ለብሄራዊ ቡድኖች እና ለክለቦች ተተኪ የሚሆኑ አትሌቶችን ለማፍራት በታዳጊ ደረጃ ስልጠና መስጠት ውጤታማ እንደሚያደርግ ይታወቃል። ከፕሮጀክቶች የተሻለና የላቀ ችሎታ ያላቸው ታዳጊዎች ሳይንሳዊ ስልጠና አግኝተው ክለቦችንና ብሄራዊ ቡድንን ለመቀላቀል ብቁ እንዲሆኑም የማሰልጠኛ ማዕከላት መኖር ወሳኝ ነው። በኢትዮጵያም ውስን ማዕከላት ተከፍተው ወጣቶችን ለማፍራት እየሰሩ ይገኛሉ።
የአትሌቲክስ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላቱ በትግራይ ክልል ማይጨው፣ በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን፣ በኦሮሚያ ክልል በቆጂ እንዲሁም በደቡብ ብሔር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ሃገረ ሰላም ላይ የተገነቡ ናቸው። በ2000ዓም ወደ ሥራ የገቡት እነዚህ ማዕከላት በተለየ መልኩ ሊመረጡ የቻሉትም ለአትሌቲክስ ስፖርት ምቹ የሆነ የቦታ አቀማመጥና የአየር ሁኔታ ስላላቸው ነው።
የስፖርት ማዕከላቱ ከተቋቋሙ በኋላም ለሚገኙባቸው ክልሎች በኃላፊነት ተሰጥቷል። ይሁን እንጂ ማዕከላቱ በእርስ በእርስ የመማማሪያ መድረክ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት በክልሎቻቸው የሚያገኙት ድጋፍ የተለያየ መሆኑ ነው ለማስተዋል የተቻለው። አንዳንድ ክልሎች ድጋፍ በማድረጋቸው የተሻለ ሥራ ሲያከናውኑ አንዳንዶች ደግሞ ድጋፍ ስለማድረጋቸውም በሚያጠራጥር ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። በመሆኑም ክልሎች ለማዕከላቱ የሚያደርጉት ድጋፍ ምን ይመስላል የሚለውን መመልከት ይገባል።
ተሞክሯቸውን ካቀረቡት ማዕከላት መካከል በተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኘውና እነደ ተምሳሌትም ሲታይ የነበረው የሃገረ ሰላም አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ነው። በደቡብ ስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ እስራኤል ቡአ፤ ኮሚሽኑ ከማዕከሉ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ይገልጻሉ። በማዕከሉ በሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት እንዲሁም የሚቀርቡ ጥያቄዎችን በረጅም፣ አጭርና መካከለኛ ጊዜ ምላሽ ይሰጥበታል። ያለ ጥሬ ዕቃ ስልጠናውን ማስኬድ የማይቻል በመሆኑም፤ በመንግሥት ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠውና በቂ በጀት እንዲመደብለትም በቅንጅት ይሰራል።
ከዚህ ቀደም በማዕከሉ የሚገኘው የወንድና ሴት ሰልጣኞች መኖሪያ በአንድ አካባቢ የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ ማስፋፊያ በማድረግ ለማለያየት ተችሏል። ኮሚሽኑ ማስፋፊያውን ከማድረጉም ባሻገር 1ነጥብ6 ሚሊዮን ብር ለካሳ መክፈሉንም ነው የሚገልጹት። ከዚህ ባለፈ በቤንቺ ማጂ እና ደቡብ ኦሞ ዞን የራሱን የታዳጊ ማሰልጠኛ ተቋም በመገንባት ላይ የሚገኝ ሲሆን፤ አንዱ በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝም ነው ዳይሬክተሩ የሚገልጹት።
ማዕከሉ ከምልመላ ጀምሮ መስፈርቱን ተከትሎ ሥራው በጥንቃቄ እንዲካሄድ ለማድረግም ኮሚሽኑ ክትትል ያደርጋል። የምልመላ ቡድኑ ወደ ተለያዩ ሥፍራዎች ሲንቀሳቀስ ጥብቅ መመሪያ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሲመለስም ክትትሉ የሚቀጥል ይሆናል። ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ እና ኮሚሽኑ ጋር ተገቢ መናበብ ቢኖርም አልፎ አልፎ አንዳንድ ገባ ወጣ ማለቶች ይስተዋላሉ፤ ግምገማ በማካሄድም ለማስተካከል ጥረት ይደረጋል።
