈጠርንበት ዓላማ የተለያየ ነው፤ በዚህም የየራሳችንን ራዕይ ሰንቀን እንንቀሳቀሳለን። ግባችን ላይ ለመድረስ ደግሞ በትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ክበባት ወሳኝ ሚናን ይጫወታሉ›› የምትለው ተማሪ ዜማ፤ ክበባት ተማሪዎች የራሳቸውን የወደፊት ራዕይ አንግበው እንዲሠሩ ያደርጓቸዋል። ዓላማ ያላቸው ዜጎች በመሆንም ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲመሩ ያስችሏቸዋል ትላለችም። እሷ በትምህርት ቤቷ ተቋቁ መው በሚገኙት የፓርላማ ክበብ፣ የሥነ ተዋልዶ እና የአካባቢ ጥበቃ ክበብ በተጨማሪም የሚኒ ሚዲያ ክበብ አባል በመሆን እየተሳተፈች ቆይታለች። ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ እንደጠቀማትም ትናገራለች።

በክበባቶቹ ውስጥ መሳተፏ ወደ ፊት ልትሠማራበት የምትፈልጋቸውን ሙያዎች በሚገባ እንድትረዳቸው አስችለዋታል። እናም ሌሎች ተማሪዎችም ከክበባቱ በርካታ ጠቀሜታዎች ያገኛሉና ቢሳተፉባቸው መልካም እንደሆነ ምክሯን ትለግሳለች። ያለንበት ዘመን በቴክኖሎጂ የረቀቀ እንደመሆኑ መጠንም ዘመኑን የዋጁ አዳዲስ ክበባት በትምህርት ቤቶች እየተቋቋሙ ስለሆነ በእነርሱም ላይ ቢሳተፉ ጥሩ ግንዛቤ እንደሚጨብጡም ትመክራለች። ዜማ ምንም እንኳን የስምንተኛ ክፍል ፈተናዋን አጠናቃ ከትምህርት ቤት ውጪ ብትሆንም በሚቋቋሙት አዳዲስ ክበባት አማካኝነት ያገኘቻቸው እውቀቶች ስላሉ በቤቷ ጭምር እንደምትጠቀምባቸው ነግራናለች።

‹‹በትምህርት ቤታችን የተለያዩ ክበባት አሉ። ከእነዚህ ክበባት መካከል እኔ በፓርላማ ክበብ ስሳተፍ ቆይቻለሁ›› ያለን ደግሞ ሌላኛው የዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማኅበራዊ ሳይንስ የ12ኛ ክፍል ተማሪው ፍሬው ሚሊዮን ነው። ተማሪ ፍሬው በዚህም ንቃተ ሕሊናውን ለማዳበር መቻሉን ይናገራል። ተሳትፎው ወደፊት ትምህርቱን አጠናቅቆ እና በሕዝብ ተመርጦ ፓርላማ የመግባት ዕድል ቢያገኝ ልምምዱ ጥሩ ተሞክሮ እንደሚሆነውም አጫውቶናል።

በቀጣይ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ሲሆንም በዚህ የፓርላማ ክበብ በመሳተፍ ልምዱን የበለጠ እንደሚያዳብር ገልጾ፤ ከፓርላማው በተጨማሪ ዋናውን የትምህርት ጊዜውን በማይሻማ መልኩ በቲያትር እና ድራማ እንዲሁም በእግር ኳስ ክበብ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል።

በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የሥርዓተ-ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ስር የቋንቋ እና ተጓዳኝ ትምህርቶች ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅት እና ትግበራ ዴስክ ኃላፊ አበበ ጋረደው (ዶ/ር) እንደሚሉት ደግሞ፤ እንደ ሀገር ባሉት ትምህርት ቤቶች ቀደም ሲል የተቋቋሙት ነባር ክበባት ለተማሪው ልዩ ልዩ አገልግሎቶችን ይሰጡ ነበር። በርካታ ተማሪዎች እንደየዝንባሌያቸው በስፖርት፤ በኪነ ጥበብ እና ሥነ-ጽሑፍ እንዲሁም እንደ ደም ልገሳ ያለ ተግባር በሚከናወንባቸው የቀይ መስቀል ማኅበር በጎ ፈቃድ አገልግሎትና በሌሎች መስኮች በተቋቋሙ ክበባት ሲሳተፉ ቆይተዋል። ክበባቱ በዚህ መልኩ ተዋቅረው አገልግሎት መስጠታቸው ደግሞ በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፁ እና ትምህርት ቤታቸውን እንደዚሁም አካባቢያቸውን ብሎም ሀገራቸውን ሊጠቅሙ የሚችሉ ተማሪዎች ከማፍራት አንጻር ሚናቸው ከፍተኛ ነው።

