ወጣቶች ናቸው። ከዚህ በፊት ከህትመትና ዲዛይን ጋር የተያያዙ ስራዎችን በተናጥል ሲሰሩ ቆይተዋል። በተመሳሳይ የስራ መስክ ላይ መሆናቸውና በስራ አጋጣሚ መገናኘታቸው ደግሞ የኩባንያዎችንና የተለያዩ ድርጅቶችን መለያዎችን፣ ህትመቶችን፣ የትስስር ገፅ ዲዛይኖችን፣ ቪዲዮ ፕሮዳክሽኖችን፣ የግራፊክ ዲዛይኖችንና ሌሎችን ስራዎችን በጣምራ እንዲሰሩ እድል ፈጥሮላቸዋል። ስራው የራስ የፈጠራ ክህሎትና ብዙ ወጪ የሚያስወጣ ባለመሆኑ በቀላሉ የራሳቸውን ኩባንያ በማቋቋም በጋራ ተጠቃሚ እያደረጋቸው ይገኛል።
ኩባንያው ስፔክተረም ብራንድ ሶሉሽንስ ይባላል። ወጣት ቢኒያም አያሌው ኩባንያውን ከመሰረቱ ሶስት ወጣቶች አንዱ ነው። ወጣት እዮብ አበረና ሚካኤል ፍቃዱም የኩባንያው መስራቾች ናቸው።
ወጣት ቢኒያም ተወልዶ ያደገው በአዲስ አበባ ቄራ አካባቢ ሲሆን ፣ በማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመጀመሪያ ዲግሪውን ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ አግኝቷል።
በወቅቱ እርሱ በተማረበት የትምህርት ዘርፍ እምብዛም ስራ ባለመኖሩና አስቀድሞ የዲዛይን ስራ ፍላጎት ስለነበረው ከአስራ ሶስት ዓመት በፊት በቤተሰቡ አነስተኛ የፅህፈት መሳሪያ መደብር ውስጥ የቢዝነስና የጥሪ ወረቀት ካርዶችን መስራት ይጀምራል።
በመቀጠልም ማተሚያ ቤት በማቋቋም ልዩ ልዩ የህትመት ስራዎችን ለአብነትም የካለንደር፣ መፅሄትና የአጀንዳ ስራዎችን ከወንድሙ ጋር በመሆን ሰርቷል። ይህ አጋጣሚ ተመሳሳይ የማስታወቂያና የህትመት ስራ ከሚሰሩ ሁለት ጓደኞቹ ጋር አገናኘው። በጋራ የመስራቱ ሃሳብም በዚህ ወቅት ይፀነሳል። ቀስ በቀስም የህትመት ስራዎችንና የማስታወቂያ ባነሮችን መስራት ጀመሩ። በዚህ መልኩ የጀመረው ስራቸው ወደ ዲዛይን ስራዎች ያመራል፤ በወቅቱ የዲዛይን ስራ የተከበረና ለብቻው በክፍያ የሚሰራ አልነበረም።
ወጣት ቢኒያም የግራፊክ ዲዛይን የመስራት ፍላጎቱ የነበረው መሆኑ ግን እርሱና ጓደኞቹ የማተማያ ቤት በመከፈት ሙሉ በሙሉ ወደ ህትመት ስራዎች ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደርጋቸዋል። በወቅቱም የጓደኛሞቹ ፍላጎት አንድ ቡድን እንዲኖርና ይህ ቡድን የዲዛይን ስራ ብቻ እንዲሰራ ነበር። በሌላው ሀገር የዲዛይን ስራ ራሱን የቻለ የቢዝነስ ዘርፍና ክፍያ የሚጠየቅበት ነው። በኢትዮጵያ ዘርፉ ገና ያልዳበረ መሆኑን በመረዳት ከማስታወቂያና የህትመት ስራዎች ጎን ለጎን የዲዛይን ስራውንም መስራት ቀጠሉ።
ለዲዛይን ስራ የሚሰጠው ዋጋ ቢሂደት ከፍ እያለ በመምጣቱ ከዛሬ ሁለት ዓመት ተኩል በፊት ስፔክትረም ብራንድ ሶሊዩሽን በሚል ስያሜ ኩባንያ በማቋቋም ሙሉ በሙሉ በዲዛይን ስራዎች ላይ በማተኮር መስራት ጀመሩ። በወቅቱ ስራውን ሲጀምሩም ብዙ ካፒታል የሚጠይቅ ባለመሆኑና ከዚህ ይልቅ ጭንቅላትን በመጠቀም የመፍጠር አቅምን የሚጠይቅ በመሆኑ ለስራቸው የሚያስፈልጉ እንደ ኮምፒዩተር የመሰሉ እቃዎችን በመግዛትና ቢሮ በመከራየት ስራቸውን ቀጠሉ።
