የጋዛን ኢኮኖሚ ወደ ነበረበት ለመመለስ እና ለመልሶ ግንባታ 350 ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል ተመድ አስታወቀ::
የተመድ የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ጦርነቱ ነገ ካበቃ እና ጋዛን ወደ ቅድመ ጦርነት ደረጃዋ ለመመለስ 350 ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ እጅግ ገዳይ እና አውዳሚ ወታደራዊ ዘመቻዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለትን የጋዛ ጦርነት ለመልሶ ግንባታ አስርት ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል ሲያስጠነቅቁ እንደሰነበቱ ይታወሳል፡፡
አሁን ጦርነቱ ከተጀመረ ከአንድ ዓመት በኋላ እየወጡ የሚገኙ አዳዲስ ሪፖርቶች ደግሞ የጋዛን ኢኮኖሚ መልሶ ለመገንባት መቶ ዓመታትን ሊወስድ እንደሚችል እያመላከቱ ነው፡፡
የመልሶ ግንባታው እና ኢኮኖሚውን ድጋሚ ለማነቃቃት የሚወስደውን ጊዜ ለማሳጠር እስራኤል የጣለችው የእንቅስቃሴ እገዳ ሊነሳ ይገባል ተብሏል፡፡
ከጦርነቱ በፊት ሀማስ በ2007 ስልጣን ከያዘ ጀምሮ ጋዛ በእስራኤል እና በግብፅ ኢኮኖሚያዊ እገዳ ስር ነበር፡፡
በሃማስ እና በምዕራቡ ዓለም የሚደገፈው የፍልስጤም አስተዳደር በዌስት ባንክ መካከል የተደረጉ አራት ጦርነቶች እና መከፋፈል እንዲሁ በጋዛ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫናን አሳድረዋል፡፡
አሁን ያለው ጦርነት በግዛቱ ላይ አስከፊ ውድመት አስከትሏል፣ መንደሮች በሙሉ ወድመዋል፣ መንገዶች እና ወሳኝ መሰረተ ልማቶች ፈርሰዋል።
መልሶ ግንባታው ከመጀመሩ በፊት በአስክሬን እና ባልፈነዱ ቦምቦች የተሞሉ ፍርስራሾች እና ተራሮች መጽዳት አለባቸው።
የተመድ የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከ2007-2022 በጋዛ የነበረው ዓመታዊ ጥቅል ምርት እድገት 0.4 በመቶ ሲሆን እስራኤል አሁን ተግባራዊ እያደረገች በምትገኝው እገዳ ጋዛን በ2022 ወደነበረበት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመመለስ 100 ዓመታትን ይፈልጋል ብሏል፡፡
እስራኤል እገዳው ያስፈለገው ሃማስ የጦር መሳሪያ እንዳያስገባ ለማድረግ ነው ስትል ታጣቂ ቡድኑን ለጋዛ ችግር ተጠያቂ አድርጋለች።
በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር ዳኒ ዳኖን ለሪፖርቱ ምላሽ ሲሰጡ “የጋዛ ህዝብ በሃማስ መያዙን እስከቀጠለ ድረስ የጋዛ ነዋሪዎች የወደፊት ተስፋ የላቸውም” ብለዋል።
በጥር ወር መጨረሻ የዓለም ባንክ በጋዛ የደረሰው ጉዳት 18.5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚገመት አስቀምጦ ነበር፤ ይህ ግምት የእስራኤል ታንኮች እና የአየር ጥቃቶች በደቡባዊ ራፋህ እና በሌሎች ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባቸው የጋዛ አካባቢዎች ጠንካራ ጥቃት መክፈት ከመጀመራቸው በፊት የተተነበየ ነበር፡፡
በሌላ በኩል መስከረም ላይ በሳተላይት ምስል ቀረጻ ተመስርቶ በተደረገ የተባበሩት መንግሥታት ግምገማ በጋዛ ውስጥ ከሚገኙት ህንጻዎች ሩብ ያህሉ መውደማቸውን ወይም ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስቀምጧል፡፡
ከ227 ሺህ በላይ የመኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ 66 በመቶ የሚሆኑ መሰረተ ልማቶች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግሯል።
በኖርዌይ የስደተኞች ምክር ቤት የሚመራ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጪዎች ጥምር የሆነው ሼልተር ክላስተር የፈረሱትን ቤቶች ብቻ ለመገንባት ምን ያህል ጊዜ እንደሚፈጅ ሲያሰላ 40 ዓመታት እንደሚፈጅ አረጋግጧል።
እንደ ሳኡዲ አረብያ እና አረብ ኢምሬትስ ያሉ ሀገራት ለጋዛ መልሶ ግንባታ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ቢሆኑም ጋዛ ከእስራኤል ቁጥጥር ነጻ ወጥታ ፍልስጤም ወደ ነጻ ሀገርነት የሚወስዳትን መንገድ ስትጀምር ብቻ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም