በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለውን የመኖሪያ ቤቶች ችግር ለማቃለል አስተዳደሩ ባቀረባቸው የተለያዩ አማራጮች በመጠቀም የመኖሪያ ቤቶችን መገንባት እንደሚቻልና ኅብረተሰቡም በዚህ ዕድል ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ከንቲባ አዳነች አቤቤ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ከንቲባዋ ይህንን የገለጹት ሰንሻይን ኮንስትራክሽን የገነባቸውን አምስት ሺህ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ባስተላለፈበት መርሀ ግብር ላይ ነበር፡፡
መንግሥት ለብቻው የመኖሪያ ቤቶችን እየገነባ የቤት ባለቤት ማድረግ የማይችል በመሆኑ፤ አስተዳደሩ አዲስ በቀረጻቸው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ መሆን የሚቻልበት ዕድል መመቻቸቱን ጠቁመውም ነበር፡፡ በተለይ በከተማዋ ነዋሪዎች በዋነኛነት የሚነሳው የመኖሪያ ቤት ችግር መሆኑን ያመለከቱት ከንቲባዋ፤ አስተዳደሩም ይህንን ጉዳይ ከሁሉም በላይ በአንገብጋቢነት እንደሚመለከተው ተናግረው ነበር፡፡
እንደ ወይዘሮ አዳነች አበቤ ገለጻ፣ መንግሥት ለብቻው መኖሪያ ቤቶችን እየገነባ ሁሉንም የቤት ባለቤት ማድረግ የማይችል በመሆኑ አስተዳደሩ አዲስ በቀረጻቸው የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮግራም ላይ ተሳታፊ መሆን የሚቻልበት ዕድል ማመቻቸቱን አመልክተዋል፡፡ ስለሆነም የቤት ችግርን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የተለያዩ አማራጮች እየተተገበሩ መሆኑን በማስታወስ የከተማው ነዋሪም እነዚህን አማራጮች መጠቀም ይገባል፡፡
ምክንያቱም በመንግሥት በኩል በተለያየ መልኩ የተቀየሱ አማራጮችን በመጠቀም የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመፍታት በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ ቢሆንም አሁንም የመኖሪያ ቤት አቅርቦትና ፍላጎቱ ሊጣጣም አልቻለም፡፡ በመሆኑም የመኖሪያ ቤት አቅርቦቱን ለመጨመር በርካታ የቤት አቅርቦት ፕሮግራሞች በመቅረጽና አስፈላጊው የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፍ በማዘጋጀት አብሮ የማልማት እንቅሰቃሴ ተጀምሯል፡፡ በዚህም መሠረት የከተማ አስተዳደሩ አቅም ላላቸው የከተማው ነዋሪዎች፣ ለባለሀብቶች፣ ለግል አልሚዎችና ሌሎችም በዚህ ሥራ መሳተፍ የሚችሉትን ሁሉ የከተማ አስተዳደሩ እያበረታታ ይገኛል፡፡
በእነዚህ የቤት ግንባታ አማራጮች ለመሳተፍ የሚፈልጉ በሩ ክፍት ስለመሆኑ፤ አስተዳደሩ በአማራጭነት ባቀረባቸው የቤት ግንባታ አሠራሮች ኅብረተሰቡ ተሳታፊ ይሆን ዘንድም ጥሪ አቅርበው፤ በዚህም የከተማ አስተዳደሩ አምስት የቤት ልማት አማራጮችን ማቅረቡ ተጠቁሟል። በዚህ መሠረትም አስተዳደሩ በአማራጭነት ካቀረባቸው የቤት ማልሚያ ፕሮግራም ውስጥ አንዱ በፓርትነርሺፕ ወይም በአጋርነት አብሮ መሥራት፤ ሁለተኛው በሪልስቴት በማልማት ነው፡፡
ሦስተኛውና ኅብረተሰቡ በአማራጭነት ሊጠቀምበት የሚችለው ደግሞ፣ በማኅበር ተደራጅቶ ቤት መሥራት ሲሆን፤ ቤት የሚፈልጉ መሬት ያላቸው ገንዘብ ግን የሌላቸው ነዋሪዎች ገንዘብ ካለው አልሚ ጋር በአጋርነት አብረው ማልማት የሚችሉበት ዕድል እንደ አራተኛ አማራጭ የተመቻቸ ነው፡፡ አምስተኛ አማራጭ ደግሞ መንግሥት ራሱ እንየገነባ የሚያቀርበው ነው፡፡ እነዚህ አማራጮች የከተማዋን ዲዛይን በጠበቀ መልኩ የሚገነቡ እስከሆነ ድረስ አስተዳደሩ ድጋፍ የሚያደርግባቸው አዳዲስ አሠራር ስለመሆናቸውም ነው ከንቲባዋ በወቅቱ የገለጹት፡፡