ዛሬ በተለያዩ የሙያ መስኮች ተሰማርተው ከም ናያቸው በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች አብዛኞቹ ከእነዚህ ክበባት ባገኙት እውቀት ዳብረው የወጡ ናቸው ቢባል ማጋነን እንደማይሆን የጠቀሱት ኃላፊው፤ በርካታ ጥቅማቸው ቢኖርም በአንዳንድ ምክንያቶች የክበባቱ እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዘ መጥቷል። ትምህርት ሚኒስቴርም ይህ ጉዳይ ቀጣይ እንዳይሆን በማሰብና ቀደም ሲል የነበረ አስተዋጿቸውን ከግምት በማስገባት በአዲስ መልክ አደራጅቶ ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን ይገልፃሉ።

አበበ (ዶ/ር)፤ ክበባትን በአዲስ አደራጅቶ ወደ ሥራ የማስገባት እንቅስቃሴ አጀማመር የትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ሀገር አቀፍ ጥናት ካካሄደበት ሂደት ጋር ተሰናስሎ የተካሄደ ስለመሆኑም ያነሳሉ።

እንደ እሳቸው አባባል፤ ትምህርት ሚኒስቴር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ሲያካሂድ የቆየውን ሀገር አቀፍ ጥናት ተከትሎ የጥናቱን ግኝቶች እና የመፍትሔ ሀሳቦች መነሻ በማድረግ የትምህርት ፍኖተ ካርታ አዘጋጅቶ ነበር። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በትምህርት ሥርዓቱ ላይ መሠረታዊ ለውጦችን ለማምጣት የተለያዩ የለውጥ መርሐ ግብሮች ቀርጿል። እነዚህ የለውጥ መርሐ ግብሮች በአሁኑ ወቅት እንደ ሀገር በትምህርት ሚኒስቴር ተግባራዊ እየተደረጉ ናቸውም ይላሉ።

ከእነዚህ መካከል አንዱ የአጠቃላይ ትምህርት ሥርዓተ ትምህርት ሪፎርም እንደሆነ ጠቅሰው፤ ሪፎርሙ ከቅድመ አንደኛ ደረጃ እስከ 12ኛ ክፍል ሥርዓተ ትምህርት ላይ የተደረገው ለውጥ መሆኑን እና ክበባትን በአዲስ አደራጅቶ ወደ ሥራ መግባቱም ከዚሁ ጋር ተሰናስሎ ወደ ሥራ የተገባበት እንደሆነም ያብራራሉ።

‹‹ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል›› የሚሉት ዴስክ ኃላፊው አበበ (ዶ/ር)፤ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በሚዘጋጅበት ወቅት ቀድሞ የነበረው የክበባት አደረጃጀት እና አተገባበር ሥርዓትም በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን መደበኛ ሥርዓተ ትምህርት በሚያጠናክር መልክ ተዘጋጅቶ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር መግባቱን ያስረዳሉ።

ክበባትን በአዲስ አደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ እያሽቆለቆለ መጥቶ በነበረው የተማሪዎች ውጤት እና የትምህርት ጥራት ላይ ውጤታማ ለውጥ እያመጣ መሆኑም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዘረጋው የክትትልና ድጋፍ ግምገማ ማረጋገጡን ያወሳሉ። አክለውም የሚኒ ስቴሩን ድጋፍና ክትትል አሠራር መሠረት በማድረግ ታች ትምህርት ቤት ተወርዶ እንደተገመገመም ይናገራሉ። ከዚህ አንጻርም ተማሪዎች ውጤት ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ይላሉ።

እስከ 50 ከመቶ ያመጡ የነበሩ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ከሚሰጠው ትምህርት በተጨማሪ በቤተ ሙከራ ጭምር በተግባር በተደገፉ እንደ ሳይንስ እና ሂሳብ፤ የቋንቋ ትምህርቶች፤ ሙዚቃ፤ ሥነጽሑፍ ቲያትርና ድራማ እንዲሁም ፓርላማ ክበባት በመሳተፋቸው እስከ 70 እና 80 ከመቶ በማምጣት ውጤታቸውን ማሻሻል መቻላቸውንም ያስረዳሉ።

በተለይ በፓርላማ ክበብ አባል በመሆን ልምምድ በማድረጋቸው ቀድሞ መልሱን ቢያውቁትም ለመመለስ ይፈሩ የነበሩ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ መልስ ከመመለስ ጀምሮ የነቃ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ማድረጉንም በግምገማው መረጋገጡን ይናገራሉ።

“የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው ተማሪዎች በዚህ መልኩ ውጤታቸው ሲሻሻል እንዲሁም በተጨባጭ በቂ እውቀት መጨበጣቸው ሲረጋገጥ ነው” የሚሉት ኃላፊው አበበ (ዶ/ር)፤ ክበባቱን በአዲስ አደራጅቶ ወደ ሥራ ማስገባቱ በትምህርት ጥራት ላይም ለውጥ ማምጣቱን ያስረዳሉ።

