እንደምን ሰነበታችሁ! እንኳን በጤና ተገናኘን!
ባሳለፍነው ሳምንት በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በምርጫ ላይ ያሳረፈውን ጥቁር ጥላ በተመለከተ ዳሰሳ ማድረጋችን ይታወሳል።
በዚህኛው ጽሑፋችን ደግሞ ከሕገመንግሥት ትርጉም ጋር በተያያዘ ማብራሪያ እናቀርባለን።
የሕገመንግሥት ዝምታ አለ የለም –
የእሰጥ አገባው መነሻ
መንግሥት የሚመሰረተው በየአምስት ዓመት በሚደረግ ምርጫ ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በአስቸኳይ ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች። እናም ምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአንድ ላይ ውለዋል – “ሰኔና ሰኞ”ም እንዲሁ ዘንድሮ ዘልቀዋል።
“ሰኔና ሰኞ” ከተገጣጠሙ መቼም ለኢትዮጵያ በጎ ዕድል ይዘው እንደማይመጡ እናት አባቶቻችን ሲናገሩ ሰምተናል። እኛም በዘመናችን ወርሃ ሰኔ በዕለተ ሰኞ ብቶ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ማለፉን አንዘነጋውም።
የሆነው ሆኖ የሰኔና ሰኞ መጥፎ ዕድል ሳይሆን አይቀርም፤ ኮሮና ይሉት ወረርሽኝ በአንድ በኩል አገራችንን አስጨንቋታል። ወዲህ ደግሞ ከለውጡ በኋላ ሕዝቦቿ በተስፋ ሲጠብቁት የነበረው ምርጫም በዚሁ የሰኔና ሰኞ ዓመት ውሏል። ይሁንና ምርጫውን ማድረግ እንደማይቻል መንግሥት ወስኗል። እንዳለመታደል ሆኖ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሕዝቡን አስተያየት እየሰበሰቡና ጥናት እያካሄዱ ለፖሊሲ አውጪዎችም ሆነ ለመንግሥት ውሳኔ ሰጭዎች መረጃ የሚያቀርቡ ድርጅቶች የሉንም እንጂ ቢኖሩን ኖሮ በጥናት የተደገፈ አሃዝ እናገኝ ነበር። ያም ሆኖ አብዛኛው ሕዝብ በዚህ ክፉ ወቅት ምርጫ ስለማድረግ ቀርቶ ስለማሰቡም እርግጠኛ መሆን አይቻልም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት ምርጫ ማድረግ እንደማይቻል መወሰኑን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ የሕገመንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፣ ፓርላማውን መበተን ወይም የሕገ-መንግሥት ትርጉም መጠየቅ ከሚሉት አራት አማራጮች ሕገመንግሥቱን የመተርጎም አማራጭን በሥራ ላይ አውሏል።
ለዚህ ዋነኛ መነሻው ደግሞ የሕገመንግሥቱ ዝምታ ነው – የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ምርጫ ሲገጣጠሙ አገረ-መንግሥቱ በምን ሁኔታ መቀጠል እንዳለበት የሚያስቀምጠው መፍትሔ የለም በሚል።
የሕገመንግሥት ትርጉም ጥያቄ የቀረበለት የሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔም ጉዳዩን በመመርመር ላይ የሚገኝ ቢሆንም ሁኔታው በሁሉም ዘንድ መነጋገሪያ ብቻ ሳይሆን የእሰጥ አገባም አጀንዳ ሆኗል።
በአንድ በኩል ሕገመንግሥቱ “Black and White” እንደሚባለው መንግሥት በየአምስት ዓመቱ በሚደረግ ምርጫ እንደሚመሰረት በግልጽ ያስቀመጠ ሰነድ በመሆኑ ትርጉም እንደማያሻው የሚናገሩ አሉ። ስለሆነም “ምርጫ የግድ መደረግ አለበት” ባዮች ናቸው።
በሌላ በኩል በጉዳዩ ላይ የሕገመንግሥቱን ዝምታ አምነውበት ሰነዱ የሕግ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካም ጭምር በመሆኑ ለዝምታውና አገሪቱ ላጋጠማት ችግር መፍትሔው ሕጋዊ ሳይሆን ፖለቲካዊ መሆን እንዳለበት የሚሞግቱም አልጠፉም። “የሽግግር መንግሥት መመስረት አለበት” በማለት።
ሕገመንግሥቱ ግልጽ ሆነም ክፍተት ይኑርበት አሁን ኢትዮጵያን ሰቅዞ ለያዛት ሕመም መድሃኒቱ የሕገመንግሥት ትርጉም ሳይሆን ከነችግሮቻቸውም ቢሆን ሌሎቹን ሦስቱን አማራጮች መንግሥት መተግበር እንዳለበት ምክር ብጤም የሚለግሱ አሉ።
ሕገመንግሥቱ ዝምታ አለውን?