‹‹በየትም ሀገር የቤት አቅርቦት እየጨመረ እንዲሄድ ይደረጋል እንጂ መንግሥት እየገነባ ሁሉንም ነዋሪ የቤት ባለቤት ማድረግ አይችልም፣ ይሄ በየትኛውም ዓለም አልተደረገም፤›› ያሉት ከንቲባዋ፤ ነገር ግን አዲስ አበባ የቤት አቅርቦትን የሚያሳድጉ አቅሞቻችንን ማቀናጀት በጋራ ማልማት የሚቻል፤ አሁንም አስተዳደሩ ይህንን ሥራ ለማጠናከር እየሠራ መሆኑን እና አስተዳደሩ ከቤት አልሚዎች ጋር በትብብር ከተሠራ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ነው ከንቲባዋ ያመለከቱት።
በዚህ መልኩ መሬትን ወስደው ለተፈለገው ዓላማ ከሚያውሉ አልሚዎች ጋር የከተማ አስተዳደሩ በትኩረት እንደሚሠራ እና ወደፊትትም ቤት ለማልማት አቅሙና ፍላጎቱ ያላቸው በትክክል ማቅረብና መተግበር ለሚችሉ አስተዳደሩ መሬት በነፃ ባያቀርብ እንኳ በርካታ ማበረታቻዎችን የሚያደርግ መሆኑን፤ እነዚህ አማራጮች ሌሎች ኩባንያዎች ለሠራተኞቻቸው ቤት መገንባት የሚችሉ ከሆነ ይህንን ለማበረታታት አስተዳደሩ ቦታ እንደሚያቀርብ ከንቲባ አዳነች አስታውቀዋል፡፡
ለምሳሌ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሠራተኞቹ አምስት ሺህ ቤቶችን ለማስገንባት የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ፕሮግራም ላይ የተገኙት ወ/ሮ አዳነች ኩባንያዎች ለሠራተኞች ቤት መገንባት የሚፈልጉ ከሆነ ይበረታታሉ ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የወሰደውን ርምጃ በምሳሌነት በመጥቀስ በከተማ ውስጥ በርካታ ትልልቅ ኩባንያዎች ስላሉ ለሠራተኞቻቸው ቤት በመገንባት የቤት አቅርቦት ችግርን ለማቃለል ለሚያደርጉት ጥረት አስተዳደሩ መሬት የሚያቀርብ በመሆኑ ኩባንያዎች ይህንንም የቤት ማልሚያ መንገድ በመጠቀም መገንባት እንደሚችሉ፤ አስተዳደሩ በአማራጭነት ካቀረባቸው አሠራሮች ውስጥ በተለይ ከግሉ ዘርፍ ጋር በጋራ ለማልማት በተቀረጸው ፕሮግራም 70 የሚሆኑ አልሚዎች ከአስተዳደሩ ጋር የመግባቢያ ስምምነት አድርገዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑት ወደ ሥራ የገቡ ሲሆን ቀሪዎቹም በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንዲህ ላሉ የቤት ልማቶች አስተዳደሩ 1 ሺህ 500 ሔክታር መሬት መዘጋጀቱ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ እንዳስታወቀው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎች ቁጥር ከ600 ሺህ በላይ ደርሰዋል፡፡ ባለፉት 20 ዓመታት ደግሞ በመንግሥት የተገነቡ ቤቶች 316 ሺህ ሲሆኑ በዚህ የግንባታ ሒደት የቤት ፍላጎትን ማሟላት እንደማይችል በመታወቁ አስተዳደሩ በአማራጭነት በቀረቡ የቤት ማልሚያ ፕሮግራሞች እየተሳተፉ ያሉ አልሚዎች የቤት ችግርን ለማቃለል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብሎ ያምናል፡፡
ከዚሁ አንፃር በከተማዋ እየተካሄደ ያለውን የቤቶች ልማት በተመለከተ በ2016 በሙሉ በጀት ዓመቱ ግንባታቸውን ለማስጀመር ከታቀዱት 120 ሺህ ቤቶች በግማሽ ዓመቱ ውስጥ 99ሺህ 113 ቤቶች ማልማት መቻሉን ከንቲባዋ በቅርቡ የስድስት ወር የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በበጀት ዓመቱ 111 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት የሚያስችል የአጋርነት ውልና የመሬት ዝግጅት እየተከናወኑ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል፡፡