‹‹ብራንድ›› የአንድ ምርት ወይም ድርጅት የጥራት መለያ ወይም መገለጫና ሰዎችም ስለምርቱ ወይም ስለ ኩባንያው ያላቸው አመለካከት እንደመሆኑ መጠን ስፔክትረም ብራንድ ሶሊዩሽን ኩባንያም በዋናነት ለልዩ ልዩ ምርቶችና ኩባንያዎች ዲዛይን በማድረግ ብራንዶችን /መለያዎችን/ ይሰራል። ልዩ ልዩ ስራዎችን ለሚሰሩ ኩባንያዎችም ከሚጠቀሙበት ቀለም አንስቶ አስከሎጓቸው ድረስ መገለጫዎችን ይሰጣል። ወጥነት ያለውና አንድ አይነት እይታ እንዲኖረው ታሳቢ በማድረግና ሁሉንም መገለጫዎች ባቀፈና እነርሱን በሚገልፅ መልኩም የትስስር ገፅ፣ ቢልቦርድ፣ የሚታተሙ ፕሮፋይሎች ፣ ብሮሸሮችና በአጠቃላይ ሌሎችም ስራዎች እንዲሰራላቸው ያደርጋል። ይህም በኩባንያዎቹ ወይም በድርጅቶቹ ደምበኞች ወይም ተጠቃሚዎች አዕምሮ ውስጥ ተቀርፆ እንዲቀር ያደርጋል።
በህትመትና የማስታወቂያ ባነር ስራ የጀመሩት እነዚሁ ወጣቶች ይህንኑ ኩባንያ ካቋቋሙ በኋላም በወረቀት ላይ የሚታተሙ የኩባንያዎችን፣ ድርጅቶችን፣ የንግድ ተቋማትንና የሌሎችንም ፕሮፋይሎች በመፅሄት ማዘጋጀት፣ የመፅሃፍ ከቨሮችን የተለያዩ ይዘትና ቅርፅ ያላቸውን ካላንደሮችን፣ የምግብ ማሸጊያዎችንና የገበያ ቦርሳዎችን፣ መፅሄቶችን፣ፖስት ካርዶችን፣ የምርቃት መፅሄቶችን እየሰሩ ይገኛሉ።
ኩባንያቸው የድርጅቶችንና የኩባንያዎችን መለ ያዎችን በሁሉም ሚዲያ እንዲሰራጭ ያደርጋል። የኩባንያዎች ሎጎ ዲዛይንና የብገራንድ መመርያ፣ ማስታወሻ መፃፊያና የቢዝነስ ካርድና የመሳሰሉ የፅህፈት መሳሪያ እቃዎችንም ያዘጋጃል። ዌብ ዲዛይን ያደርጋል፤ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ሚዲያ ገበያ፣ የግራፊክ ዲዛይንና የህትመት አገልግሎቶችንም አያይዞ ይሰጣል።
ኩባንያው የአንድን ምርት ሎጎ በቅድሚያ ይሰራል። በመቀጠልም ሌብል በስታንዳርድ ዲዛይን ካደረገ በኋላ ልሙጥና ባዶ የነበረውን ምርት ሙሉ ቅርፅ፣ ይዘትና መልክ ሰቶ ለገበያ እንዲቀርብ ያደርጋል። ምርቱ እንዴት እንደሚናገርና ምን አይነት ፀባይ እንዳለው ስብእናም ሰጥቶ ለገበያ ያወጣል። እቃዎችን በኦንላይን ለመግዛት የሚያስችል ፕላት ፎርም በማዘጋጀት የዲጂታል ቴክኖሎ ጂዎችን ጨምሮ ከዲዛይን እስከ ህትመት ድረስ ያሉ ሁሉንም አገልግሎቶች ይሰጣል።
ከግንዛቤ ክፍተት የተነሳ በተወሰነ መልኩ ለስራው ዋጋ የሚሰጥ ሰው እንደሌለ ወጣት ቢኒያም በመጥቀስ፣ በሰዎች ዘንድ ያለው አመለካከት በሂደት እየተሻሻለ በመምጣቱ ስራቸው በአሁኑ ወቅት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱን ይናገራል። በውጭው ዓለም የብራንድና የግራፊክ ዲዛይን ኢንዱስትሪው ትልቅ ግምት የሚሰጠውና ከዚህ ዘርፍ ውጪ የኩባንያዎች፣ ድርጅቶች፣ የንግድና ሌሎችም ተቋማት ስራ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችልም ይጠቁማል። አንድ ኩባንያ የተለየ ነገር ይዞ መምጣት እስካልቻለ ድረስ ማንም ሊለየው እንደማይችል አብራርቶ፣ዘርፉ ስነልቦናዊ የማርኬት ስትራቴጂም ጭምር ያለው መሆኑንም ያብራራል።