ክልሉ ያለፈው ዓመት ሊካሄድ ለነበረው መላ ኢትዮጵያ ጨዋታዎች በጀት ቢመድብም፤ ውድድሩ ግን በሀገር አቀፍ ደረጃ አልተካሄደም ነበር። በመሆኑም ገንዘቡን ለማዕከሉ የጂምናዚየም ቁሳቁስ ግዢ ለማዋል ተችሏል። ይሁን እንጂ ከመብራት ኃይል ጋር ተያይዞ አገልግሎት መስጠት ያልጀመረ ሲሆን፤ በቅርቡ ከሚመለከተው አካል ጋር በመነጋገር ሥራ እንደሚጀምርም ነው ዳይሬክተሩ የሚጠቁሙት።
ሀገራዊና ወጥ የሆነ የአሰራር መመሪያ በማዕከላቱ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ያስችላል። የልምድ ልውውጥ መድረኩን መካሄድ ተከትሎም የአሰራርና አደረጃጀት መመሪያ የሚዘጋጅ በመሆኑ፤ የሰልጣኞች ሽግግርና ዝውውር ላይ የሚፈጠሩ ችግሮችን የሚመልስ መመሪያ ይበጃል ብለው እንደሚጠብቁም ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ስፖርት ታሪክ ሰፊውን ድርሻ የሚይዙት ውጤታማ አትሌቶች ከበቆጂ የተገኙ መሆኑ ይታወቃል። በዚሁ ምክንያትም አካባቢው በዓለም ደረጃ «የሯጮች ምድር» እስከመባል ደርሷል። በዚህ ወቅትም በርካታ የረጅም ርቀት አትሌቶች ከአካባቢው እየወጡ ይሁን እንጂ ከስሙ አንጻር የበቆጂ አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል በሚጠበቀው ልክ በመስራት ላይ ይገኛል ለማለት አያስደፍርም። ከአትሌቲክስ ማዕከል ባሻገር የፊፋ ጎል እግር ኳሰ ማሰልጠኛ ፕሮጀክት የሚገኝ መሆኑም ይታወቃል።
የክልሉ ስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ ግርማዬ ለታ፤ ማዕከላቱ ከውጤት አንጻር ሲመዘኑ እንደሚጠበቀውም ባይሆን ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን ይገልጻሉ። ይህ ሊሆን የቻለው ደግሞ ባለድርሻ አካላት፤ ስፖርት ኮሚሽን፣ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ፌዴሬሽኑ እንዲሁም የክልል ቢሮዎች እኩል ትኩረት ሰጥተው በተቀናጀ መልኩ እየተሰራ ባለመሆኑ ነው። ማዕከላቱን በማሰባሰብ ተሞክሯ ቸውን በመቅሰም እርስ በእርሳቸው ልምድ እንዲለዋወጡ ማድረግ የተለመደ ባለመሆኑም የሰሩተን ስራ በትክክል ማቅረብ ላይ ችግር አለ።
ኮሚሽኑም በአካባቢው የተሻለ ሥራ እንዲሰራ ባለሙያዎችን የማብቃትና የሙያ ማሻሻያ እንዲያገኙ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ። ለማዕከሉ ጽህፈት ቤት በመስጠት፣ በጀት በመመደብ፣ ጂምናዚያም እንዲሁም የሁለቱን ማዕከላት መዋቅር በመከለስ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሰራም ዳይሬክተሩ ይጠቁማሉ። ትኩረት እየተሰጠ አይደለም ይባል እንጂ ከሌሎች ክልሎች የተሻለ በጀት በመመደብና ትኩረትም በማድረግ ላይ ይገኛል። በዚህም ካሉት ማዕከላት በተጨማሪ አንድ ቢሊዮን በሚሆን ወጪ ሱሉልታ ላይ በርካታ ስፖርቶችን የሚያሰለጥን አካዳሚ በመገንባት ላይ እንደሚገኝም በማሳያነት ያነሳሉ።
የማሰልጠኛ ማዕከላቱ እና አካዳሚው ተመሳሳይ ሥራ የሚሰሩ ቢሆንም በሀገር አቀፍ ደረጃ ግን ትኩረት አልተሰጠውም። መሆን የሚገባው ግን አንዳቸው ከሌላው በተለየ የረጅም ጊዜ እቅድ በመያዝ የተሻለ ነገር ላይ ማተኮር ነው። እንደ ክልል ግን ያሉትን ነገሮች በማየት በተሻለ መልክ እንደሚካሄድበት ነው የሚገልጹት።
የትግራይ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ከሃሳይ ፍሰሃ፤ የማይጨው አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል ከተመሰረተበት 2002ዓ.ም ጀምሮ እድገት በማሳየት ላይ ያለ መሆኑን ይጠቁማሉ። ቢሮው ጅምናዚየም በማስገንባት፣ የሰልጣኞችን ቁጥር ከ35 ወደ45 በማሳደግ እንዲሁም በጀት በመመደብ ቢሮው ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ።
