ደማቅና ውብ ባህላዊ ሥርዓት ካላቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል የሃላባ ብሄረሰብ እንዱ ነው፡፡ ሃላባ በውብ ልጃገረዶቿ፤ በአዘፋፈንና ጭፈራዋ እንዲሁም አለባበስ ሥርዓቷ በእጅጉ ትታወቃለች። በተለይም የአካባቢው መለያ በሆነው ረጅሙና በማራኪ ዲዛይን በስንደዶ ተገምዶ የተሰራው ኮፍያዋ ሁላችንም በያለንበት ሆነን ሃላባን ከነውበቷ በእዝነ ልቦናችን እናስባታለን፡፡
ሃላባዎች የውብ ታሪክና ጥንታዊ ሕግ ሥርዓት ባለቤትም ጭምር ናቸው፡፡ ማህበረሰቡ ከትውልድ ትውልድ ተቀብሎ ሲተገብራቸውና ሲጠብቃቸው ከቆዩ ክዋኔዎች መካከል ደግሞ የኦገቴ ሸንጎ ሥርዓት ዋነኛው ነው፡፡
በሃላባ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ የባህል ዘርፍ ሃላፊ አቶ ከማል ሃሰን እንደሚሉት፤ የሃላባ ሕዝብ ከተበታተነና ከዘላን ኑሮ ወደ መደበኛ ኑሮ እንደወጣ ሕግና ሥርዓት ባልነበረበት ወቅት ላይ የራሱን ኑሮ የሚመራበት፤ የሚተዳደርበት የሴራ ሥርዓት አበጅቷል፡፡ ይህም ሴራ ለኑሮ የሚያስፈልጉትንም ነገሮች በሙሉ የሚያስተዳድርበትና የሚመራበት ‘ኦገቴ’ የተሰኘውን የሸንጎ ሥርዓት ፈጥሯል፡፡
የ’ኦገቴ’ ሸንጎ የፍትሕ ሥርዓቱን የሚመራበት እርከን ወይም አደረጃጀት ያለው ሲሆን፣ ይህም የሚጀምረው ከቤተሰብ እርከን እንደሆነ አቶ ከማል ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በቤተሰብ እርከን ደረጃ የሚታዩት ጉዳዮች አነስተኛና ቀለል ያሉ አለመግባባቶች ናቸው፤ በቤተሰብ ደረጃ በተዘረጋው የሸንጎ ሥርዓት የተፈጠሩ ቤተሰባዊ ችግሮች ሁሉ በእነሱ የሚፈቱ ናቸው›› ይላሉ።
በመቀጠልም የጎሳ እርከንና እንዲሁም ጠቅላላ የሃላባ ሸንጎ እርከን እንደየቅደም ተከተላቸውና እንደ ችግሩ ክብደት እየታየ ሕዝቡን በዳኝነት ሥስርዓት የሚያገለግሉበትና ፍትሕ የሚያሰፍኑበት ሁኔታ መኖሩንም ያስረዳሉ፡፡
ኦገቴ በመደበኛው መንግሥታዊ አሰራር ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት እንደሚባለው ሁሉ ከታች ባሉ የሸንጎ እርከኖች ያልተፈቱ ችግሮች አልያም አለመግባባቶች የሚፈቱበት በብሔረሰቡ ተወላጆች ትልቅ ስፍራ የሚሰጠውና የሚከበር የዳኝነት ሥርዓት እንደሆነም ኃላፊው ያብራራሉ፤ ‹‹በነገራችን ላይ በቤተሰብ ደረጃ ያለው ሸንጎ እስከ አያትና ቅድመ-አያት ያሉ የቤተሰብ አባላት በቤተሰባቸው መካከል አለመግባባት ሲከሰት ቁጭ ብለው የሚመክሩበት፤ ያጠፋን መልሰው ከተበዳይ ጋር እርቅ እንዲፈጽም የሚያደርጉበት ሥርዓት ነው ›› በማለት ያብራራሉ፡፡
