የሕብረት ሥራ ማህበራት በተለያዩ አገራት እንደየአገራቱ ተጨባጭ ሁኔታ በተለያየ መልኩ ተደራ ጅተው የህብረተሰብን ችግር ለማቃለል፤ የአገር ኢኮኖሚንም በመደገፍ ተግባር ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በኢትዮጵያ በኃይለሥላሴ ዘመን መሰረቱን እንደጣለ የሚነገርለት የኅብረት ስራ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደጊዜ አድማሱን እያሰፋና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ድርሻውንም እያጎለበተ ይገኛል፡፡ እኛም በዛሬው እትማችን በኢትዮጵያ የህብረት ስራ ማህበራት በአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ያላቸው ሚና ምን ይመስላል በሚለው ዙሪያ የፌዴራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ሱሩርን አነጋግረን ለንባብ በሚመች መልኩ አቅርበነዋል፡፡
ኤጀንሲው
ኤጀንሲው ከሚያከናውናቸው በርካታ ተግባራት ውስጥ አንደኛው በአገራችን ያሉ ህብረት ስራ ማህበራትን ማደራጀት፣ ማጠናከርና የተደራጁበትን ተልዕኮ እንዲወጡ ማድረግ ነው፡፡ ከተደራጁበት ተልዕኮ ደግሞ አንደኛው የኢኮኖሚው መሰረት የሆነውን ግብርና በማዘመን ሂደት ውስጥ የድርሻቸውን መወጣት ሲሆን፤ ግብርናውን በዘላቂነት ለማሳደግና ለማዘመን ደግሞ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ቀጣይነት ባለው መልኩ አርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ቀዬ ድረስ የማቅረብ ተልዕኮ ነው የተሰጠው፡፡ ሁለተኛም ግብርናው ሊዘምንና ቀጣይነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው አርሷደሩ ላመረተው ምርት ፍትሃዊና ተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል ማድረግ ነው፡፡ በግብርና ምርት ላይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ የአርሷደሩ የመደራደር አቅም እንዲያድግ ማስቻል፤ ለዚህም የህብረት ስራ አመራሩም ተዋናይ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
ብድርና ቁጠባ
በዚህ መልኩ ደግሞ ገበያ ከመጣ ሃብት ተፈጠረ ማለት እንደመሆኑ የተገኘውን ሃብት ማሰባሰብ ይገባል፡፡ በዚህ መልኩ ሃብቱን ለማሰባሰብ ደግሞ በቁጠባ ትልቅ ድርሻ ስላለው የቁጠባ ባህል እንዲያድር የማስተማርና የማንቃት እንዲሁም መላውን ህብረተሰብ በተለይም የህብረት ስራ ማህበራትን የማሰልጠን ተግባር እየከናወነ ነው፡፡ ይሄን በማድረጉም ህብረተሰቡ ካገኘው ላይ ቆጥቦ እንዲበደርና ተበድሮም በተለይም በግብርናው ስራ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርግና ተጨማሪ ሀብት እንዲፈጥር፣ የስራ እድል እንዲፈጥርና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያመጣ የማስቻል ተደማሪ ተልዕኮው እንደመሆኑም እነዚህኑ ተግባራትንም እያከናወነ ይገኛል፡፡
የህብረት ስራ ማህበራትም ጤናቸውና ደህንነታቸው እንዲጠበቅ እና ለአባላት ግልጽ እንዲሆኑ የኦዲት፣ ኢንስፔክሽንና የቁጥጥር ስራዎችንም እየሰራ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በሁሉም ረገድ ሲወሰድ ህብረት ስራ ማህበራቱ በአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ላይ ያላቸው አስተዋጽዖና ተጽዕኖ ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ የመጣ መሆኑን መገንዘብ ተችሏል፡፡ ለዚህ እድገታቸውም በርካታ ማሳያዎች ያሉ ሲሆን፤ ያለፉትን አምስት ዓመታት ብቻ ወስዶ ማየት ቢቻል እንኳን የማህበራቱና የአባላቱ ቁጥር ብሎም ቁጠባ በፍጥነት እያደገ መሆኑን መመልከት ይቻላል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታም አባላቱ 20 ሚሊዮን የደረሱ ሲሆን፤ እነዚህ አባላት ደግሞ በገጠርም ሆነ በከተማ፣ በአርሶ አደሩም ሆነ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚኖሩ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ 32 በመቶዎቹ ሴቶች፤ ከ15 በመቶ በላይ ደግሞ ወጣቶች ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ መላውን ህዝብ ተደራሽ፣ ህብረተሰቡንም ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ የህብረት ስራ ማህበራቱ ሚና ከፍ እያለ መምጣቱ አመላካች ነው፡፡