መቼስ ሕገመንግሥቱ በታሪኩ እንዲህ ያለ ሁነኛ ትኩረት ተሰጥቶት መነጋገሪያ የሆነበት ጊዜ አልነበረም። እርግጥ የጸደቀበትን ሕዳር 29 ቀን ለመዘከር በየዓመቱ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን በሚል ይከበራል። በየጊዜውም የሕገመንግሥት አስተምህሮና ሌሎች ጉዳዮችም ይሰናዳሉ።
ይሁንና እንዲህ እንደዛሬው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ምርጫ ተገጣጥመው ወሳኝ ጊዜ ላይ ስለተገኘ “እስኪ መፍትሔ አምጣ” ተብሎ የተጠየቀበት ጊዜ አልነበረም። በልጅ በአዋቂው፤ በምንዝሩ በባለስልጣኑ፤ በመንግሥት በተቃዋሚው፤ ፊደል ባልቆጠረውም ሆነ በሊቁ ሁሉ ተገልጧል፤ ተነቧል።
ሕገመንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ እንደሚመረጡ ደንግጓል። አክሎም ምክር ቤቱ የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት መሆኑን፤ የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊትም አዲስ ምርጫ ተካሂዶ እንደሚጠናቀቅ ይገልጻል።
የፖለቲካ ሥልጣንን በደነገገበት አንቀጹም በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የሕግ አስፈጻሚውን እንደሚያደራጁና እንደሚመሩ ይገልጻል።
እነዚህ ድንጋጌዎች በግልጽ እንደሚነግሩን ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ሊካሄድ እንደሚገባ ነው። ከ1992 ዓ.ም ጀምሮም ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ተካሂዷል።
የሆነው ሆኖ ከዚህ አንጻር ካየነው ሕገመንግሥቱ “Black and White” ሆኖ ስለተቀመጠ ምንም ይሁን ምን በአምስት ዓመት ምርጫ ሊደረግ የግድ ነው። እናም የዚህ ሃሳብ አራማጆች ትክክል ናቸው ማለት ይቻላል።
ሕግ በመርህ ደረጃ ግልጽና በበቂ አመክንዮአዊ ሊቀረጽ ይገባዋልና ሕገመንግሥቱም ለሕግ ባለሙያዎችና ለፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም ሰው ሁሉ ለመረዳት ግልጽ መሆን አለበት። ስለዚህም ሕገመንግሥቱ በአምስት ዓመት ይደረጋል በሚል ያስቀመጠው ግልጽ ድንጋጌ ነው።
ነገር ግን ይህንን ድንጋጌ ሕገመንግሥቱ ራሱ ካስቀመጠው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድንጋጌና ከወቅታዊው ሁኔታ አንጻር ካልተረዳነው “ሳሩን አይቶ ገደሉን” እንዳለማየት ያስቆጥራል። ስለዚህ ምርጫውንና አዋጁን በጣምራ ማየት ያስፈልጋል።
የውጭ ወረራ ሲያጋጥም፤ ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰት፤ የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት በፌዴራሉ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ይታወጃል።