እንደ አቶ ከማል ገለፃ፤ የ’ኦገቴ’ ሴራ ግጭት የሚፈታበት፤ የተበደለ የሚካስበት፤ የተቸገረ የሚረዳበት ከመሆኑም ባሻገር ብሄረሰቡ የግብርና ሥራውን እየገመገመ የሚሄድበት ሕዝባዊ መድረክ ነው፡፡ በሃለባ ማህበረሰብ ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ይህ የሸንጎ ሥርዓት ታዲያ የራሱ የሆነ ሕግና የአሰራር ደንብ ያለው ሲሆን፣ ዛሬም ድረስ ከመደበኛ የፍትህ ሥርዓቱ እኩል ተቀባይነት ኖሮት እየተተገበረ ይገኛል፡፡ ኦገቴ እስከነፍስ ማጥፋት ያሉ ግጭቶች በሚከሰቱበት ጊዜ ከመደበኛ ሕጉ ጋር ሳይጣረስ ፍትሕ እንዲሰፍን የሚደረግበትን ምቹ ሁኔታም ፈጥሯል፡፡
‹‹በተለይም በፀብ ምክንያት ሆዳቸው የሻከረ ቤተሰቦች ወይም የጎሳ አባላት እንዲሁም ለበቀል የተነሳሱ ሰዎችን ወደ ትክክለኛው መንገድ በመመለስ ረገድ የላቀ አበርክቶ አለው፤ ለግድያ የሚፈላለጉ ወገኖች ሳይቀሩ ከኦገቴ ሸንጎ በኋላ ታርቀው ቤተሰብ ሆነው የሚሄዱበት ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ለአካባቢው ብቻ ሳይሆን ለሀገርም ጭምር ሰላም ለማስፈን ፋይዳው ከፍ ያለ ነው›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ የተከሰቱ ችግሮችን መነሻ በማጥናት የመፍትሔ አቅጣጫ የሚቀመጥበት፤ ተመጣጣኝ ቅጣት የሚበየንበት፣ የካሳ አከፋፈል ሥርዓት በማበጀት አካባቢው ሰላማዊ ቀጣና እንዲሆን በማድረግ ረገድም ኦገቴ የማይናቅ አስተዋፅኦ እንዳለውም ነው ያስረዱት፡፡
አቶ ከማል እንደሚሉት፤ በአጋጣሚ የጠፋው ንብረት ከሆነና ተመልሶ የማይገኝ እንኳን ቢሆን ንብረት የዘረፈው አካል ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህም መሆኑ በማህበረሰቡ ዘንድ ተዓማኒነትና ተቀባይነት እንዲኖረው አድርጓል። ያም ቢሆን ግን ሊሳት የማይገባው ጉዳይ የዳኝነት ሥርዓቱ ከወንጀልም ሆነ ከፍትሐ ብሔር ሕጉ ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ ሕጎች የሚመራ መሆኑ ነው። ቀደም ባለው ጊዜ ምንም አይነት በወረቀት የተፃፈ ሕግ ባልነበረበት ሁኔታ ማህበረሰቡ ያልተፃፈንና ግን ደግሞ ሁሉም የሚቀበላቸውን የኦገቴን ሕጎችና ደንቦች በአዕምሮው ከትቦ ሳይዛነፍ የሚዳኝበት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል፡፡
ስለኦገቴ ሴራ (ሸንጎ) በውል የተጠና ነገር ባይኖርም የሃላባ ብሔረሰብ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ሥራ ላይ አውሎ ይጠቀምበት እንደነበር ይነሳል። በዚህ ረገድም ኃላፊው ‹‹አባቶቻችን ከአባቶቻቸው ተረክበው፤ በጥንቃቄ ይዘው አሁንም ድረስ መሠረቱን ሳይለቅ ያቆዩልን ሥርዓት ነው፡፡ ከብዙ ዘመናት ጀምሮ አባቶቻችን ፍትህ ያሰፈኑበት፤ አሁንም ያለነው ትውልዶች ተቀብለን በአግባቡ የምንተገብረውና ታሪክ ብቻ ሳይሆን ሕይወት ያለው ሥርዓት ነው›› ሲሉም ሥርዓቱን ይገልጹታል፡፡