ግብርናውን ለመደገፍ
የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ከማዘመንና ከማሳደግ ጋር ተያይዞ በተለይ ገጠርን ትራንስፎርም ለማድረግ የግብርና ምርቶች ላይ እሴት በመጨመርና የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት የገጠር ሽግግሩን በማገዝ ረገድ ሚናቸው ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ፣ አሁን ላይ ከ870 በላይ ማህበራት ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ የተለያዩ አይነት ኢንዱስትሪዎችን ከፍተው በአባላቶቻቸው የግብርና ምርቶች ላይ እሴት እየጨመሩ ነው፡፡
አንዳንዶቹም በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከውጭ የሚገቡ ዘይትና መሰል ምርቶችን አገሪቱ ባላት ሰፊ ምርት ተጠቅመው በማምረት በአገር ውስጥ ምርት የመተካትና ለአገር ውስጥ ገበያ የማቅረብ ስራ እያከናወኑ ይገኛል፡፡ እነዚህ ማህበራት እንደ አጠቃላይ ሲታይ የካፒታልና ቁጠባን ጨምሮ አሁን ላይ ሃብታቸው ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡ ይህ ደግሞ በኢኮኖሚው እድገት ላይ የማህበራቱ ተጽዕኖ ከፍ እያለ መምጣቱን ነው የሚያሳየን፡፡
በተመሳሳይ ወደ አምስት ሚሊዮን አባላት የገንዘብ ቁጠባና ብድር አባላት ናቸው፡፡ እነዚህ አባላት ወደ 16 ቢሊዮን ብር የቆጠቡ ሲሆን፤ ይህ የቆጠቡት ገንዘብ ደግሞ በብድር መልክ ተመልሶ ወደ ኢኮኖሚው ተሰራጭቷል፡፡ ምክንያቱም ይህ ገንዘብ በተለይ ግብርናውን ለማዘመንና ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አርሶአደሩ ተበድሮ በአካባቢው ባሉ የግብርና ጸጋዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ላይ ነው፡፡ በዚህም የአርሷደሩ ምርታማነት እንዲያድግና ገበያም እንዲያገኝ ከማስቻሉም በላይ፤ ለወጣቶች የስራ እድል ከመፍጠር አንጻር የማይተካ ሚና እየተወጡ ለመሆናቸው አስረጅ ነው፡፡
ፈተናዎች
ምንም እንኳን እነዚህ ማህበራት በዚህ መልኩ ተልዕኳቸውን እየተወጡ፤ ለግብርናውም መዘመን የድርሻቸውን እያበረከቱና የአገር ኢኮኖሚን የመደገፍ ተጽዕኗቸው እየጎለበተ ቢመጣም፤ አሁንም በርካታ ችግሮችና እጥረቶች አሉባቸው፡፡ ይህ ደግሞ በማህበራቱ ውስጥ መምጣት ያለበት ለውጥ በተገቢው መልኩ እንዳይመጣ አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ፣ የአባላቱ ቁጥር 20 ሚሊዮን ደርሷል፤ በአንጻሩ ግን የገበያ ድርሻቸው ሲታይ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ የሚፈለገውን ያህል አይደለም፡፡ ምክንያቱም በወጪ ንግድ የሚያመጡት ገቢ በጣም ከፍተኛ ቢመስልም፤ ቡናን እንኳን ማየት ቢቻል በመጠን ደረጃ እንደ አገር የሚላከው ቡና ስምንት በመቶ አካባቢ ነው ያለው፡፡ ነገር ግን ወደ ገንዘብ ተቀይሮ ሲታይ 14 በመቶ አካባቢ ነው፡፡ እናም ይሄን ስምንት በመቶ ወደ አርባ በመቶ ማሳደግ ቢቻል፤ በዋጋ ደረጃም ወደ 60 በመቶ ማድረስ የሚቻልበት እድል አለ፡፡
በተመሳሳይ የፋይናንስ ተቋማቱ ለአርሶ አደሩ የሚሰጡ ብድሮችና የአከፋፈል ሂደቶች ጋር ተያይዘው የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸው አይካድም፡፡ ይሄን ችግር ተገንዝቦ ለማቃለል እየተሰራ ሲሆን፡፡ አርሶ አደሩ የቁጠባ አባል በመሆን ካገኘው ላይ እንዲቆጥብና ተበድሮም ተጠቃሚ እንዲሆን የማስተማርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ በኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ጥሩ ለውጥ እየታየ ሲሆን፤ በተቀሩት አካባቢዎችም ተመሳሳይ ስራ የሚከናወን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በመደራጀት መቆጠብና ብድር ማግኘት ይቻላል፤ በፈለጉት ጊዜም ቴክኖሎጂን ከፈለገው ቦታ ማግኘት ይቻላል፤ ጥራት ያለውን ምርት ለገበያ ማቅረብና ለምርቱም ተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት ይቻላል፡፡