ክልሎችም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት በክልላቸው ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያውጃሉ።
ከዚህ በመነሳት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በየትኛው ዓመት እንደሚታወጅ አይታወቅም፤ መገመትም አይቻልም። በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለው ግን በሕገመንግሥቱ ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ አንዱ ወይም ተደራርበው በተከሰቱ ጊዜ እንደሚታወጅ ነው።
እንዲህ ከሆነ ደግሞ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ምክንያት የሆነው ድንገተኛ ነገር እንዳሁኑ ባለ ምርጫን ለማድረግ በተዘጋጀንበት የመንግሥቱ አምስተኛው የሥልጣን ዓመት ላይ ሊሆን ይችላል።
በመሆኑም ምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አንድ ላይ ከተፍ ብለዋል። በዚህ ጊዜ ታዲያ ሕገመንግሥቱ ምን ይላል ነው ቁልፉ ጉዳይ።
ሕገመንግሥቱ የፖለቲካ ሥልጣንን በተመለከተ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ ተደርጎ መንግሥቱ ይመሰረታል ባለበት አፉ በምርጫው ጊዜ እንደዛሬው ዓይነት ከባድ ሁኔታ ቢያጋጥም የፖለቲካው ሁኔታ እንዴት ይሆናል ስለሚለው ጉዳይ ትንፍሽ አይልም።
ይህ ብቻም አይደለም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በተመለከተ በየትኛውም ጊዜ ተፈጥሯዊ ወይም ሰው ሠራሽ የሆነ ድንገት ደራሽ ነገር ሲያጋጥም እንደሚታወጅ ሲገልጽ፤ አዋጁ እንዲታወጅ የሚያስገድደው ምክንያት ምርጫ በምናካሂድበት ወቅት ቢገጣጠም ምን ማድረግ አለብን ለሚለው ጥያቄ “በነካ እጁ” መልስ ሳያስቀምጥ ዝምታን መርጧል።
ከዚህ የምንገነዘበው መሰረታዊ ጉዳይ ታዲያ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ ይደረጋል የሚለውን ብቻ አንጠልጥለን ሕገመንግሥቱ ግልጽ ስለሆነ ትርጉም አያሻውም፤ ምርጫውም በወቅቱ መደረግ አለበት ማለት እንደማይገባን ነው።
ይልቁንም “Read between the lines” እንደሚባለው እማሬውን ሳይሆን በእያንዳንዱ የሕጉ ቃላት ውስጥ ያለውን ፍካሬያዊ አንድምታ እንዲሁም ከሌሎች ድንጋጌዎች ጋር በማጣመር መረዳት የግድ ነው።
የቃላትን የላይ ገጽታ ብቻ ከማንበብ አልፎ መንግሥት የቆመበትን ምሰሶና ወጋግራ የያዘውን ሕገመንግሥት በቅጡ ልንረዳው የምንችለው ድንጋጌው ከአጠቃላዩ የሕጉ መንፈስ ጋር ተሰናስሎ የሚሰጠው ምስል ሲገለጽልን ነው።
ለዚህ ደግሞ የሕገመንግሥቱ የዝምታ መጋረጃ ሊገለጥልን ያስፈልጋል “ንበብ ይገድላል፤ ትርጉም ያድናል” እንዲሉ።
የሕገመንግሥት ዝምታ ለትርጉም ምክንያት አይሆንምን?
ሕገመንግሥቱ ግልጽ ስለሆነ ትርጉም አያሻውም በሚል የሚያስተጋቡ አካላት እንዳሉ ሁሉ ሕገመንግሥቱ ክፍተት ያለበት እንኳ ቢሆን ዝምታው ትርጉም ለመጠየቅ ምክንያት አይሆንም የሚሉ ወገኖችም አሉ።
መንግሥት ሕገመንግሥቱ እንዲተረጎም ለሕገመንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የመራው በጉባዔው አዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀጽ 3/2/ሐ አግባብ ነው።
በድንጋጌው መሰረት አንድ ሦስተኛ በሆነ የፌዴራል ወይም የክልል ምክር ቤት አባላት አማካኝነት በፍርድ ሊወሰን በማይችል በማንኛውም ጉዳይ ላይ የትርጉም ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል።
ይሁንና አንዳንዶች የሕገመንግሥት ክፍተት የሕገመንግሥት ትርጉም ያስፈልገዋል ተብሎ ወደ ጉባዔው ሊላክ የሚችልበት የሕግ አግባብ እንደሌለው አጥብቀው ይሞግታሉ።
የሙግታቸው ማጠንጠኛም በአዋጁ አንቀጽ 3/1 ላይ “አጣሪ ጉባዔው ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሠራር ወይም የመንግሥት አካል ወይም የባለስልጣን ውሳኔ ከሕገመንግሥቱ ጋር ይቃረናል የሚል ጥያቄ በጽሑፍ ሲቀርብለት ያጣራል” በሚል የተገለጸው ኃይለ-ቃል ነው።
ከዚህ በመነሳትም የሕጎች፣ የልማዳዊ አሠራሮችና ውሳኔዎች ከሕገመንግሥቱ ጋር መቃረናቸው ካልሆነ በስተቀር በሌላ ምክንያት የሕገመንግሥት ትርጉም ሊቀርብ አይገባም ባይ ናቸው።
ይሁንና ይህ አስተሳሰብ ከሕገመንግሥት ትርጉም አስፈላጊነት፣ መርህና አጠቃላይ አንድምታ እንዲሁም ከአዋጁ መሰረታዊ መርሆዎች፤ ይበልጡኑም የሕጎች የበላይ ከሆነው ሕገመንግሥቱ ድንጋጌዎች አንጻር ሲመዘን ውሃ የሚያነሳ አይመስልም።
ሕገመንግሥቱን ስለመተርጎም ከሚለው የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 83 እንደምናነበው የሕገመንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል። ምክር ቤቱን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር ከወጣው አዋጅም ይህንኑ እናገኛለን።
የፌዴሬሽን ምክር ቤትን በሕግ ጉዳዮች ለማገዝ የተቋቋመውን የጉባዔውን ሥልጣንና ተግባር የደነገገው የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 84 ደግሞ ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ሥልጣን እንደሚኖረውና በሚያደርገው ማጣራትም ሕገመንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ እንደሚያቀርብ ይገልጻል።
ከእነዚህ ድንጋጌዎች እንደምንረዳው የሕገመንግሥት ትርጉም የሚያስፈልገው የሕገመንግሥታዊ ጉዳዮች ክርክር ሲነሳ ወይም ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ነው።
እናም የሕጎች፣ የልማዳዊ አሠራሮችና ውሳኔዎች ከሕገመንግሥቱ ጋር መቃረን ሕገመንግሥቱን ለመተርጎም እንደአንድ የሕገመንግሥት ክርክር የሚነሳበት ወይም ሕገመንግሥታዊ የሆነ ነጠላ ጉዳይ እንጂ የሕገመንግሥት ትርጉም የሚጠየቅበት ብቸኛው ምክንያት እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል።
