በዚህ ዘመን ዓለምን ስጋት ላይ ከጣሉ የተፈጥሮ ክስተቶች ውስጥ አንዱ የተፈጥሮ መዛባት እንደሆነ በተደጋጋሚ የተገለጸ እውነታ ነው ። በተለይ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ በርካታ ችግሮችን አስከትሏል ። ጎርፍ፣ ከፍተኛ ሙቀት፣ አውሎ ንፋስና የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎች የሰውን ልጅ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፈታተኑ ይገኛሉ ።
እነዚህን አደጋዎች በዘላቂነት ለመከላከል ደግሞ ተፈጥሮን መንከባከብ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ። በተለይ ከሰለጠኑ አገራት ትልቅ ኢንዱስትሪዎች እና ቁጥራቸው በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ከሄዱት ተሽርካሪዎች የሚወጣው ጭስና የሚለቀቁ ኬሚካሎች የኦዞንን መጠን በማሳሳትና ተፈጥሮን በማዛባት ዓለም ለሰው ልጅ ምቹ እንዳትሆን ከፍተኛ አሉታዊ ጫና ፈጥረዋል ። በዚህ ደግሞ አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ አገሮች ተጎጂዎች ናቸው ። መፍትሔውም እየተመናመነ የመጣውን የደን ሀብት መልሶ እንዲያገግም ማድረግ ነው ።
ኢትዮጵያም ይህን ከግንዛቤ በማስገባት የአረንጓዴ ልማትን ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች ። በተለይ ባለፈው ዓመት በአንድ ዓመት ብቻ ከአራት ቢሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል ዓለምን ማስደመም የቻለች ሲሆን፤ ዘንድሮም አምስት ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ዝግጅቷን አጠናቃለች ። እነሆ በዛሬው ዕለትም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና በከፍተኛ የመንግሥት ባስልጣት መሪነት መርሐግብሩ ይጀመራል ።
የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ መርሐግብር ከሌላው ጊዜ የተለየ የሚያደርገው ተከላው የሚካሄደው በዓለም ላይ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ ዓለምን እያስጨነቀና በአገራችንም የስርጭት መጠኑ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ በመጣበት ወቅት የሚካሄድ መሆኑ ነው ። በዚህ የተነሳ ዘንድሮ ችግኝ ሲተከል በተለየ ሁኔታ የቫይረሱ ስርጭት እንዳይስፋፋና የበለጠ ጉዳት እንዳያስከትል ጥንቃቄ በማድረግ ጭምር መሆን አለበት ። በማንኛውም አጋጣሚ በዚህ ሥራ ላይ የሚሳተፉ ዜጎችም የችግኝ ተከላውም ሆነ የኮሮና ቫይረሱን የመከላከል እንቅስቃሴው ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን በመገንዘብ እነዚህን ሁለት ወሳኝ ጉዳዮች በጥንቃቄ ማከሄድ ይጠበቅበታል።
በአንድ በኩል ችግኝ የምንተክለው ነገን እያሰብን እንደሆነ መገንዘብ ተገቢ ነው ። ምክንያቱም የነገ ብልጽግናችንን እውን ለማድረግ ምቹ መደላድል መፍጠር የምንችለው ተፈጥሮን በመንከባከብ እንደሆነ ልንገነዘብ ይገባል ። በግብርና ላይ ለተመሰረተው የአገራችን ኢኮኖሚ የተፈጥሮ የአየር ንብረት ጤናማ መሆን ወሳኝ ነው ። አሁን ባለን ኋላቀርና ደካማ ኢኮኖሚያችን ላይ የአየር ንብረት መዛባትና የተፈጥሮ አደጋ ከተጨመረ የምናልመውን ብልጽግና ለማሳካት መቸገር ብቻ ሳይሆን ነገን ይበልጥ በፈተና የተሞላ ያደርገዋል ። በመሆኑም ነገን የተሻለ ለማድረግ ተፈጥሮን መንከባከብ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ።
ከዚህም ባሻገር ለሚተከሉት ችግኞች አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግም ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ነው ። ምክንያቱም ዛሬ የምተክላቸው ችግኞች ነገ ዛፍ እንዲሆኑና ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውሉ በአግባቡ መትከል ወሳኝ ነው። በመሆኑም ችግኞችን ስንተክል በተቻለ መጠን በአንድ በኩል ጉድጓዶቹ በአግባቡ መቆፈራቸውን ማረጋገጥ፤ በሌለም በኩል አፈሩን አቅፎ የያዘው ፕላስቲክ የችግኞቹን እድገት እዳይገታ በጥንቃቄ መቆረጣቸውን ወይም መውለቃቸውን ማረጋገጥ ይገባል ። ከዚህም ባሻገር ችግኞችን ከተከልን በኋላ እስከሚያድጉ ድረስ መንከባከብ እንዳለብን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም ። ለመትከል ያህል ብቻ የምንተክል ከሆነ ግን ትርፉ ኪሳራ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ።
ይህንን ስናደርግም የተከሰተውን ወረርሽኝ ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን አለበት ። በመሆኑም በህክምና ባለሙያዎችና በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሚነገሩንን የጥንቃቄ መንገዶች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ሊዘነጋ አይገባም ። በዚህ አጋጣሚ የቫይረሱ ስርጭት አሁን ካለበት ሁኔታ ይበልጥ እየሰፋ ከሄደ አደጋው የከፋ ስለሚሆን እነዚህን ሁለት ወሳኝ ሥራዎች በማጣጣም በጥንቃቄ ማከናወን እንደሚገባ መገንዘብ ከእያንዳዱ ዜጋ ይጠበቃል ። ኮረናን እየተከላከልን የአረንጓዴ ልማታችንን በማስቀጠል የድርብ ድል ባለቤት መሆኑ እንችላለን።