ማዕከሉ የራሱ ስታንዳርድ የሌለው ሲሆን፤ አንድ ማዕከል ምን ምን መያዝ አለበት የሚለው፣ እንዲሁም ወደየት ማደግ አለበት በሚለው ላይ ስታንዳርድ አልነበረውም። ከሌሎች የታዳጊ ስፖርት ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች ጋርም ትስስር አልነበረውም። በመሆኑም በምን መልኩ መዋቀር ይገባዋል በሚለው ላይ ቢሮው ጥናት እያደረገ ይገኛል። ጥናቱ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባም ችግሮቹን ይፈታል ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ከነችግሮቹ ሰልጣኞችን ወደ ተለያዩ ክለቦች በመመገብ ሀገርን ወክለው በውድድሮች ላይ የሚካፈሉ አትሌቶችን ማፍራት ችሏል። የማዕከል ቆይታቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞችም ወደ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ፣ ጥሩነሽ ዲባባ ስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከል እንዲሁም በክልሉ የሚገኙ ክልሎችን እንደሚቀላ ቀሉም ባለሙያው ይጠቁማሉ።
ሊተኮርበት የሚገባውም ማዕከላቱ በየራሳቸው ከሚያደርጉት ጥረት ይልቅ ኮሚሽኑ ወጥ የሆነ መዋቅር ቢሰራ የተሻለ እንደሚሆንም ይጠቁማሉ ባለሙያው። ይህ ሲሆንም ክልሎች ማሟላት የሚገባቸውን አውቀው ሥራቸውን ያከናውናሉ። በዚህም ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚችልም እምነታቸው ነው።
በአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን የተሳትፎ፣ ስልጠና ውድድር ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አክሊሉ፤ በክልሉ በሚገኘው የደብረ ብርሃን አትሌቲክስ ማሰልጠኛ ማዕከል አስተያየታቸውን ይሰጣሉ። አሁን ባለበት ሁኔታ እንዲሁም በሚያፈራቸው አትሌቶች አንጻር ሲታይ ጥሩ ሥራ እየሰራ ይገኛል ለማለት እንደሚያስደፍር ይጠቁማሉ። በፓራሊምፒክ ስፖርትም ማዕከሉን እንዲጠቀሙት በማድረግ ላይ ይገኛል። የደብረ ብርሃኑን ተሞክሮ በመያዝ መሰል ማዕከልም በሌሎች ዞኖች ላይ በማደራጀት ጥረት ላይ አንዳሉም ይገልጻሉ።
ክልሉ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን ብር ያላነሰ ድጋፍ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ክልሉ ትኩረት በመስጠት በኩል የሚጠበቅበትን እንዳላደረገም ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። ከዚህ በኋላም ክልሉ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ችግር ባለበት የሽግግር ሥርዓት ላይ የአሰራር ማኑዋል በማዘጋጀት ወጥ በሆነ መንገድ መስራት ይገባል። በቀጣይም ማሰልጠኛ ማዕከላት አንድን ስፖርት ብቻ መሰረት አድርገው ሳይሆን ቀስ በቀስ ሌሎች ስፖርቶችንም ማካተት እንደሚገባ ከመድረኩ ተሞክሮ ለማግኘት እንደቻሉም ዳይሬክተሩ ይገልጻሉ። በመሆኑም በቀጣይ የቀሩትን ሥራዎች በማከናወን በኩል ከክልሉ በርካታ ነገር የሚጠበቅ ይሆናል።
አቶ ሲሳይ ሳሙኤል በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር፤ በመድረኩ ላይ በርካታ ጉዳዮች መነሳታቸውን ይጠቁማሉ። የመጀመሪያው ነገር በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ የታየ ጉድለት ነው። ይህም ወጥ የሆነ አሰራርና መመሪያ በማበጀት ማዕከላቱ ተመጋጋቢ እንዲሆኑና ውጤታማ አትሌቶችን ለማፍራት ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑ ታይቷል። ችግሩን የመቅረፍ ኃላፊነት የኮሚሽኑ ሲሆን፤ ተግባራዊነቱ ላይ ደግሞ ክልሎች ኃላፊነቱን መውሰድ እንዳለባቸውም ያሳስባሉ። ከዚህ በኋላም ይህ ዓይነት መድረክ በማይቋረጥ መልኩ የሚካሄድም ይሆናል።
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
ብርሃን ፈይሳ