የቀጣይ ስራዎች
በዚህና መሰል መልኩ ጥቅም ላይ ያልዋሉ በርካታ እድሎች በመኖራቸው ቀጣይ ሰፊ ስራን የሚጠይቅ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማህበራቱን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም ማህበራቱ የሚደግፋቸው፤ ችግሮቻቸውንም የሚፈታላቸው ይፈልጋሉ፡፡ ሂደቱም ማህበራቱ ያሉባቸውን የፋይናንስ፣ በሰለጠነ የሰው ሃይል የመመራት፣ የመሰረተ ልማት፣ የግብዓት፣ የገበያ መረጃና መጋዘን ችግሮች ፈትሾ ማቃለልና መስራትን ይጠይቃል፡፡ እነዚህን መፍታት ከተቻለም የህብረት ስራ ማህበራት አጠቃላይ ለአገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት፣ ሰላም ያላትና የተረጋጋች አገር ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ወሳኝ የሆነው የህብረት ስራ ማህበራት ሚናን ለመጠቀም፤ የተገኙ ስኬቶችንም በሁሉም ቦታ ለማስፋት እድል ይፈጥራል፡፡
ሰው ባለበት ሁሉ ቁሳዊና መንፈሳዊ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ከማቃለል አኳያ ደግሞ የህብረት ስራ ማህበራት ፍቱን መድሃኒት ናቸው፡፡ የኤጀንሲው መርህም “ሰው ካለ ሁሌም ችግር አለ፤ ችግር ካለ ደግሞ ህብረት ስራ አለ” የሚል ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር መርህ ጥንትም በህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት መኖሩን ነው፡፡ ምክንያቱም በማህበራቱ መደመር እውቀታቸው፣ ክህሎታቸው፣ ገንዘባቸውና ጊዜያቸው ይደመራል፡፡ የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ የሰዎችን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ችግር ይፈታል፡፡ ከዚህ አኳያ በህብረት ስራ ማህበራት ጥሩ ጅማሮ አለ፡፡ ሆኖም ይሄን ስራ የበለጠ ማጠናከር ይጠይቃል፡፡
ለምሳሌ፣ ገንዘብ ለህብረተሰብ ለውጥ ወሳኝ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ገንዘብ ለሁሉም ተደራሽ አይደለም፡፡ ሁሉም በዚህ ተጠቃሚ ሆኗል ማለትም አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ ኢ-ፍትሃዊነትን ያመጣል፡፡ እናም ይሄንን ወደ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልና ተጠቃሚነት ከማምጣት አኳያ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ህብረት ስራ ማህበራት የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ ያንን የማይተካ ሚናቸውን እንዲጫወቱ ተግሞ ለሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል እንደየፍላጎቱ ተደራሽ የሚሆን አሰራርና ስርዓት ዘርግቶ መ
ስራት ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ተቋማት ተግባራዊ ሊደረግ የታሰበው የወለድ አልባ የፋይናንስ አገልግሎትም የዚህ ስራ አንድ አካል ነው፡፡
የኢኮኖሚው መሰረት የሆነውን ግብርናውን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ምንም እንኳን ማህበራቱ ብድርን አባል ለሆነውም ላልሆነውም የሚያሰራጩ ቢሆንም፤ በዚህ መልኩ በአባልነት የሚገኙ ጥቅሞችንና አባል ባለመሆን የሚታጡ ጥቅሞችን በማስረዳት የበለጠ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ይሰራል፡፡ ባለድርሻዎችም በዚሁ አግባብ መስራትና መደገፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ባለፉት አምስት ዓመታት የተሰራውን ያክል ላለፉት ሃያ ዓመታት ተሰርቶ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ የላቀ ይሆን ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 13/2011
ወንድወሰን ሽመልስ