«ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ በማቅረቧ ኮርተናል»  የካፍ ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ

ኢትዮጵያ የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረባ እንዳኮራቸው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ፓትሪስ ሞሴፔ ተናግረዋል። ካፍ 46ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ አድርጎ ከትናንት በስቲያ ባጠናቀቀበት ወቅት ፕሬዚዳንቱ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮጵያ አህጉራዊ ውድድሩን ለማዘጋጀት ያቀረበችው ጥያቄ በትክክለኛው ወቅት ላይ መሆኑን ገልፀው በዚህም የካፍ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ኩራት እንደተሰማቸው አስረድተዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ለማስተናገድ ያሳየችው ፍላጎትና እቅድም የሚደነቅ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጠቅላላ ጉባዔው ላይ ለመታደም ከተለያዩ ሀገራት ለመጡ ልዑካን ያደረገችው አቀባበል እንዳስደሰታቸው የገለፁት ሙሴፔ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ለሁላችንም ቤታችን ናት›› በማለት ተናግረዋል። ኢትዮጵያ በእግር ኳስ ትልቅ ታሪክ እንዳላት ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ በኢትዮጵያ ያላው የእግር ኳስ ፍቅርና ስሜት እንዳስደነቃቸው ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የስፖርት መሠረተ ልማቶችን እንዳስጎበኟቸው በማስታወስ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ለእግር ኳስ እድገት የሚሠራውን ሥራ መታዘባቸውንም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ጨምሮ 13 ሀገራት የ2029ኙን የአፍሪካ ዋንጫን ለማዘጋጀት ጥያቄ እንዳቀረቡ የተናገሩት ሙሴፔ፣ የኢትዮጵያን መንግሥትና እግር ኳስ ፌዴሬሽኑን እንደሚያበረታቱም ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት እንደማንኛውም ሀገር እቅዷን የማቅረብ መብት አላት። ጥያቄዋ ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱም በካፍ አሠራር መሠረት በሥራ አስፈፃሚው የሚታይ ይሆናል።

ሙሴፔ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ባደረጉት ውይይት የእግር ኳስ እድገት ላይ በመሥራት ትልልቅ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት ፍላጎት እንዳላቸው ማስተዋላቸውንም አክለዋል። የኢትዮጵያን የእግር ኳስ መሠረተ ልማቶች ከካፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በመሆን እንደተመለከቱት ጠቁመውም፣ ኢትዮጵያ ውድድሩን ለማዘጋጀት ያላትን ሁሉንም እቅዶች በተቀመጠው ሕግና የአስተዳደር መመሪያ መሠረት እንደሚመለከቱት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ የካፍ መሥራች አባል እንደመሆና ውድድሩን ለማዘጋጀት እቅዷን እንድታቀርብ አበረታታለሁም ብለዋል። በዚህም መሠረት ሁሉንም መስፈረቶች ካሟላች፣ ውድድሩን ለማስተናገድ እጩ ሆና መቅረብ እንደምትችል ገልፀዋል።

ለአህጉሪቱ አግር ኳስ እድገት፣ በኢትዮጵያ እና በሁሉም ሀገራት የሚሠራው ሥራ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸውም፣ በዚህም የኢትዮጵያ መንግሥት እግር ኳስን የሚወድ በመሆኑ፣ የወደ ፊቱ የሀገሪቱ እግር ኳስ ጊዜ ጥሩ ይሆናል የሚል ተስፋ አላቸው።

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻነት ትልቅ ሚና የተጫወተች ሀገር እንደሆነች ያስታወሱት ሙሴፔ፣ የአፍሪካ ሀገራት ውድድሮችን ለማስተናገድ የካፍን መመዘኛ መስፈርቶችን ያሟሉ ስታዲየሞች መያዝ እንዳለባቸውም አያይዘው ገልፀዋል። አሁን ላይ 24 የአፍሪካ ሀገራት የካፍና የፊፋን ደረጃ የሚያሟላ ስታድየም እንደሌላቸው ገልጸውም፣ ሁሉም ሀገራት ቢያንስ አንድ የካፍና ፊፋን ደረጃ የሚያሟላ ስቴድየም ሊኖራቸው እንሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ እግር ኳስ ትልቅ መሰረት የጣለች ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ ዋንጫን ሦስት ጊዜ በማስተናገድ አንድ ጊዜ ዋንጫ ማንሳቷን በማስታወስ በአቶ ይድነቃቸው ተሰማ የካፍ ፕሬዚዳንት ዘመን ለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ትልቅ ሚና መጫወተን ተናግረዋል።

አቶ ኢሳያስ ኢትዮጵያ ከአምስት አስርተ ዓመታት በኋላ የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅ መሆን እንደምትፈልግና ከአምስት ዓመት በኋላ በ2029 የሚካሄደውን የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቧን አስረድተው፣ ለዚህም መሳካት በቁርጠኝነት እንደምትሠራ ቃል ገብተዋል። በአሁኑ ወቅት 11 ስታዲየሞች በግንባታ እና በማሻሻያ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመውም፣ የካፍ እና ፊፋ መስፈርትን እንዲያሟሉ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዓለማየሁ ግዛው

አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You