የእውቀት ብርሃንን ፈንጣቂው – ሙአለ ሕጻናት

የወይዘሮ ሰናይት የኋላወርቅ የሰርግ ዕለት እድምተኛው “የዛሬ ዓመት የማሙሽ እናት፤ የዛሬ ዓመት የማሙሽ አባት፤”… እያለ ያዜመው ሊሰምር ቀን እየተቆጠረ ነው። የከተማ ነዋሪ ናትና እሷም በሆዷ ያለውም ጽንስ ደህና እንዲሆን የህክምና ክትትል አልተለያትም። ሆኖም የእናትየው የደም ግፊት ከዕለት ወደ ዕለት ከፍ እያለ ሄደ። የሰባት ወር ነፍሰ ጡር እያለች ለጽንሱም ለእናትም ጤና በቀዶ ጥገና (በኦፕራሲዮን) መውለድ እንዳለባት የህክምና ባለሙያዎች ወሰኑ። በሰባት ወሯ ወንድ ልጇን ታቀፈች። ይሁንና ህጻኑ ያለጊዜው በመወለዱና ኪሎው አነስተኛ በመሆኑ ለተወሰነ ጊዜ በሆስፒታል ቆይቶ ህክምና ማግኘት የግድ ነበር፡፡

እናትና አባት ሳሙኤል ደረጄ ሲሉ የሰየሙት የበኩር ልጃቸውን የህክምና ክትትል አጠናቀው በደስታ ወደ ቤታቸው አመሩ። ከሦስት ወር በኋላ የልጃቸው አይን ላይ ችግር መኖሩን አስተዋሉ። ህጻን ሳሙኤልን ይዘው ወደ ህክምና ተቋም አመሩ። ያኔ ታዲያ የአይን ብርሀኑን ለመመለስ ጊዜው ማለፉንና ረቲናው በመላቀቁ አይነስውር መሆኑ ተነገራቸው። የልጃቸውን ዕይታ ለማሻሻል በርካታ የህክምና ተቋማትን አንኳኩ። ህጻኑ ማሞቂያ ክፍል እያለ አስቀድሞ በህክምና ባለሙያዎች መታየትና ተገቢውን ህክምና ማግኘት የነበረበት መሆኑ ተገለጸላቸው። እነሱ ወደ ህክምና የወሰዱበት ወቅት በአይኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት መመለስ የሚቻልበት ጊዜ ካለፈ መሆኑ ተነገራቸው።

እውነታውን ተቀብለው በቤት ውስጥ ለልጃቸው አስፈላጊውን ፍቅር እየሰጡ ቆዩ። ልጃቸው ለትምህርት ሲደርስ ለልጃቸው የእውቀት ብርሃንን ሊሹ አማራጮችን ለማየት ሞከሩ። ያኔ ታዲያ አይነስውር ህጻናት ሰባት ዓመት ሲሞላቸው ቀጥታ አንደኛ ክፍል መግባት እንጂ ሙአለ ህጻናት አልነበረም። ሌሎች ሙአለ ህጻናት ውለው ሲመጡ የእሷ ልጅ እቤት መዋሉ ያልተዋጠላት እናት ብቻዋን በምትብሰለሰልበት ወቅት አንድ እናት ከእሷ ጋር ተመሳሳይ ሀሳብ ይዛ በመገናኛ ብዙሀን አየቻት። ተመሳሳዮች ይሳሳባሉ ነውና አድራሻዋን ፈልጋ አገኘቻት። መሰል ልጆች ያሏቸው ሰባት ወላጆች የጋራ ህብረት ፈጥረው “ለምን ለልጆቻችን መማሪያ አንከፍትም?” ሲሉ በጋራ መከሩ። ያኔ ቪዥን ማየት የተሳናቸው ህጻናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅት ተመሰረተ፡፡

የድርጅቱ መስራችና ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሰናይት የኋላወርቅ ድርጅቱ እንደተመሰረተ ለአይነስውራን ህጻናት ከክፍያ ነጻ ሙአለ ህጻናት መከፈቱን ታስረዳለች። መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም የተመሰረተው ድርጅት ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ የግለሰብ ቤት በመከራየትና በልዩ ፍላጎት የሰለጠኑ መምህራንንና ሞግዚቶችን በመቅጠር ለአይነሥውራን ህጻናት ከክፍያ ነጻ የሙአለ ህጻናት ትምህርት አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ድርጅቱ ለጊዜው ዋና ትኩረቱ የሙአለ ህጻናት ትምህርት ላይ ሲሆን፤ በቀጣይ ያለጊዜአቸው የሚወለዱ (ፕሪማቹር) ህጻናት ላይ አይነስውርነት እንዳይከሰት መከላከል እና አነስተኛ አቅም ያላቸውን የአይነስውር ህጻናት ወላጆችን በኢኮኖሚ የመደገፍ ሀሳብ አላቸው። ትምህርት ቤቱ ቋሚ መደበኛ ገቢ ባይኖረውም ሙአለ ህጻናቱን ያዩ ግለሰቦች በሚያደርጉት ድጋፍ እስካሁን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መቆየቱን ታነሳለች፡፡

የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ደጀን ድርጅቱ ለአይነስውር ልጆቻቸው በቂ የትምህርት እድል ማግኘት ባልቻሉ ሰባት ወላጆች መመስረቱን ይናገራል። መስራቾቹ የልጆቻቸውን ችግር ለመቅረፍ ሲንቀሳቀሱ ከእነሱ አልፈው ለሌሎች ልጆችም መትረፍ የቻለ ድርጅት መስርተዋል። ከትምህርት አገልግሎቱ በተጨማሪ ለወላጆች የግንዛቤ ፈጠራም ይሰራል። በተለያየ መንገድ ድጋፍ ከሚያደርጉ ወገኖች በሚገኘው ገቢ ድርጅቱ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ይጠቅሳል። ያም ቢሆን ውድ የሆነ የቤት ኪራይ እንደሚከፍሉና የመምህራን ደመወዝ ክፍያ፣ የተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስና የሥልጠና ግብአት ለማሟላት ቋሚ ባልሆነና ከግለሰብ በሚገኝ ድጋፍ ወጪዎቹ ይሸፈናሉ። በዚህ የተነሳ ድርጅቱ ችግር ላይ መሆኑን ይጠቅሳል፡፡

ከክፍያ ነጻ የትምህርት አገልግሎት በሚሰጡ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እያሉ የነሱ ድርጅት ትምህርት ቤት ያቋቋመበትን ምክንያት ሲያስረዳም፤ በአካቶ ትምህርት አይነስውራን ህጻናት ከሌሎች አካል ጉዳት ካለባቸው እንዲሁም የአካል ጉዳት ከሌለባቸው ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ የሚል ፕሮግራም መውጣቱን ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት የመስማት ችግር የእይታ ችግር እንዲሁም ሌሎች ችግር ያለባቸውን ልጆች አንድ ላይ በአንድ ክፍል በሚማሩበት ወቅት ያለባቸውን የአካል ጉዳት ግምት ውስጥ ያስገባ የትምህርት አሰጣጥ ፕሮግራም አይኖርም። ተማሪዎች በጋራ አንድ ክፍል ተቀምጠው እንዲማሩ መደረጋቸው ህጻናቱን ውጤታማ እያደረጋቸው ስላልሆነና ማግኘት ያለባቸውን እውቀት እያገኙ ስላልሆነ ትምህርት ቤቱ መከፈቱን ያነሳል።

ትምህርት ቤቱ የሚገኘው ለብዙሀኑ አማካኝ ቦታ ባለመሆኑ ህጻናቱ ወደትምህርት ቤት እንዲሄዱ ወላጆች በየቀኑ ለከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ ይዳረጋሉ። በዚህ ምክንያት የኢኮኖሚ አቅማቸው የሚችል ወላጆች ብቻ ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ የትራንስፖርት ወጪውን መሸፈን ያልቻሉ በርካታ ወላጆች ልጆች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ተገደዱ።

እንደ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢዋ ማብራሪያ የትራንስፖርት አገልግሎት ቢመቻች በርካታ ቤት ውስጥ ያሉ ህጻናት ወደ ትምህርት ቤት ይመጣሉ። ለተማሪዎቹ የምገባ አገልግሎትና የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የታቀደ ቢሆንም የድርጅቱ ገቢ ይህን ለማድረግ ውስን በመሆኑና ቀጣይነቱ ላይ እርግጠኛ መሆን ስላልተቻለ ጀምሮ ከማቋረጥ በሚል አገልግሎቱ ሳይጀምር ቀርቷል። በቀጣይ ድርጅቱ የተሻለ ገቢ ካገኘ የተማሪዎች ምገባና የህክምና አገልግሎት እንደእቅድ በመያዙ የማስጀመር ሃሳብ አለ፡፡

ወደ ድርጅቱ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ ከሚሄዱ ወላጆች ውስጥ የተወሰኑት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲመቻች ይጠይቃሉ። ይህን አገልግሎት ማግኘት ባለመቻላቸውም አመላልሶ የማስተማር አቅም እንደሌላቸው በመግለጽ የሚቀሩ ወላጆች አሉ። ድርጅቱ በአዲስ አበባ ቅርንጫፎችን በመክፈት ህጻናቱ ብዙ ርቀት ሳይጓዙ ወላጆችም ለከፍተኛ ወጪ ሳይዳረጉ የትምህርት አገልግሎት የሚመቻቸበት ሁኔታን ለመፍጠር ሀሳብ አለ። የድርጅቱ ትልቅ ወጪ የኪራይ ክፍያ ነው የሚለው ሥራ አስኪያጁ አቶ ጌታቸው፤ ድርጅቱ የትምህርት አገልግሎት የሚሰጥበት ለሁሉም አካባቢዎች አማካኝ የሆነ የማስተማሪያ ቦታ ቢመቻች ትልቁ የድርጅቱ ችግር ይቃለላል ይላል። ይህም ያሉትን ተማሪዎች ቁጥር ከመጨመር ባሻገር የትምህርት ጥራቱን ማሻሻልና ተማሪዎቹ በምቹ ሁኔታ እንዲማሩ ማድረግ ያስችላል። ሕብረተሰቡ የተለያዩ ወጪዎችን ለመሸፈን የገንዘብም ሆነ የአይነት ድጋፍ በማድረግ ድርጅቱን ከመዘጋት እንዲታደገው ጥሪ አቅርቧል።

ቤዛ እሸቱ

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You