‹‹አንድ ሎጎ ከ500 አስከ አንድ ሚሊዮን ብር ማሰራት የሚቻል በመሆኑ ከዘርፉ የሚገኘውን ትክክለኛ ገቢ ለመወሰን ያስቸግራል›› የሚለው ወጣት ቢኒያም፤ ከዘርፉ ከፍተኛ የሚባለውን ገቢ ለማግኘት ትልቅ ልምድና ስም እንደሚያስፈልግ ነው ያመለከተው። አሰሪው አካል የሚሰራለት ሎጎ በደምብ ሊለውጠው እንደሚችል ማሳመን እንደሚጠይቅም ያስረዳል።
ከአስር ዓመታት በፊት በህትመትና በዲዛይን ስራዎች ላይ ተሰማርተው ያሉ ሰዎች ጥቂት ነበሩ የሚለው ወጣት ቢኒያም፣ በኢትዮጵያ በዚህ ኢንዱስትሪ ላይ በአሁኑ ወቅት በርካታ ሰዎች ተሰማርተው እየሰሩ እንደሚገኙም ይናገራል።
ወጣት ቢኒያም እንደሚገልፀው ፤ ሰዎች ለብራንዲንግ /መለያ/ እና ግራፊክ ዲዛይን ስራ የሚሰጡት ዋጋ የወረደ ሲሆን፣ በዘርፉ ተሰማርተው እየሰሩ ያሉ ሰዎች ሊሰማቸው ይችላል። በደምብ አወቀ የሚባለው ሰው እንኳ ለዚህ ስራ ዋጋ መስጠት አይፈልግም። ይሁንና አልፎ አልፎ ደግሞ የስራውን ዋጋ ተረድተው የሚያሰሩ አሉ። ይህም ሆኖ ታዲያ ስራው ተሰጥኦና የመስራት ፍላጎት የሚጠይቅ በመሆኑ ኢንዱስትሪው ለሁሉም ሰው የሚሆን ቢዝነስ አይደለም። የተወሰነ የአርት ሙያ ከሌላቸውም ስራውን ቢልጉት እንኳ ላይሰሩት ይችላሉ።
‹‹በዚህ ዘርፍ ላይ ህብረተሰቡ ያለው አመለካከት ዝቀተኛ መሆን እንጂ በዘርፉ ተሰማርቶ ለመስራት የሚያግዱ ችግሮች የሉም›› የሚለው ወጣት ቢኒያም፣ ሰዎች ቢዝነሱን ካመኑበትና ችሎታው እንዳላቸው ካረጋገጡ ብሎም ከሌሎች የተለየ ነገር በማቅረብ ስራውን በተሻለ ሁኔታ የሚሰሩ ከሆነ በዘርፉ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ይጠቁማል። ስራው አሳይቶና አሳምኖ አሰሪው ለስራው የሰጠውን ዋጋ መረዳት መቻል እንዳለበት የሚጠይቅ በመሆኑም የግድ ተሰጥኦ እንደሚፈልግም ያመለክታል።
ወደ ስፔክትረም ብራንድ ሶሊዩሽን በመምጣት በአሁኑ ወቅት በብዛት ደምበኞች እያሰሩ ያሉት የዌብሳይት፣ የኮርፖሬት ብራንድና የህትመትና ማስታወቂያ ስራዎች መሆናቸውንም ወጣት ቢኒያም ተናግሮ፤ ለአገልግሎት የሚጠየቀው ክፍያም እንደ ድርጅቶቹ ደረጃና በዘርፉ እንዳላቸው ልምድ የሚወሰን መሆኑን ያመለክታል። በትንሹ ከዘርፉ ከ5 እስከ 10 ሚሊዮን ብር እንደሚገኝበት ይጠቁማል። ስፔክትረም ደግሞ የአንድ ኩባንያ ብራንድን ለመስራት በትንሹ ከ50 እስከ 300 ሺ ብር እንደሚጠይቅ ይናገራል።
