በስፖርት የመጨረሻውን ደረጃ ክብር የሚያስገኘው ውድድር ኦሊምፒክ መሆኑ ይታወቃል። በዓለም ትልልቅ ስም ያላቸው ዝነኛ አትሌቶች ሃገራቸውን ወክለው የሚሳተፉበት እንዲሁም በርካታ ክብረወሰኖች የሚሰባበሩበትም ነው። በመሆኑም በአትሌቶች ዘንድ በመድረኩ የሜዳሊያ ባለቤት መሆን ብቻም ሳይሆን ተሳትፎውም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው።
ኦሊምፒክ በየአራት ዓመቱ ስለሚካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት የሚደረግበት ሲሆን፤ ወጥ አቋም የሌላቸው አትሌቶች በተደጋጋሚ ኦሊምፒክ ላይ ሊታዩ አይችሉም። በመሆኑም በርካታ ተሳትፎ ያላቸው አትሌቶችን ለማግኘት አዳጋች ነው። እንግሊዛዊቷ አትሌት ግን በመጪው ዓመት ስድስተኛ የኦሊምፒክ ተሳትፎዋን ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኗን ነው ያሳወቀችው። በተለይ ለወጣት አትሌቶች አስተማሪ የሆነ ተሞክሮዋንም ለቢቢሲ አጋርታለች።
ጆ ፓቬ አምስት አሊምፒኮች ላይ የተሳተፈች አንጋፋ አትሌት ስትሆን በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ስድስተኛ ተሳትፎዋን በማድረግ የክብረወሰን ባለቤት ለመሆን ፍላጎት አላት። ከዚህ ቀደም የሃገሯ ልጅ የሆነችው ጦር ወርዋሪ ቴሳ ሳንደርሰን ስድስት ኦሊምፒኮች ላይ ሀገሯን የወከለች አትሌት በመባል ተመዝግባለች። ፓቬ ስድስተኛዋን ተሳትፎ የምታደርግ ከሆነ ደግሞ በመም አትሌት የመጀመሪያዋ ትሆናለች።
ፓቬ እአአ በ2014 ከወሊድ በኋላ በአውሮፓ ሻምፒዮና በ10ሺ ሜትር ስትሳተፍ በአንጋፋነቷ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆና ነበር። ይሁን እንጂ በ40ዓመቷ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት በመሆን ብቃቷን ማስመስከር ችላለች። በቶኪዮው ኦሊምፒክ ስትሳተፍም ዕድሜዋ 46 ስለሚሆን ምናልባትም በኦሊምፒኩ አንጋፋዋ አትሌት ልትሆን ትችላለች። ፓቬ ለቢቢሲ በሰጠችው አስተያየት ላይም «ዕድሜዬን ረስቼ ስድስተኛውን የኦሊምፒክ ተሳትፎዬን አደርጋለሁ» ብላለች።
አትሌቷ ሃገሯን ወክላ በኦሊምፒክ የመጀመሪያ ተሳትፎዋን ያደረገችው እአአ በ2ሺ በተካሄደው የሲድኒ ኦሊምፒክ ላይ ነበር። «በቶኪዮ የሚካፈለው ብሄራዊ ቡድን ጥሩ ተፎካካሪ እንዲሆን እፈል ጋለሁ። በመሆኑም ዝግጅታችንን ቀድመን መጀመር ይገባናል፤ ፉክክሩ ደግሞ ይበልጥ ደስ የሚያሰኝ ነው» ብላለች። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው አትሌቷ ከኦሊምፒኩ አስቀድሞ በዘንድሮው የዶሃ ዓለም ሻምፒዮና አቅሟን የመፈተሽ ፍላጎት እንዳላትም ጨምራ ገልጻለች። እአአ በ2017 በለንደን በተካሄዱት ሁለት ትልልቅ የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ ተሳታፊ ብትሆንም አልተሳካላትም ነበር። በለንደን ማራቶን ውድድሯን ሳታጠናቅቅ አጋማሽ ላይ ስታቋርጥ፤ በ10ሺ ሜትር በተካፈለችበት ሻምፒዮና ደግሞ በጉዳት ምክንያት ውድድሯን ለማጠናቀቅ አልቻለችም ነበር።
ያለፈው ዓመት በተካሄደ ሌላ ውድድር ግን በረጅም ርቀት የመም ላይ ውድድር ሶስተኛ በመሆን የነሃስ ሜዳሊያውን ወስዳለች። በባለቤቷ የምትሰለጥነው አትሌቷ በልምምድ ቦታዎች ላይም ነፍስ ያላወቁ ልጆቿን ይዛ ትሄዳለች «ሩጫ እወዳለሁ፤ የአእምሮ እና ሰውነት ጤናን ለማግኘት ያግዛል። ከቤተሰብህ ጋር ሆነህ ስትከውን ደግሞ ይበልጥ መነሳሳትን ይፈጥራል። ባለቤቴ ያግዘኛል፤ ሥራችንን የምንሰራውም እንደ ቡድን ነው። ሯጭ ስትሆን መጨናነቅን ማስወገድ የግድ ነው ይህም የአእምሮን ጤና ይሰጣል። እድሜህንም እንደ ልምድ መጠቀም ትጀምራለህ» ስትልም የህይወት ልምዷን ታጋራለች።
የአትሌቷ የኦሊምፒክ ተሳትፎ በተለያዩ ችግሮች የታጀበ ይሁን እንጂ ተስፋ አለመቁረጧ ግን ለብዙዎች ተሞክሮ የሚሆን ነው። እአአ 1997 ከባድ የሆነና ውስብስብ ቀዶ ጥገና የሚያስፈልገው የጉልበት ጉዳት የደረሰባት ቢሆንም፤ ከዚያ አገግማ በሲድኒ ኦሊምፒክ 12ኛ ደረጃን በመያዝ ነበር ያጠናቀቀችው። እአአ በ2004ቱ የአቴንስ ኦሊምፒክ ከመሳተፏ ሶስት ወራት በፊት የጡንቻ ጉዳት ቢደርስባትም አምስተኛ ደረጃ በመያዝ የዲፕሎማ ተሸላሚ ነበረች።
በ2008ቱ የቤጂንግ ኦሊምፒክ 12ኛ ደረጃ በመያዝ ውድድሯን ያጠናቀቀችው ደግሞ በውድድሩ ዋዜማ በምግብ መበከል የጤና መታወክ ስለደረሰባት ነበር። በሀገሯ በተዘጋጀው የ2012 ኦሊምፒክ በ5 እና 10ሺ ሜትር ውድድሮች ተሳትፎዋ ሰባተኛ ደረጃ በመያዝም የመጀመሪያዋ አውሮፓዊት አትሌት ተሰኝታለች። በሪዮ በተካሄደው የ2016ቱ ኦሊምፒክ ደግሞ ዘግይታ ውድድሩን በመጀመሯ በ10ሺ ሜትር 15ኛ ደረጃን ነበር የያዘችው። «የሪዮ ኦሊምፒክ ተሳትፎዬ በጣም አስደሳች ነበር፤ አብረውኝ የሮጡት አትሌቶችም ከእኔ በ20ዓመት የሚያንሱ ነበሩ። ቢሆንም ሁሌም ሃገሬን መወከል ለእኔ ኩራት ነው» ስትልም ትገልጻለች።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
ብርሃን ፈይሳ