በዚሁ መነሻ በጉባዔው አዋጅ መሰረት የሕገመንግሥቱ ዝምታ የትርጉም ጥያቄ ለማቅረቢያ ምክንያት ሆኖ ባይጠቀስም ሕገመንግሥታዊ ክርክር ያስነሳ በመሆኑ በራሱ በሕገመንግሥቱ ድንጋጌዎች መሰረት ለጉባዔው የሚቀርብ ሕገመንግሥታዊ ጉዳይ ነው።
ሕገመንግሥት ግልጽ ካልሆነ ይተረጎማል። እርስ በእርሱ የሚጣረስና አሻሚ ከሆነም እንዲሁ። ለመረዳት የማይቻል ደብዛዛ ድንጋጌ ሲኖረውም ትርጓሜ ያሻዋል። በሚጸድቅበት ጊዜ ያልተከሰተ ነገር ግን ኋላ ላይ ለሚያጋጥም ችግር የመሸጋገሪያ ድልድይ ካላስቀመጠም መተርጎም አለበት።
እናም ምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተገጣጠሙ ጊዜ የሕዝብና የመንግሥት የአምስት ዓመት የሥልጣን ውል በምን መልኩ ይፈጸማል የሚለውን ስለማይዳስስ ሕገመንግሥቱ ክፍተት አለበት ማለት ነው። ስለዚህ በአምስት ዓመት ምርጫ ይደረጋል የሚለው የሕጉ እውነተኛ ትርጉም በተደቀነብን ነባራዊ ሁኔታ መነጽርነት ታይቶ ጥርት ሊልልን ይገባል።
ከሁሉም በላይ ምርጫ በየአምስት ዓመቱ እንዲካሄድ ሕግ ያወጡት የያኔዎቹ ኢትዮጵያውያን በምርጫ ወቅት ጦርነት፣ ረሃብ፣ በሽታ ወዘተ… ቢኖርስ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ሳያስቀምጡ ለምን አለፉት የሚለው የሃሳባቸው አመክንዮ ምን እንደሆነ ማወቅ ይገባል።
እርግጥ ነው የያኔዎቹ የሕገመንግሥቱ አርቃቂዎችና አጽዳቂዎች ሰው ናቸውና ወደፊት ሊከሰቱ ለሚችሉ የማይጠበቁ ሁኔታዎች ሁሉ መፍትሔ የሚሰጥ ድንጋጌ ማካተት ሊሳናቸው ይችላል። ነገር ግን ሕዝቡን ወክለው በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ይህንን ውል (ሕገመንግሥቱን) አጽድቀው ስንመራበት ከቆየን በኋላ የዛሬዎቹ ኢትዮጵያውያን ምርጫና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተገጣጥመውብናል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው የመጨረሻ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥም መሆኑን፤ በሥራ ላይ ሲውልም የዴሞክራሲ መብቶችንም ጭምር (ምርጫን ጨምሮ) እንደሚገድብ በሕገመንግሥት ጉባዔ ቃለ-ጉባዔ ላይ ሰፍሯል።
ከዚህ የምንረዳው ሕገመንግሥቱን በማጽደቅ ሂደት ያልተደመጡና የተጨቆኑ ድምፆች እንደነበሩ ቃለ-ጉባዔው የሚያሳብቅ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሕዝቡን ወክለዋል የተባሉት የያኔዎቹ እንደራሲዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው የመጨረሻ የተባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥም ለመሆኑ ከግንዛቤ አስገብተዋል።
የሽግግር መንግሥት አማራጭ – “የማያዋጣ ባል ቅንድብ ይስማል”
አንዳንዶች ሕገመንግሥቱ ሕጋዊ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊ ሰነድም በመሆኑ ለወቅታዊው ችግር መፍትሔው ፖለቲካዊ መሆን አለበት ይላሉ – የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም በመጠየቅ።