እንደ ወጣት ቢኒያም ማብራሪያ፤ ዘርፉ በስፋት ሊያሰራ የሚችል በመሆኑ ስፔክትረም ብራንድ ሶሊዩሽን በራሱ የጀመራቸውና ወደፊት የሚወጡ የተለያዩ ፕሮጀከቶች እንዳሉ ሆነው በቀጣይ በራሱ የሚሰራቸውን ምርቶች ቁጥጥር በማድረግ አሳድጎ ይሰራል። በቱሪዝም ዘርፈ ላይ ያሉና ከዘርፉ ጋር የሚገናኙ ስራዎችንም ለመስራት አቅዷል። የዘርፉ ቢዝነስ ሊያድግ የሚችለው የአሰሪዎችን ቁጥር በማሳደግ በመሆኑና ከስራው የሚገኘው ገቢም እንደየስራው ጥራት፣ የፈጠራ ችሎታና የስራ ደረጃ በመሆኑ የሰው ሃይል ማሳደግን ይጠይቃል። በመሆኑም ኩባንያው በስሩ ያሉ ሰራተኞች ጥቂት በመሆናቸውና በዚህ የሰው ሃይል የሚሰራው ስራ ውጤቱ አነስተኛ በመሆኑ በቀጣይ የሰው ሃይሉን በመጨመር አቅሙን ለማሳደግ ይፈልጋል።
‹‹እንደ ጀማሪነት በዚህ የቢዝነስ ዘርፍ ከወቅታዊ ሁኔታ አኳያ ስኬታማና በጥሩ ደረጃ ላይ እንገኛለን›› የሚለው ወጣት ቢንያም፣ እሱና ጓደኞቹ በመደጋገፍና በትጋት መስራታቸው ለስኬት እንዳበቃቸው ይናገራል። የስራ ጓኞቹን በመወከልም ለሌች በዚህ የቢዝነስ ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ መሆን ከፈለጉ ሰዎች በቅድሚያ ፍላጎቱና ተሰጥኦው ሊኖራቸው እንደሚገባና ሁሌም አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ይመክራል። ዘርፉ በርካታ ሰዎች ሊቀላቀሉበት የሚችል ከመሆኑ አኳያም በዚህ ዘርፍ ገብተው ለመስራት ወደኋላ ማፈግፈግ እንደማይኖርባቸውም ይጠቁማል።
ዓለም ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እየተለወጠ መምጣቱን ተከትሎ የዘርፉ ተፈላጊነት እየጨመረ መጥቷል። ይሁንና ወደ ቢዝነሱ በቶሎ ገብቶ በቶሎ ገንዘብ የሚገኝበት ባይሆንም ፅናቱና ለሙያው ፍቅሩ ካለ የኋላ ኋላ ገንዘቡን ሊገኝ እንደሚችልም ይናገራል።
ሰዎች ይህን ዘርፍ በወጣትነት እድሜያቸው ቢቀላቀሉ መልካም ነው የሚለው ወጣት ቢኒያም፤ በዘርፉ ገንዘብ ለማግኘት ግን ልምድ እና የፋይናንስ አጠቃቀም ብልጠት ሊኖራቸው እንደሚገባ ያስገነዝባል፤ በጋራ ቢሰራ ውጤታማ ሊሆኑ እንደሚቻልም ያስረዳል። የማርኬቲንግና የፋይናንስ እውቀት ካላቸው እንዲሁም ከሌሎች ሰዎች ጋር በጋራ የሚሰሩበት እድል ካለ በዘርፉ ገብተው አትራፊ ሊሆኑ እንደሚችሉም ያመለክታል።
እንደ ወጣት ቢኒያም ገለጻ፤ ዘመኑ ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ እያደገ መጥቷል። እያደገ ከመጣው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር ታዲያ የብራንድና የግራፊክ ዲዛይን ስራም አብሮ እየተመነጠቀ መጥቷል። ይህም በርካታ ጥበብ የታከለባቸውን የህትመት፣ የማስታወቂያ፣ የሎጎና ሌሎችንም ልዩ ልዩ ስራዎች ለመስራት እገዛ አድርጓል። ከዘርፉ የሚገኘውም ገቢ እያደገ መጥቷል።
እነሱን ጨምሮ ለስምንት ዜጎች የስራ እድል የፈጠረው ኩባንያው በቴክኖሎጂ እና እውቀት ሽግግር ለኢንቨስትመንት፣ ንግድና የመሳሰሉት ተግባሮች መሳለጥ የራሱን ድርሻ እንደሚያበረክት ይታመናል። ሌሎች የተማሩ ወጣቶችም ከዚህ ተሞክሮ እንደሚቀስሙ ይታሰባል።
አዲስ ዘመን ግንቦት 25/2012
አስናቀ ፀጋዬ