የበረሃው ፈውስ

ዜና ሐተታ

ወታደራዊ ማሠልጠኛው ከተመሠረተበት 1972 ዓ.ም ጀምሮ ለብዙሃኑ ፈውስ በመሆን ዘመናትን ተሻግሯል፡፡ የሠራዊትና የሠራዊት ቤተሰብ እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ የጤና አገልግሎት በመስጠት የቀኝ እጅ ሆኖ አገልግሏል፡፡ የጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታል፡፡

ሆስፒታሉ ትምህርት ቤቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁንም በሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታል የሚገኙ አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡ በረሃ ላይ የተለያዩ ወረርሽኞች በየጊዜው ይከሰታሉ፡፡ ታዲያ ይህ የጤና ችግር ተቋቁሞ ለማለፍ፣ ብቁና ጤናማ የሀገርን ዳር ድንበር የሚያስጠብቅ ወታደሮች ለማፍራት የጤና ተቋሙ ሚና ከፍተኛ ነው። በተለይም ማሠልጠኛው የተመሠረተበት አካባቢ ከመሠረተ ልማት የራቀና ሌሎች ጤና ተቋማት በአካባቢው ባለመኖራቸው ሚናው ይበልጥ ከፍተኛ እንዲሆን አድርጎታል ሲሉ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

በጦላይ ከፍተኛ ባለሌላ ማዕረግተኛ ወታደራዊ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ሻምበል ዶክተር መኮንን ጉቼ ለኢፕድ እንዳሉት፤ ሆስፒታሉ ማሠልጠኛው ተመሥርቶ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ አንስቶ እስከአሁን የሚገባውን አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡

ሆስፒታሉ በተለያዩ ጊዜያት ለሚገቡ ምልምል ሠልጣኞች፣ የሠራዊቱና የሠራዊቱ ቤተሰቦች እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል የሚሉት ዶክተር መኮንን፤ በተለይ በአካባቢው ምንም አይነት የጤና ተቋም ባልነበረበት ጊዜ ህብረተሰቡን የጤና አገልግሎት ሲሰጥ እንደቆየ ያስታውሳሉ፡፡

እንደ ዶክተር መኮንን ገለጻ፤ በሆስፒታሉ የተመላላሽ ህክምና፣ ተኝቶ ህክምና፣ የማዋለድ አገልግሎት፣ የጽንስና እርግዝና ክትትልና፣ የቅድመ በሽታ መከላከል እንዲሁም ሌሎች ህክምናዎች በሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታሎች መሰጠት ያለባቸው አገልግሎቶች አሟልቶ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ሆስፒታሉ ማከም ብቻ ሳይሆን ቅድመ መከላከል ላይ ይበልጥ ትኩረት ይደረጋል። በማሠልጠኛው ያሉ ሁለት ክሊኒኮች ላይ አብዛኛው ሥራ የሚሠራው ቅድመ መከላከል መሆኑንም ነው ዶክተር መኮንን የሚጠቁሙት፡፡

ሆስፒታሉ አሁን ላይ በቀን ከ50 እስከ 60 ተመላላሽ ታካሚዎች እና እስከ 40 ተኝቶ ማክም የሚያስችል አቅም አለው፡፡ ሆስፒታሉ አሁንም ለአካባቢው ማህበረሰብ የኤች አይ ቪ ምርመራ እየሰጠ ነው፡፡ በተጨማሪም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙ አሁንም ተጨማሪ አገልግሎት ይሰጣል። ሆስፒታሉ በሀገሪቱ ጤናማ ሠራዊት ለመገንባት እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ጎን ለጎንም ስለ ጤና ሁኔታ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው እያደረገ እንደሆነ ያስረዳሉ።

አንዳንድ የህክምና መሻሪዎች፣ መሠረተ ልማትና የሙያተኛ እጥረት ቢኖርም ባለው ሀብት የሚጠበቀውን ያህል አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ያሉት ደግሞ የሆስፒታሉ ሜዲካል ዶክተር ሌተናል ኮረኔል ነጋ ጣሰው ናቸው፡፡ አሁን ላይ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሠልጣኝ ምልምል ወታደሮችን እንዲሁም የሠራዊት ቤተሰቦች በአካባቢው የሚገኙ የሲቪል ሠራተኞች በተለይ የኤች አይ ቪ ህሙማን በሆስፒታሉ አገልግሎት እያገኙ ነውም ይላሉ፡፡

ሆስፒታሉ ሙያተኛው ከተሟላና ያሉበት የመሠረተ ልማት እንዲሁም የመሣሪያ እጥረቶች መቅረፍ ከቻሉ ከሠራዊቱና የሠራዊቱ ቤተሰብ በተጨማሪ ለአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳለው ያስረዳሉ፡፡

ልጅዓለም ፍቅሬ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You