‹‹ክበባት ለተማሪዎች ግለ-ስብዕና እድገት፤ ማኅበራዊ ትስስር፤ የአመራር ክህሎት እድገት፤ የትምህርት እውቀት መዳበርና የትምህርት አቀባበል ችሎታቸውን ከመጨመር አኳያ ሚናቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥና ወደፊት መሆን የሚፈልጉትን ሙያ ለማሳካት ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው›› ሲሉም አብራርተዋል።

ክበባት በአዲስ ማደራጀት ያስፈለገበት ምክንያት ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ጋር የሚናበቡ ክበባት መቋቋማቸው አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑኑን በመጥቀስ፤ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሳብ የሚማሩት ትምህርት በቂ አለመሆኑ በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት ዙሪያ የተደረገው ጥናት በተጨባጭ አረጋ ግጧል። በመሆኑም ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ከሚማሩት ትምህርት በተጨማሪ ከክፍል ውጭ እንደ ዝንባሌያቸው እና ክህሎታቸው በተለያዩ ተግባራት ላይ የሚሳተፉበት ዕድል መፍጠር አስፈላጊ ነው። በዚህም በትምህርት ሚኒስቴር አቅጣጫ ሰጪነት በየትምህርት ቤቶች አዳዲስ ክበባት እንዲከፈቱ ተደርጓል ይላሉ።

እንደ ዴስክ ኃላፊው አበበ (ዶ/ር) ማብራሪያ፤ የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት እና አተገባበር ማንዋል በ2015 ዓ.ም ፀድቋል። በአሁኑ ወቅትም ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል። በዚህ የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት እና አተገባበር ማንዋል ውስጥ እንደተቀመጠውም በስምንት ጉድኝት ትምህርት ዘርፎች ሥር 21 የሚሆኑ ክበባት ተቋቁመዋል።

ሁሉም ትምህርት ቤቶች ሁሉንም የክበባት ዓይነቶች እንዲያቋቋሙ አይገደዱም። ይሄ ሁኔታ በማንዋሉም በአስገዳጅነት አልተቀመጠም የሚሉት ኃላፊው፤ ማንዋሉ ክበባትን ትምህርት ቤቶች ሲያቋቁሙ የተማሪዎቻቸውን ብዛትና ተጨባጭ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲያደርጉት ይፈቅድላቸዋል። የክበባት ብዛት እና ዓይነትም ከዚህ አንጻር እንዲወስኑት ዕድል ይሰጣቸዋል፡ ተማሪዎችም ቢያንስ ከተቋቋሙት ክበባት መካከል በአንዱ የክበብ ዓይነት እንዲሳተፉ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነም ይገልጻሉ።

በትምህርት ሚኒስቴር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የቋንቋና ተጓዳኝ ትምህርቶች ሥርዓተ-ትምህርት ዝግጅትና ትግበራ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ገርቢ በበኩላቸው፤ ትምህርት ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት እነዚህ ክበባት የሚጠናከሩበትን የአሠራር አግባብ ዘርግቶ ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ እየሠራ ስለመሆኑ ይናገራሉ። የክበባት ድጋፍ እና አደረጃጀት በክፍል ውስጥ እንደሚሰጠው ሥርዓተ ትምህርት ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት እንዲተገበር የሚያስችል አሠራርም ተፈጥሯል ሲሉ ያስረዳሉ።

አቶ ሀብታሙ እንደሚናገሩት፤ በሥራው ከተከናወኑት ተግባራት መካከል ወጥ የሆነ የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት ማንዋል ዝግጅት እንደ ማሳያ ይጠቀሳል። የተጓዳኝ ትምህርት ከፍተኛ ባለሙያ መድቦ እንዲመራ ማድረግም ሌላው ነው። ክበባት የሚጠቀሙባቸውን ማንዋሎች፤ ሥልጠናዎች መስጠትም በተጨማሪነት የሚነሳ ነው።

‹‹ተጨማሪ የቁሳቁስ ድጋፍ እና ሥራዎችን እያከናወን ክበባት ተጠናክረው ተማሪዎች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲያደርጉ ጥረት እያደረግን ነው›› የሚሉት ባለሙያው፤ የክልል እና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች የበኩላቸውን ጥረት እያደረጉ ስለመሆናቸውም ያብራራሉ።

የአጠቃላይ ትምህርት አዋጅ 1368/2017 መሠረት የክበባት አደረጃጀት ተፈፃሚነት እንዲኖረው ለማድረግ በትምህርት ሚኒስቴር ደረጃ የተጓዳኝ ትምህርት አደረ ጃጀት እና አተገባበር መመሪያ ተዘጋጅቷል። ይህ መሆኑም በአጠቃላይ የትምህርት ቤት ክበባት ውስጥ የሚሳተፉ ተማሪዎች የወደፊት ራዕይ ኖራቸው እንዲንቀሳቀሱ ያግዛቸዋል። ይህ ብርቱ አስተዋፅዖው ግን እንዲጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራበት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በሰላማዊት ውቤ

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You