ታላቅ እህቷን በኮቪድ – 19 ተህዋሲ ያጣችው ዶርዚ ዳፊ በኀዘን በተሰበረ ቅስምና በሰለለ ድምጽ ፣ ” የእህቴ ሞት ከቁጥር በላይ ነው፡፡” ስትል የገለጸችበት አግባብ በመደበኛም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት መነጋገሪያ ሆኗል።የእህቷ አሳዛኝ ህልፈት ከእንግሊዝ የሕዝብ ብዛት በአንድ የመቀነስ ወይም በወረርሽኙ የተቀሰፉ ሰዎችን ቁጥር በአንድ የመጨመር ጉዳይ አይደለም ማለቷ ነው።በፍቅር የሚንሰፈሰፉላት ልጆቿ ፣ እህቶቿ ፣ የልጅ ልጆቿ፣ ዘመድ አዝማድ ፣ አብሮ አደጎቿ ፣ የስራ ባልደረቦቿ ፣ ጓደኞቿ አጥተዋታል ።ዳፊ ስለእህቷ ስታወራ ውላ ብታድር አትደክምም።ደግ ፣ እሩህሩህ ፣ የዋህ ፣ በደስታም በኀዘንም ቀድማ የምትደርስ ፣ አለኝታ ፣ ምርኩዝ ፣ መካር ዘካር ነበረች ትላለች።እሷን በማጣቴ የተፈጠረው ባዶነት በምንም ሊሞላ አይችልም ትላለች።ከእነ ዳፊ ቤተሰብ የጎደለው ቁጥር ብቻ አይደለም።ፍቅር ፣ ተስፋና ትዝታ ጭምር እንጂ፡፡
ተመልካች ፣ አድማጭና አንባቢ ኮቪድ – 19ኝን በቅጡ ሰውኛ አድርጎ ተገንዝቦ ከእንዝህላልነት ፣ ከመዘናጋትና ካልተገባ መረበሽና መደናገጥ ተናጥቦ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት አካል እንዲሆን ስለወረርሽኙ የሚወጡ ሾላ በድፍን የሆኑ አኃዞች ፤ በቤተሰብ ፣ በማህበረሰብ ፣ በሕዝብ ከፍ ሲል በሀገር ላይ የሚያስከትለው ሁለንተናዊ ዳፋ ከማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ከሥነ ልቦናዊና ከሰው ልጅና ከሀገር ህልውና አንጻር መተንተን ፣ መተርጎም ፣ መበየንና ሰው ሰው እንዲሸቱ ቀለል ባለ ቋንቋ ማፍታትን ይጠይቃል።ወረርሽኙ የሰው ልጅ በታሪኩ የገጠሙት እንደ ጥቁሩ ሞት ፣ ፈንጣጣ ፣ ስፓኒሽ ፍሉ ፤ የ1 ኛውና 2ኛው ጦርነት ፣ የ1935ቱና የ2008ቱ እኤአ የኢኮኖሚ ቀውስ ፤ የ2001ዱ የሽብር ጥቃት ፣ የአፍጋኒስታንና የኢራቅ የጸረ ሽብር ዘመቻ ፣ ወዘተረፈ አንድ ላይ ተደምረው እንኳ ጉዳታቸው ፣ የደቀኑት አደጋ ፣ ያስከተሉት ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች የኮቪድ – 19 ያህል የከፉ እንደማይሆኑ በበርካታ ልሒቃን ተተንትኗል፡፡
የጤና ሚኒስቴርም ሆነ የማህበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሚሰጧቸው መግለጫዎች ይህን ያህል ሰው ተመርምሮ ፣ ይህን ያህል ሰው ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።ከእነዚህ ውስጥ ይህን ያህሉ ወንዶች ሲሆኑ የቀሩቱ ደግሞ ሴቶች ናቸው።ይህን ያህሉ የውጭ የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ ፣ ያን ያህሉ ደግሞ ከእነሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው ፣ ይህን ያህሉ ደግሞ ምንም አይነት የውጭ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ናቸው።ከእዚህ ዓመት ህጻን እስከ እዚህ ዓመት አረጋዊ ይገኙባታል።ይህን ያህሉ በለይቶ ማቆያ ሆነው ከተደረገ ምርመራ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሲሆን ይህን ያህሉ ግን ነጻ ሆነው ተገኝተዋል።በአጠቃላይ ይህን ያህል ሰው በቫይረሱ የተያዘ ሲሆን ይህን ያህሉ አገግመዋል።ይህን ያህሉ ግን ሞተዋል።
