በሱዳን ተመቶ በወደቀው አውሮፕላን ሩሲያውያን ሳይሞቱ እንዳልቀረ ተጠቆመ

በካርቱም የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በዳርፉር በወደቀው ሩሲያ ሰራሽ አውሮፕላን ውስጥ የነበሩ ሩሲያውያንን እጣ ፈንታ እያጣራ መሆኑን ገልጿል።

“ኢልዩሺን አይኤል -76” የተሰኘው ሩሲያ ሰራሽ የጭነት አውሮፕላን በሱዳን ጦር ወደተያዘችው ኤል ፋሸር መድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጭኖ ሲጓዝ ነበር ተብሏል።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሃይል (አርኤስኤፍ) በግብጽ ጦር አብራሪዎች ሲበር ነበር ያለውን የሩሲያው አውሮፕላን መትቶ እንደጣለው ከትናንት በስቲያ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በጀነራል ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) የሚመራው ጦር ግብፅ በምትፈፅመው ጥቃት የንጹሃንን ህይወት እየቀጠፉ ነው ሲል ይከሳል።

ካይሮ ግን 18ኛ ወሩን በያዘው ጦርነት ለሱዳን ጦር ወታደራዊ ድጋፍ እያደረገች ነው በሚል የሚቀርብባትን ወቀሳ በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።

በዳርፉር ተመቶ ስለወደቀው ሩሲያ ሰራሽ አውሮፕላን ዛሬም እየወጡ የሚገኙ መረጃዎች ማብራሪያ የሚሹና አሻሚ ናቸው።

አውሮፕላኑ ሶስት ሱዳናውያን እና ሁለት ሩሲያውያንን አሳፍሮ እንደነበርና ከቻድ ድንበር አካባቢ ተነስቶ ወደ ኤል ፋሸር ሲጓዝ መመታቱን ሱዳን ትሪቡን ዘግቧል።

የፈጥኖ ደራሽ ሃይሉ በበኩሉ የአውሮፕላኑን ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) እና የጉዞ ሰነዶችን ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፤ ከግብጽ ጋር ስላለው ግንኙነት ግን ማስረጃ አላቀረበም።

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You