ማህበረሰቡ አሁንም ድረስ ከምንም በላይ የሚቀበለው ቢሆንም ቅሉ መንግሥታዊውንም ሕግ የሚያከብርና ተቀብሎ እኩል እየተገበረ ነው የሚገኘው ይላሉ፡፡ ‹‹የሃላባ ኦገቴ (ሸንጎ) ከሕግ ጋር የተጋጨ አይደለም፤ ይልቁንም ተናቦና ተግባብቶ የሚሠራበት ነው፤ አንዳንድ ጊዜ እንዳውም በመደበኛ ፍርድ ቤቶች ቶሎ ሊፈቱ ላልቻሉ ችግሮች በአጭር ጊዜ መፍትሔ በመስጠት የፍትሕ ሥርዓቱን የሥራ ጫና የሚያቀሉበት ሁኔታም አለ›› ሲሉ ያብራራሉ፡፡ አክለውም ‹‹ኦገቴው ከመደበኛ ፍትሕ ተቋማት የተረከበውን ጉዳይ በሙሉ ሃላፊነትና ጥያቄው መመለስ ባለበት አግባብ ምላሽ የሚሰጥ ሂደትን ነው የሚከተለው›› ይላሉ፡፡
እንዳውም በመደበኛው የፍትሕ ሥርዓት ብዙ የቆየውንና ተንጠልጥለው የኖሩትን ጉዳዮች ግፋ ቢል በሁለትና ሶስት ቀጠሮ ምላሽ እንዲያገኙና ወደ ውጤት እንዲመጡ የሚደረግበት መሆኑን አቶ ከማል ያመለክታሉ፡፡ ‹‹በነገራችን ላይ በኦገቴ ዳኝነት ቀርቦ በምንም መልኩ ክህደት መፈፀም ወይም በሃሰት መናገር አይፈቀድም፤ የትኛውም ተከራካሪ አካል ንፁህ ከሆነ ንፅህናውን ቀርቦ ያሳምናል እንጂ በሃሰት ንፁህ ነኝ ብሎ አይከራከርም፤ የሚበየነውንም ፍርድ በቀናነት ተቀብሎ ሰላማዊ ሕይወቱን የሚያስቀጥልበት ነው፤ ይህ እንዲሆን ያደረገው ባህሉም ጭምር ነው›› ሲሉ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነትና ሃላባዎች ለሕጉ ያላቸውን ተገዢነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡
ከዚህ ባሻገር በተለይ በግድያ የሚፈላለጉ የብሔረሰቡ ተወላጆች በኦገቴ የፍርድ አደባባይ ቀርበው ፀባቸውን አብርደውና ታርቀው በደላቸውን ፈፅመው ሊረሱበት የሚችሉበት እድል እንደሚፈጥርም አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ከእርቁ በኋላ የገዳይ ቤተሰብ ለሟች ቤተሰብ ልጅ ሆኖ የሚያገለግልበት እድል የሚፈጥር ሥርዓትም ጭምር ነው›› ይላሉ፡፡
እንደ አቶ ከማል ማብራሪያ፤ ኦገቴን የሚመሩ እና የሚዳኙ ግለሰቦች በሃላባ ማህበረሰብ በመልካም ስብዕናቸው የሚታወቁ፤ በእድሜና በተሞክሮ የጎለበቱ የሀገር ሽማግሌዎችና ቁቡልነት ያላቸው የሃይማኖት አባቶች፣ ገራድዎች፣ አዝማቾችና ኢማሞች ናቸው። እነዚህ አባቶች ህብረተሰቡ የሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ በመፈፀምና ፤ ፍትህ ያለምንም መሸራረፍና አድሏዊ አሠራር እንዲሰፍን በማድረግ ረገድ ያላቸው ሚና የላቀ ነው፡፡
ለፍርድ በሚሰየሙበት ጊዜም ጋቢ፣ ኢማምና መሰል ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውን አልባሳትን ለብሰውና የሃላባን እሴት በጠበቀ መልኩ ተጠንቅቀው እንደሆነ ኃላፊው ያመለክታሉ። ‹‹ከባህላዊ አልባሳት ውጪ ቲሸርትና ቁምጣ ለብሶ መገኘት ፈፅሞ የተከለከለ ነው፤ በመሆኑም የሃይማኖት አባቶች ኢማማቸውን፤ የሀገር ሽማግሌዎች ደግሞ ጋቢያቸውን ለብሰው ነው የዳኝነት ሥርዓቱን የሚመሩት፤ በተጨማሪም እያንዳንዱ የኦገቴ ሽማግሌ አለንጋ በእጁ ይዞ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ ከሌላው የተለየ የኦገቴ ሽማግሌ መሆኑን የሚለይበት ሁኔታ አለ›› ይላሉ፡፡