ሕገመንግሥቱ የፖለቲካም ሰነድ ነው በሚለው ብንስማማ እንኳ አንድም ስፍራ ላይ የሽግግር መንግሥት አማራጭን አላስቀመጠም። ከምርጫ በቀር በሌላ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝን ከልክሏል። እናም የሽግግር መንግሥት ሕጋዊም ፖለቲካዊም መፍትሔ ሊሆን አይችልም።
ስለዚህ አገሪቱ ላጋጠማት የፖለቲካ ችግር ሕጋዊ መፍትሔ እንጂ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደማያሻት ግልጽ ነው። የሕግ የበላይነት መገለጫውም ይኸው ነውና።
በተለያዩ አገራት እንደታየው ፖለቲካዊም ሆነ ሌሎች ከሕገመንግሥት ውጪ ያሉ አማራጮች የፖለቲካ ቀውስ አስከትለዋል። በኢትዮጵያ የዳበረ የሽግግር መንግሥት ተሞክሮ የለም።
ተመሳሳይ የብሔር ወይም የሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄ አንግበው የሚቋቋሙ የፖለቲካ ፓርቲዎች በርካታ ናቸው። የተለያዩ ነገር ግን ተመሳሳይ ርዕዮተ-ዓለም የሚያራምዱትም ብዙ ናቸው። መቻቻልና የዳበረ የፖለቲካ ባህል የለንም። ቢሮ ሳይኖራቸው ቢሯቸው ቦርሳቸው የሆኑና የግለሰቦችም የሚመስሉ ፓርቲዎች ሞልተውናል። ማህተም በኪሱ ይዞ የሚዞር አመራር ያላቸውም አልጠፉም። እንዲህ ያሉ የፖለቲካ ኃይሎች ባሉበት አገር የሽግግር መንግሥት አማራጭ “የማያዋጣ ባል ቅንድም ይስማል” እንደሚባለው ነው።
ፖለቲካዊ ንግግርና መቻቻል የግድ ነው
የፖለቲካ መፍትሔ ሕገመንግሥታዊ አይደለም ቢባልም ቅሉ በሕዝቡም ሆነ በልሂቃኑ መካከል ፖለቲከኞችን ጨምሮ ተደጋጋሚ የፖለቲካ ምክክሮች ሊደረጉ ያስፈልጋል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ቁልፍ ኃላፊነት አለበት። የተሻለ ያለውን የሕገመንግሥት ትርጉም አማራጭ በግልጽነትና በከባድ ኃላፊነት ከመፈጸም ባሻገር ጫፍና ጫፍ የረገጡ የሃሳብ አለመግባባቶችን ሊያጠብቡ የሚችሉና ወደተሻለ የፖለቲካ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ የንግግር መድረኮችን ሊፈጥር ያስፈልጋል።
በዚህ ፈታኝ ቅርቃር ነገር ግን ታሪካዊ በሆነ አጋጣሚ አገርን እየመራ ገዥው ፓርቲ ሕገመንግሥቱን በሚተረጉመው የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ በፓርላማው ውስጥ ያለውን አብላጫ ሥልጣን ተጠቅሞ የሚወስናቸውን ማናቸውንም ውሳኔዎች ሁሉን አቀፍ በሆነ አሳታፊና ብዙሃኑን በሚያስማማ አኳኋን ሊተገብራቸው ይጠበቃል።
ሃሳብ በማፍለቅ የማህበረሰብ አስተሳሰብ የመቅረጽ ኃላፊነት ያለባቸው ልሂቃንም ሆኑ ፖለቲከኞች ለአገርና ለሕዝብ ሰላምና ደህንነት ቅድሚያ በመስጠት አሻጋሪ አስተሳሰቦችን ሊቀርጹና ሊያሰርጹ ይገባቸዋል።
ሕዝቡም በበኩሉ በ1960ዎቹ እና በ1980ዎቹ ተገኝተው ያመለጡትንና እስከዛሬም ድረስ ላልተፈቱ የፖለቲካ ቋጠሮዎች ምርኮኛ ያደረጉትን አጋጣሚዎች በከፈለው ዋጋ መነጽርነት እየቃኘ ከአሻጋሪ ሃሳቦች ጎን ሊቆም ይገባዋል።
በደህና እንሰንብት!
አዲስ ዘመን ግንቦት 26/2012
በገብረክርስቶስ