እንዲህ ባሉ በአጋርነት ቤት በማልማት ሥራዎች በሪል ስቴት ኩባንያዎችና በግለሰብ አልሚዎች በግማሽ ዓመቱ ውስጥ አሥር ሺህ ቤቶች ተገንብተዋል፡፡ በግለሰብና በሪል ስቴት ኩባንያዎች ከተገነቡት አሥር ሺህ ቤቶች ሌላ በመንግሥት በጀት 4ሺህ 200፣ በበጎ አድራጊ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በኩል ደግሞ 5ሺህ 23 ቤቶች፤ በአጠቃላይ 19ሺህ 223 ቤቶች ስለመገንባታቸውም መገለጹን የአማርኛው ሪፖርተር ዘግቦ ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር በትብብር ለመሥራት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የኦቪድ ግሩፕ ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ገልጸው፤ ‘ኩባንያው በኢትዮጵያ የግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አዲስ ተስፋ መኖሩን በተግባር ማሳየት መቻሉን፤ የ”ኦቪድ” ግሩፕ የግንባታ ኩባንያ ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር በመተባበር በ 18 ወራት ዘመናዊ የመኖሪያ መንደር ገንብቶ መጠናቀቁን፤ ኩባንያው እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2013 በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሚታየውን ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ መቋቋሙን አውስተዋል።
የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኩባንያው ከተመሠረተ ጀምሮ አማራጭ የግንባታ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ያለውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመፍታት የዘርፉ ተዋናዮች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገርና ሰፊ ሕዝብ ያላት እንደመሆኗ ሁሉም በትብብርና በቅንጅት ቢሰራ የበለጠ ውጤት ይገኛል። “ኦቪድ” ኩባንያም ይህንኑ በመረዳት በቀጣይ ከተለያዩ አጋሮች ጋር ትብብር እየፈጠረ የተሻለ ሥራ ለመሥራት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የድርጅቱ እህት ኩባንያ “ኦቪድ” ሪል ስቴት 12 ወለል ያለው ሕንጻ በሦስት ወራት፤ 10 ወለል ያለው ሕንጻ በ69 ቀናት ገንብተው ማጠናቀቃቸውን፤ በዚህም በአጭር ጊዜ ውስጥ መኖሪያ ቤት ሠርቶ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሳየታቸውን ተናግረዋል። በተጨማሪም ከፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ጋር የተሠራው የገርጂ ሳይት የመኖሪያ መንደር ሕንጻዎቹ ከ 1 እስከ 10 ወለሎች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መገንባታቸውን አንስተዋል። በግንባታው ከተያዘው ጊዜ ውስጥ ስድስት ወራት የሚሆኑት የዝግጅት ሥራዎች የተሠሩባቸው እንደነበር፤ “ኦቪድ” በዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታገዙ ብቻ ውጤታማ እንደማያደርግ በአግባቡ የተረዳ ኩባንያ መሆኑን፤ ኩባንያቸው ከፕሮጀክቱ መሪዎች እስከ ሠራተኞች ድረስ በሀገር ወዳድነት ስሜት በግንባታው ላይ የሚሳተፉ መሆኑን፤ በተለይም የኩባንያው ሠራተኞች ፕሮጀክቶችን መገንባት ሀገር መገንባት መሆኑን እንዲረዱ ማስቻልና አስፈላጊውን ማበረታቻዎች እንደሚያገኙ፤ ኩባንያው ማህበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አንጻር በተለያዩ አካባቢዎች ቤቶች ግንባታና እድሳት ላይ መሳተፉንም አቶ ዮናስ አንስተዋል።