ስለወረርሽኙ በፍጥነትና በስፋት መዛመት ፤ በተለይ የውጭ ጉዞ ታሪክ ካላቸው ይልቅ ምንም የጉዞ ታሪክ የሌላቸው በብዛት መያዛቸው ወረርሽኙ በሕዝቡ መካከል እየተሰራጨ መሆኑን ፤ ስለተጠቂዎች የጾታና የእድሜ ስብጥር ፣ ስለ አገገሙ ፣ ስለሞቱ ፣ ወዘተረፈ የተወሰነ መረጃ ሊሰጥ ይችላል።ለዛውም ታዳሚው መረጃውን ወስዶ ካብላላው።ይሁንና በሚፈለገው ደረጃ ለሰዎች እንዲቀርብ ሰውኛ ሆኖ መተርጎም ይገባዋል ።በፎቶ ፣ በተንቀሳቃሽ ምስልና በድምጽ ታግዞ በሰዎች አእምሮ ውስጥና እዝነ ህሊና እንዲቀረጽና እንዲቀር ሊደረግ ይገባል ።መረጃው በሰዎች ዘንድ ወረርሽኙን አስመልክቶ የአመለካከትና የባህሪ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ተጨማሪ ጉልበት ሊኖረው ይገባል።እስካሁን የተመጣበት የመረጃ አሰጣጥና አገላለጥ ክፍተቶች አሉበት። ስለሆነም የጤና ሚኒስቴር እለታዊ መግለጫ ፣ የሚሰጠው መረጃው ይዘት ፣ የመልዕክቱን አቀራረፅ ፣ ለሕዝብ የሚደርስበትን አግባብ መፈተሽ ፤ ስለ ኮቪድ – 19 የሚሰጡ መረጃዎች ይበልጥ የየአንዳንዱን ሰው የአእምሮ ጓዳና ቤት እንዲያንኳኩ መፍታታት ፣ መዘርዘር ፣ መተርጎምና መብራራት አለባቸው፡፡
ከዚህ በላይ የሚኒስቴሩ መግለጫ አሰጣጡ ቅርጹ /ፎርማት/፣ ይዘቱ /ኮንቴንት / ዝቅ ብዬ በዘረዘርሁት መረጃዎችን መተርጎምና መተንተን አለበት።በሕዝቡም ሆነ በብዙኃን መገናኛዎች ተገቢውን ትኩረትና ክብደት እንዲያገኝ መግለጫው ቀጥታ LIVE ሊሆን ይገባል።ጋዜጠኞች ማብራሪያ እንዲጠይቁ ቅርጹ ጋዜጣዊ ጉባኤ ሊሆን ይገባል።ከክብርት ሚኒስትሯ በተጨማሪ ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በመግለጫው እንዲሳተፉ መደረግ አለበት።ጋዜጣዊ መግለጫው በቂ ጊዜ ተሰጥቶት ተራና ቀላል የሚመስሉ ነገሮችን ሳይቀሩ በስፋት መብራራት አለባቸው።ለመነሻ ያህል ይሄን አቀርቤአለሁ፡፡
የሟቾች ስብጥር
በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ማንነት ከቁጥር ፣ ከእድሜና ከጾታ በላይ መገለጽና መተንተን አለበት።በሀገራችን ስለሞቱ ሰዎች ከቁጥራቸውና ከእድሜአቸው ባሻገር የሚታወቅ ነገር የለም።በወረርሽኙ ከመያዛቸው በፊት ሌላ በሽታ ይኑርባቸው አይኑርባቸው ፣ ስለስራ ባህሪያቸው፣ እንዴት በወረርሽኙ እንደተያዙ ፣ ጥለዋቸው ስለሄዱት ቤተሰቦቻቸው ፣ የትዳር አጋሮቻቸው ፣ ልጆቻቸው ፣ ወላጆቻቸው ፤ ከወረርሽኙ ራሳቸውን ለመከላከል ስላደረጉት ጥረት ፣ ምልክቱ እንደታየባቸው ወዲያው ወደ ህክምና ስለመሄድ አለመሄዳቸው ፣ ከቤተሰቡ አባላት ምን ያህሉ ቫይረሱ እንደተላለፈባቸው ፤ በቤተሰብ ፣ በዘመድ አዝማድ የፈጠረው ኀዘን ፣ የፈጠረው ክፍተትና ሌሎች ተዛማች መረጃዎች ቢገለጹ ወረርሽኙን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ብርታት ይሆናል።ከወረርሽኙ የአገገሙ ሰዎችን ማንነትም በተመሳሳይ መንገድ ሊብራራ ይችላል።
የስራ ባህሪና የእድሜ ስብጥር
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች የስራ ባህሪ ቢገለጽ ስራቸው እንዴት ለወረርሽኙ ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ከማሳየቱ ባሻገር በተመሳሳይ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ሰዎች ሳይዘናጉ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ያግዛል።ጤና ሚኒስቴርም ለወረርሽኙ ይበልጥ ተጋላጫ የሆነውን የስራ ባህሪ /ሪስክ ግሩፕ/ ለይቶ እርብርብ ለማድረግ ያግዘዋል።እንዲሁም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች እድሜ በደፈናው ከዚህ ዓመት እስከዚህ ከሚባል ፤ ይሄን ያህሉ ህጻናት ፣ ወጣት ፣ ጎልማሳ ፣ አረጋዊ ተብሎ ቢገለፅ ፤ ወረርሽኙን ከእድሜ ስብጥር አኳያ ያለውን ስርጭት መረዳት ስለሚያስችል ይበልጥ ተጋላጭ የሆነውን የእድሜ ክልል ለይቶ ትኩረት ለማድረግ ያግዛል።የተለያዩ የህብረተሰቡ ክፍሎችም ከእድሜ አንጻር ምድባቸውን አውቀው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሊያነቃቸው ይችላል፡፡
ቤተሰባዊ ማንነት
ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ወላጆቹ ካሉት ብቸኛ ልጅ ነው ወይስ እህት ወንድሞች አሉት ? ወላጆቹን የሚጦረው ፣ ታናናሾቹን የሚያስተምረው እሱ ነበር ? ተምሯል አልተማረም ? ራዕዩ ምን ነበር ? አግብቷል ? ወልዷል ? ልጆች አሉት ? ካሉት ለአካለ መጠን የደረሱ ናቸው ወይስ ህጻናት ? የትዳር አጋሩ ስራ አላት ወይስ የቤት እመቤት ? ባለቤቷ ቫይረሱ ሲገኝበት የተፈጠረው መደናገጥ ፣ ቫይረሱ ወደልጆቹና ወደሷ ወይም ወደ ሌላ የቤተሰብ አባል ተሰራጭቷል ? ከተሰራጨ የነበረው የጥንቃቄ ጉድለት ምን ነበረ ? ካልተሰራጨ ምን አይነት ጥንቃቄ ቢደረግ ነው ? የህክምና ባለሙያዎች ምክር ሳያጓድል ይተገብር ነበር ? እንዴት መከላከል ተቻለ ? ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ተገቢውን ጥንቃቄ ያደርግ ነበር ወይስ ዝንጉ ነበር ? ወዘተረፈ የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ የሚችል የተሟላ መረጃ መስጠት ሚዲያው የማብራራት ጋዜጠኝነትን / ኤክስፕላናቶሪ ጆርናሊዝም/ ተጠቅሞ ቫይረሱ የተገኘበት ሰው ለአድማጭ ተመልካቹና ለአንባቢው ከቤተሰብ እንደ አንዱ እስኪመስለው ድረስ ቅርብ ሆኖ እንዲሰማው በማድረግ ወረርሽኙን በግንባር ቀደምትነት እንዲከላከል ማድረግና ማስተማር ይቻላል፡፡
በምስልና በድምፅ ማጀብ
የጤና ሚኒስቴር በየቀኑ የሚሰጠን መረጃ ዛሬ ነገ ሳይባል ተገምግሞ የመልዕክት አቀራረጹ እንደገና መፈተሽ እንዳለበት ተመካክሮ መግባባት ላይ መድረስ ያሻል።እስከዚያ ድረስ ግን አኃዙን ይበልጥ ህይወት ከመስጠት ፣ ሰው ሰው እንዲሸት ለማድረግ ከመተርጎም ፣ ከማብራራትና ሰውኛ ከማድረግ ጎን ለጎን የዜጎችን የግል መብት /ዘ ራይት ኦፍ ፕራይቬሲ / ባከበረ መልኩ፤ ሚዲያዎች ቀብርን ጨምሮ የሟች ቤተሰብን ፣ የታመሙና ያገገሙ ሰዎችን ቃለ ምልልስ ፣ ምስል ፣ ፎቶና ድምጽ አካተው እንዲዘግቡ መፈቀድ አለበት።ይፋ ያልሆነው ግን እየተተገበረ ያለው የኮቪድ – 19 መረጃ አሰጣጥ እቀባ ደረጃ በደረጃ ለቀቅ ሊደረግ ይገባል።እነዚህ መረጃዎችን መስጠት የዜጎችን የግል መብት በከፊል የሚጋፉ እንኳ ቢሆኑ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከተገደቡ መብቶች እና ከሕዝብ ጥቅም / ፐብላክ ኢንተረስት / ስለማይበልጡ በየእለቱ መግለጫዎች ማካተትና ሆስፒታሎችን፣ ለይቶ ማቆያዎችንና ተዛማችነት ያላቸውን ቦታዎች የሚያሳዩ በጥንቃቄ የተለዩ ምስሎችንና ድምጾችን በመግለጫውና በሚሰሩ ዘገባዎች ማካተት ያስፈልጋል፡፡
ሀገራችን ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ፈጣሪ አብዝቶ ይጠብቅ!
አዲስ ዘመን ግንቦት 27/2012
በቁምላቸው አበበ ይማም ( ሞሼ ዳያን )
fenote1971@gmail.com