የኦገቴ ሥርዓት ፈፅሞ ቤት ውስጥ ወይም አዳራሽ ውስጥ የማይፈፀም መሆኑን አቶ ከማል ያብራራሉ፤ ይልቁንም ሰፊና የዋርካ ጥላ ያለበት ሜዳ ላይ እንደሆነ ይጠቅሳሉ፡፡ ‹‹ሰፊ ሜዳ ላይ የሚደረግበት ምክንያት ኦገቴን መታደም ወይም መሳተፍ የሚፈልጉ ሰዎችን በቁጥር ላለመገደብ ሲባል ነው›› ሲሉ ይገልጻሉ። በፍርድ ሸንጎ ላይ መሳተፍ የሚፈልግ ማንኛውም የሃላባ ተወላጅ በእድሜም ሆነ በፆታ ሳይገደብ ሂደቱን መከታተል የሚችልበት አግባብ መኖሩንም ነው ያመለከቱት፡፡
ይህ የሚደረገውም የፍትህ ሥርዓቱ አሳታፊና አካታች እንዲሆን ከማድረግ በዘለለ በተለይም ወጣቶች በሚገባ እንዲከታተሉ፣ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ያስገነዝባሉ። ‹‹ወጣቶች የኦገቴን የሸንጎ ሥርዓት ቁጭ ብለው በማዳመጥ እውቀት እንዲቀስሙ ፤ ተሞክሮ እንዲወስዱ በማድረግ፤ ወደፊት ደግሞ እነሱም ሥርዓቱን ተረክበው የሚዳኙበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በማለም ነው›› ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል ማንኛውም ሰው እንዲታደም በመደረጉ በጉዳዩ ዙሪያ መረጃ ያላቸው አካላት አስተያየት የሚሰጡበት፤ የሚመሰክሩበት ሁኔታ በመኖሩ፤ በዳይም ሆነ ተበዳይ በምንም አይነት መልኩ ለመዋሸት ወይም የሃሰት ማስረጃ ለማቅረብ እንደማይዳዳ አቶ ከማል ይናገራሉ፡፡ ይህም ሥርዓቱን ከሃሜትና ቅሬታ የፀዳ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ፋይዳው የጎላ እንደሆነ ነው ያስገነዘቡት፡፡ ከዚህ ባሻገርም አሳታፊ መሆኑ አሁን ላይ ላለው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መነሻ እንደሆነ አመላካች ነው ባይ ናቸው፡፡
አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችና እናቶች የሀገር ሽማግሌዎችን በምግብና በተለያዩ መስተንግዶዎች በማገዝ የሚሳተፉበት ሁኔታ መኖሩን ይጠቅሳሉ። ‹‹በባህሉ መሰረት ሥርዓቱ በሚፈፀምበት አካባቢ ያሉ ጎሳዎች ሃላፊነት ይወስዳሉ፤ በዚያ ጎሳ ውስጥ ያሉ ሴቶችና እናቶች ሻይ ቡና ቁርስና የተለያዩ ምግቦችን በማዘጋጀት ለሀገር ሽማግሌዎቹ ያቀርባሉ›› ሲሉም ይጠቅሳሉ፡፡ ማንኛዋም ሴት ፍትህ የምትፈልግበት ጉዳይ ሲያጋጥማት እንደማንኛውም የብሔረሰቡ ተወላጅ የምትዳኝበት ሁኔታ በኦገቴ ሥርዓት ያለ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ዓርብ ሚያዝያ 18 ቀን 2016 ዓ.ም