– በኢትዮጵያ የሚገኘውን የሉባን ወርክሾፕ ለማስፋፋት የሚረዳ ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያና ቻይና በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት አጠናክረው ለማስቀጠል እየሠሩ መሆኑን የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ገለጹ። በኢትዮጵያ የሚገኘውን የሉባን ወርክሾፕ ለማስፋፋት የሚረዳ ስምምነት መፈረሙንም ጠቁመዋል።
በቻይና ምክትል ትምህርት ሚኒስትርና በሀገሪቱ ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ ዉ ያን የተመራ ልዑክ የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያና ሥልጠና ኢንስቲትዩትን ትናንት ጎብኝቷል።
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ጉብኝቱን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፤ ቻይናውያን የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያና ሥልጠና ኢንስቲትዩትን ከመገንባት ጀምሮ፣ ሙያቸኞችን በመላክ፣ የመምህራንን አቅም በማሳደግ እና ሌሎች ድጋፎችን በማድረግ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ አጋርነት አላቸው።
በቀጣይም ቻይና እና ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ልማት፣ በሥልጠና ጥራት እና በቴክኒክና ሙያ ዘርፎች ጥራት ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲ ዩኒቨርሲቲ ግንኙነትን በማጠናከር የኢትዮጵያ ተማሪዎች ቻይና ሄደው እንዲሠለጥኑ እንዲሁም ቻይናውያን አሠልጣኞች ኢትዮጵያ መጥተው እንዲያሠልጥኑ የሚያደርግ ተከታታይ የመምህራን የአቅም ግንባታ በመስጠት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነች ለማጠናከር እንደሚሠራም አብራርተዋል።
የሁለቱን ሀገራት የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለማጠናከር የቲያንጂን ቴክኖሎጂ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ እና የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያና ሥልጠና ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ የሚገኘውን የሉበን ወርክሾፕ ለማስፋፋት የሚረዳ ስምምነት መፈራራማቸውን አስታውቀዋል።
ቴክኒክና ሙያ ከፍተኛ መዋለ ንዋይ የሚጠይቅ ተቋም በመሆኑ የተፈረመው ስምምነት ለኢትዮጵያ የሥልጠና ጥራትን ለማሳደግ፣ የግብዓት አቅርቦትን ለመጨመር እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን ያስገኛል ነው ያሉት።
የቻይና ፕሬዚዳንት ከአራት ዓመት በፊት በተመረጡ የተለያዩ ሀገራት የሉባን ወርክሾፕን ለማቋቋም ባመነጩት ሃሳብ በኢትዮጵያ የሉባን ወርክሾፕ መቋቋሙን አስታውሰው፤ ወርክሾፑ በአርተፊሻል ኢንተለጀንስ እና በሮቦቲክስ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ዘመኑን የሚመጥኑ ሥልጠናዎች እየተሰጡበት ነው ብለዋል።
በሉባን ወርክሾፕ ሠልጣኝ መምህራን፣ የኢንዱስትሪ ተዋንያኖች እና አጫጭር ሥልጠና የሚወስዱ ተማሪዎች ተጠቃሚ እየሆኑ መሆናቸው ገልጸው፤ ባለሙያዎች በጨርቃጨርቅ፣ በመጠጥ፣ በሲሚንቶ እና በሌሎች ዘርፎች ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት ሥልጠና እያገኙ መሆኑን አስረድተዋል።
የቲያንጂን ቴክኖሎጂ ትምህርት ዩኒቨርስቲ ሉባን ወርክሾፕን በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት እንዲያቋቁም ኃላፊነት የተሰጠው ተቋም መሆኑን አመልክተው፤ በኢትዮጵያ ያለውን የሉባን ወርክሾፕ በሰው ሃይል፣ በግብዓት እና በቴክኖሎጂ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል በቻይና ምክትል ትምህርት ሚኒስትርና በሀገሪቱ ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ ው ያን የተመራ ልዑክ የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ኢንስቲትዩትን የጎበኙ ሲሆን፤ ጉብኝቱ ሁለቱ ሀገራት በትምህርቱ ዘርፍ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ዓላማ ያደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያና ሥልጠና ኢንስቲቲዩት የቴክኒክና ሙያ አሠልጣኞችን፣ ቴክኒሻኖችን እና መሪዎችን የማፍራት ተልዕኮ የተሰጠው ተቋም ሲሆን፤ ይህንን ተልዕኮ ለመወጣት የውስጥ አቅም የመገንባትና ጊዜውን የዋጀ ቴክኖሎጂ መላበስ አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
ይህንንም ጥረት ማሳካት የሚቻለው በሀገር ውስጥ ካሉ አጋር አካላት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ አጋሮችን ማፍራት ሲቻል መሆኑን በመጠቆም፤ ኢንስቲትዩቱ ከቻይና ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል።
ስምምነቱን የቲያንጂን ቴክኖሎጂ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ሊቀመንበር ዣንግ ጂንጋንግ እና የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያና ሥልጠና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር (ዶ/ር) የፈረሙት ሲሆን፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እና የቻይና ምክትል ትምህርት ሚኒስትርና የሀገሪቱ ኮሙኒስት ፓርቲ ተወካይ ዉ ያን ተገኝተዋል።
ቻይናውያን የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩትን ከመገንባት ጀምሮ፣ ሙያተኞችን በመስጠት፣ የመምህራንን አቅም በማሳደግ እና የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
ሄለን ወንድምነው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2017 ዓ.ም