ነገርን ነገር ያነሳዋልና እግረ መንገዴን ስለ ሰሞነኛው የአከራይ ተከራይ አዋጅን በወፍ በረር እንቃኝ። መንግሥት ጣልቃ ገብቶ የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናርን ለማስተካከል፣ የቤት ኪራይ ውል በሕግ እንዲመራ ለማድረግ የሚያስችለውንና በአከራይና ተከራይ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን አዋጅ፣ ባለፈው መጋቢት 24 ቀን 2016 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀደቀ። አዋጁ ‹‹የመኖሪያ ቤት ኪራይ ቁጥጥርና አስተዳደር›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ ዓላማው ግልጽና ተገማች የሆነ የመኖሪያ ቤት ኪራይ አስተዳደር፣ እንዲሁም የአከራይና ተከራይን መብት ሚዛናዊ በሆነ መልኩ የሚያስተናግድ ሥርዓት ለመዘርጋት ያለመ ነው።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ሕጎች ከሚታወቁ ሠብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት ሲሆን፣ መንግሥት የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ለማሻሻል የተለያየ ጥረት ቢያደረግም ከፍላጎቱ ጋር መጣጣም እንዳልቻለ የሪፖርተር ዘገባ ያወሳል። በቤት ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት በመጠቀምም ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪዎች በሀገሪቱ ከተሞች እየተስተዋሉ መምጣታቸውን፣ በዚህም ሳቢያ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች መቸገራቸውንና ተረጋግተው ኑሯቸውን እንዳይመሩ ማድረጉን፣ በተጨማሪም የመኖሪያ ቤት የኪራይ ዋጋ መናር በከተሞች የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት እያባባሱ ከሚገኙ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ የመንግሥትን አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ የኪራይ ዋጋ ጭማሪን በተመለከተም በተቆጣጣሪው አካል ከሰኔ 30 ቀን ጀምሮ ለአንድ ዓመት የፀና የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡
አዋጁ ከመታተሙ በፊት ከፀደቀበት ዕለት ጀምሮ የፀና እንደሚሆን የፍትሕ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) አብራርተው፣ አንድ የውል ዘመን ከሁለት ዓመት ሊያንስ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ የቤት ኪራይ ውልና ዋጋ እንደ ክልሎች ነባራዊ ሁኔታ መወሰን እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን፣ ይህንንም የሚቆጣጠር በክልል ደረጃ የሚሰየም አካል እንዲኖር መደረጉን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ በዚህ መሀል በሁለቱ ወገኖች መካከል አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ጉዳዩን ተቆጣጣሪው አካል እንደሚመለከተውና ወደ ፍርድ ቤት እንደማይሄድ ገልጸው፣ ይህም የሆነው በመደበኛ የሕግ ሒደት ላይ ጫና እንዳይፈጠር በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አዋጁ ስለቤት ኪራይ ሲያብራራ፣ ለመኖሪያ ቤት የሚያገለግል ከአንድ ክፍል ቤት ጀምሮ መሆኑን፣ ለአጭር ጊዜ የኪራይ አገልግሎት የሚሰጡ ማለትም ሆቴል፣ ሪዞርት፣ እንዲሁም አልጋ ቤቶችን እንደሚያካትት ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡ አዲስ የተገነባ ወይም ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከራይ ቤት የኪራይ ዋጋ በአከራይና በተከራይ ስምምነት የተዋዋይ ውል እንዲፀና ይደረጋል ሲሉ ጌዲዮን (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡ ተከራዩ ውሉን ማቋረጥ ቢፈልግ ከሁለት ወራት በፊት ቀድሞ ማሳወቅ እንደሚኖርበት በአዋጁ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፣ ቤቱን ተከራይቶ ሲኖር የኪራይ ክፍያውን ለመጀመሪያ ጊዜ ለ15 ቀናት ካሳለፈና ለሁለተኛ ጊዜ ለሰባት ቀናት ካሳለፈ፣ አከራዩ ውሉን ማቋረጥ እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ተከራይ ሊጠየቅ የሚችለው ቅድመ ክፍያም ከሁለት ወራት የቤቱ ኪራይ ዋጋ ሊበልጥ አይችልም፡፡
አከራዩ ቤቱን ለመሸጥ ሲፈልግ ለተከራዩ የማሳወቅ ግዴታ ባይኖርበትም፣ ቤቱን የሚገዛው ግን ውሉ እንዲቀጥል ካልፈለገ ለተከራዩ የስድስት ወራት ጊዜ መስጠት እንደሚኖርበት፣ ለአዲስ ተከራይ ሲያከራይም ከዚህ በፊት ከነበረው የኪራይ ዋጋ በላይ አድርጎ ማከራየት እንደማይችል ተደንግጓል። ነገር ግን ቤቱ የሚተላለፈው በስጦታ ከሆነ የውል ዘመኑ እስኪጠናቀቅ ድረስ ውሉ ቀጣይነት ይኖረዋል፡፡ በሌላ በኩል ቀደም ሲል ሲከራይ የነበረ የመኖሪያ ቤት ወይም ግንባታው የተጠናቀቀ አዲስ ቤት ያለ አገልግሎት ከስድስት ወራት በላይ እንዲቀመጥ ከተደረገ፣ ቢከራይ አከራዩ ሊከፍል ይችል የነበረውን የኪራይ ገቢ ግብር ተሠልቶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡
የቤት ኪራይ ክፍያን በተመለከተም በባንክ ወይም በሌላ ሕጋዊ የኤሌክትሮኒክ ዘዴ ብቻ እንዲፈጸም በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ አዋጁ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት የነበሩ የአከራይ ተከራይ ውሎችን የሚያስቀር አለመሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ አዋጁ ሲወጣ የነበረ ውል እስከ ቀጣዩ ሦስት ወራት ድረስ እንዲመዘገብ ይጠበቃል፡፡ ይህን አዋጅ የጣሰ አከራይና ተከራይ የወንጀል ቅጣት እንደማይጣልበት፣ ነገር ግን አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት ተገልጿል።
አዋጁ የአከራዩንና የተከራዩን መብት በማጣጣም የሚያስከብር ስለመሆኑ ጠቁመው፣ በሁለቱ መካከል አለመግባባት ካለ በተቆጣጣሪው አካል በሚደረግ አስተዳደራዊ ፍትሕ የሚቀረፍ መሆኑን ሚኒስትር ጌዲዮን (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡ አዋጁ የመኖሪያ ቤት ችግር በስፋት በሚስተዋልባቸው ከተሞች ተግባራዊ የሚደረግ ስለመሆኑና ዝርዝር አፈጻጸሙ ግን ለከተማ መስተዳድሮችና ለክልሎች እንደሚሰጥ አመላክተዋል።
መንግሥት የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን ለማሟላት ስላልቻለ ቁጥጥሩ ላይ ትኩረት አድርጓል የሚባለው አግባብ አይደለም ያሉት፣ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ በቤት ግንባታ ዘርፍ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ገልጸዋል፡፡ አዋጁ አነስተኛ ገቢ ያላቸው የመንግሥት ሠራተኞችና የከተማ ነዋሪዎች በአሁኑ ወቅት ያጋጠማቸውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሻሎም ! አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም